የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ቀን ጀምሮ የሕዝባችንን የመለወጥ ተስፋ እውን ለማድረግ በሀገሪቱ ሰላምና አንድነትን በማስፈን፣ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስትራቴጂክ ተግባራትን እያከናወነ ነው። በዚህም ተጨባጭ የሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያተረፉ ተስፋ ሰጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።
ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ ያለው ትልቅ ሕዝብ ለዘመናት በማይመጥናቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ሕይወት ለመኖር የተገደዱ ሕዝቦች ናቸው። ይህንን እውነታ ለመቀየርም በየዘመኑ ያደረጓቸው ጥረቶች ስትራቴጂክ መሆን ባለመቻላቸው ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ከዚህም የተነሳ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት፤ ለልማት የተነቃቃ አምራች የሰው ኃይል እና ከፍ ያለ የማደግ ፍላጎት እያላት እነዚህን አቅሞች አቀናጅታ ፤ ዘመኑን በሚዋጅ አስተሳሰብ ወደ ልማት መለወጥ ባለመቻሉዋ ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኋላቀርነትና በድህነት ተርታ በቀዳሚነት ከሚሰለፉ ሀገራት መካከል በዋነኛነት ተጠቃሽ ለመሆን ተገዳለች።
ለዚህም አጠቃላይ ለሆነው የመልማት መሻቷ ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ አቅም የሆነውን የዓባይን ግድብ በመገንባት፣ ትልቅ ሀገራዊ መነቃቃት መፍጠር ተችሏል። በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ የግድቡን ግንባታ በማፋጠንም መላው ሕዝባችን በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ለዘመናት ከኖረበት ቁዘማ ወጥቶ የይቻላል መንፈስ ማበልጸግ የሚችልበትን የታሪክ ትርክት መፍጠር ችሏል።
ይህ በዓባይ ወንዝ ላይ ትውልዱ የፈጠረው አዲስ ትርክት፣ በዚህ ትውልድ ሆነ በመጪዎቹ ትውልዶች ላይ ሊፈጥር ከሚችለው የይቻላል መንፈስ ባልተናነሰ ፣ እንደ ሀገር ያለንን የተፈጥሮ ሀብት ክልሎች የሀብቱ ተጋሪ ሀገራት/ሕዝቦች ጋር በፍትሀዊነት መጠቀም የሚያስችለንን መተማመን ሊያሳድግልን የሚችል ተጨባጭ ተሞክሮ ነው።
ወቅቱ እንደ ሀገር የማደግ መሻታችንን እውን ለማድረግ አማራጮችን ሁሉ እስከመጨረስ መጠቀምን የሚጠይቅ ነው። ለዚህ በይቻላል መንፈስ የተቃኘ/የተገራ አዲስ ስትራቴጂክ እይታ፤ ከቁዘማ ወጥተን ከአይቻልም ወደ ይቻላል የሚያሻግር ሀገራዊ የአእምሮ ውቅር መፍጠር ይጠበቅብናል። ይህ ደግሞ ዘመኑን የምንዋጅበት ትልቁ አቅማችን ነው።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለረጅም ዓመታት ከሀገራዊ አጀንዳነት ብዙ ርቆ በነበረው በቀይ ባህር/ የወደብ ጉዳይ ዙሪያ ለተወካዮች ምክር ቤት የሰጡት ማብራሪያ የዚህ እውነታ አንድ አካል ነው። በርግጥ እንደ ሀገር ለዘመናት አብሮን ያለውን የማደግ መሻት እውን ለማድረግ የወደብ ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር መሠረታዊ አጀንዳ መሆኑ የማይቀር ነው
በተለይም የኢትዮጵያውያን የማደግ መሻት በጋራ እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ፤ እንደ ሀገር የወደብ ጉዳይን አጀንዳ አድርገው ለመወያየት መነሳታቸው ፤ በዙሪያቸው ለሚገኙ የወደብ ባለቤት ሀገራት እንደ ስጋት ሳይሆን እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ ተደርጎ ሊወስድ፤ አብሮ የማደግ አማራጭ ተደርጎ ሊታሰብ የሚገባ ነው።
የወደብ ጉዳይ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ኢትዮጵያ ን ከኤርትራ እና ከጂቡቲ ጋር ወደ ግጭት የሚወስድ ሳይሆን፤ ከነዚህ ሀገራት ጋር ያለንን የቀደመ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ፤ የሕዝቦቻቸውን የጋራ ተጠቃሚነትና፤ የጋራ እጣ ፈንታ ብሩህ ማድረግ የሚያስችል ትልቅ ስትራቴጂክ እይታ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም