ኢትዮጵያ ሆይ ማእድሽ ሙሉ ይሁን! ሰላምሽም ይብዛ፤

የጉዞ ማስታወሻ

እለተ ረቡዕ መስከረም 16/2016- የመስቀል ደመራ የሚበራበት ቀን ነበር:: በመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር የሚመራውና ከ 11 የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎችን የያዘውን ቡድን ለመቀላቀል ከመኝታዬ የተነሳሁት ማልጄ ነበር:: የጉዞው መዳረሻው የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ሲሆን ዓላማው ደግሞ በክልሉ እየተከናወኑ ፣ በመንግሥትና በባለሀብቶች እየተከናወኑና በመከናወን ላይ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እንዲሁም እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን በመጎብኘት፤ የተለያዩ ዘገባዎችን በማዘጋጀት ለህብረተሰቡ ማሳወቅ ነበር::

የመኪናው የጉዞው መስመር መኖሪያ ሰፈሬን ወይም ዘነበወርቅን አቋርጦ የሚያልፍ በመሆኑ ወደ ጉዞ መነሻው ወይም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ መሄድ ሳያስፈልገኝ እዛው በሰፈሬ ቆሜ የመኪኖቹን መምጣት መጠባበቅ ጀመርኩ:: የጉራጌና የደቡብ ልጆች ሻንጣዎቻቸውን በተለያዩ እቃዎች እስከአፍጢማቸው ሞልተው ፤ ወዳጅ ዘመድ ለመጠየቅም ሆነ በዓልን ከቤተሰብ ጋራ ለማሳለፍ ፤ ብቻ ወደ ሀገር ቤት እያቀኑ ነበር::

ወጪ ወራጁን፤ አላፊ አግዳሚውን ስመለከት የእጅ ስልኬ አቃጨለ:: አጋፔ ግዮን የመሥሪያ ቤታቸችን የካሜራ ባለሙያ መሆንዋን ከእጅ ስልኬ ተገንዝቤያለሁ:: “ከፊት የምታየው ኮስትር መኪና ውስጥ ግባ” አለችኝ:: ወደ መኪናው ገብቼ ግራ ቀኙን ሳማትር፤ ሁሉም የሚዲያ ባለሙያዎች፤ ፈንግል እንደመታቸው ዶሮዎች ወዲህና ወዲያ ፍንግል…. ፍንግል ብለዋል:: በእርግጥ ሁሉም ከሌሊቱ 9፡ 00 ሰዓት ጀምሮ እንቅልፍ እንዳይጥላቸው በአንድ ዓይናቸው ተኝተው በሌላ ዓይናችው መንጋቱን ሲጠባበቁ ማደራቸውን መገመት ከባድ አይሆንም:: ጨለማው ለንጋት ቦታውን እየለቀቀ ሲመጣ ፤ የተኛው ሁሉ ተነቃቃ:: ለወትሮው ፉልና ሌሎች ፈጣን ምግቦችን መመገብ የለመደው የጋዜጠኞች ቡድን ፤ አፉን በኬክና በውሃ እያሟሸም ከመጓዝ የተሻለ አማራጭ አልነበረውም:: መኪናዋ የጅማን የጉዞ መስመር ይዛ ትነጉዳለች::

ሰማዩ ጠቁሯል:: ከሰማይ እስከ ምድር የተለቀቀና አቅም የሌለው መጋረጃ የሚመስለው ጉም አልፎ አልፎ የሚታይ አስደማሚ ክስተት ነበር:: ተፍኪ የምትባለው መለስተኛ የገጠር ከተማ ደርሰናል:: በአስፋልቱ ግራና ቀኝ የሚገኘው ስፍራ በርከት ያለ ውሃ አዝሏል:: ውሃውን ለሁለት የሚከፍለው አስፋልት ፤ ስፍራውን ሬንጅ የፈሰሰበት በረዶ አስመስሎታል:: በመኪናው በስተቀኝ በኩል ለአበባ አልሚ ባለሀብቶች ተሰጥቶ የነበረና አሁን ላይ ምንም አይነት አገልግሎት የማይሰጥ መጠነ ሰፊ ሄክታር ላይ ዓይኔ አረፈ:: የድንኳን ማቆሚያው ብረት ሲቀር፤ የላስቲክ ድንኳኖቹ በጊዜ ብዛት ክጥቅም ውጪ ሆነዋል:: ቦታው ለምንም ዓይነት አገልግሎት ላለመዋሉ ምስክሩ፤ አደይ አበባ በቅሎበት መታየቱ ነው ::

ሰዓቱ እየገፋ ሲመጣ፤ እኛም ወደፊት እየቀዘፍን፤ ግቤ በረሃ ላይ ደረስን :: ይህን ጊዜ የፎቶን የቪዲዮ ካሜራ ባለሙያዎች በቀኝና በግራ መስኮቶች በኩል የሚታየውን ውብ ተፈጥሮ በምስል ለማስቀረት መራወጥ ጀመሩ:: ሌሎቻችንም የእጅ ስልካችንን ተጠቅመን በግብር መሰልናቸው:: ግቤ በረሃ በቀደመው ግርማ ሞገሱ እንዳለ አለ:: አንዳንድ ቦታ ላይ በአስፋልት ጥገና ምክንያት የመንገድ ለውጥ ለማድረግ ከመገደዳችን በቀር ጉዞው ቀና፤ እኛም ዘና ብለናል:: በድንቅ የተፈጥሮ ውበት እየተደመምን፤ የግቤ ወንዝን ማቋረጥና ምሳን መዝለል አንድና ያው ናቸው በሚለው ተስማምተን ፤ ከአድካሚ ጉዞ፤ ድካምና ረሃብም በኋላ ከቀኑ ዘጠኝ ተኩል ሲል ጅማ ከተማ ደረስን::

የምሳ ሰዓት አልፎም ቢሆን ሁሉም ተጓዥ ረሃቡን ለማስታገስ በእውር ድንብር የተገኘውን ለመቅመስ ከመኪናው ወረደ:: የፍቅር ከተማ ተብላ የምትጠራው ጅማም እንደሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በእለቱ የደመራና የመውሊድ በዓላትን በድምቀት አክብራለች:: የየትኛውም የሃይማኖት ተከታይ ልትሆን ችላለህ፤ በጅማ ስትኖር ሃይማኖት፤ ማህበራዊ መስተጋብርና ፍቅርን ለማጠናከር ምክንያት እንጂ ለልዩነት ስጋት ሆኖ አይውቅም ይላሉ ለምሳ ካረፍኩበት ሆቴል በጋራ ምግብ እየበሉ የነበሩ ወጣቶች:: ያስምርላችሁ ከማለት ውጪ ምን ይባላል::

አመሻሹ ላይ የጅማ ቆይታችንን አጠናቀን ወደ አመያ አቀናን፡፡ ከጅማ ወደ አመያ የሚወስደው መንገድ በኮስትር መኪና የማይሞከር ነው፡፡ መንገዱ በግንባታ ላይ እንደሆነ የሚያሳብቁ ነገሮች ቢኖሩም፤ የመንገድ ሥራው መዘግየቱ ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለ አላፊ አግዳሚው የሚያረጋግጠው እውነት ነው፡፡ ወዲህ ድቅድቅ ጨለማ፤ ወዲያ ጥቅጥቅ ያለ ደን ጉዞውን አስፈሪና ከአሁን አሁን ምን ሊከሰት እንደሚችል ማንም መገመት እንዳይችል አደረገው፡፡ በፍርሃት ተውጠው የሚቁለጨለጩ ዓይኖች በመኪናው የፊት መብራት እየታገዙ አንዳንዴም ወደላይ ከፍ እንደገና ወደታች ዘጭ ማለት ብቻ ሣይሆን በርከት ያለ አቧራ መቃም፤ የአስቸጋሪው የሌሊት ጉዞ መገለጫዎች ነበሩ::

ከሌሊቱ አራት ሰዓት ሲሆን በጉዟችን መሃል አንድ አስደንጋጭ ክስተት ተፈጠረ:: መኪናዋ ከወደ ኋሏዋ የተለየ ድምጽ ማሰማት ጀመረች:: ቀድሞም የመንገዱን አስቸጋሪነት የተረዳውና ሲማረር የነበረው ሹፌር ፊቱ ተለዋወጠ:: ድንጋጤው አስደነገጠን:: መኪናው የመንገዱን ዳር ይዞ ቆመ:: ሁሉም ነገር ጨለማ ሆነ:: ሁላችንም ጸጥ ረጭ አልን:: ከነፍሳት ሲርሲርታ በቀር የሚሰማ ነገር የለም:: ሹፌሩ ድቅድቁን ጨለማ በመጠኑም ቢሆን በባትሪ አብርቶ፤ በመኪናው የኋለኛ እግር አካባቢ የተፈጠረውን ነገር አጤነ::

ሹፌሩ ወደ ውስጠኛው የመኪና ክፍል ሲገባ ሁሉም የሆነው ለማወቅ “ምንድነው?” በአንድነት ጠየቅን:: “የመኪናው ባሌስትራ ተሰብሯል” አለ የለበሰው ልብስ በሚያካፋው ዝናብ የረሰረሰው ሹፌር መለሰ:: የመኪናውን በር ዘግተን ከኋላችን ሲጓዝ ነበረውን መኪና መጠበቅ የግድ ሆነብን:: ከአፍታ ቆይታ በኋላ፤ ሲጠበቅ የነበረው መኪና ደረሰ:: ሌላኛው ሹፌር የሆነውን ክስተት በቅጡ ከተረዳ በኋላ፤ ወደ እኔ መኪና ሂዱ፤ የተበላሸው መኪና ቀስ ብሎ ይምጣ አለ እኛም በሃሳቡ ተስማምተን እቃዎቻችንን ይዘን ጉዞ ቀጠልን ::

በእንቅልፍም በንቃትም ብዙ ከተጓዝን በኋላ አመያ ወደተሰኘች አነስተኛ የገጠር ከተማ ደረስን:: መምጣታችንን ሲጠባበቅ የነበረው የአመያ ህዝብ አቀባበሉ ልዩ ነበር:: የእራት ብሉ ግብዣ የቀረበልን፤ እንደደረስን ወይም ለእኩለ ሌሊት ተኩል ሰዓት ሲቀረውም ቢሆን ትንሽ ለመቀማመስ አልቦዘንም:: አኩራፊ ሰው ምሳው እራቱ ይሉለታል እንዲል ተረቱ:: በጉዞው መጎሳቆላቸው ያሰቡ አንዳንዶች ዓይናችን ለመኝታ እንጂ ለምግብ አይገለጥም ብለው ጦማቸውን አደሩ:: የሆነው ሆኖ ከአስራ ስምንት ሰዓታት ጉዞ በኋላ አዳራችን በዚያው ሆነ:: ተኝቶ እንደ መነሳት ያለ አእምሮን የሚያድስ ነገር ምን አለ:: በብዙ ድካም የዛለው ስጋችን አሁን እረፍት አገኘ::

መሽቶ መንጋቱ አይቀርምና ነጋ:: ከወደቅንበት አልጋ ዓይናችንን እንድንገልጥና እንድንነቃ ምክንያት የሆኑን የመንደሩ ህፃናት ነበሩ:: እነሱ ፤መስቀልን በዓመት አንድ ጊዜ የሚያገኙት በዓል ስለሆነ ልዩ ቦታ ይሰጡታል:: አስር የሚሆኑ ህጻናት በቅደም ተከተል ተሰልፈውና ድምጻቸው ከፍ አድርገው በኮንታ ብሔር ቋንቋ ሂዮ….. ሂዮ በዓለ… ሂዮ እያሉ ደጋግመው ይዘፍናሉ:: እንኳን አደረሳችሁ፤ እንኳን አደረሰን እንደ ማለት ነው:: ይህን በየሰዉ ደጃፍም እየቆሙ ደጋግመው ያዜሙታል:: በምላሹም፤ ትንሽ ሳንቲም የሚሰጣቸው አለ:: ሌላው ደግሞ ወደ ቤት እንዲገቡ ያደርግና ቤት ያፈራውን ይጋብዛቸዋል:: እነሱም ለዓመት ያድርሰን እያሉ አመስግነው ወደ ሌላው መንደር ይሄዳሉ::

ከበዓሉ አከባበር ጋር ተያይዞ እርድ የሚከናወነው በታዋቂ ሰዎች ደጃፍ ላይ ነው:: የስጋ ክፍፍል በሚከናወበት ጊዜም የድሃ ድሃ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ በማድረግ ነው:: በበዓሉ ሁሉም ተደስቶ እንጂ አዝኖ መዋል የለበትም የሚል የጋራ እሳቤ እዛ አለ:: በእለቱ አንድ የማህበረሰቡ አባል ቡና ተጠርቶ ሲሄድ አደይ አበባ ሣይዝ ወደተጠራበት ቤት መሄድ ነውር ነው::

ሁሉም ሰው ከተጠራበት ደጃፍ ሲደርስም ሂዮ….. ሂዮ በዓለ… ሂዮ እያለ ይገባል:: እንኳን አደረሳችሁ … እንኳን አደረሰን እንደማለት ነው:: ይህ ባህላዊ ሥርዓት ህጻን-አዋቂ ፤ ሴት-ወንድ ሳልለይ በሁሉም የብሄረሰቡ ተወላጅ የሚከወን ነው:: ከዚያም ቤት ያፈረራውን ምግብም ሆነ መጠጥ ከዘመድ፤ ወዳጅና ጎረቤት ጋር በመሆን ከአንዱ ቤት ወደ ሌለው እየተጠራሩ እየበሉና እየጠጡ በዓሉን በጋራ ከመስከረም 1 እስከ 30 ያከብራል:: ሲሊሶ፤ ሱልሶ፤ ኡስታ፤ ባጭራ፤ ኩቶኩብዋ እና ሌሎችም ምግቦች የበዓሉ መድመቂያ ናቸው:: ኩላኩሎ፤ ቦርዴ እና የመሳሰሉት መጠጦችም በዓሉን ያሳምሩታል::

የአመያ ቆይታችንን አጠናቀን ወደ ኮይሻ ተንደረደርን:: በጉዞአችንም ስለ አዳራችን ፤ ስለውሎአችን፤ በአካባቢው ስለሚታየው ድንቅ ተፈጥሮ፤ እዚህም እዚያም ከጫካ ብቅ ብለው ወዲያው ጥልቅ ስለሚሉት የዱር እንስሳት ተፈጥሮ፤ ቀልድም ቁምነገርም እያነሳንና እያወጋን የቀረንን 13 ኪሎሜትር አገባደን ኮይሻ ገባን:: ይህችን አነስተኛ የገጠር ከተማ በሰው ብዛት ደመቅ ያለች ብትሆንም እርጅና የተጫናት ትመስላለች:: ለዚህች ከተማ ህልውናዋ የንጹህ ማርና ቅቤ እንዲሁም ፍራፍሬዎች መገበያያ ማእከል መሆኑዋ ነው:: በዚያ የሚያልፍና ለቦታው እንግዳ የሆነ ሰው ሁሉ ማር ይዞ ለመሄድ መቋመጡ አይቀሬ ነው:: እኛም፤ ስንመለስ እንደርሳለን በሚል አንድ ሃሳብ ተስማምተን መንገዳችንን ቀጠልን::

ኮይሻ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ እንደደረስን ምልክቱ፤ ከፊታችን የታጠረ ኬላ መገኘቱ ነው :: ከኬላው ለማለፍ የፈቃድ ደብዳቤ ማሳየት ብቻውን አይበቃም:: በእጅ የተያዘ ሻንጣም፤ ላፕቶፕና ካሜራ ማስፈተሽና ማስመዝገብ የግድ ነው:: የተጠየቀውን መስፈርት ሁሉ ካሟላን በኋላ እንድንገባ ተፈቀደልን:: በፕሮጀክቱ የጥበቃ ሠራተኞች እየተመራን ወደተዘጋጀልን ማረፊያ አመራን::

የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ አጠገብ ተራራማ ቦታ ላይ ደረጃቸውን ጠብቀው የታነጹ የሠራተኛ መኝታ ክፍሎች ይታያሉ:: አሠራራቸው ከመለስተኛ ደረጃ ሆቴል ቢበልጡ እንጂ አያንሱም:: ከ ቪ.አይ.ፒ እስከ ተራ ሠራተኛ ድረስ ወደ ፕሮጀክቱ ለሚመጡ እንግዶች፤ ነጻ የመኝታ አገልግሎት ያቀርባል:: እኛም ለእንግዳ ማረፊያ ተብለው የተሰናዱትን ክፍሎች ቁልፍ ተረከብን:: ሻንጣዎቻችንን ከመኪናው አወረድንና ከሻወር በኋላ ወደ ምሳ ለመሄድ ተቀጣጥረን በየክፍላችን ገባን::

እያንዳንዱ ማረፊያ ክፍል፤ ሻወር፤ ሽንት ቤትና የመኝታ ክፍሎች አሉት:: ከሻወር በኋላ ወደ ምግብ አዳራሹ አመራን:: እኛ ካረፍንበት መኝታ ክፍል አዳራሾቹ ጋር ለመድረስ ከ 2-5 ደቂቃ ይፈጃል:: በቅርብ ወዳገኘነው አዳራሽ ስንገባ የፕሮጀክቱ ሠራተኞች ምሳቸውን እያጣደፉት ነበር:: የምናውቀው ሰውን ፍለጋ አዳራሹን ከጥግ ጥግ አማተርን፤ ነገር ግን ሁሉም ፊት ለኛ አዲስ ነበር:: ግራ መጋባታችንን እንግዳ መሆናችንን የተረዱ አንዳንድ ሠራተኞች ወደ ሌላኛው አዳራሽ እንድንጓዝ አመለከቱንና ወደዛው አመራን:: በጎጆ ቤት ቅርጽ ከተራራ ጫፍ ላይ ዘመናዊ ሆኖ የተገነባው ሌላኛው የምግብ አዳራሽ በዙሪያው ያለውን ውብና ማራኪ ሰንሰለታማ ተራሮች ፍንትው አድርጎ ያሳያል:: አረንጓዴ ምንጣፍ የለበሱ የሚመስሉት እነዚህ ተራሮች ጥቅጥቅ ባለ ደን ተሸፍነዋል::

ሰንሰለታማ ተራሮቹን ልዩ ውበት ያጎናጸፈቸው ደግሞ ከግርጌያቸው የሚገኙት ሜዳማ ቦታዎች ናቸው:: ይህን በዓይን ተመልክተው የሚጠግቡት አይደለምና በሞባይል ስልካችንም በካሜራዎቻችንም ውበቱን አስቀረነው:: የተገኘውን ቀማምሰን እንደጨረስን፤ የሥራ መመሪያም ተቀበለን:: ከድካም በጸዳ አዲስ መንፈስ ሆነን የግድቡን ሥራ አፈጻጸም ማየቱ ስለታመነበት ተረፈ መዓልቱን ወደ ክፍሎቻችን ሄደን እረፍት አደረግን::

በበነጋው ጠዋት ላይ ተነሳንና የተዘጋጀልንን ሆቴል የሚያስንቅ ቁርስ ተመገብን:: ቀጣዩ የጉዟችን መዳረሻ የኮይሻ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ነበርና ወደዛው አመራን:: ቀድሞ የመጣንባቸው ኮስተር ሚኒባሶች ወደ ግድቡ የሚያወርደውን ጠመዝማዛና ቁልቁለት መንገድ ለመሄድ ስለማይችሉ እዛው ባሉበት እንዲቆዩ ተፈረደባቸው:: ለዚህ መንገድ ተመራጭ የሆኑ ትንንሽ መኪኖች ውስጥ ገብተን፤ ትንሽ እንደተጓዝን አንድ ማማ ላይ ደረስን:: እዚህ ማማ ላይ ቆመህ ሁሉንም የግድቡን ሥራዎች ያለከልካይ ማየት ትችላለህ::

እጅግ በርካታ ሠራተኞች ግድቡን እውን ለማድረግ ቀንና ሌት፤ ለ 24 ሰአታት ያለማቋረጥ ይተጋሉ:: ለቃለ ምልልስ በቆምንባቸው ጥቂት ደቂቃዎች፤ ላብ ጀርባችን ላይ ይንዠቀዠቅ ያዘ:: ምላሳችንም እንደኩበት ደረቀ:: እኛ እንዲህ ከሆን፤ ሌት ተቀን የሚታትሩት ሠራተኞች ሙቀቱን እንደምን ቻሉት? ለሚለው የህሊና ጥያቄዬ መልስ አጣሁለት :: ወጣት ሴት እንጂነሮች ከወንድ የሙያ አጋሮቻቸው ጋር ሆነው ይወጣሉ ይወርዳሉ:: እንደገና ከማማው የሚያሰወርዱትን ጥቂት መንገዶችን ቁልቁል ወረድን:: የግድቡ የሲቪልና የመካኒካል ሥራዎች የሚከናወኑበት ቦታ ላይ ሆነን ሁሉን በቅርበት ተመለከትን:: የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ እራትም መብራትም ለመሆን ግስጋሴውን አጠናክሮ ቀጥሏል::

ግድቡ ለኢትዮጵያውያን የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማእከልም ሆኖ እያገለገለ ይገኛል:: ፕሮጀክቱ፤ አሁን ላይ ቁጥራቸው 5000 ለሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል ፈጥሯል:: እነዚህ ሠራተኞች እውቀትና ልምዳቸውን እንዲያሳድጉ ብቻ ሳይሆን የሥራና የደመወዝ እድገት እንዲያገኙም ምክንያት ሆኗል ፕሮጀክቱ:: ብዙዎች ከዝቅተኛ የሥራ ደረጃ ተነስተው የትልቅ ሙያ ባለቤት ለመሆናቸው ቋሚ ምስክሮች ናቸው:: ይህ አይነቱ የአቅም ግንባታ ሥራ ሀገሪቱ ወደፊት በራስዋ አቅም መሰል ፕሮጀክቶች እንድትገነባ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ መገመት አያዳግትም::

የኮይሻ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አጠቃላይ የግንባታ ሥራው 61 በመቶ የደረሰ ሲሆን ከሶስት ወይም አራት ዓመት በኋላ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ፤ 1800 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት ወደ ሀገሪቱ የሃይል ቋት እንደሚያስገባም ከጉብኝቱ ተገንዝበናል:: ለሥራችን ይጠቅመናል ያልነውን መረጃ ሰብስበን ወደ ማረፊያ ክፍሎቻችን የሽምጥ ጋለብን:: ቃለምልልሶችን ለመስራት በሚዲያ ባለሙያዎች መካከል የነበረው የሥራ ክፍፍልና ትብብ ሥራዎቻችን በጊዜ እንድናጠናቀቅ ያስቻለ ድንቅ ዘዴ ነበር:: ዜናዎቻችንን ወደ ሚዲያ ተቋሞቻችን ከላክን በኋላ ለእራት ወደ ምግብ አዳራሾች ተጓዝን:: የምግብ ጠረጴዛው በኮንታ ብሔር ባህላዊ ምግቦች የተሞላ ነበር:: ቅቤ የጠጣውን ምግብ አጣጣምነው:: ግብዣው ቀ—ጥ—ሏ—ል:: ኢትዮጵያ ሆይ ማእድሽ ሙሉ ይሁን! ሰላምሽም ይብዛ! አሜን::

ውድ አንባቢያን በክፍል ሁለት የጉዞ ማስታወሻዬ ደግሞ በጨበራ ጩርጩራ እና ሃላላ ኬላ መስህቦች ያደረግነውን ምርጥ ውሎ አስቃኛችኋለሁ:: ቸር እንሰንብት::

በግርማቸው ጋሻው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2016

Recommended For You