የጥበብ ጥሪውን በጊዜ የተረዳው እጀ ወርቅ

ጥቅምት 7 ቀን 1960 ዓ.ም በአዲስ አበባ አብነት በኪራይ ቤት ውስጥ መኖሪያቸውን ላደረጉት የሁለት ወንድ ልጆች እናትና አባት ቤተሰቦች ተጨማሪ ወንድ ልጅ በማግኘታቸው መንደሩን ሳይቀር እልል ያስባለ ነው። ያኔ ሁሉም ቢደሰትም ኢትዮጵያ ብዙም በማትታወቅበት የክላሲካል ፒያኖ በአንዴ ብዙ ርምጃዎችን ወደፊት የሚያራምዳት እጀ ወርቅ ፒያኒስት እንደሚሆን የተነበየ ግን አልነበረም። በሀገራችን ክላሲካል ሙዚቃ ዓለም በደረሰበት ልክ አድማጭ ስላላገኘ ከእኛ ይልቅ የምዕራባውያኑ ኮከብ የሆነው ክላሲካል ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ።

በተወለደበት አብነት ብዙ አልቆየም፤ ቤተሰቦቹ መኖሪያቸውን ወደ የካ ሚካኤል ስለቀየሩ አብዛኛው የልጅነት ትዝታው ከየካ ሚካኤል ሰፈርና በኋላ መኖሪያቸው ከሆነው ኮተቤ ጋር ይያያዛል። የልጅነት አስተዳደጉ በህብረትና በኪነት የታጀበ ነበር። ከሰፈራቸው ሰፋ ያለ ቤት ተመርጦ መጋረጃ ጋርደው ትያትር ያሳዩ ነበር። በዚህ እንቅስቃሴ ላይ እያሉ ኪነት ተጀመረ። በአካባቢያቸው የነበረውን የኪነት እንቅስቃሴ ይበልጥ ዳበረ። ያኔ ታዲያ በአካባቢያቸው በነበረው በከፍተኛ 16 ኪነት በመታቀፍ በህብረ ዝማሬውም ሆነ ክራር በመጫወት ያገለግል ጀመር። በዚህ ሒደት ላይ እያለ እውቁ የግጥምና ዜማ ደራሲ ሙሉ ገበየሁ በኪነታቸው ይገኛል። የኪነቱን እንቅስቃሴ የታዘበው ባለሙያው ታዳጊ ግርማን አንተ ያሬድ ገብተህ ሙዚቃን ብትማር ጥሩ ነው የሚል ጥቆማ ሰጠው።

ከልጅነቱ ጀምሮ መማር የፈለገው ሙዚቃንና ሙዚቃን ብቻ ነበር። ለዚህም ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ ወደ ያሬድ ተመላልሷል። ቤተሰቦቹ ብዙም ባይጫኑቱም የተሻለ ሥራ ያስገኛል ብለው የሚያስቡትን ትምህርት ቢማር ምርጫቸው ነበር። ለዚህም አባቱ ሃሳቡን ሊያስቀይረው ይችላል ብለው ላሰቡት አጎቱ፣ አቶ ሞገስ ደስታ እንዲያናግረው አድርገው ነበር። ሆኖም አጎቱ በተቃራኒው ምክራቸው “በፍጹም እንዳታስቆመው ፍላጎቱ የት እንደሚደርስ አታውቅምና ተወው በመንገዱ ይሂድ” ሲሉ አባትየውን መከሩ።

ከበርካታ ዓመታት መመላለስ በኋላ ሙዚቃን ለመማር አስፈላጊውን የትምህርት ደረጃ በማሟላቱ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገባ። የሙዚቃ ትምህርት ቤቱ እንደተቀበለው ለተወሰነ ጊዜ ለሁሉም ተማሪዎች በጋራ የሚሰጠውን ኦረንቴሽን ጀመረ። ያኔ ታዲያ የመተዋወቂያ ትምህርቱ የሚሰጠው በፒያኖ ነበርና በፒያኖ ፍቅር ለመውደቅ አፍታም አልወሰደበትም። የስድስት ሳምንት ኮርሱ ሳይጠናቀቅ “እኔ እዚህ ትምህርት ቤት አልፌ ከገባሁ የምማረው ፒያኖ ነው፤ ያለዛ አልማርም፣ ብሎ ወሰነ።

በያሬድ ፒያኖ ፈላጊው ብዙ ነው። ትምህርት ቤቱ በዓመት ቢበዛ አራት ወይ አምስት ተማሪዎችን ቢቀበል ነው። ለዚህም ይመስላል ፒያኖን ለመማር በርካታ መስፈርቶች የተቀመጡለት። ካሉት በርካታ መስፈርቶች መሃል በኦሬንቴሽን ኮርስ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ፣ ቁመና እና ጣት ዋናዎቹ ናቸው። ግርማ በኦረንቴሽን ኮርሱ አጥጋቢ ነጥብ ስላመጣና አስፈላጊው ተክለ ቁመና ስላለው እንደልቡ መሻት ፒያኖን ለመማር ታደለ። ክራርንም የፒያኖውን ያህል ባይገፋበትም በባህል መሣሪያ ዘርፍ ተምሯታል።

ግርማ ያሬድን በተቀላቀለበት ዓመት ፒያኖን በዋናነት ለመማር የተመረጡት አራት ልጆች ፒያኖን በሜጀርነት መማር ጀመሩ። የሚለማመዱበት ፒያኖ የሚመደብላቸው ከተማሪዎች ጋር በጋራ በመሆኑ ግርማ በቂ የመለማመጃ ጊዜ ለማግኘት በማሰብ ማልዶ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ጊቢ በመገኘት የመጀመሪያው የትምህርት ክፍለ ጊዜ እስኪጀመር በቂ ልምምድ ያደርጋል።

የትምህርት ክፍለጊዜ ሳይጀመር ማልዶ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ጊቢ መገኘቱ፤ ከፒያኖው ጋር የተሻለ ጊዜ እንዲያጠፋ አግዞታል። የትምህርት ክፍለ ጊዜው ሲያልቅና ተማሪዎች ወደየማደሪያቸው ሲሄዱ፤ እሱ እዛው ፒያኖውን እያናገረ ይቆያል። አንድ ቀን ግን በተለየ ሁኔታ ፒያኖውን እየተለማመደ አድሯል። የያኔውን ታታሪነቱን የሚያውቁት ግርማ የሚገባው ቦታ ላይ የደረሰው በሥራው መሆኑን ይመሰክራሉ። የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃልና ለመመረቅ ስድስት ወር እየቀረው በስኮላር ትምህርቱን ለመቀጠል ወደ ቡልጋሪያ እንደሚያቀና ተነገረው። ሆኖም ለመጓዝ ሂደቱ ከታሰበው በላይ ጊዜ ስለወሰደ ተመርቆ ቀጣዩን አንድ ዓመት ያሬድ አስተምሮ ወደ ቡልጋሪያ አቀና።

በኢትዮጵያ ቆይታው ከተማሪዎች መሃል ልቆ የሚታየው፤ ከተማሪነት አልፎ የፒያኖ መምህር የሆነው ግርማ ቡልጋሪያ ካሉት ተማሪዎች አንጻር ብዙ እንደሚቀረው ለመረዳት ጊዜ አልፈጀበትም። ሌሎች ተማሪዎችን ሲያይ “ጨርሰውት የለ፣ ምን ሊያደርጉ ዩኒቨርሲቲ ይመጣሉ” ብሎ ግራ ተጋብቶም ነበር። በሕይወቱ የራሱ ፒያኖ ኖሮት ሳያውቅ በፒያኖ ማስትሬቱን ሊማር ቡልጋሪያ ቢደርስም፤ እዛ ከሚገኙት ተማሪዎች ጋር ሰፊ ልዩነት እንዳለው ለመረዳት ጊዜ አልፈጀበትም። ሆኖም እነሱ የመጡት ከሌላ ሀገርና ሁኔታ ስለሆነ እራሱን ብቻ ማየት እንደሚገባው ለራሱ ነግሮ ጉዞውን ጀመረ።

በቡልጋሪያ ቆይታው የመጀመሪያው ዓመት የሀገሩን ቋንቋ የመማሪያ ጊዜው ነበር። ሆኖም የሙዚቃ ትምህርት ለመጀመር በቀጣይ ዓመት በአካዳሚው የሚሰጠውን የመግቢያ ፈተና ለማለፍ መዘጋጀት አለበት። በግሉ እንዳይዘጋጅ ፒያኖ የለውም። ለዚህም ስኮላር ባገኘበት የትምህርት ተቋም ልምምድ እንዲፈቀድለት በማሰብ በተቋሙ ትምህርቱን ከተከታተለ ኢትዮጵያዊ ጋር ወደ አካዳሚው ያመራል። በዚህ አጋጣሚ ነው “ሕይወቴን የቀየረልኝ” ከሚለው መምህር ጋር የተገናኘው።

ከግርማ ጋር አብሮ የሄደው የሀገሩ ልጅ ከአካዳሚው በቫዮሊን የተመረቀ በመሆኑ በፒያኖ አንጋፋ ከሆኑት ፕሮፌሰር ጋር ሲገናኙ ፕሮፌሰሩ “ምን እግር ጣለህ?” ሲሉ ይጠይቃሉ። ቫዮሊኒስቱም “ይሄ ልጅ ከኢትዮጵያ ፒያኖ ለመማር ከመጣ ሁለት ወሩ ነው። ለመግቢያ ፈተናው ለመዘጋጀት ልምምድ የሚያደርግበት ሁኔታና፣ ከተቻለ አስተማሪ ቢያገኝ ብለን ነው ይሉታል።” ያኔ ታዲያ ፕሮፌሰሩ “ቃል አልገባም፤ ግን ሦስት ሳምንት ልስጠውና በዚህ ጊዜ ውስጥ ተዘጋጅቶ ልየው” አሉ።

በቀጣዩ ሦስት ሳምንታት ግርማ ቋንቋ በሚማሩበት ተቋም ላይብረሪ ውስጥ የሚገኘው ፒያኖ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት መሠረተ። የትምህርት ክፍሉን ለመቀላቀል ከነበረው ጉጉት የተነሳም ምንም እንኳን በላይብረሪ ውስጥ የሚያጠኑ ተማሪዎች ቢኖሩም ከሕይወት ጥሪው ጋር ከመገናኘት አይበልጡምና ያለሃሳብ ፒያኖውን ይለማመዳል። የቀጠሮአቸው ጊዜ እንደደረሰ ከፕሮፌሰሩ ጋር ተገናኙ። ፕሮፌሰሩን ለማሳመን ያቅሙን ውብ አድርጎ ተጫወተ። ሲጫወት በጥሞና የተከታተሉት ፕሮፌሰር “ስታንዳርድህ ዝቅ ያለ ነው። እዚህ ትምህርት ቤት ካሉ ሌሎች ተማሪዎች ጋር አትገናኝም። ግን ተሰጥኦ አለህ፤ ስለዚህ ልረዳህ እፈልጋለሁ” አሉት። በሳምንት ሁለት ቀን በመደበኛነት ከሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ጋር ተቀላቅሎ ሲማር ቆይቶ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የመግቢያ ፈተናውን ተፈተነ።

አብሮአቸው የሚማራቸው የቡልጋሪያ ዜጎች ሁሉ ተመቻችቶላቸው በመኖሪያቸው የሚማሩ ናቸው። ከሀገሪቷ ዜጎች ውጭ ከእሱ ጋር ይማሩ የነበሩ ጃፓናዊና ግሪካዊ የውጭ ዜጎች ነበሩ። ታዲያ እነሱ ቤት ተከራይተውና ፒያኖ ገዝተው እንደልብ እየተለማመዱ ሲማሩ ግርማ ግን ዶርም እያደረና ልምምዱም በትምህርት ቤት ብቻ ተገድቦ ነበር። እነሱን ሲያይ ነሸጥ አርጎት በቡልጋሪያ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በማምራት የፒያኖ ይገዛልኝ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ምንም እንኳን መልሱ ባይሰምርም።

የራሱ ፒያኖ ኖሮት እንደልቡ መሻት ከፒያኖው ጋር አብዛኛውን ጊዜ እያጠፋ ለመማር ያሰበው እቅድ ባይሰምርም በሰላም ትምህርቱን እየተከታተለ ነበር። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ በመላው ዓለም የኮሚኒዝም ሥርዓት ወደቀ። ያኔ የነሱ ትምህርትም ስኮላርሽፕነቱ ቀርቶ ክፍያ ተጠበቀባቸው። የቡልጋሪያ መንግሥት “ሶሻሊዝም ነው ያመጣችሁ፤ አንከፍልም” አለ። ያኔ ግርማም ወደ ጣልያን ተሰደደ። ሮም እንደደረሰ እድሉ ሲሰምር የኢትዮጵያና የኤርትራ ስደተኞችን ከምትቀበል የኔዘርላንድ መነኩሴ ጋር ተገናኘ።

መነኩሴዋ ሁሉንም ምን እንደሚፈልጉ ትጠይቃለች፤ ግርማንም ፍላጎቱ ወደ ተሻለ ሀገር መሰደድ መሆኑን ጠየቀች። “አይ አቅም ስላነሰኝ እንጂ ፍላጎቴ ወደ ቡልጋሪያ ተመልሼ ትምህርቴን መቀጠል ነው” አለ። እስከዛው በሚል ክርስቲያን ብራዘር የሚባሉ የአይሪሽ ካቶሊኮች ጋር አገናኘችው። ይሄኛው ማረፊያው የተሻለ፤ ምግቡ የተመቸ የሚባልና ፍላጎቱን የሚያሟላ ነው። በዚያ ላይ የግርማ ወዳጅ የሆነው ፒያኖ አለ።

ድጋሚ “ምንድነው ፍላጎትህ? ብለው ጠየቁት። አሁንም ፍላጎቱ አልተቀየረም። የሱ ብቸኛ ፍላጎት ወደ ቡልጋሪያ ተመልሶ ትምህርቱን መጨረስ ነበር። የተሻሉ የሚባሉ ሀገራት መሄድ ሲችል ቡልጋሪያን ያጠበቀበት ምክንያት ፕሮፌሰሩ ነው። ግርማ እውነትም ፕሮፌሰሩ እንዳለው በወቅቱ ተሰጥኦ ቢኖረውም ብቃቱ ገና ነበር። በዚያ ሁኔታ እያለ ሌላ ሀገር ቢሄድና ከአዲስ መምህር ጋር ቢገናኝ ደረጃህ ገና ነው በማለት እንደሚተወው ገብቶታል። የቡልጋሪያው ፕሮፌሰር ግን ተሰጥኦው ስለታየው መታገስና ማብቃትን መርጧል። እናም ግርማም ይሄንን እድል ማጣት አልፈለገም።

ስፖንሰር በመሆን ብራቸውን ከማውጣታቸው በፊት እውነትም ተሰጥኦ መኖሩን ማረጋገጥ ፈለጉ። ለዚህም የፒያኖ ፕሮፌሰር አምጥተው ግርማ ሲጫወት እንዲሰማው አደረጉ። ፕሮፌሰሩም “ይሄ ልጅ ታለንት አለውና እባካችሁ እርዱት” ሲል ተማጸናቸው። ያኔ ብቃቱን ስላረጋገጡ ከስድስት ወር የጣልያን የስደት ኑሮ በኋላ በእነሱ ስፖንሰርነት ወደ ቡልጋሪያ ተመለሰ። ያኔ በሚላክለት ብር ቤት ተከራይቶ ካለው ላይ ሌሎች ኢትዮጵያውያንንም እየረዳ፤ ያረጀም ቢሆን ፒያኖ ገዝቶ በተመቻቸ ሁኔታ ትምህርቱን ቀጠለ።

ቀሪውን ሦስት ዓመታት በጥሩ ውጤት እንዳጠናቀቀ ስፖንሰሮቹን ለማመስገን ወደ ጣልያን አቀና። እነሱም ታዲያ ሮም ውስጥ ኮንሰርት አዘጋጅተውና ታዳሚ ጋብዘው ጠበቁት። ይህ ብቻ ሳይበቃ አዲስ ፒያኖ ገዝተው ወደ ኢትዮጵያ ላኩለት። ከቡልጋሪያ አስፈላጊዎቹን እቃዎች ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ፒያኖው ቀድሞ ኢትዮጵያ ደርሶ ነበር። ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ማስተማር ቢጀምርም፤ የመማር የማወቅ ፍላጎቱ ትኩስ ነበርና አጫጭር ኮርሶችን በእንግሊዝ፣ በጀርመን የስፔሻላይዜሽን ፕሮግራሞችን ሲያገኝ ወጣ ገባ ማለቱ ከተቋሙ መርሀ ግብር ጋር አልገጥም ስላለው ሥራውን ለቀቀ።

አልበም ለመቅዳት በሀገራችን ለክላሲካል ሙዚቃ የተመቸ ሁኔታ ስለሌለ ጀርመን፣ ቡልጋሪያና አሜሪካ በተለያዩ ጊዜያት የወጡት ሰባት የክላሲካል አልበሞቹ የተቀረፁባቸው ሀገራት ናቸው። በ 14 የአፍሪካ ሀገራት ለብቻው ክላሲካል ፒያኖ ያቀረበበት ቱር በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቁን ተከትሎ ከአልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ ለምን ከአንድ ኢትዮጵያዊ ድምጻዊ ጋር በጋራ አትሰሩም የሚል ሃሳብ ተነሳ። የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለፒያኖና ለድምጽ በሚሆን መልኩ በማቀናበር ከድምጻዊ ጸደንያ ገብረማርቆስ ጋር ሠሩ።

የጀርመንና ፈረንሳይ ኤሊዜ ትሪቲ (የባህል ስምምነት) 40 ዓመታቸውን በሚያከብሩበት ወቅት ለበዓል አከባበሩ የሚሆን ፕሮጀክት ካለህ የሚል ሃሳብ መጣ። ያኔ ግርማን ጨምሮ የአራት ሰዎች ጥምረት መለያ ቀለሜ የተሰኘውን አልበም ፈጠረ። ግርማ በፒያኖ ጨዋታ እንዲሁም በማቀናበርና በማስተባበር ዋና ድርሻ የወሰደበት፣ ድምጻዊ ሚካኤል በላይነህ በድምጽ የተሳተፈበት፣ ፈረንሳዊ ቫዮሊን ተጫዋችና ጀርመናዊ ቼሎ ተጫዋች የተሳተፉበትና ተወዳጁ መለያ ቀለሜ አልበም ተሠራ።

ግርማ “በአካል ባላውቃቸውም ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ በየሄድኩበት ሀገር በምሠራው ኮንሰርት ሁሉ አስባቸዋለሁ” ይላል። ሥራቸው በብዙ ኢትዮጵያውያን ትዝታ ውስጥ እንደሰፈረ በማንሳት ፈጣሪ ቢፈቅድና ቢሳካላት ኢትዮጵያ ውስጥ በስማቸው የሙዚቃ ማእከል ቢከፈት የሚል ሃሳብ እንዳለውና ይሄ ሃሳቡ እንዲሳካ እየጣረ መሆኑንም ያነሳል።

ከሠራቸው ሥራዎች ጠንካራው መንፈሴ (ማይ ስትሮንግ ዊል) የምወደው ሥራዬ ነው ይላል። እዛ ውስጥ የተካተቱ ሥራዎች የሱ ታሪክ ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ይጠቅሳል።

ከወይዘሮ ቤተልሄም ወጋየሁ ጋር በትዳር ከተጣመረ 20 ዓመት አስቆጥሯል። ትዳር ከመመሥረቱ በፊት በርካታ ጊዜውን ፒያኖው ላይ ያጠፋ ስለነበር የሙዚቃ ሕይወቴ እንዴት ሊሆን ነው ብሎ ተጨንቆ ነበር። ግን ትዳሩን ተከትሎ በርካታ በረከቶች ማግኘቱን ይናገራል። ትምህርቱም የለኝም የሚለው የኮምፖዝሽን ሥራም ከትዳር በኋላ የመጣ መሆኑን በማንሳት፣ ከትዳር በኋላ በብዙ የተባረከ መሆኑን ይመሰክራል። በአብ ግርማ፣ ብሩክ ግርማ እንዲሁም ቤዛ ግርማ የተባሉ ልጆች ከትዳሩ የተገኙ የአብራኩ ክፋይ ናቸው።

ግርማ ሀገራችንን በዓለም መድረክ በሥራው ከማስተዋወቅ ባሻገርም በሥራው የሚገኘውን ገቢ ለሀገሩ የተበረከተ ኮንሰርት ከዓመት በፊት አዘጋጅቶ ነበር። “ኢትዮጵያ የኛ እናት” የተሰኘውና በርካታ የኢትዮጵያ አርቲስቶች የተሳተፉበት ትልቅ ኮንሰርት በብሔራዊ ትያትር አዘጋጅቶ ነበር። የኮንሰርቱ መግቢያ ሙሉ በሙሉ ለተቸገሩ ወገኖቹ እንዲውል አድርጓል። ሥራው “የኢትዮጵያዊነት ማንነትን በኣለም ላይ ለማሳየት ያደረኩት ጥረት ነው” ይላል።

በቀጣይነት በመደበኛነት ልጆችን ማስተማርና ከተቻለም ሙዚቃን የሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ማቋቋም ይፈልጋል። ዓለም ላይ ከቬንዙዌላ ተጀምሮ 65 ሀገራት የተተገበረ ፕሮግራም አለ። ኑሮዋቸውን ጎዳና ያደረጉና ለሱስ የተጋለጡ ህጻናትንና ታዳጊዎችን ሰብስበው የሙዚቃ ፕሮጀክት ውስጥ በማስገባት የልጆቹ ሕይወት ላይ ለውጥ መታየቱና ከፊሎቹ ፕሮፌሽናል ሙዚቀኛ ሲሆኑ ሌሎቹም ሕይወታቸውን መቀየር መቻሉን ይናገራል። ያንን ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ አምጥቶ መተግበር ይፈልጋል። አዲስ አበባ እንደአፍሪካ መዲናነቷ የዓለም የሙዚቃ መድረክ የማድረግ ፍላጎት አለው። ለዚህም ፌስቲቫል በማዘጋጀት ዓለም አቀፍ ሙዚቀኞችን ኢትዮጵያ ውስጥ በማምጣት ለኢትዮጵያ የቱሪዝም እድል የሚፈጥርና በሀገራችን ለሚገኝ ተሰጥኦ እድል የሚከፍት መድረክ መፍጠር ይፈልጋል።

ከጣልያን ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ግርማ በጣልያን ፕሬዚዳንት የሚሰጠውን “ስታር ኦፍ ኢታሊያ” የተሰኘ ሜዳልያ አዲስ አበባ በሚገኘው የጣልያን ኤምባሲ በተዘጋጀ ትልቅ ዝግጅት ተሸልሟል። ሽልማቱ የፈጠረበትን ስሜት ሲያስረዳም “ጣልያኖች ስደተኛ ሆኜ በሀገራቸው ከመቀበል አልፎ፤ በኢትዮጵያም ኮንሰርት ስጀምር አንስቶ የጣልያን ባህል ማእከል በብዙ መልኩ ተባብረውኛል፤ ለምስጋና ሽልማት መስጠት የሚኖርብኝ እኔ ብሆንም አክብረው ስለሸለሙኝ ተደስቻለሁ” ይላል።

ቡልጋሪያዎችም የባህል አምባሳደራችን ሆነህ ስለሙዚቃ ትምህርታችን ሕያው ምስክር ሆነህ ስማችንን አስጠራህ ብለው ለሱ ያላቸው ክብር የተለየ ነው። ለዚህም የቡልጋሪያ ባህል ሚኒስቴርና በቡልጋሪያ የተማረበት አካዳሚ በጋራ በመሆን ሜዳሊያ ተሸልሟል። ቢዘገይም በሀገራችንም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አንጋፋ የኪነጥበብ ተሸላሚዎች በሚል እውቅና ከተሰጣቸው መሃል አንዱ ነው።

እኛ በሚገባው ልክ ያልተረዳነው ግርማ በሌላ ሀገር በሥራህ ይገባሀል ተብሎ በሽልማት የተበረከተለትን የ 180ሺህ ዶላር ፒያኖ ማስቀመጫ ቦታ አጥቶ ተቸግሯል። ያኔ በፒያኖው ተጠቅሜ ሌሎችን አስተምሬ ተተኪዎችን አፈራለሁ ብሎ ቢያስብም ፒያኖውን ማስቀመጫ ቦታ ማጣቱ ተስፋ አስቆርጦት ነበር። ያንን ጊዜ መለስ ብሎ ሲያስብ “እባካችሁ ቦታ ስጡኝ፤ ላስተምር ችሎታዬን ላካፍል” ሲል ቦታ በማጣቱ ተሰምቶት ኑሮውን ከሀገር ውጭ ለማድረግ አስቦ ነበር።

ተስጥኦዬን የሚረዱ ሰዎች ያሉበት አካባቢ ሄጄ መኖር አለብኝ የሚል ውሳኔ ላይ ደርሶም ነበር። በዚህ ውሳኔው ጸንቶ እንዳለ ወሬው የብሔራዊ ቤተመፃህፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጆሮ በመድረሱ ጠርተው አናግረው ለምን እዚህ አትሞክርም ይሉታል። በኤጀንሲው ፒያኖው ቦታ ከማግኘቱ በተጨማሪ ልጆችንም ለማስተማር ተፈራርመዋል። አሁን ሌሎችም አማራጮች እየመጡ ስለሆነ ሀገሬ ለካ ታየኛለች የሚል ስሜት ተሰምቶት፤ እሱም የሀገሩን ውለታ ልጆቿን በሙዚቃ በማብቃት ለመመለስ እየተዘጋጀ ነው።

 ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You