የ80 ዓመት የእድሜ ባለጸጋዋ ወይዘሮ ዓይናለም ደሳለኝ በብዙ የሕይወት ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፈዋል። በባለቤታቸው፣ በልጆቻቸው እንዲሁም በእናትና አባት ሞት ብዙ መጎዳታቸውን ይገልፃሉ።
“በልጅነት ካገኘኋቸው ሁለት ወንድ ልጆቼ ጋር ረሃብ ሲገርፈኝ የማበላቸው ሳጣ፤ አቅም ባለኝ ጊዜም ሰው ቤት እንጀራ እየጋገርኩ፣ ልብስ እያጠብኩ እየሠራሁ ማታ ያገኘኋትን አጎርሻቸዋለሁ።›› ሲሉ ያን የመከራ ዘመን የሚያስታወሱት ወይዘሮ አይናለም፤ ያለ አባት ያሳደጓቸው ልጆቻቸው አድገው ሰው ይሆናሉ ሲሉ በሞት መነጠቃቸውን ይገልጻሉ፡፡ በዚሀ ሁሉ ተደራራቢ ኀዘን መጎዳታቸውን ጠቅሰው፣ ይህ ፈተናና አደጋ ለኀዘንና ብስጭት ብቻ ዳርጎ አልተዋቸውም፡፡ ተስፋ አስቆርጦ ጎዳና እስከመውጣት አድርሷቸዋል፡፡
በዚህ ሁሉ ማጥ ውስጥ ያለፉት ወይዘሮ አይናለም የሰንሻይን ፊላንትሮፊ የአረጋውያን መጠለያ እና መጦሪያ ማዕከል ስቦ እንዳወጣቸው ይናገራሉ፡፡ “ፈጣሪም በቃሸ ብሎኝ አሁን እዚህ ገብቼ ሌሊት እና ቀን ዓለም እያየሁ ነው። ስታመም ህከምና እያገኘሁ ምንም ሳይጎልብኝ እየኖርኩ ነው” ሲሉም ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ናቸው።
ማዕከሉ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመረቀ ሲሆን፣ የተገነባውም በሰንሻይን ፊላንትሮፊ የአረጋውያን ፋውንዴሽን መስራችና ፕሬዚዳንት የክብር ዶክተር ሳሙኤል ታፈሰ ነው፡፡ ከከተማ አስተዳደሩ በሰሚት ኮንደሚኒየም አካባቢ በተሰጠው 30 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ከ634 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባው ይህ የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከል በቅርቡ ነው ሥራ የጀመረው።
ወይዘሮ አይናለም አሁን በማእከሉ ችግራቸው ተፈትቷል፤ ስለሚበሉት፣ ጎናቸውን ስለሚያሳርፉበት ማሰብ አቁመዋል፡፡ ለህመማቸውም ህክምና እያገኙ በደስታ መኖር ጀምረዋል፡፡ የማእከሉ አገልግሎት የቀደሙትን ችግሮቻቸውን ሁሉ ረስተው በደስታ እንዲኖሩ እያረጋቸው መሆኑን ወይዘሮ አይናለም ይናገራሉ።
ከፈጣሪ በመቀጠል ይሄንን የመሰለ የአረጋውያን መጦሪያ አሳምረው ሠርተው ለአገልግሎት ላበቁትና እነሱን አሰባስበው ወደ ማእከሉ ላስገቡት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። አንድ ቤት የሚቆመው ምሰሶ ሲኖረው ነው ያሉት ወይዘሮ አይናለም፣ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በመረዳዳት እና በመደጋገፍ መኖር እንደሚገባቸውም ነው የመከሩት።
የኮልፌ አካባቢ ነዋሪ የነበሩትና በወትድርና ለበርካታ ዓመታት ማገልገላቸውን የገለጹት አስር አለቃ አሰፋ በየነ የማእከሉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ አስር አለቃ አሰፋ በአዛውንት እድሜያቸው ብዙ ፈተናዎችን አሳልፈዋል፤ የሰው እጅ አይተዋል፡፡
በ19 ዓመታቸው ነበር የውትድርናውን ሕይወት የተቀላቀሉት፡፡ ኤርትራ ውስጥ ለ15 ዓመታት በውትድርና አገልግለዋል። ከአራት ጊዜ በላይ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው የሚናገሩት አስር አለቃ አሰፋ፣ በ1981 ዓ.ም ከረን ላይ ከቆሰሉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ መደረጉን ይገልጻሉ። በ1982 ዓ.ም በ85 ብር “ቦርድ ወጣሁ” የሚሉት አስር አለቃ አሰፋ፣ በአዲስ አበባ ለጋብቻ ዝግጅት ላይ እያሉ በ“ዳግም ዘማች አባት ጦር” ጥሪ ተደርጎላቸው በጉደር ጥይት ፋብሪካ በቃኚነት እንደገና ሥራ መጀመራቸውን ያስታውሳሉ።
በ1983 ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ በወቅቱ ሠራዊቱ ሲበተን ጡረታቸውን ለማስከበር ብዙ እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡ ጉዳዩ እስከፈጸም በሚል በአናጢነት ሲሰሩ ቆይተው የ85 ብር ጡረታ ተከፋይ ይሆናሉ፡፡ ሀገር ሰላም ነው ብለው ሶስት ልጆቻቸውንም ሰብስበው መኖር ይጀምራሉ፡፡
አሁንም የቀድሞ ሠራዊት በሚል ማሳደድ የደረሰባቸው እኚህ የሀገር ባለውለታ፣ “የደርግ አባል ነህ” መባላቸውን ይናገራሉ፤ እሳቸው ደግሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ነኝ የሚል ምላሽ ይሰጣሉ። ቀጣይ እጣ ፈንታቸው በእስር ጦላይ መወሰድ ሆነ። በዚያም ምርመራ ሲደረግላቸው ምንም የተመዘገበ ወንጀል ስላልተገኘባቸው ይለቀቃሉ።
በተደጋጋሚ ጊዜ የደርግ አባል በሚል ያለምንም ምርመራ ታስረው እንደነበር የሚያስታወሱት አስር አለቃ አሰፋ፣ በደረሰባቸው እንግልት ተስፋ በመቁረጥ ገጠር ገብተው ከብት ጠባቂ ሆኑ። ያም አልሆን ሲላቸው አዲስ አበባ የተመለሱት አስር አለቃ አሰፋ፣ በየቤተከርስቲያኑ ደጅ በመቆም እስከመለመን ደርሰዋል፡፡ ቃሊቲ መናኸሪያ አካባቢ ባለው አረጋውያን መጠለያ ለዘጠኝ ዓመታት ኖረዋል።
‹‹ወደዚህ ዓለም ወደ ሆነው የአረጋውያን መጠለያ በመግባቴ ደስታዬ የላቀ ነው›› የሚሉት እኚህ የሀገር ባለውለታ፣ በማእከሉ አገልግሎት በእጅጉ መርካታቸውን ይገልጻሉ፡፡ አግልግሎቱን ሲያስቡት “ይቺ ሀገር አለች ወይ›› በማለት ራሳቸውን እንዲጠይቁ እያረጋቸው መሆኑን ነው በአድናቆት የሚናገሩት፡፡
“ጠይቆን፣ ተንከባክቦን፣ በምግብም፣ በመኝታም ይሄንን የመሰለ ምቾት በእድሜዬ አላየሁም” ሲሉም የድርጅቱን መስራች አመስግነው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት መበተኑ የብዙዎችን ሞራል ክፉኛ መጉዳቱን ተናግረዋል፡፡ እሳቸውም የዚህ ሰለባ መሆናቸውን ገልጸው፣ መንግሥት ከዚህ በመማር እያደረገ ያለውን መሻሻል አድንቀዋል። በሀገራችን ሰላም ጉዳይ ላይ መንግሥት ጠንክሮ ሊሠራበት ይገባል ብለዋል፡፡
ማእከሉ በተመረቀበት ወቅት እንደተገለጸው፤ ማእከሉ 750 አረጋውያንን የመቀበል አቅም አለው፡፡ የራሱ ክሊኒክ፣ የመድሃኒት መደብር፣ የመጻህፍት ቤት፣ ላውንደሪ፣ መመገቢያ አደራሽና መዝናኛ ክበቦችም አሉት፡፡ በአጠቃላይ ለአረጋውያን ምቹ ተደርጎ የተገነባ ነው፡፡
የማዕከሉ ጊቢ አረንጓዴ እና ለእይታ ማራኪ መናፈሻ ቦታዎች በስፋት ያሉት ይህ ማእከል፣ ለአረጋውያኑም የጤና፣ የምግብ የአልባሳት እንዲሁም የተለያዩ የዕደ ጥበባት ማዕከሎች የተሟሉለት ነው።
የሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳምሶን ተስፋዬ እንደገለጹት፤ ፕሮግራሙ ዘለቄታዊነት እንዲኖረውም የተገነባው ተጨማሪ ባለሁለት ወለል የገበያ ማዕከል ህንጻ የኪራይ ገቢ ለ750 አረጋውያን የምግብ፣ የጤና፣ የንጽህና እና ሌሎች ግበዓቶችን ማሟላት ያስችላል። ከፍተኛ የወንድ አረጋውያን ወደጎዳና የሚወጡ መሆኑ በጥናት በመለየቱም 500 ወንዶች እና 250 ሴት አረጋውያንን ይይዛል። የአረጋውያን ማዕከሉ ዝቅተኛ ወርሃዊ ወጪ አራት ሚሊዮን ብር ያህል መሆኑንም አቶ ሳምሶን ጠቁመዋል።
አረጋውያኑም ኮሚቴ አቋቁመው እርስበርሳቸው የሚደጋገፉበት እና የሚመካከሩበት ሁኔታ የተመቻቸ ሲሆን፣ ቀለል ያሉ የሻማ፣ የጧፍ፣ የነጠላ፣ የጋቢ፣ ሥራዎችንም ሠርተው ገቢ የሚያገኙባቸው ማዕከላት ተዘጋጅተዋል።
ፕሮጀክቱን በጋራ የሚደግፉ ባለድርሻ አካላትም ከአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ህፃናት እና አረጋውያን ቢሮ ጋር በመፈራረም ጧሪ ደጋፊ የሌላቸውን አረጋውያን እየመለመሉ በጋራ እየሠሩ ናቸው። እክል ሲያጋጥም በማዕከሉ በተደራጀ አንደኛ ደረጃ የህክምና ማዕከል የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና እንዲያገኙ ይደረጋል። በማዕከሉ መደገፍ የማይችሉም ከወረዳው ጤና ቢሮ ጋር ትስስር ይደረጋል። የከፋ ከሆነም ከየካቲት 12 ሆስፒታል ጋር በመተደረገ ትስሰር መሠረት ክትትል እንደሚደረግላቸው ዋና ሥራ አስኪያጁ አመላክተዋል።
አረጋውያንን የሚጦሩ፣ ህፃናት ልጆችን የሚደግፉ፣ በርካታ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ቢኖሩም፣ ቀጣይነት ያለው ድጋፍን ለማከናወን ቋሚ ገቢ ማግኘት ላይ ይቸገራሉ ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ ከገበያ ማዕከሉ የሚገኘው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የኪራይ ገቢ ተሰብስቦ በቀጥታ ለአረጋውያን መጦሪያ ማዕከሉ መተዳደሪያ እንደሚውልም አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአረጋውያን መጦሪያ እና መንከባከቢያ የሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውንዴሽን ፕሮግራም ኦፊሰር እና ካውንስለር ወይዘሮ ፈቃደነሸ ዳንኤል በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት 54 ወንዶች እና 17 ሴቶች በጠቅላላው 71 ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያንን ተቀብሎ ከጳጉሜ አንድ 2016 ጀምሮ አገልግሎቱን እየተሰጠ ይገኛል።
ማዕከሉ የህከምና፣ የምግብ፣ መጠለያ እና አልባሳት እንዲሁም የሥነልቦና ድጋፍ ይደረግላቸዋል ያሉት ወይዘሮ ፈቃደነሽ፣ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ወጪውን የሰንሻይን ኮንስትራክሸን እየሸፈነ ሲሆን፣ በቀጣይ ግን በማዕከሉ የተገነባው ሞል ተከራይቶ የሚገኘው ገቢ ሙሉ በሙሉ ለማዕከሉ መተዳደሪያ እንደሚውል ገልጸዋል። በማዕከሉ የሚሰሩ ለ150 ሠራተኞችም ቋሚ የሥራ ዕድልም ተፈጠሮላቸዋል ብለዋል።
ማእከሉን የመረቁት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ ማዕከሉ አረጋውያን ጉልበት ባላቸው እና በጉበዝና ዘመናቸው ሃላፊነትን ተወጥተው ትውልድን ቀርፀው ሀገርን ያገለገሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በመጨረሻው እድሜያቸው የተጣሉ እና የወደቁ እንዳይሆኑ፣ ለምድራቸው በረከትን ትተው እንዲሄዱና እንዳይማረሩ የሚያደርጉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ይህ ማዕከልም በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል እና አረጋውያኑ ሥራ ጭምር እንዲሠሩ የሚያሰችላቸው በርካታ ለአገልግሎት ምቹ የሆኑ መሠረተ ልማቶች የተገነቡለት መሆኑንም አስታውቀዋል። መንግሥት ብቻ ሰርቶ የዜጎችን ጥያቄ መመለሰ፣ የዜጎችን ጫና መቀነስ ሕይወትን መመለስ እንደማይቻል በመረዳት በልብ ቀናነት የሚከናወኑ መሰል የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች በመዲናዋ ባህል እየሆኑ መምጣታቸውንም ከንቲባዋ ተናግረዋል። የከተማዋ ባለሀብቶች ቢዝነስ ሠርተው ማትረፍ ብቻ ሳይሆን ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን ሰርተው የዜጎችን የኑሮ ጫና እንዲያቃልሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተገቢ መሆኑን አመላከተዋል።
የማእከሉ መስራች አቶ ሳሙኤል ታፈሰ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ባለቤት ናቸው፡፡ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አነስተኛ የገቢ ምንጭ ካለው ቤተሰብ የተገኙ መሆናቸውን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። የስምንተኛ ክፍል ተማሪ በነበሩበት ወቅትም የትምህርት ቤት ክፍያ ለመክፈል ተቸግረው እንደነበር መረጃው አስታውሶ፣ ይህን ችግር ለማሸነፍ ለስላሳ በመሸጥ እና ሌሎች ሥራዎችን በመሥራት ራሳቸውን ያስተማሩ መሆናቸውን ጠቁማል።
አቶ ሳሙኤል የትምህርት ቁጭታቸውን ለመወጣት በገቢ እጥረት ሳቢያ ወደ ትምህርት ቤት ሳይሄዱ የሚቀሩ ተማሪዎችን ለማገዝ ከራሳቸው ተሞክሮ በመውሰድ ትምህርት ቤቶችን ከፍተው ተማሪዎችን እየረዱ ይገኛሉ። በዚህም ሀገራዊ የበጎ ሥራዎችንና እና ማህበራዊ ኃላፊነቶቹን ለመወጣትም የትምህርት እድል ማግኘት በሚገባቸው እድሜ ጎዳና ወጥተው የሊስትሮ፣ የናብኪን ሽያጭ እና መሰል ሥራዎችን እየሠሩ የሚገኙ ልጆችን በመሰብሰብ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የትምህርት እድል እንዲያገኙ አድርገዋል።
በመሆኑም በትግራይ አክሱም፣ በኦሮሚያ ነቀምት፣ በደቡበ አገና እንዲሁም በአማራ ደብረብርሃን ከተማ ላይ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት፣ የተማሪዎችን ሙሉ ወጪ በመሸፈን እና የኪስ ገንዘብ 250 ብር በመክፈል በርካታ ተማሪዎችን ላለፉት 12 ዓመታት እየደገፉ ይገኛል። አቶ ሳሙኤል የትምህርት ቤቶቹን መተዳደሪያ ወጪ በቋሚነት ለማግኘትም ፊላሚንጎ አካባቢ ያለውን ባለ 12 ወለል ህንጻ በማከራየት ትምህርት ቤቶቹ እንዲተዳደሩበት አድርገዋል።
አሁን ለአረጋውያን የቋቋመው ማእክል የአቶ ሳሙኤል ማህበራዊ ሃላፊነትን የመወጣት ሁለተኛው ምእራፍ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በዚህ ምዕራፍ የማህበራዊ ሃላፊነት ሥራቸውን ለሀገራቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ፣ ወገን ሲረዱ ሀኪም ሆነው ያገለገሉ እና በማምሻ እድሜያቸው ላይ የሚጦራቸውና የሚደግፋቸውን ያጡ እና ቤተክርስቲያን እና መስጊድ አካባቢ ድጋፍ በመጠየቅ ሕይወታቸውን ሲመሩ የነበሩ አረጋውያንን መርዳት እና መደገፍ ሥራውን ጀምሯል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2016