ኢራን በአንድ ወገን፤ የባሕረ ሰላጤው አገራትና አሜሪካ ደግሞ በሌላ ወገን ሆነው የገቡበት አዲስ ፖለቲካዊ ፍጥጫ ወትሮውንም ቢሆን ሰላም ለራቀው የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ተጨማሪ ስጋት ሆኗል። ከባሕረ ሰላጤው አገራት መካከል በተለይ ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በየመን እየተካሄደ ባለው የእርስ በእርስ ጦርነት በተጨማሪ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከኢራን ጋር ያላቸው ልዩነት የከረረ ነው።
ባለፈው ሳምንት በሁለት የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ጣቢያዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ አዲስና የጋለ ውዝግብ ውስጥ የገቡት አገራቱ፤ ጦርነት ቀስቃሽ የሆነ ዛቻ እየተመላለሱ ነው። በነዳጅ ጣቢያዎቹ ላይ የተፈፀሙትን ጥቃቶች ኢራን የምትደግፋቸውና በየመን የእርስ በእርስ ጦርነት ከሳዑዲ አረቢያና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር በተቃራኒ ተሰልፈው የሚዋጉት የሐውቲ (Houthi) ታጣቂዎች ፈፅመናቸዋል ብለው ኃላፊነት ወስደዋል። ሳዑዲ አረቢያ ግን በነዳጅ ጣቢያዎቼ ላይ ለተፈፀሙት ጥቃቶች ከኢራን ራስ አልወርድም ብላለች።
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ አደል አል-ጁቤር፤ አገራቸው ወደ ጦርነት መግባት እንዳማትፈልግና ወደ ጦርነት ለመግባት ከተገደደች ግን ጥቅሟን ለማስጠበቅና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር በሙሉ ኃይልና በቆራጥነት ርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቀዋል። “በቀጣይ ሰላም እንዲሰፍን ትልቅ ፍላጎት አለን። ኢራን ጥቃት ከሰነዘረችብን ግን እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም። ኳሷ በኢራን ሜዳ ላይ ናት፤ መፃኢ እድል ፈንታዋን የመወሰን መብቷም በእጇ ላይ ነው፤” ብለዋል።
ኢራን በበኩሏ በነዳጅ ጣቢያዎቹ ላይ በተፈፀሙት ጥቃቶች እጇ እንደሌለበትና ወደ ጦርነትም መግባት እንደማትፈልግ በአንድ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣኗ በኩል አሳውቃለች። ባለስልጣኑ በአንድ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ላይ በታተመ አስተያየታቸው “ኢራን ጦርነትን እንደ አማራጭ የማየት ፍላጎት የላትም” ብለዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ወቅታዊው ሁኔታ የባሕረ ሰላጤው አገራት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኅብረታቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያስገድድ እንደሆነ ገልጿል። የኤምሬቶቹ መንግሥት በሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ጣቢያዎች ላይ ለተፈፀሙት ጥቃቶች እስካሁን ማንንም ተጠያቂ አላደረገም።
የአሜሪካ ባሕር ኃይል በበኩሉ፤ የባሕረ ሰላጤው አገራት የባሕር ኃይሎችና የወደብ ጥበቃ ዘብ አባላት ከአሜሪካ ባሕር ኃይል አባላት ጋር በትብብር እየሰሩ እንደሆነ አስታውቋል። የአሜሪካ ባለስልጣናት ጥቃቶቹ የተፈጸሙት አንድም በሐውቲ ታጣቂዎች፤ አሊያም ደግሞ ኢራቅ ውስጥ በመሸጉ የሺኣ ታጣቂ ቡድኖች ሊሆን እንደሚችልና ጥቃቶቹ እንዲፈፅሙ ያበረታታቻቸው ግን ኢራን እንደሆነች ያምናሉ።
የሳዑዲ አረቢው ንጉሥ ሳልማን ቢን- አብዱልአዚዝ አል-ሳዑዲ በጉዳዩ ላይ ለመምከር የባህረ ሰላጤውን ጨምሮ የአረብ አገራት መሪዎችን በአስቸኳይ ወደ መካ ጋብዘዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ጃቫድ ዛሪፍ በበኩላቸው “ኢራን ጦርነት አትፈልግም፤ ነገር ግን አትፈራም” በማለት አገራቸው ከአሜሪካና ከባሕረ ሰላጤው አገራት እየተሰነዘረባት ላለው ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሰጥተዋል። ይህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሃሳብ በአብዮታዊ ዘቡ (Revolutionary Guard) ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል ሐሰን ሳላሚም ተደግሟል። “ጦርነት ምርጫችን ባይሆንም አንፈራውም” የሚለው የኃላፊው ንግግር “ታስኒም” (Tasnim) በተባለው የዜና አገልግሎት ላይ ተጠቅሷል።
የሳዑዲ አረቢያው አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን በቀጣናው ባለው ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ዙሪያ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዎ ጋር በስልክ ስለመወያየታቸው የአገሪቱ መንግሥት አስታውቋል።
“ኤግዞን ሞቢል” (Exxon Mobil) የተባለው ግዙፍ የአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያ ኢራቅ ውስጥ በሚገኝ የነዳጅ ማውጫ ላይ የሚሰሩ የውጭ አገራት ሰራተኞቹን አስወጥቷል። ባህሬን ደግሞ ዜጎቿ ወደ ኢራንና ኢራቅ እንዳይጓዙ አስጠንቅቃለች። ወደ አገራቱ የሄዱትም እንዲመለሱ ትዕዛዝ ሰጥታለች። የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር በበኩሉ፤ በባሕረ ሰላጤው የአየር ክልል አቋርጠው የሚያልፉ የአሜሪካ አውሮፕላኖች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ እስላማዊቷን ሪፐብሊክ አጥብቀው በመኮነን የሚታወቁት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ኢራን ጦርነትን ከፈለገች መጥፊያዋን እንደመረጠች ትቁጠረው” የሚል የኢራንን ባለስልጣናት ክፉኛ ያበሳጨ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ከተናገሩ ከጥቂት ቀናት በኋላ ባሰሙት ማስጠንቀቂያ “ኢራን የአሜሪካን ጥቅሞች የምትጋፋ ከሆነ ሙሉ በሙሉ የሚያወድም ቅጣት ይጠብቃታል” በማለት ዝተዋል።
ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “ኢራን ጦርነት ለመግጠም ፍላጎት ካላት፤ መጨረሻዋ ይሆናል። ከአሜሪካ ጋር መፋጠጥ አደገኛ አካሄድ ስለሆነ አያዋጣም፤” ብለዋል። ባለፈው ሳምንት በሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ጣቢያዎች ላይ እንዲሁም በኢራቅ የአሜሪካ ኤምባሲን ጨምሮ የበርካታ አገራት ኤምባሲዎችና ጉዳይ ማስፈጸሚያ ጽሕፈት ቤቶች በሚገኙበት የባግዳድ አረንጓዴ ቀጣና ላይ የተፈፀሙት የሮኬት ጥቃቶች አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን ጥቅሞች የሚፃረሩ ናቸው ብለው ክፉኛ የተበሳጩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ ኢራንን በከባድ ኃይለ ቃላት አስጠንቅዋል።
ከዚህ በተጨማሪም፤ የአሜሪካ መንግሥት ባግዳድ በሚገኘው የአገሪቱ ኤምባሲና በሰሜናዊ ኢራቅ፤ ኧርቢል ባለው ቆንስላ ውስጥ ከሚሰሩ ሰራተኞች መካከል እጅግ አጣዳፊና አስፈላጊ በሚባሉ ተግባራት ላይ ያልተሰማሩት ወደ አሜሪካ እንዲመለሱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። በኢራን የሚደገፉና ኢራቅ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች በአሜሪካ ጥቅም ላይ የደቀኑት አደጋ ስለመኖሩም ዋሽንግተን ይፋ አድርጋለች።
የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር በኢራን ላይ ግልፅ የሆነ አቋም አለው ለማለት እንደሚያስቸግር ብዙዎች ይስማማሉ። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ከተናገሩ ከጥቂት ቀናት በኋላ አስፈሪ የሆነና የጦርነት አዋጅ የሚመስል ማስጠንቀቂያ ወደ ቴህራን ይልካሉ። የፕሬዚዳንቱ ካቢኔ አባላትም በኢራን ላይ የተለያየ አቋም እንዳላቸው ይነገራል።
“ጦርነት ናፋቂ ናቸው” ተብለው በተደጋጋሚ የሚወቀሱትና ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር መስማማት አቅቷቸው “ከትራምፕ ጋር መስራት ይብቃኝ” ብለው የለቀቁትን ሌተናል ጀኔራል ኸርበርት ሬይሞንድ ማክማስተርን ተክተው የፕሬዚዳንቱ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሆነው እየሰሩ ያሉት ጆን ሮበርት ቦልተን፤ በኢራን ላይ የማያወላውል አቋም አላቸው።
ቦልተን ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን የምታደርገውን ሙከራ ለማስቆም እስራኤል የኢራንን ወታደራዊ መሳሪያዎች እንድታወድም ሲገፋፉ ኖረዋል። ባለፈው ዓመት በኢራን ከተሞች ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ሲደረጉ “የኢራን ተቃዋሚዎች የውጭ መንግሥታትን ድጋፍ ከፈለጉና ለመቀበል ዝግጁ ከሆኑ አሜሪካ ድጋፍ ማድረግ አለባት” ብለው ነበር። በአጭሩ ቦልተን “ለኢራን የተሻለው አማራጭ ስምምነት ሳይሆን ወታደራዊ እርምጃ ነው” የሚል አቋም አላቸው። ይሁን እንጂ፤ ይህን ዓይነቱን አካሄድ የማይደግፉ ሌሎች የትራምፕ ባለስልጣናትም አሉ።
ዶናልድ ትራምፕ ወደ ነጩ ቤት ከመጡ ወዲህ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ጨምሮ በኢራን ላይ የተለያዩ ርምጃዎችን ወስደዋል። ለአብነት ያህል፤ አገራትና ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከኢራን ነዳጅ እንዳይገዙ አስጠንቅቀዋል። አሜሪካንን ከ2015ቱ የኢራን የኑክሌር ስምምነት (Iran Nuclear Deal) አስወጥተዋታል። የኢራንን አብዮታዊ ዘብ በአሸባሪዎች መዝገብ አስፍረውታል። ከባድ የጦር መሳሪዎችን ኢራን ወደምትገኝበት ቀጣና ልከው አሰማርተዋል።
ሳዑዲ አረቢያና ኢራን በቀጣናው ተፅዕኖ ለመፍጠር ይፎካከራሉ። ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙ ወዲህ ደግሞ ለወትሮውም ቢሆን በድርበቡ የነበረው የአሜሪካና የኢራን ግንኙነት ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል። ይህ የአገራቱ ውዝግብም በመካከለኛው ምስራቅ ብቻ ሳይወሰን ለመላው ዓለም ሰላም የስጋት ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2011
አንተነህ ቸሬ