ጉዞ ከቱሪስት መተላለፊያነት – ወደ መዳረሻነት

በአዳራሹ የተገኙ ታዳሚዎች በዞኑ የቱሪስት መስህቦች ላይ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንስቲትዩትና በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የቀረቡ የውይይት መነሻ ጽሁፎችን አዳምጠው ጥያቄዎችን፣ ማብራሪያዎችንና አስተያየቶችን በማንሳት መምከራቸውን ቀጥለዋል። እምቅ ሀብቱ ብዙ መሆኑ፣ ግን እንዳልለማ ይጠቀሳል፤ ለእዚህ ችግር መፍትሄ ይሆናል የተባለውም አቅጣጫ ይጠቀሳል።

በአዲሱ የማእከላዊ ኢትየጵያ ክልል ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ አስተዳደር በስልጤ ባህል ማዕከል አዳራሽ በቅርቡ የተካሄደው ይህ መድረክ የዓለም የቱሪዝም ቀን በዓለም ለ44ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ36ኛ ጊዜ የተከበረበት ነው። መድረኩ በዞኑ የቱሪስት መስህቦች ላይ ለመምከር መልካም አጋጣሚ የፈጠረም ተብሏል።

ዞኑ የበርካታ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች ባለቤት ስለመሆኑ አስቀድሞም የሚያውቁ ቢኖሩም፣ ጥናታዊ ጽሁፎቹ ደግሞ በሚገባ አመላክተዋቸዋል። ዞኑ በርካታ ለቱሪስት መስህብነት ሊውሉ የሚችሉ ጸጋዎች እንዳሉት በመጥቀስ፣ የቱሪስት መስህቦቹን አውጥቶ በማሳየት፣ በማስተዋወቅ፣ በማልማትና ለገበያ በማቅረብ በኩል ግን ምንም እንዳልተሠራ ነው ሁሉም ያረጋገጡት።

‹‹የስልጤ ዞን የቱሪዝም መስህቦች እምቅ ሀብቶችና የቱሪዝም እድገት ተግዳሮቶች›› በሚል ርእሰ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የወራቤ ዩኒቨርሲቲው ጥናት አቅራቢ መምህር አንዋር አየነው፣ የቱሪዝም ድርጅት ኢትዮጵያን በሁለት የቱሪዝም መስመሮች እንደሚከፍል ይጠቅሳሉ። አንዱ የሰሜኑ ታሪካዊው መስመር፣ ሁለተኛው ደግሞ የደቡቡ የተፈጥሮ ቱሪዝም መስመር መሆኑን ይገልጻሉ።

ድርጅቱ የስልጤ ዞን የቱሪዝም መስመርን በቱሪዝም መስመሩ አለማካተቱንም አመልክተው፣ በዚህ የተነሳም ቱሪስቶች ወደ ደቡብ ሲመጡ የጥያ ትክል ድንጋይን ጎብኝተው በስልጤ ዞን አልፈው ቀጥታ ወደ አርባ ምንጭ እንደሚሄዱም ነው ያመለከቱት። ለእዚህ አንዱ ምክንያት የዞኑ የቱሪስት መስህቦች በደንብ አለመጠናት እና አለመተዋወቅ መሆኑንም መምህር አንዋር አየነው ገልጸዋል።

መስህቦቹን የሚያስተዋውቁ፣ የሚያመላከቱ፣ ለገበያ ማቅረብ የሚያስችሉ በቀላሉ ሊሠሩ የሚችሉ ሥራዎች ሳይቀሩ አልተሠሩም ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ ተሳታፊዎችም ተደምጠዋል። መስህቦቹ ያሉባቸውን ስፍራዎች የሚያመላክቱ መረጃዎች፣ መጠቆሚያዎች፣ መንገዶች፣ ለጎብኚዎች መሠረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ አካላት እንደሌሉ ነው እነዚህ ተሳታፊዎች ያመለከቱት። በዚህ ሳቢያም ዞኑም ህዝቡም ሀገርም አልፎም ተርፎም ቀጣናውም ተጠቃሚ ሊሆኑ እንዳልቻሉም መምህር አንዋር አየነው ተናግረዋል።

ዞኑ ከቱሪስት መዳረሻነት ይልቅ የቱሪስት መተላለፊያ ሆኗል የሚል አስተያየትም ተሰጥቷል። ዞኑ የደቡብ የቱሪስት ኮሪደር /መተላለፊያ/ መሆኑ፣ ለአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱ ከቱሪዝም እምቅ ሀብቶቹ ተጠቃሚ እንዲሆን ሊያስችለው ሲገባ ነገሮች ከዚህ በተቃራኒው ሆነው መገኘታቸው በእጅጉ ሊያሳስብ እንደሚገባም ተጠቁሟል።

የሚዲያና ፕሮሞሽን ባለሙያው አቶ መሀመድ ካሳ ‹‹አሁን መቆጨቱ ቀርቶ እንስራ›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ‹‹ለእዚህም ግብረ ሃይል /ታስክ ፎርስ/ ይቋቋም፤ አርክቴክቶች ይምጡ፤ ወደ መስህብ ቦታዎች የሚያስገቡ መንገዶች፣ ካርታዎችና መስመሮች ይሠሩ፣ መስመሮቹ ይተሳሰሩ›› ሲሉ አስገንዝበዋል።

እሳቸው ዞኑን በውሎ ገባ ለማስጎብኘት ቱሪስት ይዘው በአካባቢው ተገኝተው እንደነበር አስታውሰው፣ ወደ ሀጂ አሊዬ ወይም አልከሶ መስጊድ የሚወስደው መንገድ ግን ልክ አይደለም በማለት ችግሩን ለማሳየት ሞክረዋል፤ ‹‹ወደ ሀረ ሼጣን›› የሚል ላይን ቀስት የለም፤ ከሀረ ሼጣን ቀጥሎ የምልክት ሰሌዳዎች የሉም ሲሉ አመልክተዋል።

አቶ መሀመድ እንዳሉት፤ እነዚህን ሰሌዳዎች /ቦርዶች/ ለማዘጋጀት በጣም ትንሽ ብር ቢጠይቅ ነው። ሰሌዳዎቹ ከተማው ላይ በተለይ ከሀላል ቱሪዝም አኳያ ምን አለ ለሚለው መልስ ሊሰጡ ይችላሉ። ይህ ቢሆን መስህቦቹን ወደ ሆሳእና እና ሶዶ የሚሄድም ሊጎበኛቸው ይችላል። እነዚህ በአስቸኳይ ሊተገበሩ ይገባል።

‹‹ያሉንን አላህ የባረከልንን ማናቸውንም አይነት የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ጸጋዎችን በአግባቡ ተንከባክበን ለቱሪዝም ሀብት ብናውል እኛ ነዳጅና ሌሎች ነገሮች አያስፈልገንም›› ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ በተለይ የሃይማኖታዊ ቱሪዝም ጥቅሙ ተዘርዝሮ እንደማያልቅ ጠቁመዋል። ‹‹ሰው ልቡ ቅን ነው፤ መሬት ላይ፣ ድንጋይ ላይ፣ አልጋ ላይ ብታስተኙት በቅንነት ይመጣል ሲሉ ጠቅሰው፣ እባካችሁ ከዚህ ውይይት አንድ ፍሬ እናግኝ፤ እድለኞች ናችሁ ተጠቀሙበት፤ እንጠቀምበት›› ብለዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪም ተመሳሳይ ሃሳብ ሰንዝረዋል። ሌሎች ሀገሮች ታሪክ ሳይኖራቸው ታሪክ ሠርተው ያስጎበኛሉ፤ ተራራ ሳይኖራቸው ተራራ ይሠራሉ፤ ቅርስ ሳይኖራቸው ከየትኛውም ቦታ ቅርስ አሰባስበው ያስጎበኛሉ ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ እኛ ያለንን በቆሻሻ ሸፍነን ሁልጊዜ ምክንያት እየፈጠርን ነው ሲሉ አስገንዝበዋል። አንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን እንደ ቀበሌ፣ እንደ አንድ ቅርስ ያለበት አካባቢ፣ ሠርቶ ልዩነት መፍጠር ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ ቅርብ ርቀት ላይ ከ100 መቶ በላይ ባህላዊ ምግብ ያለው ብሄረሰብ፣ የሌሎች በርካታ መስህቦች ባለቤት የሆነ ዞን፣ ይህን ያህል ግዙፍ ሀብት ይዞ ጎብኚዎች አልፈውት አርባምንጭን ይጎበኛሉ ሲሉ አመልክተዋል። ይህን መሸጋገሪያ የተደረገ መስህብ የዞኑ አመራር በትኩረት ሊመለከተው እንደሚገባና በዚህ ላይ በመሥራት ታሪክ መቀየር መቻል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

‹‹ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች ሀገር ናት፤ የቱሪዝም ሀብቷ ያልተነካ ተፈጥሯዊ ፣ ሃይማኖታዊ እያልን የቱሪዝም ሀብቱን ለንግግር ማድመቂያ እያደረግነው ነው፤ እኛም ሳንጠቀም ልጆቻችንም ሳይጠቀሙ እኛም እናልፋለን›› ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ ይህ ዞን በቱሪዝም ሀብቱ ላይ ታሪክ ከሠራ ለሌችም ትምህርት እንደሚሆን ጠቁመዋል። ለዚህም መዳረሻው ባለበት አካባቢ ካለው ማህበረሰብ ጀምሮ እያንዳንዱ አካል ሳይሰለች መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

የዞኑ አስተዳደር፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ቱሪስት ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት፣ የወራቤ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች ተቋማት የሥራ ሃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃንና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ከመከሩበት ከእዚህ መድረክ፣ የዞኑ የቱሪስት መስህቦች አለመልማታቸውን፣ አለመተዋወቃቸውንና ለገበያ አለመዋላቸውን፣ በዚህም ከፍተኛ ቁጭት መፍጠሩን መረዳት ተችሏል። በመድረኩ መስህቦቹን ለማልማት ለማስተዋወቅና ለገበያ ለማቅረብም ቃል ተገብቶበታል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ንጉሡ ጥላሁን ከአምስት ዓመት በፊት የወጡ መረጃዎችን ዋቢ አድርገው እንደተናገሩት፤ ቱሪዝም በየዓመቱ በአራት በመቶ እያደገ ይገኛል። በዓለም ከሚፈጠሩ አስር የሥራ እድሎች አንዱ በቱሪዝም ዘርፍ የሚፈጠር ነው፤ ዘርፉ ለዓለም አጠቃላይ እድገትም 10 በመቶ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

ኢትዮጵያ ምንም አንኳ በተፈጥሮ ፣ ሰው ሠራሽ፣ ባህላዊ መስህቦቿ በዓለም ብትታወቅም፣ በርካታ መስህቦችን በዩኔስኮ ብታስመዘግብም ፣ በዘርፉ ከአፍሪካ ቀዳሚ ስፍራ ላይ ብትሆንም፣ ከዚህ ሁሉ ጸጋዋ ግን የሚገባትን ያህል ጥቅም እያገኘች አይደለችም ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል።

‹‹ከመስህቦቹ ተጠቃሚ ለመሆን ዛሬ መስራት መጀመራችን ትክክለኛ ወቅት ነው›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በእዚህ ጉዳይ ላይ እየተነጋገርን ያለነው የዓለም የቱሪዝም ቀን እየተከበረ ባለበት እንዲሁም የስልጤ ዞንን የቱሪስት መስህቦች ለማልማት፣ ለማስተዋወቅና በመሸጥ ተጠቃሚ ለመሆን ወሳኝ ሚና ያላቸውና በቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት የተሠሩ የጥናት ሰነዶች ለርክክብ ዝግጁ በተደረጉበት ወቅት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የስልጤ ዞን አያሌ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዳሉት በመድረኩ ከቀረቡ ዝግጅቶች መረዳት መቻላቸውን ጠቅሰው፣ ከዞኑ የቱሪስት መስህቦች የሀጂ አሊዬ መስጊድ፣ የኢማም ሳቦታ ቤተመንግሥት፣ የአምስቱ ንግሥቶች መቀመጫ፣ የአይናጌ ዋሻ፣ ሀረ ሼጣን ሀይቅ፣ የተለያዩ ፍልውሃዎችና አጥኚዎቹ በዝርዝር ያጠኗቸውና በፎኖተ ካርታው /ሮድ ማፑ/ የሚካተቱት ጥናቶች አካባቢው በቱሪዝም እምቅ ሀብቶች የበለጸገ መሆኑን እንደሚያመለክቱ አብራርተዋል።

ዞኑ ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለኢኮኖሚ እድገት፣ የህብረተሰቡን ሕይወት ለመቀየር፣ አካባቢውን ከሌሎች አካባቢዎች ለማስተሳሰር፣ ባህሉን እንዲያስተዋውቅ ፣ አካባቢውም የሌሎችን ባህል እንዲያውቅ በአጠቃላይ በሀገሪቱም፣ በቀጣናውም፣ በዓለምም ደረጃ እንዲታወቅ የሚያደርጉ እጹብ ድንቅ የቱሪስት መስህቦች እንዳሉት ጠቅሰዋል።

መስህቦቹ ለዞኑም ህዝብ፣ ለሀገርም ጠቀሜታ ሳይውሉ በመኖራቸው በሁሉም ዘንድ ቁጭት መፈጠሩንም ጠቅሰው፣ ቁጭቱን ወደ ተግባር በመቀየር ከዘርፉ ለመጠቀም መረባረብ እንደሚገባ አስገንዘበዋል። እነዚህን ሀብቶች ለመጠቀም በርካታ ተግዳሮቶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉም ነው አቶ ንጉሡ ያስታውቁት። ‹‹እነዚህ ችግሮች ተባብረን ከሠራን፣ ከተጋገዝን የማይፈቱ፣ የማንሻገራቸው አይደሉም›› ሲሉ ገልጸዋል።

የአካባቢው ጸጋ ችግሮቹን እንደሚያሳንሳቸው ያመለከቱት አቶ ንጉሡ፣ ጸጋዎቹ ችግሮቹን ተሻግሮ ለመሥራት ወኔና ስንቅ እንደሚሆኑም ተናግረዋል። የተጀመረውን የጥናትና ምርምር ሥራ ከኢትዮጵያ የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት፣ ወራቤ ካለው የቴክኒክና ሙያ ተቋምና ከወራቤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን አጠናክረን እናስቀጥላለን ብለዋል።

ከችግሮቹ አንድ ሁለቱ በቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ጥናት መፈታታቸውን ጠቅሰው፣ ኢንስቲትዩቱ የቱሪስት ካርታ መሥራቱንና የስልጤ ማህበረሰብ ባህላዊ ምግቦች አዘገጃጀትን መሰነዱን ጠቅሰዋል። በዚህ ተግባርም አንድ ርምጃ ወደፊት መራመድ መቻሉንም ነው ያስታወቁት። ‹‹አሁን የተሰራው ሥራ አንድ ምእራፍ ወደፊት ያራምዳል፤ ለእዚህም እውቅና መስጠት ይገባል ብለዋል።

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር እንዳሉት፤ የስልጤ ብሄረሰብ የራሱ ልዩ የሰላምና የመቻቻል ተምሳሌት የሆነ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት፣ የማንነቱ መገለጫ የሆኑ የእደ ጥበብ ሥራዎች፣ ባህላዊ አልባሳት፣ የጸጉር አሠራር፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የበዓል አከባበር፣ የራሱ የዘመን አቆጣጠርና የንግሥና ሥርዓት /ደረጋዊ/ ያለው ማህበረሰብ ነው።

ዋና አስተዳዳሪው እንዳመለከቱት፤ እነዚህ ድንቅ መስህቦች ዞኑን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ሊያደርጉት ይችላሉ። እነዚህን ሀብቶች በመጠበቅ፣ በማልማትና በማስተዋወቅ በኩል ባለፉት ዓመታት የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት በማቋቋም እና ያለውን እምቅ አቅምና ችግሮችን የመለየት ጥናት ተሠርቶ ወደ ትግበራ ተግብቷል። ይሁንና የቱሪስት መስህቦቹ ለገበያ እንዲውሉ በማድረግ በኩል አሁንም ችግሮች ይስተዋላሉ።

ችግሮቹን ለመፍታት የዞኑ መንግሥት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ አሊ አስታውቀው፣ ያሉትን ሀብቶች በመጠበቅና በመንከባከብ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችሉ ጥናቶችና ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደሚደረጉም አመልክተዋል። ‹‹መስህቦቻችን በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ ስልቶችን ቀይሶ ለመተግበር የሚያስችሉ አሠራሮችን በመፍጠር ለዞኑና ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ልማት ለማዋል ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

ዋና አስተዳዳሪው የግል ባለሀብቶችም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በብዛትና በጥራት በመገንባት በዘርፉ የሚታየውን ችግር በመቅረፉ በኩል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አስተላልፈዋል። ለእዚህም የዞኑ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

‹‹እነዚህ ተግባሮች ከተከናወኑ ከአዲስ አበባ ቅርብ ርቀትና በደቡብ የቱሪዝም ኮርደር ላይ የሚገኙትን የስልጤ ዞን የቱሪስት ሀብቶችን በቀላሉ ለገበያ ማቅረብ እንደሚቻል እምነቴ የጸና ነው›› ሲሉም አቶ አሊ ከድር አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በዞኑ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን በአጠቃላይ እንዲሁም የሀላል ቱሪዝም ቦታዎችን በተለይ በማስተዋወቅ የአካባቢውን ቱባ ባህሎችና ወጎች በማሳወቅ፣ በኢንዱስትሪው የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና በማሳደግና በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ሥራ በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ ይሠራል፤ ለእዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን እንዲወጣ ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።

ከዞኑ ቱሪዝም ማነቆዎች መካከል የቱሪስት ጋይድና የቱር ፓኬጅ አለመዘጋጀት መሠረታዊ ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰው፣ የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ይህን ችግር የሚፈታ ጥናት አካሂዶ የቱር ፓኬጅ ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

ኢንስቲትዩቱ በስልጤ ብሄረሰብ የባህል ምግቦች አዘጋጃጀት ላይ ጥናት በማካሄድ ማንዋል በማዘጋጀት ምግቡ የእሴት ሰንሰለቱን ጠብቆ እንዴት እንደሚዘጋጅ ጭምር የሚያሳይ የጥናት ሰነድ ማዘጋጀቱንም እንዲሁ አስታውቀዋል። ዋና አስተዳዳሪው ኢንስቲትዩቱ ላከናወናቸው ተግባሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የዞኑን ትላልቅ የቱሪስት መስህብ ጸጋዎች በማልማት፣ በማስተዋወቅ መሸጥ አካባቢውን ብሎም ሀገርን ለመቀየር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አስታውቀው ፣ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን በአካባቢያችን ያሉ ጸጋዎችን ለመሸጥ እየተጋግዝን በተቀናጀ መንገድ እንሥራ ሲሉም ጠይቀዋል። በዚህም የስልጤን ማህበረሰብ ከፍ እናድርግ ፤ የስልጤ ማህበረሰብ ከፍ ሲል ኢትዮጵያም ከፍ ትላለች፤ ድምር ውጤቱ ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ነውና ሁላችንም በዚህ ሥራ ላይ እንረባረብ የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ያዘጋጃቸውን የስልጤ ብሄረሰብ የባህል ምግቦች አዘጋጃጀትን እንዲሁም የቱሪስት ካርታ /ማፕ/ ሰነዶች ርክክብ ከዞኑ አስተዳደር ጋር ተደርጓል። የቱሪስት መዳረሻ ጉብኝት በሀረ ሼጣን ሀይቅ የተካሄደ ሲሆን፣ የብሄረሰቡን ምግቦች የሚያስተዋውቅ ዝግጅትም ቀርቧል።

ኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You