ወደብን ጨምሮ በማንኛውም የትብብርና የልማት ጉዳይ ዙሪያ መነጋገርና መወያየት ሊበረታታ ይገባዋል!

ሰላም እና አንድነት፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ሀገራዊ ሉዓላዊነት፣ በጥቅሉም ሁለንተናዊ ብልጽግና ለአንድ ሀገርና ሕዝቦች ዘለቄታዊ ሕልውና ወሳኝ ጉዳዮች፤ ዘመኑም የሚፈልጋቸው መሠረታዊ አጀንዳዎች ናቸው:: ኢትዮጵያም እንደ ሀገር በኅብር የደመቀው አንድነቷ እንዲጸና፤ ሰላሟና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ እንዲረጋገጥ፤ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷ እንዲጠበቅ፤ ሁሉን አቀፍ ብልጽግናዋም እውን እንዲሆን የልጆቿ ሕልምና ምኞት ነው::

ይሄ የልጆቿ ሕልምና ምኞት ግን በሃሳብ ብቻ የሚሳካ አይሆንም:: ይልቁንም ለተግባር የቆረጠ ልብን፤ ለሥራ የማይሰንፍ ጉልበትን፤ ለፈተናዎች የማይንበረከክ ሥብዕናን፤ በሂደቱ የሚጠይቀውን ዋጋ እና መሥዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀ ማንነትን፤… በእጅጉ ይፈልጋል:: ከዚህም በላይ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ አቅምን መለየት እና በጊዜውና በትክክለኛው አግባብ መጠቀምን ይጠይቃል::

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ትልቅ የመልማት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፣ የመልማት አቅምን ጭምር በጉያቸውና በዙሪያቸው የያዙ ሀገራት፤ የሕዝቦቻቸውን የሰላም፣ የአብሮነት፣ የልማት፣ የሉዓላዊነትና ሁሉን አቀፍ ብልጽግናን እውን የማድረግ ከፍ ያለ ጥያቄ ለመመለስ ይሄንን በውስጥም በዙሪያም ያለን ሀብትና አቅም ለይቶ ለመጠቀም የሚያስችል ርዕይን መያዝ ከመሪዎች ይጠበቃል::

በኢትዮጵያም ይሄን አይነት የዜጎች ጥያቄ ለመመለስ ብቻም ሳይሆን፤ እንደ ሀገር የመቀጠልና ያለመቀጠል ህልውናዋን ለማረጋገጥ እንዲህ አይነቱን ርዕይ መጎናጸፍ በእጅጉ የሚጠይቅ ነው:: በዚህ ረገድ፣ ኢትዮጵያ የ 120 ሚሊዮን ዜጎቿን አብሮነት ማስቀጠል፤ ሰላማቸውን ማጽናት፤ የኢኮኖሚ እና የልማት ጥያቄያቸውን መመለስ፤ ሉዓላዊነታቸውን ማረጋገጥ፤ ሁለንተናዊ ብልጽግናቸውን እውን ማድረግ የዘመኑ የቤት ሥራ ነው::

ይሄን ከማድረግ አኳያም እንደ ሀገር የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ውጤት እያመጡ ናቸው:: ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያን ከተረጂነት ወደ ላኪነት ያሸጋገራት የስንዴ ልማት ሥራ እንደ አንድ አብነት የሚጠቀስ ነው:: በሩዝ፣ በፍራፍሬ፣ በሻይና ሌሎችም መስኮች እየተከናወኑ ያሉ የግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ጅምሮችም የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን አቅምም ያሳዩ ሆነዋል::

በዚህ መልኩ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በዲፕሎማሲው ዘርፍ ውጤቶች መታገዝ ስለሚገባቸውም፣ በዲፕሎማሲው መስክ እየተሠሩ ያሉ ተግባራትም የኢትዮጵያን ትልቅነት ብቻ ሳይሆን የቀጣይ የልማትና ዕድገት ስበት ማዕከልነትም ያረጋገጡ ናቸው:: ከሩስያ፣ ከአሜሪካ፣ ከቻይና፣ ከአውሮፓ፣ ከአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር እያደረገች ያለው ፍሬያማ ዲፕሎማሲ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርቶ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ብዙ ያተረፈችበት፤ እያተረፈችም ያለችበት ሆኗል::

ይሄ በውስጥ ያለ አቅምን ለይቶ የማልማትና የመጠቀም ጅምር፤ የውጭ ትብብርና ወንድማማችነትን የማጠናከር ሂደት ደግሞ ሌላ ከፍ ያለ የመልማት ጥያቄን መውለዱ አይቀሬ ነው:: ምክንያቱም፣ ማምረት ካለ ከራስ አልፎ ወደ ውጪ መላክ አለ:: ማምረት ካለ ከውጭ ግብዓቶችን ማስገባት አለ:: የበለጠ ማደግ ካለ ደግሞ ሀገራዊ ሉዓላዊነት ላይ የሚደቀኑ ፈተናዎችን ማቋቋም የሚያስችል ዘርፈ ብዙ ዝግጁነትን ማጠናከር አለ::

እነዚህ መኖሮች ደግሞ እንደ ሀገር ለብቻ የመቆም ጉዳይ አይደሉም:: ይልቁንም ከጎረቤቶች ጋር አብሮ ማደግን፤ አቅምና ሀብትን አስተሳስሮ ለተሻለ ብልጽግና መራመድን፤ ወንድማማችነት ትብብርና ትስስርን ማጠናከርን፤ በጥቅሉ ቀጣናዊ አቅምን ማደራጀትን ይጠይቃል::

ይሄ ቀጣናዊ መደርጀት ደግሞ ኢኮኖሚያዊም፣ ፖለቲካዊም፣ ዲፕሎማሲያዊም፣.. ጉዳዮችን የሚጨምር ነው:: ለዚህ ደግሞ ሰላም ያስፈልጋል፤ ለሰላም ደግሞ መነጋገር ይጠይቃል፤ መነጋገር ሲኖር ደግሞ አብሮ የመልማት ፍላጎት ያድጋል:: አብሮ ለማደግ ፍላጎት ካለ ደግሞ ሀብትን፣ ጉልበትን፣ ቴክኖሎጂን ባጠቃላይ ለሁለንተናዊ ብልጽግና የሚሆኑ አቅሞችን አስተባብሮ ለመጠቀም እድል ይሰጣል::

ኢትዮጵያም ዛሬ ላይ ሁሉ ነገር ቢኖራትም አንድ የጎደላት ነገር አለ:: በአንጻሩ ጎረቤቶቿ ሁሉ ነገር ቢኖራቸውም ሌላ የጎደላቸው ነገር ይኖራል:: ይሄ ጉድለት ደግሞ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ፤ ጎረቤቶቿም ከእሷ ማሟላት የሚችሉበት እድልም አቅምም አለ:: ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ የወጪና የገቢ ሸ ቀጦችን አስተማማኝና ቀልጣፋ በሆነ መልኩ የምታሳልጥበት የባህር በር (ወደብ) ያስፈልጋታል::

ይሄን የባህር በር ስትሻ ደግሞ እንዲሁ ከመሬት ተነስታ አይደለም:: የ 120 ሚሊዮን ሕዝብን የመልማትና የደኅንነት ጥያቄ ለመመለስ እንጂ:: ይሄን የሕዝቦቿን የመልማትና የደኅንነት ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ የጎረቤቶቿን ወዳጅነት፤ የቀጣናውን አብሮ የመልማትና ለዚህ አቅም የሚሆኗቸውን ሀብቶች በጋራ አልምቶ የመጠቀም መርህን ታላሚ በማድረግ ነው::

ምክንያቱም ወቅቱ ሰላምን፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን፣ ሀገራዊም ሆነ ቀጣናዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በጋራ መሥራትን የሚጠይቅ ነው:: ይሄ በጋራ መሥራት ደግሞ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል አቅም እና ሀብትን ከመለየት ይጀምራል:: እንዴት በጋራ አልምቶ በጋራ መጠቀም እንደሚቻል ቁጭ ብሎ መምከርና መግባባት ላይ መድረስን ይጠይቃል:: ይሄ የሚሆነው ግን በጋራ መሥራትና በጋራ መልማት ያለውን ፋይዳ መገንዘብ ሲቻል ነው::

ኢትዮጵያም ‘ሁሉ ኖሮኝ በወደብ (የባህር በር) ችግር ምክንያት የዜጎቼን የመልማትም፣ የአንድነትና ሉዓላዊነትም ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ የማልችልበት ደረጃ ላይ እየደረስኩ ነው፤ ስለዚህ ያለኝን አካፍዬ ያላችሁን ተካፍዬ በጋራ መልማትም፣ መበልጸግም እንድንችል እንነጋገር እና የባህር በር ላግኝ’፤ ብላ መጠየቋ ከኢትዮጵያ ግላዊ ጥቅም አኳያ የሚገለጽ አይደለም::

ይልቁንም ቀጣናዊ አቅሞችን አስተባብሮ የመጠቀም፤ ሀብትን በጋራ የማልማትና ሁሉን አቀፍ የጋራ ብልጽግናን እውን ማድረግ የመቻልን እውነታ በመረዳት እንጂ:: በመሆኑም የኢትዮጵያ የወደብ ፍላጎት ሃሳብና ጥያቄ ለቀጣናዊ ልማትንም፣ ለፍትሃዊ የሀብት ተጠቃሚነትም እድልና መንገድ መሆኑን መገንዘብ የተገባ ነው!

አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2016

Recommended For You