የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የወላጆችና የአሳዳጊዎች ድርሻ ከፍ ያለነው

በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ውጤት ይፋ ከሆነ ቢሰነባብትም የፈተናውን ውጤት መሠረት በማድረግ የሚሰጡት የተለያዩ አስተያየቶችና መላምቶች ግን አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው። ገሚሱ ስለተማሪው ስንፍና፣ ሌላው ያስተማሪውን የአቅም ማነስ፣ የትምህርት ሥርዓቱ ችግር እንዳለበትም በመተቸት ሁሉም እያነሳ እየጣለ የመሰለውን ሀሳብ ይሰጣል። በዚህ መሐል አንድ የሀገራችን አባባል ትዝ አለኝ። ‹‹ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ሲያምር፣ ሲይዙት ያደናግር›› የሚለው። ሥራ መሥራቱ እንጂ አቀበት የሚሆነው፣ ሌላውን መተቸትማ ለአፍ አይዳግትም።

አንዳንዱ አስተያየት ሰጪማ ነገሩን ሁሉ የዓለም ፍጻሜ አድርጎ ነው የሚያወራው። በትምህርታቸው የወደቁ ተማሪዎች ሌላ ዕድልና አማራጭ የሌላቸው እስኪመስል ድረስ ነው ነገሩን እያጋነኑ የሚያወሩት። በእርግጥ በትምህርት ዘመኑ የተመዘገበው ውጤት አስደንጋጭ ነው። ካስፈተኑት ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንድም ያለፈ ተማሪ የሌለው ትምህርት ቤት መኖሩ ደግሞ የበለጠ ግራ ያጋባል።

በአንድ ወቅት ላይ ብዙ ተማሪ በማሳለፍ ስማቸው ከፍ ብሎ እንዲነገር ያደርጉ የነበሩ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው አይዘነጋም። ዛሬ በተገላቢጦሽ መሆኑ ጥያቄ ያስነሳል። እንደ ሐሜት ይነሱ የነበሩ ነገሮች እውነት ናቸው ብለን እንድንቀበል እያደረጉንም ጭምር ነው። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ለማሳለፍ የሚጠቀሙት ዘዴ እንዳላቸው በሐሜት ደረጃ ይነሳባቸው ነበር።

እንዲህ እንዲህ ያሉ ነገሮች መጥራት አለባቸው። በዝምታ ሊታለፍ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ችግሩን ከሥር መሠረቱ መፈተሽ ይገባል። እንደሀገር ቁጭት ውስጥ የሚከት ጉዳይ በመሆኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁሉንም ይመለከታል።

ለውድቀቱ ተማሪዎችን፣ መምህራንን፣ የትምህርት ቤቶችን የተሳሳተ አካሄድ፣ የትምህርት ሥርዓቱን ተጠያቂ አደረግን። የወላጅና የአሳዳጊስ ሚናስ? ለልጅ አስፈላጊ ነገሮችን አሟልቶ ትምህርት ቤት መላክ ብቻውን በቂ ነው? ራስንም መፈተሽ አይገባም ትላላችሁ?

ችግሩ የተወሰነ አካል ብቻ እንደሆነ አድርጎ መውሰድ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። መቼም ከአብራካችን የተገኙ ልጆችን ባናስተምርም፣ እህትና ወንድሞቻችን፣ የዘመድ ልጅም ያስተማርን እንኖራለን። የጎረቤቶቻችንንም ቢሆን ለመታዘብ እድሉ አለን። እንዴት ነው የየእለት የትምህርት ሁኔታቸውን የምንከታተለውና ልጆቹ ውጤታማ እንዲሆኑ የምናግዛቸው? እስኪ ሁላችንም ወደየቤታችን ተመልሰን እንቃኝ።

ተደጋግሞ እንደሚባለው ልጆች በትምህርታቸውም ሆነ በሥነምግባር መልካም የሆኑ ዜጎች ሆነው አድገው ሀገር እንዲረከቡ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ኮትኩቶ ማሳደግ ይገባል። ይሄን ለማለት ብቻ ሳይሆን፣ በተግባር ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል። ወላጆችም ሆኑ አሳዳጊዎች ከሥር ከደከሙ ልጆቹ መሠረት ይዘው ስለሚያድጉ ችግሮችን መቅረፍ ባይቻል እንኳን መቀነስ እንደሚቻል ነው ምክረ ሀሳብ የሚሰጠው።

ምክንያቱም ልጆቹ የሚገኙበት እድሜ ቁምነገር እንዲሠሩ የሚጠበቁበት አይደለም። ልጆቹ ባሉበት እድሜ የሚያስደስታቸው ጨዋታ ነው። ከጨዋታ የሚከለክላቸው፣ ጊዜያቸውን ለትምህርት እንዲያውሉ የሚገፋፋቸውን ለመቀበል ዝግጁ አይደሉም። ወደዚህ መሥመር ላለማምጣት ብዙ ሰበብ ያቀርባሉ። ታግሎና መሥመር ማስያዙ ፈታኝ በመሆኑ አብዛኛው ወላጅና አሳዳጊ ሲሰላች ይስተዋላል።

ግን ስንቶቻችን በትዕግሥት ልጆችን ወደ መሥመር ለማምጣት ጥረት እናደርጋለን ስንል ምክንያታዊ የሆነ መረጃ ለመሥጠት ጥናት የሚያስፈልግ ቢሆንም ከምንታዘበው በመነሳት ግን የሚደክሙት ጥቂቶች ናቸው። እነዚህ በልጆቻቸው ወይንም በሚያሳድጓቸው ልጆች ላይ የሚደክሙ ቤተሰቦች የየእለት የትምህርት ሁኔታቸውን ለመከታተል ደብተራቸውን ይፈትሻሉ። ስለውሎአቸውም ይጠይቃሉ።

ትምህርት ቤት በመሄድም ስለትምህርት አቀባበላቸውና ባሕሪያቸው ይጠይቃሉ። ምክርና ተግሳፅም ይሰጣሉ። ከቻሉም አስጠኚ በመቅጠር በትምህርታቸው የበለጠ እንዲተጉ ያግዟቸዋል። በዚህ መንገድ ጥቂት የማይባሉ የድካማቸውን ፍሬ ያፈሩና ለሌሎችም አርአያ የሆኑ ቤተሰቦች አሉ።

በተቃራኒው ደግሞ እንኳን በዚህ መንገድ ለመከታተል ልጆቹ ትምህርት ቤት ውለው ስለመምጣታቸው እንኳን የማያውቁ ወላጆችና አሳዳጊዎች መኖራቸውን ማንሳት ይቻላል። እዚህ ላይ እኔም የታዘብኩትን ለአብነት ላንሳላችሁ። በምኖርበት መንደር በተለያየ እድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ሲጫወቱ አያለሁ። እነዚህ ልጆች የተለያየ ቤተሰብ ነው ያላቸው። በወላጆች፣በአያቶች፣ በቅርብ ዘመድ የሚያድጉ እንደሆኑ በቆዬታዬ ለመገንዘብ ችያለሁ።

ታዲያ አብዛኞቹ ለልጆቻቸው የሚያደርጉት ክትትል ስታዘብ ልጆቹ የጨዋታና የጥናት ጊዜ እንዳልተሰጣቸው ነው። ከትምህርት ቤት መጥተው እስከ ምሽት በጨዋታ ነው የሚያሳልፉት። አንዳንዶችም ሰዓቱን ሳይሆን የምሽቱን ሁኔታ በማየት ነው ጠርተው ወደ ቤት የሚያስገቧቸው። እንዲህ ያለው ልማድም በአንዳንድ ቤተሰብ ላይ የተደጋገመ ሆኖ ነው የታዘብኩት።

በተለይም በትምህርት ቤት ውሎአቸው ላይ የሚያደርጉት ድጋፍም ሆነ ክትትል አናሳ እንደሆነ የታዘብኩት ደግሞ በጣም ቅርብ ከሆንኩት ጎረቤት ነው። በየዓመቱ ልጆቹ ከክፍል ወደ ክፍል ሲዘዋወሩ የሚያመጡት ውጤት አጥጋቢ አይደለም። ተንጠልጥለው ነው የሚያልፉት። ታች ላይ ባለው የትምህርት ሥርዓት ተማሪዎች ከክፍል ወደ ክፍል እንዲዘዋወሩ የሚፈቅድ በመሆኑ ወላጆችም ተማሪዎቹ የሚያመጡት ውጤት ላይ ሳይሆን አለመውደቃቸውን ነው የሚያዩት።

ይሄ ደግሞ ተማሪዎቹ በትምህርታቸው ከፍ እያሉ ሲሄዱ ትምህርቱ እየጠነከረና ከክፍል ወደ ክፍል ለመዘዋወርም እንደሚቸገሩ እንዳያስተውሉ አድርጓቸዋል። ልጆች ጨዋታ እንደሚወዱ ይታወቃል። ግን ለጨዋታና ለትምህርት ጊዜ እንዲሰጡ ማድረግ ደግሞ የወላጅ ኃላፊነት ነው። ግን ልጆች እስከ ምሽት በጨዋታ ሲያሳልፉና የየእለት የትምህርት ሁኔታቸውን በመከታተል መሠረት ማስያዝ ሲገባው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሲወጡ አይስተዋልም።

ትምህርት ቤቶች ስለተማሪዎቹ ሥነምግባርና የትምህርት ውጤታቸው ከወላጆች ጋር የሚመክሩበት መድረክ ያመቻቻሉ። ይሁን እንጂ የሚመቻቸውን መድረክ በአግባቡ ተጠቅመው ወደ ተግባር የሚለውጡ ወላጆችና አሳዳጊዎችም እንዲሁ ጥቂት እንደሆኑ ነው የታዘብኩት። ትምህርት ቤቶች ከወላጆች ጋር ምክክር የሚያደርጉበት ዓመታዊ መድረክ አላቸው።

እንደአስፈላጊነቱም በተናጠል ወላጆችን ጠርተው ያነጋግራሉ። ግን ምክክሩ ለውጥ ሲያመጣ አይስተዋልም። ከዓመት ዓመት ተመሳሳይ ከሆነ ምክክር መርሐ ግብርን ከማሟላት ያለፈ አይሆንም። በሚኖራቸው ውይይት ወቅትም ስለልጆቹ የሚነግሯቸውን መሠረት አድርገው ልጆቻቸውን ለማስተካከል ጥረት ከማድረግ ይልቅ በትምህርት ቤቱ አስቸጋሪ የሆኑ ልጆች ያደረጓቸውን መጥፎ ነገሮች መልሰው ሲያወሩ ነው የምሰማቸው።

የሚገርመው ደግሞ ሁሉም ስለሌላው ተማሪ ሥነ ምግባር መጓደል እንጂ ስለራሱ ልጅ አይደለም የሚያወራው። የእነርሱ ልጆች በባሕሪ ብልሹ ከሆኑ ልጆች ጋር እየተማሩ እንደሆኑ ይዘነጉታል። ይሄ ነገር ሲደጋገም አስተውላለሁ። ሀሳብም ለመስጠት ሞክሪያለሁ። ግን ሲሻሻል አላየሁም።

ዛሬ በትምህርት ውጤት ላይ እየታየ ያለው ድክመትና ደውል መሆኑ መዘንጋት የለበትም። እንደአጠቃላይ የሀገር ሸክም ነው ብንልም። ቤተሰብ የሚከፍለው ዋጋ ደግሞ ልጅ ሆኖ ካሳደገው በላይ ሊሆን እንደሚገባ መገንዘብ ይገባል። ከትምህርት በኋላ ወደሚቀጥለው የማይሸጋገር ልጅ ፍላጎቱ የተለያየ ስለሚሆን አደጋው የከፋ ነው። ስለዚህ ወላጆችም ሆኑ አሳዳጊዎች ቆም ብለው ማሰብ ይኖርባቸዋል። ከዚህ በኋላ ያለውን ለማትረፍ መረባረብ የሁሉም ድርሻ ይሆናል።

 ለምለም መንግሥቱ

 አዲስ ዘመን እሁድ ጥቅምት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You