በሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሠረተ የወደብ አማራጭ እና የባህር በር ጥያቄ

 ዓለም ከተፈጠረች ጊዜ ጀምሮ ሁሉ ነገሯ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ ነው። ሁሉም ነገሯ ሲባል ተፈጥሮንም ይጨምራል። ለምሳሌ ገበሬ ለመሬት ውሃ እና ዘር ባይሰጣት ኖሮ መሬት ለአርሶአደሩ ፍሬ ልትሰጠው አትችልም ነበር። ገበሬ ከመሬት የተሻለ ፍሬ ለማግኘት ሲል ለመሬት የተሻለ ምርጥ ዘር እና ማዳበሪ ይሰጣል። በሰጠው የዘር እና ማደባሪያ ልክም ፍሬ ያገኛል።

ከጥንት ጀምሮ ያለው የፖለቲካው ዓለምም እንደዚሁ ነው ። አንድ ነገር ትሰጣለህ በምትኩ ሌላ ነገር ትቀበላልህ። በተለይ በዘመናዊት ዓለም የሰጥቶ መቀበል መርህ የተሻለ ውጤት እንዲያስገኝ በመሳብ ሀገራት በጥናት ላይ የተመሠረተ የውስጥ እና የውጭ ህግጋቶች እና ፖሊሲዎች ይነድፋሉ። የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች በንድፉ መሠረት በጥንቃቄ ያከናውናሉ።

ዓለም በሰጥቶ የመቀበል መርህ ስለምትዘወር እንጂ ሃያላን ሀገራት እንዴት አድርገው በጂቡቲ ፣ በሶማሊያ ፣ በኬንያ ወዘተ በመሰሉ ሉዓላዊ ሀገራት የባህር በር መሬት ላይ የባህር ሃይላቸውን ቤዝ መመሥረት ይችሉ ነበር? በነገራችን ላይ ሰጥቶ መቀበል በራሱ በቂ አይደለም። የሰጥቶ መቀበል መርህ አክሳሪ እንዳይሆን ጥብብ የታከለበት አመራር እና አስተዳደር ያስፈልገዋል።

ጥበብ የሌለው ሰጥቶ መቀበል ከትርፉ ኪሳራው ያመዝናል። ኪሳራ ሲባል እንዲሁ ኪሳራ ብቻ አይደለም። ምን አልባትም አንድን ሀገር ከነመፈጠሯ ሊያስረሳ የሚችል ኪሳራ ያመጣል። ስለሆነም የሰጥቶ መቀበል መርህ ሁልጊዜም በጥብብ ሊከናወን ግድ ነው። ምክንያቱም ስለሰጠን ብቻ ጥሩ ነገር ማግኘት አንችልምና።

ሰጥቶ መቀበል በጥብበ ካልተመራ ሊያደርሰው የሚችለው ኪሳራ ሳስብ ሁሌም በአእምሮዬ ቀድሞ የሚመጣው አጼ ዮሐንስ አሟሟት ነው ። እኤአ ሰኔ 3 ቀን 1884 በዓድዋ ከተማ አጼ ዮሐንስ በአንድ ወገን እንግሊዝ እና ግብጽ ደግሞ በሌላኛ ወገን አንድ ስምምነት አደረጉ። ይህ ስምምነት የሕይወት ወይም የዓድዋ ስምምነት (Hewett Treaty or Treaty of Adwa) እየተባለ ይጠራል።

እንግሊዝ እና ግብጽ ከአጼ ዮሐንስ ጋር ይህን ስምምነት ያደረጉበት ሰጥቶ መቀበልን መርህ ተጠቅመው ነበር። ነገሩ አንዲህ ነው ፡- የሕይወት ወይም የዓድዋ ስምምነት (Hewett Treaty or Trea­ty of Adwa) እስኪደረግ ድረስ እንግሊዝ እና ግብጽ በጥምረት ሱዳንን በቅኝ ግዛት ያስተዳድሩ ነበር። ይህ በእንዲህ እያለ የእንግሊዝ እና የግብጽ ጦር በሱዳን ጦር የኃይል የበላይነት ተወስዶበት ተከበበ።

በዚህ ሰዓት ብቸኛ መውጫ የነበረው በኢትዮጵያ በኩል ነበር። ይሄን ብቸኛ መውጫ ለመጠቀም የእንግሊዝ እና የግብጽ መንግሥታት ከአጼ ዮሐንስ ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ ተጠቅመው ድርድር ጀመሩ። ድርድሩም ሰምሮ ስምምመት ላይ ደረሱ። ስምምነቱም የእንግሊዝ እና ግብጽ ጦር በኢትዮጵያ በኩል አድርጎ ከከበባው እንደወጣ ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ ኢትዮጵያም በግብጽ በወረራ ከተያዘባት የምጽዋ ወደብ በኩል የጦር መሣሪያዎችን ጨምሮ ከቀረጥ ነጻ ንግድ ማካሄድ እንድትችል ፤ ለበርካታ ዓመታት በግብጽ ተይዞ የነበረው “የቦጎስ” ወደብ ለኢትዮጵያ እንዲመለስ የሚል ነበር።

ስምምነቱን እውን ለማድረግ ኢትዮጵያ በራስ አሉላ አባነጋ የሚራ ጦሯን ወደ ሱዳን አስገብታ እንግሊዞችን እና ግብጾችን ከከበባ ለማወጣት ኩፊት ላይ ከሱዳኞች ጋር ተፋለመች። በሱዳን ጦር ተከበው በሞት እና በሕይወት መካከል የነበሩ የእንግሊዝ እና የግብጽ ቅኝ ገዢዎች ከሞት መንጋጋ ወጡ። በዚህም ሱዳኖችም በአጼ ዮሐንስ አስተዳደር ክፉኛ ቂም ያዙ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አጼ ዮሐንስ የተከተሉት የሰጥቶ መቀል መርህ ጥብብ ያልታከለበት ስለነበር እንግሊዞች የገቡትን ቃል አጥፈው ቀይ ባህርን ለጣሊያኖች አሳልፈው ሰጡ። የ Hewett Treaty or Treaty of Adwa ሰነድ በእንግሊዞች መሰሪነት ከቆሻሻ ቅርጫት ተወረወረ።

በተመሳሳይ ሰዓት በ Hewett Treaty or Trea­ty of Adwa ስምምነት የኢትዮጵያ ጣልቃ ገብነት ያስቆጣት ሱዳን አጼ ዮሐንስን ለመበቀል በመተማ በኩል ኢትዮጵን ወረረች። አጼ ዮሐንስም ለሞት በቁ። ይህ ሰጥቶ መቀበል መርህ በጥብብ ያልታጀለ እና ያልታሸ ስለነበር ኢትዮጵያ ጀግና ንጉሠ ነገሥቷን ከመንጠቋም ባለፈ የዚህ ስምምነት ጦስ ዛሬ ላይ ለደረሰው የወደብ ይገባኛል ውዝግብ መነሻ የሆነውን የመጨረሻው መጀመሪያ ችግርን ወለደ።

እዚህ ላይ ሁሉም ሰው ሊገነዘበው የሚገባው የሰጥቶ መቀበል መርህ በጥብብ ሳይታጀል እና ሳይታሽ የሚደረግ ከሆነ የሚያደርሰው ኪሳራ ለመጪው ትውልድም የሚተርፍ ችግር ይዞ የሚመጣ መሆኑን ነው። ከሰጥቶ መቀበል ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ነገር ራስን መቻል (independant) የሚለውን አመለካከት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ሀገር ወይም ሰው ራሱን የቻለ ነው ( independant) ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን በወፍ በረር እንመልከት።

አንድ ሀገር ወይም ሰው ራሱን የቻለ ነው ( in­dependant) ነው ሲባል ፍጹም ምንም ከማንም ምንም ነገር አይፈልግም ፤ ሁሉንም ነገር ራሱ ሰርቶ ራሱ የሚያሟላ የሚመስለው አለ። ይህ ትክክል አይደለም። ራስን መቻል ማለት ABSOLUTE INDE­PENDENCY ማለት አይደለም። ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ እንኳን ህልውናዋን ለማስቀጠል በጣም ደሃ ከሚባሉት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሳይቀር በርካታ ድጋፍ ስትሻ ይታያል። የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለሀብቱ ቢልጌት የቱንም ያህል ሀብታም ቢሆን እንኳን ሁሉንም በራሱ ሰርቶ ይወጣዋል ማለት አይደለም። ለዚያም ነው በስሩ በርካታ ሠራተኞችን መቅጠሩ።

ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው አንድ ሀገር ወይም ግለሰብ ራሱን የቻለ (independant) ነው ሲባል absolute independat ማለት እንዳልሆነ እና ራሱን የቻለ ሰው ወይም ሀገር ራሱን የቻለ ቢሆንም የሚጎድለውን ነገር ለማሟላት ሰጥቶ መቀበል መርህ እንደሚጠቀም መገንዘብ ያስፈልጋል። ስለሆነም ማንም ግለሰብ ይሁን ቡድን እንዲሁም ሀገር ሁሉ ነገሩን በራሱ ማሟላት ስለማይችል በሰጥቶ መቀበል መርህ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ሀብቶችን ሲጋራ ይታያል።

ከዚህ ጋር አያይዘው ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል። ይህንን ተከትሎ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎች ጉዳዩን አጀንዳ አድርገውታል። ግማሹ በጥሩ ጎኑ ሲደግፍ ግማሹ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስቴሩን ሃሳብ ሲተች ይስተዋላል።

በተለይ ትችት ሲያቀርቡ የነበሩ ቡድኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩበትን አውድ በማጣመም አንድ ሉዓላዊ ሀገርን ሌላ ሉዓላዊ ሀገር ለመውርር ዝግጅት እያደረገች በማስመሰል የ21ኛውን ክፍለ ዘመን የማይመጥን ፕሮፓጋንዳ ሲያሰራጩ ይስተዋላል። ይህ ትክክል አይደለም። ትችት አቅራቢዎች ትክክል ያለመሆናቸውን ለማሳየት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ካቀረቧቸው ሃሳቦች የተወሰኑትን በወፍ በረር እንመልከት።

“የባሕር በር ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተገቢ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል።” የሚለው አንደኛው ነው። ሁለተኛው ሀገራችን በዙሪያዋ ለሚገኙ ሀገራት የውሃ ምንጭ መሆኗን እና በዚህም ወደ ኤርትራ እና ሱዳን ተከዜ፣ ወደ ግብፅ እና ሱዳን አባይ፣ ወደ ደቡብ ሱዳን ባሮ፣ ወደ ኬንያ ኦሞ፣ ወደ ሶማሊያ ደግሞ ገናሌ ዳዋ እና ዋቢ ሸበሌ ከኢትዮጵያ ተነስተው የሚሄዱ ወንዞች ስለመሆናቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪም ወደ ጂቡቲ የሚሄድ የውሃ መስመር በኢትዮጵያ ወጪ የተገነባ መሆኑን ነው። ይህ ተጨባጭ በሆነበት ሁኔታ የእናንተን እንካፈል የእኛን አትጠይቁ የሚሉ ጎረቤት ሀገር ካሉ ትክክል እንዳልሆኑ የጠቆሙበት ነው።

ሌላው ሶስተኛው ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተናገሩት ፤ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ካላቸው የታሪክ ቁርኝት በተጨማሪ ከሕዝብ አሰፋፈር አኳያ የባሕር በርን አስፈላጊነትን የተመለከተ ነበር። በዚህም በኤርትራና ጅቡቲ ያሉ የአፋር ብሔር እንዲሁም በሶማሊያ፣ በኬንያ እና በጅቡቲ የሚገኙ የሶማሌ ብሔር አባላት የውቅያኖስ ውሃን እንደሚያገኙ አንስተው “ኢትዮጵያ ያለው ሶማሊያ እና አፋር ምን በድሎ ነው? የባህር በር የሚከለከለው” ሲሉ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለመጠቀም ከምትፈልጋቸው የወደቦች አማራጮች መካከል በቀዳሚነት ያስቀመጡት ዘይላን ነው፤ ዘይላ ወደብ በሶማሌ ላንድ ግዛት በምዕራባዊ አውደል ግዛት ውስጥ የሚገኝ ነው ፣ የኤደን ባሕረ ሰላጤን መሠረት ያደረገ ነው። ይህም አሁን ላይ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ወረራ ልትፈጽም ነው በሚል በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚለውን አስተሳሰብ ውድቅ ያደርገዋል።

በ21ኛው ክፍለ ዘመን አንድን ሉዓላዊ ሀገር ሌላ ሀገር በወረራ ሊይዝ ነው ቢባል አስተሳሰቡ በራሱ ዘመኑን የማይመጥን ከመሆኑም ባለፈ ይህን የሚሉ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምስረታ ወቅት ከኃያላን ሀገራት ጋር ያደረገችውን እልህ አስጨራሽ የሙግት ታሪክ የማያውቁ ናቸው።

ነገሩ እንዲህ ነው፡- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚመሠረትበት ወቅት መሥራች የነበረችው ኢትዮጵያ በልጅ አክሊሉ ሐብተ ወልድ ተወክላ ነበር። ልጅ አክሊሉ ሐብተ ወልድን የወከለችው ኢትዮጵያም “አንድ ጠንካራ ሉዓላዊ ሀገር በኢኮኖሚ እና በሰው ሃይል ዝቅተኛ በሆነች ሌላ ሉዓላዊት ሀገር ላይ ወረራ ብትፈጽም ምን መደረግ አለበት ? የሚለው ቻርተር በመንግሥተታቱ ድርጅት እንደ ሕግ ሆኖ ሊካተት ይገባል” ስትል ጠየቀች።

ኃያላን ሀገራትም የኢትዮጵያን ጥያቄ ውድቅ ለማድረግ ተጋጋጡ። ነገር ግን ኢትዮጵያን የወከሉት ልጅ አክሊሉ ሐብተ ወልድ የሃያላኑን ሃሳብ አሸንፈው የጠየቁት ጥያቄ ብሎ የመላው የዓለም መዳኛ ሕግ ለመደረግ በቃ ። ይህ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያ ራሷ ያወጣችውን ሕግ ራሷ ትቃረናለች ብሎ ማሰብ ትክክል አይመስለኝም።

በመጨረሻም ከሰጥቶ መቀበል መርህ በተጨማሪ ለጋራ ጥቅም በጋራ መስራት (Common Good) የሚባለውን መርህ በግለሰብ ሆነ በሀገር ደረጃ መከተሉ አትራፊ ይመስለኛል። ከወደብ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ላነሳችው ጥያቄ ለጋራ ጥቅም በጋራ መስራት (Common Good) ሁነኛ መፍትሄ ይመስለኛል። ስለሆነም በታቀደው ልክ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት ከሰጥቶ መቀበል መርህ በተጨማሪ ለጋራ ጥቅም በጋራ መሥራት (Common Good) የሚባለውን መርህ ላይ ከፍተኛ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል ባይ ነኝ።

ሰላም!!!

 አሸብር ኃይሉ

 አዲስ ዘመን እሁድ ጥቅምት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You