ዋና መቀመጫውን በብሪታኒያ ለንደን ያደረገውና በዓለም መድረክ ላይ አፍሪካ በትክክ ለኛው ገጽታዋ እንትገለጽ ለማስቻል በወሳኝ አፍሪካዊ ጉዳዮች ላይ ስፋትና ጥልቀት ያላቸው መረጃዎችን በመስጠት የሚታወቀው የአፍሪካ ቁጥር አንድ ተነባቢው ኒው አፍሪካ መጽሔት በዚህ ወር ዶክተር አብይን አብይ ጉዳዩ አድርጎ ታትሟል፡፡
ከአንድ መቶ በላይ በሚሆኑ የዓለም አገራት ማከፋፈያዎች ያሉት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመው ግዙፉ አፍሪካዊነትን አቀንቃኝ ወርሃዊ መጽሔት በግንቦት 2019 እትሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ለማስፈንና ቀጣናውን በማረጋጋት ረገድ ያስመዘገቡትን ስኬትና በአገር ውስጥ የገጠማቸውን ፈተና አስመልክቶ በፊት ገጹ ላይ ሰፊ ትንታኔ ይዞ ወጥቷል፡፡ እኛም ትንታኔውን ለአዲስ ዘመን አንባቢያን በሚመች መልኩ እንደሚከተለው ለንባብ አቅርበነዋል፡፡
የ42 ዓመቱ ወጣት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ዓመት ሥልጣን ከመጡ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍንና ቀጣናው እንዲረጋጋ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ አመርቂ ስኬትም አስመዝግበዋል፡፡ ከጎረቤታቸው ኤርትራ ጋር የነበረውን የረጅም ጊዜ ጠላትነትና ቁርሾ የተሞላበት ግንኙነት የሚያስቀር የሰላም ስምምነት በመፈጸም ሥራቸውን የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸውን የአፍሪካ ቀንድ የሰላም መልዕክተኛ አድርገው በመቁጠር ለቀጣናው መረጋጋት ከፊት ተሰልፈው ሰፊ ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡
የቀጣናውን ፖለቲካዊ ትኩሳቶች ለማርገብና የአካባቢውን የሰላም ችግሮች ለመፍታት ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት ሰምሮላቸው አመርቂ ስኬት አስገኝቶላቸዋል፡ ፡ በመሆኑም የቀጣናው የፖለቲካዊ ትኩሳት መርገብና መልክ መያዝ ጀምሯል፡፡ በቀጣናው ከመቼውም በተሻለ ሰላም መስፈን ችሏል፡ ፡ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው እንደገና በሚያበረታታ ደረጃ በማገገም ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ለእርሳቸውም ሆነ ለቀጣናው ቀላል ስኬት አይደለም ይላል የኒው አፍሪካ ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ ጆሴፍ ሀመን፡፡
በዚህ ረገድ ከኤርትራ ጋር ከተፈጠረው የሰላም ግንኙነት በአሻገር የተገኘው ስኬት መለያየቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ የእርስ በእርስ ግጭቶችን እንዲሁም በሶማሊያና በኬንያ መካከል የነበረውን አለመግባ ባት ለመፍታት የሄዱበት ርቀት በእጅጉ የሚደነቅ ነው፡፡ ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣናው ለዘመናት ስጋት ሆነው የዘለቁ ችግሮችን ለመቅረፍና በአካባቢው ሠላምን ለማስፈን እስከ መጨረሻው ከመጓዝ የማይመለሱ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር የካቲት 20 ቀን 2019 ከዋናው ሶማሌ ተከፍሎ ራስ ገዝ አስተዳደር የሆነውን የሰሜኑ ክፍል ግዛት አስተዳዳሪ የሆኑትን የሶማሌ ላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ በሂ አብዲን ከሶማሌ ጋር ለማደራደር ወደ አዲስ አበባ ጋብዘዋቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የሶማሌው ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ ፎርማጆ መገኘት ባለመቻላቸው ድርድሩ ሳይሳካ ቀርቷል ይለናል ዘገባው፡፡
ከሁለት ሳምንት በኋላ በመጋቢት 4 ቀን 2019 ደግሞ ዶክተር አብይ አህመድ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በመሆን ስምንት አባል አገራት ባሉት የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት-ኢጋድ አደራዳሪነት የሚመራው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ሂደት በሚጠናከርበት መንገድ ላይ ለመምከር ወደ ጁባ አቀኑ፡፡
በዚያም በሀገሪቱ ያሉ ሁሉም ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች ትኩስ አቁመው ልዩነታቸ ውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱና ደቡብ ሱዳናውያን ወደ አንድነት እንዲመጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጠየቁት መሠረት ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር በተገኙበት ተስፋ ሰጪ የሰላም ድርድር ተካሂዷል፡፡ ዶክተር አብይ የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት እልባት እንዲያገኝ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህም በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ሂደት ላይም መነቃቃትና ተነሳሽነትን ፈጥሯል፡፡
እግረ መንገዳቸውንም ወደ ኬንያ አቅንተው የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ ፎርማጆ እና የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡህሩ ኬንያታን በናይሮቢ አገናኝተው የአገራቱ የእርስ በእርስ ግንኙነት በሚሻሻልበት ሁኔታ ላይ አወያይተዋል፡፡ በዚህም ሁለቱ አገራት ከባህር ወደብ ዳርቻ ጋር ተያይዞ በመካከላቸው የነበረውን አለመግባባትና ውዝግብ ለማስወገድ በዶክተር አብይ አቀራራቢነት ስኬታማ ውይይት ማድረግ ችለዋል፡፡
ድርድሩን ተከትሎ በአገራቱ መካከል በነበረው ግጭት ምክንያት የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብቷ ለአደጋ ይጋለጣል በሚል ስጋት አድሮባት የነበረችው ሶማሊያ ከኬንያ ጋር በድንበር አካባቢ በሚያጋጩ ጉዳዮች ላይ የምታራምደውን አቋም እንድታሻሽል አድርጓታል፡፡ ከዚህም በአሻገር ኤርትራና ሱዳን በኢጋድ እገዛ ወደ ሰላም መምጣት እንዲችሉም ዶክተር አብይ የጎላ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡
የሱዳንን ፖለቲካዊ ሁኔታም ከአገራቸው ጠቀሜታ አንጻር፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው ከምትፈጥረው ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እና የገበያ መዳረሻዎች አኳያ እንደሚያዩት የኒው አፍሪካን ትንታኔ ያመለክታል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነት የተጠናከረ ለመሆን ችሏል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳን መሠረት ያደረገ የተጠናከረ ግንኙነት ዶክተሩ በመመስረታቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡ ሱዳን ከግብጽ በተጻራሪ ተሰልፋ የኢትዮጵያን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መደገፏ ለዚህ ማሳያ የሚሆን ተግባር ነው፡፡
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቀጣናው ያስመዘገቡት ስኬት ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም በሀገር ውስጥ ግን ከባባድ ፈተናዎች እንደገጠማቸው የኒው አፍሪካ ትንታኔ ያመላክታል፡፡ በተለይም በመጪው 2012 ዓ.ም በሀገሪቱ ከሚደረገው ምርጫ ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሌሎች መቶ የሚሆኑ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ሥምምነት ቢፈራረሙም የኦሮሞ ግንባር አማጺያን ግን መስማማት ባለመቻላቸው ለዶክተር አብይ መንግሥት ስጋት ሆነው ቀጥለዋል፡፡ በሌላ በኩል በጥቅምት ወር ከየትኛው ወገን እንደሆኑ ያልታወቁ የታጠቁ ወታደሮች ቤተ መንግሥት ድረስ ዘልቀው በመግባት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጥቃት ለማድረስ ቢሞክሩም ዶክተር አብይ በታላቅ ጥበብ ነገሩን አብርደው በሰላም እንዲመለሱ አድርገዋቸዋል፡፡
ዶክተር አብይ አህመድ ቀደም ሲል በጦር ሠራዊት ውስጥ የደህንነት ክትትል ኦፊሰር ሆነው ይሰሩ በነበሩበት ወቅት እ.ኤ.አ በ1995 በሩዋንዳ በሰላም ማስከበር ዘመቻ ተሳትፈዋል፡፡ በመሆኑም በዚያ ካዩት ሁኔታ በመነሳት አገራቸው ወደ ብሔር ግጭት እንዳትገባ አጥብቀው ይሻሉ፡፡ ኢትዮጵያ በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ የመገንጠል መብትን ከፈቀዱ ሁለት ብቸኛ የዓለም አገሮች አንዷ ናት፡፡ ሌላኛዋ አገር ቅዱስ ኪተስ እና ኔቭስ ናት፡፡ በተለይም ብዙዎቹ የትግራይ ብሔር አባላት በዶክተር አብይ ዘመን ተገለልን ከሚሉት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በብሔር ግጭትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሽኩቻ በሚያስነሳው ግጭት ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ከቤት ንብረቱ መፈናቀሉም ለዶክተር አብይ መንግሥት ትልቅ ፈተና ሆኗል፡፡
ከዚህም በአሻገር በርካታ ኢትዮጵያውያን በኢኮኖሚ የደከሙ ናቸው፡፡ ይሄም በአገሪቱ ፍትሃዊነትና እኩል ተጠቃሚነት ከሌለ ከቀጣዩ ምርጫ ጋር ተያይዞ የጎሳ ግጭት መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡ እናም የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ኢኮኖሚውን ጨምሮ ሁሉንም ጠቅልሎ ይዞ እንደነበረበት እንደ ከዚህ ቀደሙ ዘመን የአንድ ወገን የበላይነትና አድልኦም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሊፈትኑ የሚችሉ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡
እናም የ42 ዓመቱ ወጣት መሪ የተረጋጋና የሰከነ ባህሪያቸው እንዲሁም ኃይል የተሞላበት የወጣትነት የመስራት ወኔያቸው ለስኬታማነታቸው ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ በዚያው ልክም ችግሮች እያደጉና እየተስፋፉ መጥተዋል፡፡ ስለሆነም የጀመሩትን ለውጥ ከእርሳቸው አንድ ሰው አንቀሳቃሽነት አውጥ ተው ተቋማዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የቀጣናውን ማኪያቬየሊያዊ ፖለቲካም በደንብ ተረድተው ሥራቸውን በጥንቃቄ ማከናወን ይገባቸዋል፡፡
የመደመር ፖለቲካዊ ፍልስፍናቸውን በመጠቀም በአፍሪካ ቀንድ የሚያደርጉትን ፖለቲካዊ መረጋጋትና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የመፍጠር ሂደት እንዳለ ሆኖ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚውንም ማጠናከር ሌላው ከዶክተሩ የሚጠበቅ ሥራ ነው፡፡ ለዜጎች በቂ የሥራ ዕድል መፍጠርም በአገሪቱ ያለውን ችግር ለመፍታት ያግዛል፡፡ በዚህ ረገድ በኢንቨስትመንት ላይ ሰፊ ሥራ መስራትም ዓላማቸውን ለማሳካት የራሱ ድርሻ አለው፡፡ ከዚህ አኳያ ከባህረ ሰላጤው ሀብታም የአረብ አገራት ጋር የጀመሩት ግንኙነት የሚያበረታታ ነው፡፡ ሰጥቶ መቀበልን መርሁ ያደረገ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸውም ለዚህ ተመራጭ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2011
መሐመድ ሁሴን