ብረትን ማስተካከል እንደጋለ !

 መንግሥት ሰፊ መሠረት ያለው፣ ፈጣን፣ ቀጣይነትና ፍትሃዊነቱ የተረጋገጠ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ልማትን አፋጥኖ ድህነትን በማስወገድ ብልጽግናን የማረጋገጥ ዓላማ ይዞ እየሠራ ይገኛል። ይህን ለማስፈጸም ደግሞ ትምህርት ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ለዚህም ትምህርትን በየደረጃው ማስፋፋትና ጥራቱን ማረጋገጥ ግድ ይላል።

የትምህርት ጥራቱን በተመለከተ በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ መመልከት ከሚያስፈልግበት ደረጃ መድረሱን ያመላከተው በ2014ዓ.ም የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ፈተና ከኩረጃ ነጻ ለማድረግ በዩኒቨርሲቲዎች በልዩ ሁኔታ መካሄድ ሲጀመር ነው።

እንደሚታወቀው የ12ተኛ ክፍል ፈተና ውጤት ተፈታኞች አጠቃላይ ትምህርትን የሚያጠናቅቁበት፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ የሚሆነውን ውጤት ለማግኘት ፈተና የሚቀመጡበት ነው።

ከዚህ የተነሳም ፈተናውን ባልተገባ መልኩ ለማለፍ የተለያዩ ጥረቶች ይደረጋሉ፣ ፈተናውን ከመስረቅ ጀምሮ በኩረጃ ውጤታማ ለመሆን ብዙ ያልተገቡ ሥራዎች ይሰራሉ። በዚህም በተለያዩ ወቅቶች ፈተናው በራሱ ብዙ ፈተናዎችን ለማለፍ የተገደደበት ሁኔታ የቅርብ ትዝታ ነው። ፈተናዎችን ከመሰረዝ ጀምሮ የፈተና ቀናትን እስከ መለወጥ የደረሱ ችግሮች ተፈጥረዋል።

ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ የአፈታተን ሁኔታው ለኩረጃ እንዳይመች በማድረግ እየተደረገ ያለው ተግባራዊ ሥራ ተፈታኞች የራሳቸውን ውጤት የሚያገኙበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። በዚህም እየተመዘገበ ያለው ውጤት የቱን ያህል የትምህርት ሥርዓቱ ስብራት ውስጥ እንዳለ አመላካች ሆኗል።

ለምሳሌ ከ2014 ዓ.ም. ለፈተና ከተቀመጡ ተማሪዎች መካከል ሃምሳ በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚያመጡት ተማሪዎች 3.3 በመቶ ብቻ ነበሩ። ይህ አሃዝ በ2015 ዓ.ም. 3.2 በመቶ ወርዷል። ይህን ውጤት በመመልከት የትምህርት ሥርዓቱ ስብራት ምን ያህል የከፋ ስለመሆኑ መገመት አይከብድም።

ከዚህ በላይ የሚያሳዝነው ጉዳይ፣ በኩረጃ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ያላቸው ተፈታኞች ትምህርት ሚኒስቴር ምንም ያህል የጠበቀ የፈተና አሰጣጥ አሠራር ቢከተል፣ እነሱም የፈተና አስተዳደሩን በግልም ሆነ በቡድን ለመፈተን የማይቦዝኑ መሆናቸው ነው።

በ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን 20‚170 ተፈታኞች እንዲሁም በ2015 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን 859 ተፈታኞች የፈተና አስተዳደር መመሪያ ድንጋጌዎች ጥሰት ፈጽመው መገኘታቸውን ትምህርት ሚኒስቴር መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ባዘጋጀው መግለጫ አመልክቷል።

በ2015 ዓ.ም. የመመሪያና ድንጋጌዎች ጥሰት ከፈጸሙት ተፈታኞች መካከል 376 ተፈታኞች በቡድን 483 ተፈታኞች በግል ጥፋት ፈጽመዋል። በሁሉም ጥፋተኞች ላይ እንደተመዘገበው የጥፋት አይነት ከአንድ የትምህርት አይነት እስከ ሙሉ በሙሉ መሰረዝ ድረስ የሚደርስ ቅጣት ተጥሎባቸዋል።

የ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ተፈታኞች የመመሪያና ድንጋጌዎች ጥሰት ከ2015 ተፈታኞች ጋር ሲነጻጸር የ2015ቱ በእጅጉ ዝቅ ያለ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም በቀጣይ አመሉ ያለባቸው ተፈታኞች ስልታቸውን ቀይረው፣ በግልም ይሁን በቡድን ተዘጋጅተው ብዛታቸውን ጨምረው የፈተና አስተዳደሩን ለመፈተን ሊመጡ ይችላሉና በተገኘው መሻሻል መዘናጋት አይገባም፤ ይበልጥ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል።

በሁለቱ ዓመት የተገኘው የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት የትምህርት ሥርዓቱን ስብራት ለሁሉም ህብረተሰብ ፍንትው አድርጎ አሳይቷል። በዚህ ልክ ስብራቱ ይከፋል ተብሎ ባይታሰብም የትምህርት ሥርዓቱ ሊፈተሽና ሊስተካከል እንደሚገባው የወተወቱ አካላትም ጥናቶችም ነበሩ።

ለአብነት ትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው በአምስተኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሃ-ግብር (2008-2012 ዓ.ም.) ሰነድ ላይ፣ “የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት የትምህርት ውጤቶች የዝቅተኛ ክፍል ደረጃ የንባብ ዳሰሳ (EGRA)” በሚል በቀረበው ገጽ 26 ላይ የሚከተለው ተካቷል።

‹‹በ2002 ዓ.ም. በሁለተኛና ሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ የዝቅተኛ ክፍል ደረጃ የንባብ ዳሰሳ ጥናት ተካሂዶ ነበር። ጥናቱ በመጀመሪያ ደረጃ አንደኛ ሳይክል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በቀጣይ ክፍሎች በአግባቡ ለመማር የሚያስችሉዋቸውን መሠረታዊ ክህሎቶች ያላዳበሩ መሆናቸውን አሳይቷል።

ለምሣሌ፣ ሁለተኛ ክፍል ከሚማሩት ተማሪዎች 34 በመቶ ለደረጃው ከተዘጋጀው ምንባብ ውስጥ አንድም ቃል ማንበብ ሳይችሉ ቀርተዋል፤ ከተማሪዎቹ 48 በመቶው ከተዘጋጀው አንብቦ የመረዳት ፈተና አንዱንም መመለስ አልቻሉም፣ በተጨማሪ ከተማሪዎቹ መካከል በደቂቃ 60 ቃላትን አቀላጥፈው ማንበብ (ተማሪዎች በደቂቃ 60 ቃላት እንዲያነቡ ይጠበቅ ነበር) የቻሉት 5 በመቶ ብቻ ናቸው። ››

ይህ የሚያሳየው የትምህርት ስብራቱ በትምህርት ባለሙያዎቹ ቀደም ሲልም የሚታወቅ መሆኑን፣ በዚያው ልክ ግን በከፍተኛ ደረጃ ባሉ የትምህርት አመራሮቹ ተግባራዊ የመፍትሔ ርምጃ አለመወሰዱን ነው። አሁን በ12ተኛ ክፍል ተፈታኞች ላይ ትምህርት ሚኒስቴር ከበፊቱ የተለየ የፈተና አስተዳደር መመሪያ ድንጋጌዎች በማውጣት ወደ ተግባር ሲገባ ቀደም ሲል የነበሩ የትምህርት ጥራት ችግሮች በአስደንጋጭ ደረጃ ታይተዋል።

አሁንም ቢሆን የነበረው ችግር ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር የተማሪዎች በፈተና ዝቅተኛ ውጤት የማምጣት ሁኔታ በቀጣይ ዓመታትም ሊቀጥል አለመቻሉ ማስተማመኛ ነገር የለም፤ የሚሻለው ግን ተስፋ ባለመቁረጥ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች የትምህርት ጥራትን የሚያስጠብቁ ተግባራትን ተግቶ መሥራት ነው።

በ2015 ዓ.ም. ተግባራዊ የሆነው በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ለመጀመሪያ ዲግሪ እጩ ተመራቂዎች የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና መሰጠቱ እንዲሁም በ2016 ዓ.ም. የተጀመረው ለሁሉም ሁለተኛ ዲግሪ አዲስ ተመዝጋቢዎች ትምህርት ሚኒስቴር በማዕከል በሚያወጣው የመግቢያ ፈተና ተመዝነው ሲያልፉ ብቻ ትምህርት የሚጀምሩ መሆኑን ስንመለከት ይበል የሚያስብል ተግባር መሆኑን እናስተውላለን።

በ12ተኛ ክፍል የተጀመረው የምዘና ሥርዓት ወደታች ስድስተኛ እና ስምንተኛ ክፍልም ችግሮችን ወረድ ብሎ በማየትና በማጥናት ጠበቅ ያለ የምዘና ሥርዓትን በመዘርጋት ችግሮቹን መፍታት ይገባል።

ብረትን መቀጥቀጥ(ማስተካከል) እንደጋለ ነውና በሁለተኛ ደረጃ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተጀመረው የትምህርት ሥርዓት ማስተካከያ ወደ አንደኛ ደረጃም በተያዘው ግለት መዝለቅ አለበት። በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያለውን የትምህርት ሂደት ስንቃኝ ተማሪዎችን ወደ ቀጣዩ ክፍል ማሳለፍ እንጂ ብቁ የማድረጉ አሠራር ትኩረት ተነፍጎት ይስተዋላል።

የትምህርት አመራሮችና መምህራን ‹‹ከመንግሥት የተሰጠን መመሪያ ተማሪዎችን አብቅቶ ማሳለፍ እንጂ መጣል እንደማይቻል ነው›› ይላሉ። ይህ አሠራር ዋነኛ ዓላማው በትምህርታቸው ደከም የሚሉ ተማሪዎችን ከመጣል ይልቅ የክለሳ ትምህርት በመስጠት ውጤታቸውን እንዲያሻሽሉ አድርጎ ወደ ቀጣዩ ክፍል ማሸጋገር ነው።

አሠራሩ ከቃል በዘለለ ተግባራዊ ቢደረግ ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ከለጋነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ማፍራት የሚያስችል ቢሆንም አስተዳዳሪዎቹና መምህራኑ ግን ስንት ተማሪ አሳልፌ ከተጠያቂነት ዳንኩኝ እንጂ፣ ስንት ተማሪ አበቃሁ የሚል አሠራራቸው የደከመ መሆኑ ይነገራል። በመሆኑም የዚህን አሠራር አተገባበር በጥናት በመፈተሽ የመፍትሔ ሥርዓት ማበጀት ይገባል።

በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የትምህርት ንቅናቄ በማካሄድ በተለያዩ ድርጅቶችና በግለሰብ ባለሀብቶች በከፍተኛ ቁርጠኝነትና የእኔነት መንፈስ ብዛት ያላቸው ትምህርት ቤቶችን የማደስና የትምህርት ግብዓቶችን የማሟላት ተግባር ተከናውኗል። ይህ ሥራ በትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻል ሀገራዊ ንቅናቄ ተፈጥሮበት እየተሠራበትም ይገኛል።

ተግባሩ ቀጣይነት ቢኖረው፤ ትምህርት ሚኒስቴርም የትምህርት ሥርዓቱን ከትምህርት ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ጥናት በማድረግ ችግር ፈቺ በሆነ ሁኔታ ሥርዓት ቢያበጅለት፤ የትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎችና መምህራን ሙያቸውን በአግባቡ ከመወጣት በተጨማሪ የመማር ማስተማሩ ሂደት በተሳለጠ ሁኔታ እንዲከናወን ከተማሪዎች፣ ከወላጆች እንዲሁም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር ያስፈልጋል።

ወላጆችና አሳዳጊዎች ልጆቻቸው ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ምክርና ቁጥጥር በማድረግ እገዛ ቢያደርጉላቸው፤ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ ለመማር መምህራንና ወላጆች የሚሰጧቸውን ምክርና አስተያየት በአግባቡ በማዳመጥ ቢተገብሩ፤ በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ለትምህርት ጥራት የበኩሉን አስተዋጽኦ ቢያደርግ፤ በየክፍል ደረጃው የትምህርት ጥራት እየተጠበቀ ይሄዳል።

ይህ ተግባር በተጠናከረ መልኩ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ የሚተገበር ከሆነ አሁን የምናየው አስደንጋጭ የአሥራ ሁለተኛ ክፍል የፈተና ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ አስደንጋጭ ወደማይሆንበት ደረጃ ይቀየራል፤ ወደፊት የተሻለ ደረጃ ላይ ይደርሳል። የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሶ ለማየት ግን ብረትን መቀጥቀጥ(ማስተካከል) እንደጋለ ስለሆነ በተያዘው የተነሳሽነት ግለት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ትምህርት የሁሉ ነገር መክፈቻ ቁልፍ፣ የሀገር እድገት ወሳኝ መሳሪያ መሆኑን በመረዳት ለትምህርት ሥርዓቱ ጥራት መጠበቅ የሚጠበቅበትን ተግባር ለማከናወን ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል።

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

ስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You