የለንደንቀጠሮ፡- የዝምታዬና ጸጸት ጉዞ

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፊልሞቻችን ወደ ዓለም አቀፍ ከተሞች እየተመሙ “ልሂድ አትከልክሉኝ ቀጠሮ አለብኝ” ማለትን ጀምረዋል። ፊልሞቻችን ግዙፍ ዓላማና ግብ አንግበው የሀገራችንን የፊልም ኢንዱስትሪ ለመለወጥ እንጂ ከሀገር ሸሽተው ለስደት አይደለም።

በሀገራችን ኢትዮጵያ ካሉት የኪነ ጥበብ ዘርፎች አንዱ የሆነው የፊልሙ ዘርፍ እድገቱ ዝግ፤ ፊቱ ጭፍግግ እንዳለ ሳይሞት ሳይሽር በዓመታት መካከል እየተፍገመገመ ለዚህ ደርሷል። ዛሬ ላይ በኩራት ደረታችንን ነፍተን የምናወራለት መሆን ባይችልም ለማውራት ግን የሚያሸማቅቀን አይደለም። ኢንዱስትሪው ክንዱ ለመፈርጥም ባይታደልም በየጊዜው ብቅ እያሉ ተስፋን የሚመግቡንን አንዳንድ ፊልሞች እየተመለከትን ‘ነገ ጥሩ ይሆናል’ በማለት ነገን እንጠብቃለን። በእርግጥም ጥሩ ከመሆን የሚያግደው አንዳችም ነገር የለም። የፊልም ኢንዱስትሪው ለመቆርቆዙ ጎበዝ የፊልም ባለሙያ…ተዋናይ…አሊያም ደራሲና ዳይሬክተር ጠፍቶ አይደለም። ትልቁ ችግር ግን ያሉንን ነገሮች በአንድ አቀናጅቶ ወደ ውጤት መቀየሩ ላይ ነው። ዛሬ በሆሊውድ ላይ ሳይቀር በሙያቸው ድንቅ ሥራን እየሠሩ ያሉ የሀገራችን ልጆች የቱንም ዳገት መውጣት እንደምንችል ማሳያዎቻችን ናቸው። የፊልም ገጸ በረከትና አንጡራ ሀብት የሆነው ታሪካችን እና አጽናፈ ዓለሙን የሞላው ባሕላችን እንኳንስ በፊልም መልክ ተሠርቶ ይቅርና እንዲሁ እዩኝ ስሙኝ የሚል እንደመሆኑ ለዓለም አቀፍ መድረክ ብቁ ናቸው። ከኛም አልፎ ለሌሎች ዓለም አቀፍ የፊልም ኢንዱስትሪዎች ግብዓት መሆን የሚችሉም ጭምር ናቸው። ታዲያ ፊልሞቻችን ባሕር ማዶ ተሻግረው ለመታየት ትንሿን ብርሃን ይዘው መሄዳቸው ይህንኑ ይዘውልን ለመምጣት ይሆናል። በዚህኛው ዓመትም ሁለት የሀገራችንን ፊልሞች ለንደን በጉጉት ትጠብቃቸዋለች። እነርሱም ለቀጠሮው ተሰናድተዋል።

ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ባሳለፍነው ቅዳሜ ለኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ በእጅጉ ደማቁ ምሽት ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያን ፊልሞች ለውጭው ዓለም በማሳየት ፈር ቀዳጅ በጎነቱን ያሳየው ሐበሻ ቪው በዘንድሮው ዓመትም ፊቱን ወደ ለንደን አዙሮ ወደዚያው በማቅናት ለዓመቱ የተመረጡ ሁለት የሀገራችንን ፊልሞች ለማሳየት ዝግጅት ማጠናቀቁን በዚሁ ዕለት ገልጿል። ጥቅምት 17 እና 18 በለንደን ከተማ ለሚካሄደው ለዚህ ፌስቲቫል ዝምታዬ እና ጸጸት የተሰኙት ሁለቱ ፊልሞች ተመርጠዋል። በቅዳሜው ምሽትም የፊልሞቹን እርክክብና የሽኝት ሥነ ሥርዓት ተካሂዶ ነበር። በእለቱ በሀገራችን ፊልሞች ላይ ታላላቅ ስም ያላቸው ተዋንያን፣ የፊልም ዳይሬክተሮች፣ ፕሮዲዩሰሮችና ደራሲያን በሀያት ሪጄንሲ አዳራሽ በመገኘት በዚህ ያማረ ዝግጅት ላይ ታድመዋል። ከትላንት እስከ ዛሬ እንዲሁም በዛሬው የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ከተወለዱ ታላላቅ ፈርጦች ማንም የቀረ የለም ለማለት ይቻላል። ምክንያቱ ደግሞ ጥሪው የሐበሻ ቪው ብቻ ሳይሆን ዘርፉን የማበልጸጊያ ፍኖት በመሆኑም ነው። ከተደረገው የፊልሞቹ የሽኝት ሥነ ሥርዓት በስተጀርባ የነበሩት የባሕላዊ ሙዚቃ መሣሪያ የኪነት ባንድ ተጫዋቾችና ተወዛዋዦች ሌላኛው የምሽቱ ሠናይ ድባብ ነበሩ። በባሕላዊው ሙዚቃ መሣሪያዎችና በውዝዋዜው የተዋሓደው ጥበባዊ ጨዋታ ግሩም ነበር። ባና ባና ..ጋሞደሬ…ዴንዳ..ሀገሬ ..አለምብሬ…ሌዊዮ..አደዬ..ኤሙሌ… ቀልብን እየነጠቁ ፈጽሞ መቀመጥን የማያስመኙና ውስጣዊ ስሜትን የሚኮረኩሩ ውብ ትርኢቶች ነበሩ።

እግረ መንገዳችንን ይህን ግዙፍ ዝግጅት ስላሰናዳው ሐበሻ ቪውና በዚህ ተግባር ቀደም ባሉት ዓመታት በውጭው ዓለም ያሳያቸውን ፊልሞች ተንተርሰን ጥቂት ነገር እንበል። ሐበሻ ቪው በፈረንጆቹ 2018 ነበር የተመሠረተው። ሲነሳም የኢትዮጵያን ፊልሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ በማሳየትና ሀገርና ባሕልን በማስተዋወቅ የሀገራችንን የፊልም ኢንዱስትሪ ወደላቀ ደረጃ የማድረስ ዓላማ ሰንቆ የተመሠረተ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲሆን የራሱ የሆነ መተግበሪያም ጭምር ያለው ነው። የዘንድሮው ፌስቲቫል ለ4ኛው ጊዜው ቢሆንም፤ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ካሳየ በኋላ በመሐል በተለያዩ እክሎች ምክንያት ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ ቆይቶ ነበር። ሥራውን በ2015ዓ.ም እንደገና ጀመረ። እስከዛሬም በ3 ዙሮች ወደ ተለያዩ የዓለማችን ከተሞች በመዘዋወር ፊልሞችን ለማስመልከት ችሏል። ባለፈው ዓመት በተካሄደው የ3ኛው ዙር በሀገራችን የፊልም ታሪክ የመጀመሪያውና የ60 ዓመት አዛውንት የሆነው ‘ሒሩት አባቷ ማነው’ የተሰኘውን ፊልምን ጨምሮ ሌሎች ሁለት ፊልሞች በቨርጂኒያ ከተማ ለእይታ በቅተዋል። ‘ሒሩት አባቷ ማነው’ ፊልሙ የተጻፈው በኤልሻዳይ ኤልሳ ሲሆን ጋምቦሮሶ ሀሪስ ደግሞ ዳይሬክት አድርጎት ነበር። ባለ ጥቁርና ነጭ ምስል የሆነው ‘ሒሩት አባቷ ማነው’ በውጭው ዓለም የነበረው ተቀባይነት አበረታች ስለመሆነም ሐበሻ ቪው በምልሰቱ አስታውሶታል።

ይህ ብቻም አይደለም ‘ሒሩት አባቷ ማነው’ ሌላ ታሪካዊ ትውስታም አለው። እንደሚታወቀው ከ60 ዓመታት በፊት ፊልሙ ሲሠራ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፊልም እንደመሆኑ ነገሮች አልጋ ባልጋ አልነበሩም። በኢንዱስትሪው ውስጥ በጥቂቱም ቢሆን የሚንቀሳቀሰው መንግሥታዊው ተቋም እንጂ በግል ደረጃ ምንም የፊልም ጭምጭምታው አልተሰማም ነበር። ይህ ፊልም ደግሞ አነሳሱ በመንግሥት ደረጃ አልነበረም። ‘ስክሪፕቱ’ ተጽፎ ከታየ በኋላ አንዳንድ አካላት ባደረጉት እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የመሥሪያ ገንዘብ በብድር መልክ ሊገኝ ቻለ። ፊልሙ ተሠርቶ ለእይታ ከበቃ በኋላ ለረዥም ዓመታት በልማት ባንክ ተቀምጧል። ፊልሙ እንደ ፊልም ብቻ ታይቶ የማይታለፍ የሀገር ቅርስ መሆኑን የተረዳው የልማት ባንክም ለኢትዮጵያ ፊልም ‘ኢንስቲትዩት’ አስረክቦታል። በዚሁ መድረክ ላይ ተጋባዥ ከነበሩ ታላላቅ እንግዶች መካከል አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆነው ሠርጸ ፍሬ ስብሐት ስለጉዳዩ እንዲህ ሲል ተናግሯል “የልማት ባንክ ፊልሙን ለኛ በማስረከብ ከተረሳበት ወጥቶ እንዲታወስ አድርጎታል። በሌላ በኩል የፊልም ኢንዱስትሪው ከእውቀት እስከ ኢንቨስትመንት በራሱ ጥረት ከዚህ በመድረሱ በራሱ ኩራት ነው። አሁን ቀድሞ እንደነበረው አይደለም። መንግሥትም እጁን አውጥቶበታል። እንግዲህ ምን ማለት ይቻላል…”

በዘንድሮው ዓመት ወደ ለንደን በመውሰድ ለመታየት የተመረጡ ሁለት ፊልሞች ናቸው። ከእነዚሁ መካከል አንደኛው ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት የተሠራው ‘ጸጸት’ የተሰኘው ፊልም ነው። ይህ ፊልም በተሠራበት በዚያን ወቅት ፊልም መሥራት በመንግሥት ደረጃ እንጂ እንደዛሬው በግል የማይሞከር ነበር። ይህም ፊልም ከተጻፈ በኋላ ፕሮዲዩስ የሚያደርገው ባለ ሀብትም ሆነ አቅም ያለው ሰው በመጥፋቱ ለረዥም ጊዜ ስለመንከራተቱ የፊልሙ ሥራ እውን እንዲሆን ከማስተባበር ጀምሮ በፊልሙ ላይ ትልቅ አሻራውን ያኖረው ተስፋዬ ሲማ በመድረኩ ላይ ገልጾታል። ጊዜውን ሲያስታውሰውም “የፊልሙን እስክሪፕት ከተመለከትኩት በኋላ ፊልሙ የግዴታ መሠራት እንዳለበት አመንኩ። ፊልሙን በባለቤትነት የሚያሠራ ፕሮዲዩሰር ማግኘቱ ግን ትልቅ ፈተና ነበር። ምክንያቱም ከዚያ በፊት ያልተለመደ በመሆኑ ማንም ደፍሮ ወደ ፊልም ኢንዱስትሪው የሚገባ ባለሀብት አልነበረም። ከብዙ ድካም በኋላ ግን አንድ ደስ የሚያሰኝ ብሥራት ሰማሁ። ሩቂያ አሕመድ እኔ ፕሮዲዩስ አደርገዋለሁ ስትል መጥታ ያለማመንታት በልበ ሙሉነት ፍላጎቷን ገለጸች” በማለት ትዝታውን አጫውቷል። ሩቂያ አሕመድም በሀገራችን የፊልም ታሪክ የመጀመሪያዋ የግል ፕሮዲዩሰር በመሆን ስሟን በደማቁ ለመጻፍ ቻለች። ታሪካዊ ለመሆን በበቃው በዚህ የ’ጸጸት’ ፊልም በመሪ ተዋናይነት መልካሙ ተበጀ የተሳተፈበት ሲሆን ፍቃዱ ተክለማሪያም፣ አበበ ተምትም እና ሌሎችም አንጋፋ የጥበብ ሰዎች ተሳትፈውበታል። ኩሪባቸው ወልደማሪያም፣ አበበ ቀጸላ እንዲሁም ቻቺ ታደሰና ሌሎች የፊልም ባለሙያዎችም አሻራቸውን አኑረውበታል። በ4ኛውና በዚህኛው ዙር ከጸጸት ጋር አብሮ ወደ ለንደን የሚጓዘው ሌላኛው የሀገራችን ፊልም ‘ዝምታዬ’ ይሆናል። ፊልሙ በቅርብ ጊዜ የተሠራና በምስልና ጥራትም ሆነ ከሙያው አንጻር ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ነው። ሰለሞን ቦጋለ፣ ቃልኪዳን ጥበቡ፣ ቴድሮስ ተሾመ የተሳተፉበት ሲሆን በአስጨናቂ ከበደ ዳይሬክት ተደርጎ ቀርቧል።

በምሽቱ በነበረው ደማቅ ዝግጅት በኢትዮጵያ ፊልሞች ላይ አሻራቸውን ላኖሩ ግለሰብና ተቋማት እውቅና በመስጠት በተቋሙ የመጀመሪያ የሆነውን የሽልማት ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል። በግለሰብ ደረጃ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ቤት ጀምሮ ላደረጉት ትልቅ አስተዋፅዖ ዛሬ በጤና እክል ሳቢያ በመድረኩ ተሳታፊ ባይሆኑም የክብር ዶክተር ተስፋዬ አበበ(ፋዘር) በእንደራሴያቸው በኩል ሽልማቱን ወስደዋል። ከዚህ በመቀጠልም ሁለት ተቋማት ሽልማቱን ለመቀዳጀት ችለዋል። በአትሌቲክሱ ብቻም ሳይሆን በኪነ ጥበቡ ዘርፍም ስሙን ማኖር በቻለው በኃይሌ ገብረሥላሴ የተቋቋመው ዓለም ሲኒማ ላበረከተው ጉልህ አስተዋፅዖ ሁለተኛው ተሸላሚ ነበር። ሲኒማ ቤቱ የኮቪድ ጊዜን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት፤ በክፉም ሆነ በደጉ ሲኒማው ከመታየት እንዳይቦዝን በማድረግ ያለምንም መቆራረጥ ሥራውን በተሳካ ሁኔታ ለመከወን ችሏል። 3ኛውና የመጨረሻውን ሽልማት የተቀበለው የአዲስ አበባ ከተማ ሲኒማ ቤቶች ድርጅት ነበር። በ1991 ዓ.ም የተመሠረተው ይህ ድርጅት ሲኒማ ኢትዮጵያ፣ ሲኒማ አምባሳደር እና አምፒርን በስሩ በማድረግ ያስተዳድራል። ሲኒማ ቤቶቹ ያለመታከት ዘወትር ፊልሞችን በማሳየት ለሚያከናውኑት አበረታች ተግባር ለምስጋና ይሆን ዘንድም ድርጅቱ ከእለቱ የክብር እንግዳ ከጸሐፊ ተውኔትና ደራሲ አያልነህ ሙላት እጅ ሽልማቱን ተቀብለዋል። በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ አያልነህ ሙላትም አንደኛው ባለ አሻራ ናቸው። በወቅቱ የቲያትርና የፊልም ማሠልጠኛ በመክፈት ዛሬ የምንመለከታቸውን ብዙዎችን አሠልጥነው ገርተዋል። በብዙዎቻችን ትውስታ ውስጥ ተቀርጾ የቀረው ‘ያይኔ አበባ’ የተሰኘው ፊልምም የኚሁ ታላቅ ሰው ነበር። “ያይኔ አበባ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ አልታየም፤ ነገር ግን በውጭ ሀገር ብዙ ታይቶ ብሩንም አላገኘሁም” ሲሉ በመድረኩ ላይ በቀልድ መልክ ጠቀስ አድርገውታል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ባሕል በፊልሞችና ልዩ ልዩ የጥበብ ሥራዎች በውጭ ሀገራት እንዲታዩ ጥረት ያደርጉ የነበሩ አንጋፋ የጥበብ ልጆች ነበሩ። ከእነዚህም ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን፣ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ እንዲሁም አበበ ባልቻ በአሊያንስ ፍራንሲስ አማካኝነት ያደርጉት የነበረው ጥረት የማይዘነጋ ነው። ዛሬ ደግሞ የሐበሻ ቪው መሥራችና ሥራ አስኪያጅ የሆነችው ትግስት ከበደና ሩቂያ አሕመድ እያከናወኑት ላለው ተግባር እውቅናና ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። በዚህ ዘርፍ ላይ እየተሠራ ያለው ፊልሞችን በዓለም ከተሞች ማሳየቱ፤ የጎበጠውን የሀገራችንን የፊልም ኢንዱስትሪ ቀና ለማድረግ ብርቱ ምርኩዝ ይሆነዋል። ባሕሎቻችንን በፊልሙ ከማስተዋወቁም ባሻገር ለፊልም ጸሐፊያን ተዋንያንና ዳይሬክተሮች እንዲሁም ለተለያዩ የፊልም ባለሙያዎች ችሎታቸውን በማሳየት የዕድል በራቸውን የሚከፍቱበት መድረክ ነው። እንግዲህ በስተመጨረሻም፤ በእለቱ የነበረው የሽኝት ሥነ ሥርዓት በባሕላዊው የሙዚቃ ባንዶችና ተወዛዋዦች እንደደራ መገባደጃውን አደረገ።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You