ቡና ለሀገሪቱ፣ ለአርሶ አደሩ፣ በዘርፉ ለተሰማራው የንግዱ ማህበረሰብና በእሴት ሰንሰለት ውስጥ ለሚገኙ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ የላቀ ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ እንዳለው ይታወቃል:: ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ብዙ ሚሊዮኖች ህዝብ በእሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚንቀሳቀስበት መባሉም ይህንኑ ያመለክታል:: የሥራ ዕድል ከመፍጠር እንዲሁም ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር እንዲኖር ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ይታወቃል::
የቡና ሥራ ከዓለም የገበያ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው፤ የዓለም ገበያ ሲፈቅድ ሀገር ፣ በእጄ ሲል አርሶ አደሩ፣ ነጋዴው እና የመሳሰሉት አካላት በእጅጉ ተጠቃሚ ይሆናሉ ፤ የዚያኑ ያህልም ገበያው ሲቀዘቅዝ ይጎዳሉ:: የከፍታና ዝቅታ አጋጣሚዎቹ የበዙ ናቸው:: በዚህ ከፍታና ዝቅታ ውስጥ መኖር ቡና እንደመጠጣት ሁሉ ሱስ የሆነባቸው ጥቂት የሚባሉ አይደሉም::
የቡና ሥራ ሱስ ከሆነባቸው መካከል የዕለቱ እንግዳችን አንዱ ነው:: እንግዳችን የቡና ሥራን ከልብ በመነጨ ከፍተኛ ፍላጎትና ሱስ ውስጥ ሆኖ እንደሚሠራው ይናገራል:: ከአርሶ አደር ቤተሰብ የወጣ ቢሆንም፣ ቡና የሚያለማ ቤተሰብም ሆነ ቡና የሚነግድ የሚያውቀው የቅርብ ሰው አልነበረውም:: ይሁንና ትኩረቱን ጥራት ላይ በማድረግ ስፔሻሊቲ ቡናን አዘጋጅቶ ለውጭ ገበያ ያቀርባል:: የዛሬ ሶስት ዓመት አካባቢም በስፔሻሊቲ ወይም በባለ ልዩ ጣዕም ቡና ኢትዮጵያን ወክሎ አንደኛ ወጥቷል::
እንግዳችን አቶ ታምሩ ታደስ ይባላል፤ የሀሎ ቡና ላኪ ድርጅት መስራችና ባለቤት ነው:: ተወልዶ ያደገው በሲዳማ ክልል በንሳ ወረዳ ውስጥ ነው:: የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተወልዶ ባደገበት በንሳ ወረዳ ተከታትሎ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተምሯል:: ከመጀመሪያ ደረጃ አንስቶ በትምህርቱ ንቁና ታታሪ እንደነበረ የሚገልጸው አቶ ታምሩ፤ ለትምህርት ካለው ፍላጎትና አቅም የተነሳ ቡና ነጋዴ የመሆን ሃሳብ ጨርሶ አልነበረውም::
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጥሩ ቆይታ የነበረው አቶ ታምሩ፤ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ትምህርቱን በጥሩ ውጤት አጠናቅቆ እንደወጣ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ ለሁለት ዓመታት የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ሲያስተምር ቆይቷል:: ከሁለት ዓመት የማስተማር ሥራ በኋላም የማስተርስ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ አዲስ አበባ ያቀናው አቶ ታምሩ፣ እግረ መንገዱን የቡና ሥራን ከሚሠሩ ሰዎች ጋር በፈጠረው ተግባቦት ምክንያት ወደ ቡና ሥራ እየተሳበ ይሄዳል::
ከማስተርስ ትምህርቱ ጎን ለጎን ቡና ላኪ በሆነ አንድ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ መሥራት የጀመረው አቶ ታምሩ፤ ይህ ሥራ ወደ ቡና ሥራ እንዲገባ ምክንያት እንደሆነው ይገልጻል:: በድርጅቱ በሠራባቸው ስድስት ዓመታት ውስጥ ስለ ቡና ሥራ እንዲሁም አጠቃላይ በዘርፉ ያለውን የሥራ እንቅስቃሴ በተረዳበት ወቅት ለቡና ሥራ ያለው ፍላጎት እያደገ መሄዱን ያስታውሳል:: በመሆኑም ከቡና ጋር ያለውን ቁርኝት በዘላቂነት አስተሳስሮ ዛሬ ላይ ደርሷል::
በድርጅቱ የነበረው ቆይታ ከተጠናቀቀ በኋላ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ የነበረ ቢሆንም ውስጣዊ ፍላጎቱ ግን ወደ ቡና ያደላ ነበር:: ለዚህም ነው ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለ ቡና የተዘጋጁ ጽሁፎችን በማንበብ እንዲሁም ስለ ቡና ቅምሻ ትምህርት በመማር ጭምር ለቡናው ዘርፍ ይበልጥ እየቀረበ የሄደው:: ከቡና ሥራ እንዲሁም ከቢዝነስ ጋር ፍጹም ግንኙነት የሌለውን የኢንጂነሪንግ ትምህርት ወደ ጎን በመተው ሙሉ ለሙሉ ወደ ቡና ሥራ መግባት የሚችልበትን ዕድል እያሰፋ ፤ የቡና ሥራ ቡና እንደመጠጣት ሁሉ ሱስ እንደሆነበት ነው አቶ ታምሩ የሚናገረው::
የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን ለመከታተል በወጣበት በቡና ሥራ ውስጥ ገብቶ የቀረው አቶ ታምሩ፤ ‹‹ወደ ትምህርቴ መመለስ ያልቻልኩት የቡና ሥራ እንደ ሱስ ሆኖብኝ ነው::›› ይላል:: እሱ እንደሚለው፤ የቡና ሥራ በጣም ደስ የሚልና ከብዙ ሰዎች ጋር የሚያገናኝ ማህበራዊ ግንኙነትን የሚያጠናክር ነው:: ቡናን በጥራት ማምረትና ማዘጋጀት ከተቻለ እንዲሁም ከገዢ ሀገራት ጋር የሚኖረው ግንኙነት ፈጣንና ቀልጣፋ ከሆነ ቡና አዋጭ ሥራ ስለመሆኑም ይናገራል::
የቡና ሥራን ሲጀምር አንስቶ የባለ ልዩ ጣዕም ቡናን አዘጋጅቶ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንደሆነ የጠቀሰው አቶ ታምሩ፤ ወደ ቡና ሥራ ሲገባ በቀጥታ ያቀናው ወደ ትውልድ አካባቢው ነው:: ምክንያቱም አካባቢው ደጋማ በመሆኑ የሚመረተው ቡና ጥራት ያለውና ተመራጭ እንደሆነ ያውቅ ነበር:: በሲዳማ ክልል በንሳ ወረዳ ሃሎ ቀበሌ ላይ ቡናን የሚያዘጋጀው አቶ ታምሩ፤ የድርጅቱን መጠሪያም በዚሁ ቀበሌ ማድረጉን ይገልጻል::
የዛሬ ሶስት ዓመት አካባቢ በሲዳማ ክልል በንሳ ወረዳ ሃሎ ቀበሌ ላይ ቡና ማዘጋጀት የጀመረው ሲሆን፤ የኤክስፖርት ፈቃድ በማውጣት በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር አድርጓል:: በወቅቱ በጥራት ያዘጋጀውን የተወሰነ ኪሎ ቡና ለውድድር በመስጠት ለቡና ሥራው ሙሉ ጊዜውን፣ ዕውቀቱንና አቅሙን አሟጦ መጠቀም በመቻሉ ውጤታማ መሆን ችሏል:: በዚህም የመጀመሪያ ውድድር ያደረገው ሃሎ ቡና አንደኛ ወጥቷል::
ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ዓለም አቀፍ የሆነ ትልቅ የቡና ውድድር መሆኑን የጠቀሰው አቶ ታምሩ፤ ዓለም አቀፍ በሆነ ውድድር አንደኛ መውጣት ደግሞ ቀላል ነገር አለመሆኑን ነው የተናገረው:: በዚህ ውድድር ‹‹አንደኛ መውጣት ማለት ኢትዮጵያን መወከል ማለት ነው::›› ይላል::
እሱ እንደሚለው፤ ውድድሩን በአንደኝነት ማሸነፍ በመቻሉ ዓለም አቀፍ የቡና ገዢዎች ትኩረታቸውን ወደ እሱ አድርገዋል:: የተለያዩ ጥያቄዎችና በርካታ የስልክ ልውውጦችን እንዲሁም በኢሜል ለሚደረጉ ጥሪዎች ሁሉ ፈጣን ምላሽ በመስጠት በርካታ ግንኙነቶችን ፈጥሯል:: ገዢ ሀገራትም በሚሰጣቸው ፈጣን ምላሾች እምነት ያሳደሩበት መሆኑን እና አብረው ለመሥራት ያላቸው ፍላጎት በመጨመሩ ዕድለኛ እንዲሆን አድርጎታል::
ዓለም አቀፉ ቡና ገዢዎች ስለ ቡናው በቂ መረጃ የሚፈልጉ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ፕሮሰስ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸውም ነው ያመለከተው:: በዚህም በርካታ የውጭ ደንበኞችን ማፍራት እንደቻለ ይናገራል:: ይሁንና ትኩረቱ ጥራት ላይ በመሆኑ መጠነኛ ነገር ግን ከፍተኛ ጥራት ያለው ቡና እያዘጋጀ ደንበኛ ለሆኑ ገዢ ሀገራት እያቀረበ ይገኛል:: ‹‹ጥራት ከተጓደለ የሚፈጠረውን ችግር መቋቋም ከባድ ነው›› የሚለው አቶ ታምሩ፤ ጥራት ሳይጓደል ድርጅትን ማሳደግ እንደሚቻል ይገልጻል::
ሃሎ ቡና ወደ ውጭ ከሚልከው ቡና 60 በመቶ ያህሉን በራሱ ማዘጋጃ ጣቢያ አዘጋጅቶ እንደሚልክ፤ 40 በመቶ ያህሉን ደግሞ ራሳቸው አዘጋጅተው ከሚያቀርቡ ገበሬዎች እንደሚገዛ የጠቀሰው አቶ ታምሩ፤ የቡና ማዘጋጃ ጣቢያዎቹ በሲዳማ ክልል በንሳ፣ ቦና፣ ቡራ ወረዳዎችና በሌሎች አካባቢዎችም እንደሚገኙ ያብራራል:: በምዕራብ አርሲ ዞንም እንዲሁ ነንሰቦ ወረዳ ላይ ሁለት የስፔሻሊቲ ቡና ማዘጋጃ ጣቢያዎች አሉት:: በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ገበሬዎችም ቡናቸው ሲደርስ እሸቱን ለቅመው ያስረክቡታል:: ሃሎ ቡናም በዘመናዊ ማሽኖች ታግዞ እሸት ቡናውን በጥራት አዘጋጅቶ ስፔሻሊቲ ቡናን ለውጭ ገበያ ያቀርባል::
በሲዳማ ክልልና በምዕራብ አርሲ ዞን በድምሩ ስድስት አካባቢዎች ላይ የቡና ማዘጋጃ ጣቢያዎች ያሉት አቶ ታምሩ፤ ቡናውን በአካባቢው ከሚገኙና ከሁለት ሺ ከሚበልጡ ቡና አምራች ገበሬዎች እንደሚረከብ ተናግሯል:: ድርጅቱ ጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ መሆኑን ጠቅሶ፣ አርሶ አደሮቹ ጥራቱን የጠበቀ እሸት ቡና ማቅረብ እንዲችሉ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ እንደሚያግዛቸው አስረድቷል::
ድርጅቱ ለአርሶ አደሮቹ ከሚያደርጋቸው ድጋፎች መካከልም ቡናው ጥራቱ ተጠብቆ የተሻለ ተከፋይ መሆን እንዲችል እንዴት መልቀምና ማከማቸት እንዳለባቸው የሚሰጠው ሥልጠና አንዱ ነው፤ ችግኞችን ያቀርባል፤ አርሶ አደሩ ለድርጅቱ ባስረከበው የቡና መጠን ልክ ተሰልቶ ማበረታቻ ይሰጣል:: ይህም ማለት ለእያንዳንዱ አርሶ አደር ከቡናው ዋጋው በተጨማሪ በኪሎ ግራም ሶስት ብር በማሰብ ለአብነትም 1000 ኪሎ ግራም ያስረከበ አንድ አርሶ አደር 3000 ብር ያገኛል:: ገንዘቡን የሚሰጠውም በክረምት ወቅት እጅ በሚያጥራቸው ጊዜ ነው::
ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻርም በሲዳማ ክልል ሃሎ ቀበሌ ላይ ሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የህጻናት ማቆያ ትምህርት ቤት ሰርቶ ለማህበረሰቡ አስረክቧል:: ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ወረዳዎች ድጋፎችን አድርጓል:: በቀጣይም መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ በማስቀጠል በተለይም ማህበረሰብን የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶችን ለመሥራት ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የጠቀሰው አቶ ታምሩ፤ በተለይም ቡና ገዢ ደንበኞቹን አስተባብሮ ለመሥራት ያቀዳቸው ሥራዎች ስለመኖራቸው ጠቁሟል::
አቶ ታምሩ ቡና በማዘጋጀት ሥራ ውስጥ 31 ለሚደርሱ ሠራተኞች በቋሚነት የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ በጊዜያዊነት ደግሞ በሁሉም የቡና ማዘጋጃ ጣቢያዎች 500 ለሚደርሱ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል::
የሃሎ ቡና ላኪ ድርጅት ትልቁ ገበያ ቻይና እንደሆነ የጠቀሰው አቶ ታምሩ፤ ቀጥሎ ጃፓን፣ ታይዋን፣ ኮርያ፣ ዱባይና አሜሪካ ይገኙበታል:: ለሀገራቱ የሚቀርበው ቡና ጥራቱን የጠበቀ ስለመሆኑ ያነሳው አቶ ታምሩ፤ የገበያ ትስስራቸው ጠንካራ እንደሆነ ነው የጠቀሰው:: ሀል ጊዜ ለጥራት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የግድ በመሆኑ ከብዛት ይልቅ ጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑንም አመላክቷል::
የ2015 ዓ.ም የቡና ምርት አልቆ የ2016 ምርት በአሁኑ ወቅት መድረሱን አቶ ታምሩ ይገልጻል:: ባለፈው ዓመት የዓለም የቡና ዋጋ በተለያዩ ምክንያቶች ዝቅ ማለቱን አስታውሶ፣ ወቅቱ እጅግ ፈታኝ እንደነበርና አብዛኛው ቡና ላኪ ችግር ውስጥ የገባበት ጊዜ መሆኑን ነው ይጠቅሳል:: በመሆኑም በ2015 በጀት ዓመት ወደ ውጭ የተላከው ቡና ከታቀደው በታች እንደሆነና አሁንም ድረስ በተለያዩ መጋዘኖች ውስጥ ያለፈው ዓመት ቡና እንደሚኖር ተናግሯል:: ይሁንና ከዚህ ጋር በተያያዘ በርካታ ቡና ላኪዎች የገጠማቸውን አይነት ችግር ሃሎ ቡና አልገጠመውም፤ ለዚህም ምክንያቱ ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት በመቻሉ ነው ሲል አስረድቷል::
የቡና ሥራ ምንም እንኳን ባለፈው ዓመት ችግር የገጠመው ቢሆንም፣ ዘንድሮ ተስፋ ሰጪ የሆኑ ጅምሮች አሉ ያለው አቶ ታምሩ፣ በአሁኑ ወቅት ቡናው ለለቀማ መድረሱንና አያያዙም ጥሩ መሆኑን ገልጿል:: የዓለም የቡና ዋጋም የሚወድቅበት አጋጣሚ አለመኖሩን ጠቁሞ፣ የቡና ሥራ እንደ መጠጣቱ ሱስ የሚያስይዝ መሆኑንና የሚተው ሥራ እንዳይደለ አመልክቷል::
ኢትዮጵያ ለቡና ምርት ምቹና ተስማሚ ሁኔታዎች እንደሏት ጠቅሶ፣ ጥራት ያለው ቡና በማምረት 80 በመቶ ያህሉን የኢትዮጵያ ቡና ወደ ስፔሻሊቲ ማስገባት የሚቻልበት ዕድል ስለመኖሩም አቶ ታምሩ ይጠቁማል:: ስፔሻሊቲ ቡና በድርድር የሚሸጥ በመሆኑ የተሻለ ገቢ ያስገኛል:: ነገር ግን ስፔሻሊቲ የሚባለው በራሱ ምን እንደሆነና ምን ማሟላት እንዳለበት ለማወቅ ቀማሽ መሆን እንዲሁም ስለ ቡና መረዳትና ለገዢዎች አስረድቶ ገበያ ማግኘትን የሚጠይቅ ሥራ ነው ሲል ያብራራል:: ስለቡና ተረድቶና አስረድቶ ከገዢ ሀገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ፈጥሮ ገበያውን ሰብሮ መግባት ካልተቻለ ስፔሻሊቲ ቡና መያዝ ብቻውን ጥቅም እንደሌለውም አስታውቋል::
ያም ቢሆን ግን ቀስ በቀስ ወደ ስፔሻሊቲ ቡና መግባት አይቀሬ እንደሆነ የገለጸው አቶ ታምሩ፤ አሁን ላይ ቡና የሚሠራው አብዛኛው ሰው ስለ ቡና የሚያውቅ ሳይሆን እንደማንኛውም ሸቀጥ ለመሸጥ ብሎ የሚሠራ ነው ይላል:: ጥቂቶች ግን ስለቡና አውቀውና ተረድተው ትኩረት በመስጠት ከልብ በመነጨ ፍላጎት እንደሚሠሩ ተናግሮ፣ ይህም ለዘርፉ ውጤታማነት ወሳኝ መሆኑን ነው ያመለከተው:: ሁሉም ሰው ስለ ቡና አውቆና ተገንዝቦ ሊሠራ እንደሚገባ አስገንዝቧል::
ሃሎ ቡና በቀጣይ ዘመናዊ በሆነ መንገድ በራሱ እርሻ ላይ ቡና የማምረት ዕቅድ ያለው ሲሆን፤ ለዚህም በሃሎ ቀበሌ 20 ሄክታር መሬት እያዘጋጀ ይገኛል:: በዚሁ እርሻ ላይ ዘመናዊ በሆነ መንገድ ከምርቱ ጀምሮ ጥራቱን የጠበቀ ቡና በማምረት ስፔሻሊቲ ቡናን በስፋት ለማቅረብ ይሠራል:: ከዚህ በተጨማሪም በአካባቢው ለሚገኙ አርሶ አደሮች ሥልጠና በመስጠት ቡናን ዘመናዊ በሆነ መንገድ እንዲያመርቱና እንዲያዘጋጁ በማድረግ የጥራት ደረጃው እንዲጨምር የማድረግ ሥራ ይሠራል:: ድርጅቱ በእሴት መጨመር ዘርፍም እንዲሁ በትንሹ ቡናን ቆልቶና ፈጭቶ የሚያቀርብ ሲሆን፤ በካፌ ደረጃም እንዲሁ ወደ ሀገር ውስጥ ለሚመጡ ቱሪስቶች ባለ ልዩ ጣዕም ቡናን ለማቅረብ ዕቅድ ይዞ እየሠራ ይገኛል
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም