የሽግግር ፍትሕ ወደ ሰላምና ልማት ለሚደረገውጉዞ ትልቅ አቅም ነው !

የሀገራችንን ታሪክ መለስ ብሎ ላጤነው የውስጥ አለመግባባት፤ ግጭትና ጦርነት የበዛበት ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን በጋራ ታሪኮቻችን ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ አለመድረሳችን እንደ ሀገር በማያባራ የግጭትና የጦርነት አዙሪት ውስጥ ለመግባት ተገደናል። በዚህም በየወቅቱ ለበርካታ ሰብዓዊ ጉዳትና ቁሳዊ ኪሳራ ተዳርገናል።


በየወቅቱ በተካሄዱ ግጭቶችና ጦርነቶች ምክንያት ከፍ ላሉ ሰብዓዊ ጉዳትና ቁሳዊ ወድመቶች ከመጋለጣችንም ባለፈ፤ ለከፋ ድህነትና ኋላቀርነትም ተዳርገናል። በዚህም በብዙ መልካም ስሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጠራታችን ያህል፤ አንገት በሚያስደፉ የምግባር መገለጫ ስሞች እንድንጠራም የግድ ብሎናል። ሁሉ እያለን በጠባቂነት ተርታ እንድንሰለፍ ሆነናል።
ይህንን እውነታ ለመለወጥ በተለያዩ ወቅቶች ጥረት ቢደረጉም፤ የሚጠበቀውን ያህል ፍሬ ሊያፈሩ አልቻሉም። በተለይም የሀገሪቱ የፖለቲካ ለውጦች በኃይልና በሴራ ላይ የተመሰረቱበት መንገድ /ባህል ጥረቶቹ ፍሬ አፍርተው ሀገሪቱ እንደ ሀገር ካለችበት የግጭት አዙሪት መውጣት ሳትችል እንድትቀር አድርገዋታል።
ይሁን እንጂ የ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ይሄንን የፖለቲካ መንገድ ወደ አዲስ ምዕራፍ የለወጠ ሆኗል። ሁሉን አጥፍቶ ከዜሮ የመጀመር አባዜን አስቀርቶ፤ መጥፎውን አርሞና መልካሙን አጎልብቶ የሚራመድ አዲስ የሪፎርም አካሄድን በኢትዮጵያ አስተዋወቀ። በሁለንተናዊ ብልጽግና እውን የማድረግ እሳቤ ውስጥም የሕግ የበላይነትን ማስፈን፤ ፍትህን ማረጋገጥም ትኩረቱን አደረገ።
ይሄን ያስተዋወቀው የለውጡ መንግሥት ታዲያ፣ ለጀመረው ሁሉን አቀፍ ልማት ከሁሉም በላይ ዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ፣ ሀገራዊ አለመግባባቶችን በድርድርና በውይይት መፍታት የሚያስችል የአስተሳሰብ መሠረት ለመጣል ረጅም መንገድ ተጉዟል። ችግሮችን በይቅርታ ለማለፍ ከመሞከር ጀምሮ ለውጡን በመተማመን ለማስቀጠል ጥረት አድርጓል።
የሕግን የበላይነት እውን ለማድረግ እና ፍትሕን በማጽናት ዜጎች በፍትህ ሥርዓቱ እንዲታመኑ፣ በተለይም በተለያዩ አጋጣሚዎች ለተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰለባ የሆኑ ዜጎች ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ የሽግግር ፍትህ ተግባራዊ የሚሆንበትን አስቻይ ሁኔታ በማመቻቸት ለፍትሃዊነት ያለውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ አሳይቷል።
ለዚህም ሲባል ህዳር 15 ቀን 2015 ከፖሊቲካ ጣልቃ ገብነትና ከተጽዕኖ ነጻ በሆነ መልኩ የሽግግር ፍትህ ከፍተኛ የባለሙዎች ቡድን እንዲቋቋም አድርጓል። ቡድኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የጋራ የሰብዓዊ መብቶች የምርመራ ውጤት ምክረ ሃሳብን እንዲሁም ጥቅምት 2015 የተደረገውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ላይ በመመሥረት ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
በእስካሁኑ ሂደት የሽግግር ፍትህ የባለሙዎች ቡድን 47 ክልላዊና 8 ሀገር አቀፍ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮችን ጨምሮ፤ 9 በልዩ ሁኔታ በተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ላይ ያተኮሩ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮችን ከተባበሩት መንግሥታት የተለያዩ ቢሮዎች፤ ከአፍሪካ ሕብረት፤ ከኢጋድ፤ እና ከሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በቅንጅት አከናውኗል። በ12 ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በመድረስ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቶችን አካሂዷል።
ውይይቶቹ በኢትዮጵያ ያለውን ብዝሃነትና ልዩነት ባማከለ፤ በሰብዓዊ መብቶች መርህ ላይ የተመሠረቱና ተጎጂዎችን ማዕከል ባደረገ መልኩ የተከናወኑ ናቸው። ከከተሞችና ከአጎራባች አካባቢዎች የመጡ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰለባዎችን፤ በሀገሪቱ ውስጥ የተጠለሉ ስደተኞችን ጨምሮ ተፈናቃዮችን፤ አካል ጉዳተኞችን፤ ሕጻናትን፤ የመሳሰሉ የተገለሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች ያሳተፈ ነው።
የምምክር ሂደቱ በሁሉም መድረኮች ቢያንስ 40 በመቶ የሚሆኑት ተሳታፊዎች ሴቶች እንዲሆኑ አድርጓል። ይህ ደግሞ በተለይም በጦርነትና በግጭት ወቅት ግንባር ቀደም ተጎጂ የሚሆኑት ሴቶች በመሆናቸው በተለያዩ ወቅቶች በሴቶች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥሰቶች ጎልተው እንዲወጡ ያስችላል።


ከቋንቋ አንጻርም ብዝሃነትን ባማከለ መልኩ በሁሉም ቋንቋ ውይይቶች እንዲካሄዱ ተደርጓል። ይህም ተጎጂዎች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹና ደረሰብኝ የሚሉትን ችግር በቀላሉ እንዲያስረዱ አስችሏቸዋል። በዚህም ሕብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ የነቃ ተሳትፎ ከማድረጉም በተጨማሪ በጉዳዩ ላይ የባለቤትነት መንፈስ እንዲያዳብር አስችሏል።


በአሁኑ ወቅት የሽግግር ፍትህ የምክክር መድረክ የማጠናቀቅ ሂደት ላይ ይገኛል። የሽግግር ፍትህ እውን መሆንም እንደ ሀገር ያለመግባባት፣ የግጭትና የጦርነት ታሪካችን ተዘግቶ በጋራ ታሪኮቻችን ላይ የምንግባባ፤ ለጋራ ሀገራችን የምንተጋ፤ ለልጆቻችንም የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማውረስ የሚያስችል ነው።

በተለይም ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል መልኩ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነትና ከተጽዕኖ ነጻ የሆነ የሽግግር ፍትህ የባለሙዎች ቡድን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱ አጥፊዎች የሚጠየቁበትን፤ ተጎጂዎችም የሚካሱበትን አሠራር ተግባራዊ እንዲሆን ያስችላል። በቀጣይም ተመሳሳይ ጥፋቶች እንዳይደገሙ ትምህርት ይሰጣል።


የምክክር ሂደቱም ተጎጂዎችን ማዕከል ባደረገ መልኩ መካሄዱም ፍትህ የሚሹ ወገኖች እንዲካሱ እና ዜጎች በፍትህ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖራቸው በር ይከፍታል። በሂደቱም የፍትህ ሥርዓቱ እንዲጠናከር መሠረት ይጥላል።


የሽግግር ፍትህ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የመላው ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል፤ በገንዘብ፣ በቴክኒክና በሃሳብ ድጋፍ እያደረጉ ያሉ አካላትም ተሳትፏቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You