አማረ ቀናው(ዶ/ር) በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ
ዶክተር አማረ ቀናው በውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት መሪ ተመራማሪና የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ጀነራል ናቸው። ዶክተሩ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ጥናት ረዳት ፕሮፌሰርና የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ሆነውም አገልግለዋል። ከዘመናዊው ዓለም አቀፍ ደህንነት ክልላዊ ውህደትና ከዓለም አቀፍ ትብብር ጋር በተያያዙ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ በርካታ ጽሑፎችንም ለማሳተም ችለዋል።
አዲስ ዘመን ከእኚህ መሪ ተመራማሪ ጋር በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እና መካከለኛው ምስራቅ ላይ ያተኮረ እንዲሁም ኢትዮጵያ በባህር በር ጉዳይ ላይ መነጋገር አለባት በሚል የሰሞኑን ዋና አጀንዳ በሆነው ቀይ ባህር ላይ አስመልክቶ ከእርሳቸው ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ የምትገኝበትን የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አሁን ካለው ዓለም አቀፍ ፖለቲካ አንጻር እንዴት ያዩታል?
ዶክተር አማረ፡– በብዙ መልኩ ምስራቅ አፍሪካ በተለይም ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ የምንለውን አካባቢ አሁን ካለው የጂኦፖለቲካ ሽኩታ አንጻር በተለየ መንገድ ሊታይ ይችላል። አካባቢው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ በኋላ ላይም በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ከፍተኛ የሆነ የኃያላን ፉክክር የሚታይበት መድረክ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ደግሞ እኤአ ከ1990ዎቹ ወዲህ ከዚህ ዓይነት ሁኔታ በተወሰነ መልኩም ቢሆን መውጣት የታየበት አዝማሚያ ነበር። ይሁንና በቅርቡ ደግሞ በቀጣናው አካባቢ የመፎካከሩ ነገር ተመልሶ መጥቷል።
ፉክክሩ የኃያላን ብቻ ሳይሆን በቀጣናው አካባቢ አዳዲስ ኃያላን ሀገራት የተፈጠሩበት ሁኔታም እየታየ ነው። ለአብነት ያህል እነዚህ አዳዲስ የተባሉ ሀገራት ከአረቡ ሀገራት እነሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች፣ ቱርክ፣ ኢራን እና የመሳሰሉት ሲሆኑ፣ ወደኃያላኑ ተርታ የመሰለፍ አዝማሚያ የታየባቸው ናቸው ማለት ይቻላል።
ከዚሁ ከኃያላን ፉክክር ጋር ተያይዞ እንደሚታወሰው በምስራቅ አፍሪካ ወይም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚገኙ ሀገራት በአብዛኛው በውክልና ጦርነት ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወቃል። አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በቀጣናው ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ቀዝቀዝ ብሎ የነበረው ሁኔታ መልሶ ማንሰራራት ታይቶበታል። ይህ እንቅስቃሴ ደግሞ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለቀጣናው ሀገራት የደህንነት ስጋት ሊሆን እንደሚችል ይስተዋላል። ከዚህም የተነሳ ምናልባትም ቀጣናው ተመልሶ የውክልና ጦርነት ውስጥ ሊገባ የሚችልበት ሁኔታ ሊከሰትበት ይችላል።
ሌላው፣ አካባቢው የመልክዓ ምድራዊ ፖለቲካ ጠቀሜታው እጅግ በጣም ከፍ ያለ ነው። የምናውቃቸው የአውሮፓ፣ የኤዥያ፣ የአፍሪካ፣ አውስትራሊያንም ጨምሮ የተለያዩ ክፍለ ዓለማትን በማገናኘት እንደ መገናኛ መስመር ተደርጎ የሚቆጠር ነው። ስለዚህ ኃያላን ሀገራት አካባቢውን ለመቆጣጠር ትልቅ ሹክቻ ውስጥ ናቸው ማለት ይቻላል። ይህ አሁንም እንደገና እየተጠናከረ ነው።
ከዚያ ጋር ተያይዞ የኃያላኑ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ እንዲሁም የቀጣናው ኃያላን ጭምር በአካባቢው ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ መፍጠራቸው እንዲሁም አካባቢውን ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ሽኩቻ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል።
እንደሚታወቀው በተለያየ ጊዜ በአካባቢው ግጭቶች ያገረሻሉ። በተለይም በሀገራቱ መካከል በድንበር ጉዳይም ሆነ ማንነትን መሠረት ባደረገ ምክንያት ግጭቶች ሲከሰቱ የነበረበት አካባቢ ነው። ይሁንና አስቀድሜ እንደገለጽኩት በተወሰነ መልኩም ቢሆን ረግበው ነበር።
ይሁንና ከኃያላኑ ፉክክር ጋር ተያይዞ እንደገና የማገርሸትና ወደግጭት የመምጣት ሁኔታ እየታየበት ያለ ቀጣና እየሆነ ነው። በተጨማሪም በተወሰነ መልኩም ቢሆን ድንበር ዘለል የምንላቸው የደህንነት ስጋቶች አሉ። እነዚህም የተለያዩ የዝውውር ዓይነቶች ሲሆኑ፣ በተለይ የመድኃኒት ዝውውር፣ የሰው ዝውውር ብሎም የመሳሪያ ዝውውር የሚደረግበት አካባቢ በመሆን ላይ ነው።
ስለዚህ በአካባቢው የሰፈረው አብዛኛው ማኅበረሰብ ተመሳሳይ ማንነት ያለው ዓይነት በመሆኑ በአብዛኛው ለእንደዚህ ዓይነት ዝውውሮች የተጋለጠ ነው። ይህ ደግሞ ለቀጣናው ሀገራት የደህንነት ስጋት እየሆነ መጥቷል። ከዚያ ጋር ተያይዞ የኃያላን ጎራ መደበላለቅ አለ። ሀገራቱ ደግሞ “ከየትኛው ኃያል ጀርባ መሰለፍ አለብኝ” የሚል ስጋት በየጊዜ እየተደቀነባቸው ነውና ራሳቸውን በየትኛው መስመር ማግኘት እንዳለባቸው የሚሻኮቱበት ሁኔታም የሚታይበት ነው።
ሌላኛው አካባቢው ከድንበር ዘለል ጦርነቶች ይልቅ በውስጣዊ ጦርነቶች የመጠመድ ሁኔታ እየተንጸባረቀበት ነው። በአንድ ወቅት አካባቢው ይካሄድበት የነበረው ድንበር ዘለል የሆኑ ግጭቶች ነው። ይህ ግን በተወሰነ መልኩም ቢሆን እየረገበ የመጣ ቢሆንም አሁን ደግሞ በውስጥ ጉዳይ የመጠመድ ሁኔታ ይስተዋላል።
ለአብነት ያህል የቅርቡን የሱዳንን የውስጥ ግጭት መውሰድ እንችላለን። ሀገራችን ኢትዮጵያም በተወሰነ መልኩ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት የውስጥ ግጭቶች የነበረብን እንደሆነ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በመሆኑም የውስጥ ግጭቶቹ የዚህ አካባቢ ጂኦፖለቲካ ባህሪ ሆኖ ጎልቶ እየወጣ ነው። ሀገራቱ በራሳቸው የውስጥ ጉዳይ የመጠመዳቸው ሁኔታ ለአካባቢው የደህንነት ስጋት ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ ይኖረዋል።
ምክንያቱም ሱዳን ላይ የሚካሄድ ግጭት እኛም ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። እኛም ዘንድ የሚካሄድ ግጭት ደግሞ ምናልባት ኬንያ፣ ጂቡቲ እንዲሁም ኤርትራ ላይ ተጽዕኖ ያሳርፋል። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት አዳዲስ የሆኑ የደህንነት ስጋቶች እንደገና በአዲስ መልክ እየመጡ ያሉ ናቸው ማለት ይቻላል። ምንም እንኳን ቀጣናውን የቀድሞዎቹ ስጋቶች ሙሉ ለሙሉ ለቀውታል ብሎ ለመናገር ባያስደፍርም አዳዲስ ስጋቶች የጂኦፖለቲካ ባህሪ መገለጫ ሆነዋል ማለት ይቻላል።
ሌላኛው በቀጣናው ባሉ ሀገራት የተካሄደው የመንግሥት ለውጥ ነውጥ አልባ በሆነ መንገድ መሆኑ የማይካድ ነው። ዴሞክራሲያዊ ነበር ብሎ ለመፈረጅ ቢከብድም የተካሄዱ የመንግሥት ለውጦች በተወሰነ መልኩ ነውጥ አልባ ነበሩ ማለት ይቻላል። ለአብነት ያህል የሀገራችንን፣ የሱማሊያን በቅርቡ ደግሞ የኬንያን የመንግሥት ለውጦች ስንመለከት ሰላማዊ ነበሩ ማለት ይቻላል። ለውጦቹ በምርጫ የተካሄዱ ናቸው፤ ምናልባት ዴሞክራሲያዊነታቸው እንደየሀገሩ ባህሪ ሊለያይ ቢችልም ለውጦቹ ያለ ግጭት መካሄዳቸውና ሕዝባዊ በሆነ መንገድ የመጣ በመሆኑ አንድ ጥሩ የሚባል ባህሪ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን።
ቀደም ሲል በድንበር ግጭት የሚታወቀው ይህ አካባቢ አሁን አሁን ግጭቶች ሲከሰቱም እንኳ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች እየበዙ የመጡበት ሆኗል። ከዚህም የተነሳ በቀጥታ ወደጦርነት የመግባቱ ነገር እየቀነሰ ይገኛል። እንደ ምሳሌ መጥቀስ የምንችለው የኢትዮጵያንና የሱዳንን በቅርብ የነበረው የድንበር ግጭትን ሲሆን፣ ይህን በአርዓያነት ልንወስደው እንችላለን።
በወቅቱ በተፈጠረ ክፍተት የሱዳን ኃይል በተወሰነ መልኩም ቢሆን የኢትዮጵያን መሬት ተቆጣጥሮ እንደነበር የሚታወቅ ነው። ስለሆነም በሁለቱ ሀገራት መካከል የዲፕሎማሲ መሻከር ሊፈጥር ይችላል የሚል ሃሳብም ነበር። በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ጥረት አድርጓል። እስካሁንም ቢሆን ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተፈቷል ባይባልም በቀጥታ ግን ወደ ጦርነት አልተገባምና ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ የመፍታት ባህሪ እየመጣ ነው ማለት ያስችላል።
በሌላ መንገድ ግን የእኛንም ጨምሮ በብዙ የአካባቢው ወይም የቀጣናው ሀገራት ታጣቂነት የምንለው ስሜት እጅግ እየተባባሰ መጥቷል ማለት ይቻላል። በእርግጥ እንደዓለም አቀፍም ሲታይ ከመደበኛ ይልቅ ወደ ኢ-መደበኛ ሁኔታ ውስጥ የመግባት ሁኔታ አዝማሚያ ተስተውሏል። ለምሳሌ በሀገራችን ያለው ሁኔታ ሲታይ ኢ-መደበኛ የሆኑ አካላት መደበኛ የሆነውን መንግሥት የሚፈትኑበት ሁኔታ እየተከሰተ ይገኛል።
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በጣም እየጎላ የመጣውና በአሁን ወቅት በተለይ የራሽያ እና የዩክሬን እንዲሁም የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ቀጣናችንን ሊያናውጡት የሚችሉበት ሁኔታ የለም ማለት አይቻልም። ለዚህ ደግሞ ቀጣናዊ መፍትሔ ማፈላለግ ያስፈልጋል። በእርግጥ ለቀጣናዊ ችግሮች ቀጣናዊ የመፍትሔ አፈላለግ መርህ አለ፤ ምክንያት በአንድ ሀገር ብቻ ቀጣናዊ ሰላምንና ደህንነትን ማስከበር ከባድ ስለሆነ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– እንደሚታወቀው ከሰሞኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለባህር በርና ስለ ቀይ ባህር ጉዳይ ገለጻ አድርገዋል። የተነሳው ርዕስ ወቅታዊ ነው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር አማረ፡– ወቅታዊ ነው ብሎ ለመፈረጅ ብዙ ነገር መጥቀስ ያስፈልጋል። አንድ ሀገር የባህር በር እንደሚያስፈልገው ይታወቃል። የባህር በር ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም ለደህንነትም ጭምር አስፈላጊ እንደመሆኑ እነዚህን ለማስጠበቅ የምንጠቀምበት አንዱ መሳሪያ ነው ማለት ይቻላል።
የባህር በር ማግኘት የሚባለው ነገር በሁለት መንገድ ሊታይ ይችላል። አንደኛው ሙሉ በሙሉ ከባህር ጋር የሚያገናኘው ወደብ በባለቤትነት ወይም የራስ የሆነ መሬት ማግኘት ነው። ሁለተኛው ደግሞ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የባህር በር ተጠቅሞ የአንድን ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ናቸው።
ከሁለቱም አንጻር ስለጉዳዩ መነጋገር ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው እኛ የራሳችን የሆነ ወደብ የለንም። እየተገለገልን ያለነው የሌሎችን ወደብ ተከራይተን ነው። ስለዚህ ጥያቄው ቀድሞም ቢሆን በውስጣችን ያለ ነው። በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ያለ ነው። የማይመለስ ከሆነም የሚቀጥል ነው።
የባህር በር የአንድን ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ሊያስጠብቁ ከሚችሉ መሳሪያዎች ውስጥ አንዱ እንደመሆኑ ርዕሰ ጉዳዩ መቼም ቢሆን ሊነሳ የሚችል ነው። ጉዳዩን መንግሥት በሚፈልገው ሰዓት ብቻ ስላነሳው አይደለም፤ እንደእነዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ዞሮ ዞሮ በሕዝብም የሚነሱ ናቸው። ስለዚህም የባህር በር ጥያቄ መጠየቅ ያለበት በዚህና በዚያኛው ጊዜ ይባላል ብዬ አላስብም። ጊዜም ይገደብለታል ብዬ አልልም። ጥያቄው በየትኛውም ጊዜ ሊነሳ የሚችል ሲሆን፣ ሊለያይ የሚችለው እንዴት ተደርጎ ነው ምላሽ ሊያገኝ የሚችለው የሚለው ነው።
የቀይ ባህርን ሁኔታ እግረ መንገድሽን ካነሳሽው አይቀር በቅርቡ አንድ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት አስተባባሪነት ተካሂዶ ነበር። ታዳሚዎቹ ከ200 በላይ የሚሆኑ የመንግሥት አማካሪዎች (ቲንክ ታንክ) ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ቀንድና ከመካከለኛው ምስራቅ ማለትም ከእስራኤልና ከአረብ ሀገራት የተውጣጡ ናቸው።
የኮንፈረንሱ ርዕስ ‹‹የቀይ ባህር የደህንነት ሁኔታ ቀጣናዊ ምክክርና ትብብር መልከዓ ፖለቲካዊ መጠላለፍ በበዛበት ዓለም ወቅት›› የሚል ነበር። ኮንፈረንሱን ስናዘጋጅ በመጀመሪያ ጽንሰ ሐሳብ ቀርጸን ነው። በቀይ ባህር አካባቢ ይካተታሉ ያልናቸውን በሙሉ አማክረንና ሃሳቡን ልከን ተሳታፊ እንዲሆኑ የተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡– በኮንፈረንሱ ምን ያህል ጥናታዊ ጽሑፎች ቀረቡ? የተዘጋጀበት ዋና ዓላማስ ምን ነበር?
ዶክተር አማረ፡– ወደ 20 ጥናቶች ሲሆኑ፣ ጥናቱን ያቀረቡት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በቀጣናው ካሉት ውስጥ ናቸው፤ ርዕሰ ጉዳዩ የቀይ ባህር የደህንነት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያጠነጠነ ነው። ወቅታዊ ሁኔታውን ካየን በኋላ ደግሞ ቀጣናዊ ትብብር የቀይ ባህርን ደህንነት ለማስጠበቅ ያስፈልጋል። ስለዚህ ኮንፈረንሱን ያዘጋጀነው ቀጣናዊ ትብብርንና ቀጣናዊ ምክክርን ለማጎልበት በማሰብ ነው።
ኮንፈረንሱን ስናዘጋጅ ሶስት ዓላማዎች ነበሩን። የመጀመሪያው ዓላማ በቀይ ባህር አካባቢ እስካሁን ያሉ ችግሮች ምንድን ናቸው? እስካሁን የነበሩት የደህንነት ስጋቶችስ የትኞቹ ናቸው? በአሁን ወቅት ደግሞ እየገዘፉ ያሉ የደህንነት ስጋቶች ምንድን ናቸው? ለቀጣዩ አምስትና አስር ዓመታትስ የደህንነት አደጋዎቹ ምን ሊሆኑ ይችላሉ? የሚል ነበር።
ሁለተኛው ዓላማ ደግሞ የቀይ ባህር የደህንነት ሁኔታን ለመከታተል ዲዛይን የሚደረጉ መድረኮች ወይም ፎረሞች ለምሳሌ አሁን እኛ የሌለንበት የቀይ ባህር ፎረም (Red sea forum) እንደሚባለው አሊያም ደግሞ የቀይ ባህር ጥምረት (Red sea Alliaince) ወይም ደግሞ የጂቡቲ የሥነ ምግባር ደንብ (Code of conduct) እንደሚባለው ዓይነት አደረጃጀቶች አሉ። ስለዚህ እነዚህና መሰል አደረጃጀቶች የአካባቢውን ደህንነት ለማስጠበቅ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው? ውጤታማ ካልሆኑ ደግሞ ለወደፊቱ እንዴት አድርገን እነዚህን ማዕቀፎች እንቅረጻቸው? የሚለው ነበር በሁለተኛ ዓላማነት የተነሳው።
ሶስተኛው ዓላማ ደግሞ የቀጣናው ሀገራት የራሳቸው የሚያመሳስል ወይም አንድ የሚያደርግ ነገር ያላቸው ናቸው። ለምሳሌ በእምነት፣ በባህል እንዲሁም በማንነትም ጭምር አንድ የሚያደርጉ ነገሮች አሉ። ስለዚህ አንድነታችንና የምንጋራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? የጋራ ተጠቃሚነታችንን ምን ያህል ሄደንበታል? የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርጉን ነገሮችስ ምን ምን ነበሩ? እንዴትስ እየሰራንበት ነው በሚል ኮንፈረንሱ አካሄደናል።
በኮንፈረንሱ ከተነሱ ነገሮች ውስጥ እንደ ሀገር እኛም እንዲነሳና ውይይት እንዲደረግበት ካደረግነው ውስጥ አንዱ አስቀድሜ እንደጠቀስኩት የነበሩ አደረጃጀቶች ምን ያህል ውጤታማ ነበሩ? የሚለው ጉዳይ ነው። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያንና እስራኤልን ያገለለ የቀይ ባህር ደህንነት ተለዋዋጭነት መድረክ (Red sea security dynamics forum) ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ ለወደፊቱ እነዚህን መሰል ማዕቀፎች አካታች የሆነ መስፈርት ወጥቶላቸው በዛ መሠረት ትብብሩ መጠናከር እንዳለበት በኮንፈረንሱ የተሰመረበት ነበር።
ለምሳሌ ከዛ ውስጥ ከደህንነት ስጋት ውስጥ ከተነሱ ነገሮች ውስጥ አንዱ አንቺ እንዳነሳሽው የወደብ ጥያቄ ነበር። በእርግጥም እኛ ጉዳዩ ላይ ውይይት እንዲደረግበት እንፈልጋለን። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ወደብ ማግኘት ያለባት እንዴት ነው? እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ያለችው በጣም በቅርበት ነው። እናም ይህን ያህል ሕዝብ የያዘ ሀገር፣ ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታው በጣም የጎላ ሀገር በምስራቅ አፍሪካ የባህር በር ተጠቃሚ መሆን ይገባዋል። እንዲህም ሲባል የባህር በር ልናገኝ የምንችልበት ምን አማራጮች አሉ? የሚለውን ማየቱ ጠቃሚ ነው የሚለው ጉዳይ ተነስቶም ውይይት የተደረገበት መድረክ ነበር ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– የታዳሚያኑ ግብረመልስ ምን ይመስል ነበር?
ዶክተር አማረ፡– እንዳጋጣሚ ሆኖ ጠርተናቸው በግል ችግር ምክንያት ያልመጡት ከኤርትራ እንዲሁም ከወቅታዊ ችግር ምክንያት ደግሞ ከሱዳን ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ተገኝተዋል ማለት ይቻላል። ከዛ ውጭ ግን የጠራናቸው ሁሉም መጥተዋል ማለት ይቻላል።
የቀይ ባህር የትብብር መድረክ ከመፈጠሩ በፊት የጂቡቲ የሥነ ምግባር ደንብ አለ። ይህ ተመሳሳይ ዓላማ ያለው ማዕቀፍ ነበር። ይህ ማዕቀፍ በምስራቅ አፍሪካ እና በቀይ ባህር አካባቢ አጠቃላይ ያሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚያውክ፣ ሽብርተኛነትንና የባህር ላይ ውንብድናን የሚከላከል ማዕከል ተደርጎ የተመሰረተው እኤአ 2009 ነው። እዛ ውስጥ ኢትዮጵያም አባል ነች።
የቀይ ባህር የደህንነት መድረክ እኤአ በሁለት ሺ አስራዎቹ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ ሆን ተብሎ አንዳንድ ሀገራት እንዳይካተቱ የተደነገገው ሊያስወጣቸው በሚችል መስፈርት ነው። ያልተካተቱትም ደግሞ ኢትዮጵያና እስራኤል ናቸው። መድረኩ ኢትዮጵያን ያላካተተው የባህር በር የሌላት በሚል ሲሆን፣ እስራኤል ደግሞ ማንነቷ ከተቀረው ጋር አይመሳሰልም በሚል ነው። ይሁንና እንዲህ ዓይነቱ መስፈርት መቀመጥ አልነበረበትም። ለወደፊቱ አካታች የሆነ መስፈርቱ ወጥቶ ያልተካተቱ ሀገሮች መካተት አለባቸው የሚል አተያይ አለን። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያና እስራኤል የሌሉበት ዓይነት የትብብር ማዕቀፍ ሊሳካለት የሚችል አይሆንም።
አዲስ አበባ በተካሔደው ኮንፈረንስ ላይ እንደ ትልቅ ምሳሌና እንደ ምርጥ ተሞክሮ የተነሳው ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ወይም በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን በመከላከል ያደረገችው መስዋዕትነት ነው። ስለዚህ ዓላማው ይህ እስከሆነ ድረስ ኢትዮጵያን ማግለል ለምን አስፈለገ? እስራኤልንስ ማግለል ለምን አስፈለገ? የሚል ሐሳብም ተነስቷል። በተወሰነ መልኩ እንኳ ቢሆን ወገንተኝነት የሚንጸባረቅባቸው መስፈርቶች መቀመጥ የለባቸውም።
ለወደፊቱ እንደዛ ዓይነት መድረኮች ሲዘጋጁ ወገንተኝነት ከተጫናቸው ውጤታማ አይሆኑም። ስለዚህ ውጤታማ እንዲሆኑ አካታች የሆነ መስፈርት መካተት መቻል አለበት። እንደሚታወቀው ደግሞ የቲንክ ታንክ ሚና ለፖሊሲ አውጪዎች ነድፎ ማቅረብ ነው። እኛም የፈለግነው በዛ መልክ ቀርቦ እንዲሰማ ነው። ከዛ አኳያ ስንመለከተው ኮንፈረንሱ ውጤታማ ነበር።
ለወደፈቱ የቀይ ባህር ፎረምም ሆኑ ሌሎቹ ተከልሰው አካታች የሚሆንበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት። የጋራ ደህንነት ደግሞ በተወሰኑ ሀገራት ብቻ የሚሸፈን አይደለም። ከጽንሰ ሐሳቡ (Theory) ከተነሳን የብሔራዊ ደህንነት ውስብስ ጽንሰ ሐሳብ (National Security Complex Theory) የሚባል አለ፤ ጽንሰ ሐሳቡ የሚለው አንድ ሀገር ወይ የተወሰኑ ሀገራት ብቻቸውን ደህንነታቸውን መሸፈን አይችሉም። ስለዚህ ትብብር ያስፈልጋል። ለመተባበር ደግሞ የግድ የባህር በር መኖሩ እንደ አንድ መለኪያ ሊሆን አይገባውም።
በርግጥ ኢትዮጵያ ደግሞ ለቀይ ባህር ያን ያህል ሩቅ ናት ወይ የሚል ነገርም በኮንፈረንሱ ሲነሳ ነበር። ምንም ሆነ ምን እኛ በዛ አካባቢ ያገባናል። ለቀይ ባህር ቅርብ መሆናችን ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ደህንነት የከፈልነው መስዋዕትነት ጭምር ስላለ የባህር በር ያስፈልገናል።
ያስፈልገናል ስንል ከማን ነው የምንወስደው? እያልን አይደለም። እንዴት ነው ማግኘት የምንችለው? በሚለው ላይ ነው እየተወያየን ያለነው። ለወደፊቱም በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ብቻም ሳይሆን በሀገራችንም እንዴት ነው ልንሔድበት የምንችለው በሚለው ላይ መመካከር ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን፡– ይህ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት የተጀመረው መድረክ ቀጣይነቱ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር አማረ፡– ይህ መድረክ የመጀመሪያው የቀይ ባህር የትብብር መድረክ ነው። ቀጣዩ ኢትዮጵያ ውስጥ አሊያም የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ውስጥ አሊያም እስራኤል ወይም ደግሞ ሳዑዲ ውስጥ ሊካሔድ ይችላል። ዋናው ነገር ግን ጀማሪዎቹ እኛ ነን። ተነሳሽነቱን ወስደናል፤ መድረኩ በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ ፖሊሲ አውጪዎች ላይ ጫና ማድረግ አለብን። ወደጋራ ተጠቃሚነትና ወደጋራ ደህንነት መምጣት ይኖርብናል። ያንን ለማድረግ ደግሞ እንደእነዚህ አይነት ፎረሞች ያስፈልጋሉ የሚል ስምምነት ላይ ተደርሷል። ስለዚህ ምናልባት ከአራትና አምስት ወር በኋላ እንዳልኩሽ በአንዱ ሀገር ላይ ይዘጋጃል ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ ማበርከት የሚያስችላት ብዙ ነገር እንዳለ ሁሉ ባለመግባቷ ደግሞ የምታጣው ምንድን ነው?
ዶክተር አማረ፡– ባለመግባታችን የምናጣው ነገር ይታወቃል። ገና ለገና ስለ ቀይ ባህር ስላነሳን ብቻ የተፈጠረው ነገር የሚታወቅ ነው። ስለዚህ የፎረሙ አባል ሀገራት በሚነጋገሩበት ወቅት በምን ጉዳይ ላይ እንደሚነጋገሩ ኢትዮጵያ ማወቅ አትችልም። ሙሉ በሙሉ አባል እንኳ ባንሆንና ውሳኔ መስጠት ባንችልም ምን እየተካሄደ ስለመሆኑ አናውቅም።
በአሁን ወቅት ደግሞ ከኮንፈረንሱም አስቀድሞ በዚህ ዓመት ከባህር በር ጋር ተያይዞ ልናጠናው ያሰብነው ጉዳይ አለ። በመሰረቱ የወደብ አልባነት ሃሳብ በብዙዎቻችን ውስጥ ሰርጿል።
ሰው ወደብ የማግኘትን ጉዳይ ከመሬት ጋር ብቻ ያገናኘዋል። ነገር ግን በጣም ብዙ መንገዶች አሉ። እነዛን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር እንዴት መጠቀም አለብን በሚል ለማጥናት ያስበነው ርዕሰ ጉዳይ አለ።
አዲስ ዘመን፡– በቀይ ባህር ቀጣና የኃያላን ሀገራት ፉክክር ኢትዮጵያ ላይ የሚያሳርፈው ጫና እንዴት ይገለጻል? መፍትሔውስ ምንድን ነው ይላሉ?
ዶክተር አማረ፡– በርግጥ ለብዙዎች በቀጣናው አካባቢ ጦሩ ስላለ ብቻ ፍርቻ አለ። በርግጥ የሚያስፈራ መሠረት አለው። በአግባቡ ከገመገምነውና ትኩረት ከሰጠነው በአካባቢው መሰባሰባቸው የራሱ የሆኑ ተጽዕኖ አለው። ዝም ብሎ ደግሞ የሚፈራም አካል አለ። ነገር ግን በአግባቡ መተንተን አለበት። አንዱና ዋንኛው ግን አስቀድሜም ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ወታደራዊ የጦር ማዘዣዎች በአካባቢው መኖራቸው በቀጣናው ያሉ ሀገራት በራሳቸው እንዳይወስኑ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ አለው።
በተለይ ከነበራቸው የቅኝ ተገዥነት የተነሳ ፍራቻ ያለበት አካባቢ ነው። ምናልባት ይህ ጉዳይ እኛን ላይመለከት ይችል ይሆን እንደሆን አላውቅም። ዞሮ ዞሮ ግን እኛንም ስጋቱ ይደርሰናል። አንደኛውና ዋነኛው ሀገራቱ በነጻነት ገለልተኛ ሆነው በሀገራቸው የውስጥ ጉዳይና ቀጣናቸው ላይ እንዳይወስኑ እንደ አንድ መሰናክል ይሆን ይሆናል ወይ የሚያስብል ነገር አለ። በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባቱም ነገር ሊኖር ይችላል። ስለዚህ ሀገራቱ ነጻ ሆነው ከመወሰን አንጻር ጫና ይኖረዋል።
ሌላው የውክልና ጦርነት ነው። በአንድ ወቅት አሜሪካና ራሽያ ኢትዮጵያንና ሱማሊያን እንዳዋጉት ሁሉ አሁንም ቢሆን ኃያላን የሚባሉ ሀገራት ብቻ ሳይሆኑ አስቀድሜ የጠቀስኳቸው አዳዲስ የመጡ የቀጣናው ኃያላን በአካባቢያቸው ያለውን ፉክክር አምጥተው ሊያራግፉብን ይችላሉ፡። ስለዚህ በአካባቢው መሰባሰባቸው ዞሮ ዞሮ ለእኛ ስጋት ነው።
አዲስ ዘመን፡– መፍትሔውስ ምን መሆን አለበት ይላሉ?
ዶክተር አማረ፡– መፍትሔው ያው ቀጣናዊ ትብብር ነው። ኮንፈረንስ የማዘጋጀታችንም ምስጢር እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ለመነጋገርም እንዲያመች ጭምር ነው። እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን በእኩልነት እንዴት ማስተዳደር እንችላለን? የሚለውን ለማጠናከር ቀጣናዊ ትብብሮችን በአግባቡ ማጠናከር አስፈላጊ ነው። ከዛ በመነሳት ደግሞ የትብብር ማዕቀፎችን ዲዛይን ማድረግ ያስፈልጋል። ተጠቃሚነትም መኖር አለበት። ጉዳዩ ገና ሲነሳ ‹‹ውሃችንን ልትወስዱ ነው›› ከመባባል ባለፈ የጋራ ተጠቃሚነታችንን ጉዳይ እንዴት አድርገን ነው ማጠናከር ያለብን በሚለው ላይ መወያየት መልካም ነው። የጋራ ተጠቃሚነት ከሌለ ግጭቶች ይኖራሉ። ይህ ደግሞ እነርሱን ተጠቃሚ ያደርጋል። በውክልና ይገቡና መንግሥት የመመስረት ዓይነት ነገር ይኖራል። ስለሆነም ይህንን ጉዳይ ሁሉ ለመቆጣጣር ቀጣናዊ ትብብር ወሳኝ ነው።
ምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ቀጣናዊ ትብብር እንደሌላው አካባቢ ብዙ ጠንካራ የሚባል አይደለም። ስለዚህም ማጠናከር ያስፈልጋል። ከማጠናከር አኳያ ሲታይ ደግሞ ከዚህ በፊት ጠንካራ ሚና ስትጫወት የነበረች ኢትዮጵያ ናት። እንዲህ ስል የሌሎቹን ሚና እውቅና ለመንፈግ ፈልጌ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡– የባህር በር ጉዳይ ቢጠፋ ቢጠፋ ሰጥቶ በመቀበል መርህ ድረስ ሊሄድ እንደሚችል መገለጹ ይታወቃል። ይህ ምን ያህል አዋጭ ነው ይላሉ?
ዶክተር አማረ፡– ይህ አባባል እንደሚመስለኝ ምናልባት የተገለጸበትን መንገድ ሰው በአግባቡ ካልተረዳው በስተቀር ጥሩ ነው። እኛ የተቸከልነው መሬት በሚለው ላይ ነው። እኛ ብቻ አይደለንም፤ ሌሎቹም ማለትም የባህር በር ሊያጋሩን የሚችሉ ሀገራት የተቸከሉት መሬት የሚለው ነገር ላይ ነው። እኛ ልንሰራቸው ካቀድናቸው የምርምር ሥራዎች ውስጥ አንዱ የባህር በር እንዴት ነው የምናገኝበት አማራጭ ማስፋት የምንችለው? የሚል ነው። ዘዴዎቹና ተሞክሮቹስ ምንድን ናቸው? የሚለውን ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳቡን ያነሱበት መንገድ ግን ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ።
ከብዙ መንገዶች አንዱ በኮሪዶር መጠቀም የሚለውን ማንሳት ይቻላል። ለኮሪዶር ደግሞ መሬት ለመስጠት ምንም ችግር የለውም። እሱ ማለት ደግሞ ዓለም አቀፍ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን እንደመዘርጋት ማለት ነው፡። ኮሪዶር የሚሰራባቸው ሀገሮች አሉ። ለምሳሌ አዛርባጃን የባህር በር የላትም። ነገር ግን በሌላ ሀገር ላይ ኮሪዶር በመገንባት የባህር በር ተጠቃሚ የምትሆንበትን እድል ፈጥራለች። ከዚህ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስተሩ እንዳሉት ሌላ ነገር ሰጥቶ መቀበል ይቻላል። ይህ ግን በተለያዩ ጥናቶች የሚመለስ ነው ብዬ አስባለሁ። በጣም ብዙ አማራጮች ስላሉ መንገዱ ዝግ አይደለም። እንዲያው አንዱ ላይ ብቻ ከምናተኩር የተለያየ ዓይነት አማራጭ ቢኖረን እኛንም ሀገራቱንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። በጣም የሚያስገርመው ነገር ሌሎች ሀገር ወደአካባቢው ሲመጡ መሬቱም ቢሆን ሲሰጣቸው ይታያል። ለምሳሌ አሜሪካ በብዙ ሺ ማይልስ ርቀት መጥታ ጂቡቲ ላይ መሬት አላት። ጃፓንና ቻይናም እንዲሁ በብዙ ሺ የሚቆጠር ማይልስ አቋርጠው መጥተው ወይ ጂቡቲ ላይ ወይም ደግሞ ኤርትራ ላይ መሬት አላቸው።
ታዲያ የአፍሪካ ሲሆን ልዩነቱ ምንድን ነው? ቢሆን የተባለው እንኳ በሊዝ፣ በኮሪዶርና መሰል ነገሮች ነው። ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን ቀጣናዊ የሆነ ትብብር ሲኖር ነው። ለምሳሌ መሬቱ ለኢትዮጵያ በተለያየ መንገድ ቢሰጥ የሚለው ሃሳብ አልተገዛም። ለአሜሪካኖቹ አሊያም ለሌሎቹ ሀገራት እንደሚሰጠው ሁሉ ለኢትዮጵያ እንስጥ የሚለው ሃሳብ በሌላውም ዘንድ አልተገዛም። እኛም እስካሁን አልገዛነውም። ይህ በጥናት መደገፍ አለበት።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ ባለችበት ቀጣና ተጽዕኖ መፍጠር እንዳትችል አድርጓታል የሚሉ አሉ። እርስዎ ይህን እንዴት ያዩታል?
ዶክተር አማረ፡– በቀጣናው ለረጅም ዘመን ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ሀገራት ቀዳሚዋ ኢትዮጵያ ነበረች፤ ነችም። በእርግጥ እንዳልሽው በአሁኑ ወቅቱ በቀጣናው ድሮ እንጫወት የነበረን ሚና እየተጫወትን አይደለንም የሚሉ አካላት አሉ። ለምሳሌ ድሮ ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበርነው ምን ምን በማድረግ ነው? ብለው መቁጠር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በርግጥ በተወሰነ መልኩም ቢሆን መቀዛቀዞች ይኖራሉ። ምክንያቱም ትኩረታችን ወደ ውስጥ ችግሮቻችን ላይ ነው፡። እሱንም ለመቅረፍ እየተሰራ ነው። እንዲያም ሆኖ ወደቀደመው ተጽዕኖ ፈጣሪነታችን የማንመለስበት ምክንያት የለም።
ከወደቡ ጋር ተያይዞ ተጽዕኖ ፈጣሪነታችን ብዙ ግንኙነት አለው ለማለት ይከብደኛል። እርግጥ ነው ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አንጻር እና እድገቱን ከማቀላጠፍ አኳያ እንዲሁም መሰል ጉዳዮች ላይ የራሱ የሆነ ሚና ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። ቢሆንም ከተጽዕኖ ፈጣሪነታችን የዚያን ያህል ቀንሶናል ብዬ ለመናገር አልችልም። እንዲያም ሆኖ የባህር በር አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም።
ወደብ አልባ መሆን ከባድ ነው። ብሔራዊ ምስጢርን መጠበቅ አይቻልም። የምናስገባቸው ነገሮች ላይ ቁጥጥር ይደረጋል። ከዚህም በተጨማሪ ከምንችለው በላይ ቀረጥ በተፈለገው ጊዜ ሊጨመርብን ይችላል። በተጨማሪም የምንፈለገውን ነገር በፈለግነው ጊዜ ላይገባልን ይችላል። መዘግየቶች ይኖራሉ። መዘግየት ሲኖር ደግሞ የስቶር ኪራይ መክፈል ይመጣል። እነዚህ ነገሮች ተፈትተው ወደ ተጽዕኖ ፈጣሪነታችን ማማ ላይ የበለጠ እንቀመጣለን ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር አማረ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም