እንደምን ሰነበታችሁ…ኧረ ለመሆኑ የፈረቃ መብራት እንዴት ይዟችኋል? አይዟችሁ “ፈረቃው እስከ ሰኔ 30 የሚቆይ ነው” ብለውናል። (“እነማን ናቸው እንደዚያ ያሉት?” ብላችሁ እንደማትጠይቁኝ ተስፋ አደርጋለሁ) … ዛሬ እስኪ ከመብራት ጋር የተያያዙ የሌሎች አገራትንና የእኔን ገጠመኞች በአጭሩ ላካፍላችሁ።
“መብራት በፈረቃ ሆነ” ሲባል ተናድጄ ነበር። የፈረቃ መርሃ ግብሩ በተገለፀበት ቀን ከስራ ቦታዬ ወደ ቤት ስመለስ ንዴቴን ፊቴ ላይ ያስተዋለውና የግቢው በር ላይ ቆሞ ያገኘሁት ጎረቤቴ “የተናደድክ ትመስላለህ። ምን ሆነህ ነው? ሰላም አይደለም እንዴ?” የሚል ጥያቄ አቀረበልኝ። እኔም “ይህ ሰውዬ መብራት በፈረቃ መሆኑን አልሰማም ወይንስ ምን ሆኖ ነው ያልተናደደው” ብዬ በማሰብ በንደቴ ላይ ሌላ ንዴት ላለመጨመር እየታገልኩ ቀዝቀዝ ባለ ስሜት …”መብራት በፈረቃ መሆኑን አልሰማህም እንዴ?” አልኩት። ጎረቤቴም ምንም ሳይደናገጥም ሳይገረምም ለስለስ ብሎ “አልሰማሁም” አለኝ። “ስላልሰማህ ነዋ ያልተበሳጨኸው” አልኩት። እርሱም ይበልጥ ዘና ባለ ስሜት “ታዲያ ይህ ምኑ ያናድዳል?” አለኝ።
የጎረቤቴ ምላሽ ሌላ ንዴት ላለመጨመር ያደረግኩትን ጥረት ውሃ እንዲበላው አደረገውና ጮክ ብዬ “እንዴት አልናደድም?!” አልኩት። ይህን እየተነጋገርን በነበረበት ቅፅበት መብራት ጠፋ። ከጎረቤቴ አንደበት ዘለግ ያለ ሳቅ፤ ከእኔ ደግሞ ዘለግ ያለ የንዴት ጩኸት ተሰማ።
ጎረቤቴ ሳቁን ገታ አደረገና ንደቴ እስከሚበርድልኝ ድረስ ጠብቆ ፈገግ ባለ ፊትና ቀለል ባለ የንግግር ኃይል “ስማኝ ወዳጄ … መብራት በፈረቃ ሆነ ብለህ አትበሳጭ። እንኳን በፈረቃ በጨረቃም ለምደነዋል” ብሎኝ ወደ ቤቱ ሲገባ “እንኳን በፈረቃ በጨረቃም ለምደነዋል” የሚለው ንግግሩ ደጋግሞ በጆሮዬ አቃጨለ። ሳቄና ንደቴ እኔ ልቅደም እኔ ልቅደም እያሉ ተናነቁ። መሽቶ ስለነበር ጨረቃዋ ሰማይ ላይ መኖሯንና አለመኖሯን ለማረጋገጥ ቀና ብዬ ስመለከት እርሷም የለችም። “ወይ አለመታደል! ጨረቃም ጨከነችብን አይደል” ብዬ በለሆሳስ ተናገርኩ። “እንኳን በፈረቃ በጨረቃም ለምደነዋል” እያልኩ ብቻዬን እያወራሁ ወደ ቤት ገባሁና ሻማ ለኮስኩኝ። (ታዲያ ሌላ ምን አማራጭ አለኝ)
በነገራችን ላይ መብራት ሲጠፋ በመብራት አመካኝተን ወጣ ለማለት አጋጣሚው ስለሚፈጠርልን መብራት መጥፋቱ አይደጋገም አንጂ አልፎ አልፎ እንኳ ጥሩ ነው ሲሉ የሰማኋቸው ወንደላጤ ወዳጆች አሉኝ። (እኔ ግን በዚህ አስተሳሰብና አመክንዮ አላምንም። ከቤቱ ወጥቶ ማምሸት የፈለገ ሰው የግድ የመብራት መጥፋትን መጠበቅ አለበት የሚል አመለካከት የለኝም)
ስለሆነም፤ እኔ እንደነዚህ ወንደላጤ ወዳጆቼ መብራት ሲጠፋ ከቤት የመውጣት ልምድ ስለሌለኝ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ወደ መኝታዬ አዘገምኩ። በጠዋት ተነስቼ በዕለቱ ቢያንስ በፈረቃው መብራት እንዲኖር ፀልዬ ወደ መስሪያ ቤት ገባሁ። መስሪያ ቤቴ መብራት ቢጠፋም ጄኔሬተር ያለው ስለሆነ ቢሮ ውስጥ ሳሳልፍ የመብራት መጥፋትንና መኖርን አላስተውለውም። ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ተገናኘንና ቁርስ ስንበላ የፈረቃ መብራት ነገር ተነሳ።
አንዱ ባልደረባዬ መብራት በፈረቃ መሆኑ እንዳስደሰተው ሲነግረን ግራ ተጋባን። ሁላችንም በአንድ ድምፅ የታዘዝን ይመስል “እንዴት?” አልነው። እርሱም “ምን መሰላችሁ … መብራት ሲጠፋ ከባለቤቴ ጋር ራት የምንበላው በሻማ ነው። የሻማ እራት ደግሞ ነፍሴ ነው…” ብሎ መለሰልን። በትንሹም ቢሆን ለቀቅ አድርጎኝ የነበረው ንዴቴ እንደገና አገረሸብኝና “ታዲያ የሻማ እራት መብላት ስትፈልግ መብራቱን አታጠፋውም እንዴ?” አልኩት። ሌላኛው ባልደረባችን ደግሞ “የሻማ እራት ከሌላው እራት በምን ይለያል?” ብሎ ጥያቄ ጨመረለት።
የሻማ እራት የሚወደው ባልደረባችንም የእኔ ንዴትና የሌላኛው ባልደረባችን ጥያቄ “ክብደት” አስጨንቆታል መሰል “ሌላ ጊዜ እነግራችኋለሁ” ብሎን ወደ ቢሮ እንድንገባ አመለከተን። እኔም ደህና የበረደውን ንዴቴን ቀስቅሼ ወደ ቢሮ ገባሁ። ቢሮ ውስጥም ይኸው የፈረቃ መብራት ጉዳይ ሰራተኛውን እያነጋገረው ደረስን። እኔም የጎረቤቴ ንግግር ትዝ አለኝና ድምጼን ከፍ አድርጌ “እንኳን በፈረቃ በጨረቃም ለምደነዋል” ብዬ ስናገር ብዙ ሰው ሳቀ።
በእድሜ ጠንከር ያሉ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ደግሞ ፈገግ እያሉ “የዛሬ ልጆች እድለኞች ናችሁ። ስትወለዱ ጀምሮ ለቴክኖሎጂው ቅርብ ሆናችሁ ታድጋላችሁ። በእኛ ጊዜ መብራት እንደልብ አልነበረም። መብራት ሲጠፋ ቶሎ ትናደዳላችሁ …” አሉኝ። ሰውየው የተናገሩት ወደእኔ እየተመለከቱ ስለነበር “መናደዴን ሁሉም አውቆታል” ማለት ነው ብዬ አሰብኩ። እኔም “እንኳን በፈረቃ በጨረቃም ለምደነዋል” ብዬ ወደ ስራዬ ገባሁ።
በሌላኛው ቀን ከቤቴ በቅርብ ርቀት ላይ ወደሚገኝ ሱቅ ሄድኩና ባለሱቋን “ትልቁን ሻማ” እንድትሸጥልኝ እጠየቅሁኝ ሱቁ በር ላይ በቆምኩበት አጋጣሚ ብዙ ሰው እየመጣ “ሻማ … ትልቁን ሻማ … ሻማ …” እያለ ትዕዛዝ በላይ በላዩ ላይ ይደራርብባታል። “ዘንድሮ የተጠቀመው የሻማ ነጋዴ ነው” እያልኩ ሻማውን ገዝቼ ወደ ቤት ተመለስኩ።
እስኪ ከመብራት መጥፋት ጋር ተያይዞ በሌሎች አገራት የተፈጠሩ ክስተቶችን ላካፍላችሁ። በዚምባብዌ መብራት በተደጋጋሚ እየጠፋ በማስቸገሩ የአገሪቱ የኢነርጂ ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት ከስልጣናቸው ተሰናብተዋል። በአንድ ወቅት ደግሞ በአንዲት እስያዊት አገር የኢነርጂ ሚኒስትሩ መብራት በአንዲት መንደር ለ20 ደቂቃዎች ያህል በመጥፋቱ ለ20 ደቂቃዎች ያህል ጎንበስ ብለው በመቆየት ሕዝቡን ይቅርታ እንደጠየቁ በመገናኛ ብዙኃን ሲወራ ሰምተናል። (በነገራችን ላይ የእኛ አገር ባለስልጣናት “እስካሁን ድረስ ለጠፋውና ለተቆራረጠው መብራት ጎንበስ ብለው ሕዝቡን ይቅርታ ይጠይቁ” ቢባል ብዙ ዓመታትን እንዳጎነበሱ ማሳለፍ ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው … የማይሆነውን!)
ለማንኛውም መብራት በፈረቃ መሆኑ እስከሚቀር ድረስ እንዳትናደዱ እመክራችኋለሁ! “እንኳን በፈረቃ በጨረቃም ለምደነዋል”ና እያሉ ጊዜውን መሸኘት ሳይሻል አይቀርም።
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2011
አንተነህ ቸሬ