መቋጫ ያልተገኘለት የመማሪያ መጽሐፍት ጉዳይ

ዘነበች ደስታ ከትምህርት ቤት የተመለሱት ልጆቿ የቤት ሥራ ባለመሥራታቸው ብስጭት ገብቷታል። 3ኛ እና 5ኛ ክፍል የደረሱት ልጆቿ ለክፍላቸው የተሰናዱ መጽሐፍትን ከትምህርት ቤታቸው ባለማግኘታቸው የቤት ሥራውን ለመሥራት አለመቻላቸውን ነገሯት። የቤት ሥራቸውን ኢንተርኔት ከፍታ እንዳይሠሩ ኔት ወርክ የለም።

ልጆቿ እንደነገሯትም ሃብት ያላቸው ቤተሰቦች ለልጆቻቸው ከኢንተርኔት መጽሐፍት በማውረድና ኮፒ በማድረግ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ ነው። መጽሐፍትን ከገበያ ለመግዛት ደግሞ ዋጋው ወገብ የሚቆርጥ ሆኖባታል። በዚህ ስሜት ውስጥ እያለች ነበር ጓደኞቿ ሮማን ባልቻ እና ማርታ ታደሰ ተከታትለው የገቡት።

ሁለቱም የፊቷ ገጽታ ተመልክተው ደሞ ምን ሆነሽ ነው። ፊትሽ የሐምሌ ጨለማ የመሰለው ብለው አፈጠጡባት። ‹‹ምን ላድርግ ብላችሁ ነው። የልጆቼ የትምህርት ጉዳይ ያላሳሰበኝ፤ ምን ያሳስበኛል ብላችሁ ነው። ››

ልጆቹ ምን ሆኑ ስትል ሮማን ጠየቀች። ‹‹ይገርማችኋል፤ በአሁኑ ወቅት ያለው የትምህርት ሁኔታ ግራ የሚያጋባ ሆኖብኛል። በአንድ በኩል የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ እየተሠራ ያለው ሥራ ሁላችንን ያስደሰተንን ያህል፤ የመጽሐፍት እጥረት ደግሞ ናላችንን እያዞረው ነው። እንዴት አንድ ተማሪ ሁለትና ሦስት ዓመት ያለመጽሐፍት ይማራል። ደግሞስ ሁለትና ሦስት ዓመታት አንድን ችግር እንዴት መፍታት ያቅታል ›› ስትል ብሶቷን ዘረገፈችባቸው።

ማርታ ከመምህርነት ሙያዋ ጋር የሚያያዝ ርዕሰ ጉዳይ በመነሳቱ ተደስታለች። ጠደፍ ብላም ‹‹እእ እሱን ነው እንዴ የምትይው። እሱንማ ኅብረተሰቡም፤ እኛ መምህራንም ሚዲያውም ብሎ ብሎ ጠብ ያለነገር ጠፍቷል እኮ። እንዳልሽው አሁን ትምህርት ሚኒስቴር የሚሠራው ሥራ ሁላችንም ለዓመታት ስንመኘው የቆየነውን ያህል የመጽሐፍ እጥረቱ ደግሞ አማሮናል።

ትምህርት ለአንድ ሀገር ዕድገት ወሳኝ መሣሪያ ነው። የአንድ ሀገር በእድገት መገስገስ ወይም ወደ ኋላ መቅረት ቀጥታ የሚያያዘው ከትምህርት ውጤታማነት ጋር ነው። የትምህርት ሥርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን ደግሞ በበቂ አቅርቦት መጠናከር ይኖርበታል። ›› እያለች ሙያዋን መከታ አድርጋ ትንታኔ ስትሰጥ ዘነበች አስቆመቻት።

‹‹የእኔ እህት አንቺ የምትይውን አይነት ትንተና ሰልችቶናል። አሁን የምንፈልገው ለልጆቻችን መጽሐፍት ነው። ልጆቻችን እኮ ለሦስት ዓመታት ያህል ያለመጽሐፍት ነው የተማሩት። ከኢንተርኔት እያወረዳችሁ ተማሩ የሚለው አባባል ምን ያህል እንደሚያስኬድ አላወቅም። ደግሞም ኢንተርኔት ያለውስ ምን ያህሉ ነው። ቢኖርስ ኔትዎርኩ ምን ያህል አስተማማኝ ነው። ደግሞስ ፕሪንት እያደረጋችሁ ተጠቀሙ መባሉስ የድሃውን አቅም ያገናዘበ ነው። እኔ አላውቅም፤ መንግሥት በዚህ ላይ ምን እንዳሰበ አላውቅም። ›› ብላ ሃሳቧን ከማሳረጓ ማርታ ቀበል አድርጋ ፤-

‹‹የተናገርሽው ስህተት ነው ለማለት ፈልጌ አይደለም። ባለፈው የትምህርት ዘመን ከገጠሙ ችግሮች ውስጥ ዋነኛው የተማሪዎች የመማሪያ መጽሐፍት እጥረት ነው። በ2014 ዓ/ም ትምህርት ዘመን በሙከራ ደረጃ እንዲሁም በ2015 ዓ/ም ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ የተገባበት አዲሱ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓትም በመጽሐፍት እጥረት ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኗል። ተማሪዎችም ለአንድ ዓመት ያህል ያለመማሪያ መጽሐፍት ለመማር ተገደዋል።

የተማሪዎች የመማሪያ መጽሐፍት ለደረጃው የሚገባው መሠረታዊ የእውቀት፤ ክህሎትና ዝንባሌ

ማስጨበጫ ይዘቶችን የያዙ ስለሆኑ ተማሪዎች በቂ እውቀት ጨብጠው ወደሚቀጥለው ደረጃ እንዲሸጋገሩ ድልድይ ሆነው ያገለግላሉ። የመማሪያ መጽሐፍት በሌሉበት ሁኔታ ተማሪዎች በደረጃቸው ሊይዙት የሚገባቸውን እውቀት እንዳይዙ እንቅፋት ከመሆኑም ባሻገር በቀጣይ የትምህርት አቀባበላቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው። ችግሩ ግን ቶሎ የሚፈታ ይመስለኛል ››ብላ ነገሩን ለማቀዝቀዝ ሞከረች።

የሁለቱን ጭቅጭቅ ስትሰማ የቆየችው ሮማን በጨዋታው ውስጥ ለመሳተፍ በመፈለግ ሃሳብ ሰነዘረች። ትምህርት ቤት የገባ ልጅ ስለሌላት እንደዘነበች ችግሩ በቀጥታ ባይነካትም ጎረቤቶቿ ሲናገሩ የሰማችውን እና ገጠር ያሉ ወንድሞቿ የነገሯትን መነሻ አድርጋ ወደ ጨዋታው ተቀላቀለች።

‹‹በጉዳዩ ላይ ተደጋጋሚ አስተያየት ሲሰጥ እንደሰማሁት በመጽሐፍቱ እጥረት ምክንያት ትምህርቱ እንዲሰጥ የታቀደው በኢንተርኔት አማካኝነት ነው። ሆኖም ከተማሪዎቻችን አቅም፤ ክህሎትና እንደሀገር ካለው የኢንተርኔት አቅርቦት ችግር ጋር ተያይዞ ውጤታማነቱ በቅድሚያ ሊፈተሽ ይገባ ነበር።

አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ እንኳን የኢንተርኔት አገልግሎት ተዘርግቶ የሚገኘው በከተሞች አካባቢ መሆኑና በገጠሩ ክፍል ተደራሽ አለመሆኑ ሰፊ ቁጥር ያለውን ተማሪ ከትምህርት ማዕዱ የሚያገል መሆኑን ታሳቢ ማድረግ ይገባል። እናም ችግሩ ከግለሰብ አልፎ የሀገርም ጉዳይ ነው። እናንተስ ከተማ ስላላችሁ ትንሽም ቢሆን ዕድሉን አግኝታችሁ ልጆቻችሁን ማስተማር ችላችኋል።

የኢንተርኔት አቅርቦት አለባቸው በሚባሉ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች እንኳን በጉዳዩ ዙሪያ ተማሪዎች ሲጠየቁም ከአስተማሪዎቻቸው የቤት ሥራና ሌሎች የትምህርት ይዘቶች በቴሌ ግራም አማካኝነት አልፎ አልፎ እንደሚደርሳቸውና ሆኖም የተሳለጠ የኢንተርኔት አገልግሎት ባለመኖሩ ምክንያት ለማንበብና ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀም እንደተቸገሩም ተናግረዋል። ስለዚህም እንኳንስ ገጠርና በከተማም ቢሆን ትምህርት በኢንተርኔት አማካኝነት ለማዳረስ የተደረገው ሙከራ በሚፈለገው መልኩ ውጤታማ እንዳልሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

የእኔ ወንድሞች የ6ተኛ እና 8ተኛ ክፍል ተፈታኞች ናቸው። በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች ላይ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተዘጋጀው የስምንተኛና የስድስተኛ ክፍል መማሪያ መጽሐፍት ተደራሽ አለመሆናቸው የ6ተኛና 8 ክፍል ሚኒስትሪ ተፈታኞች በአግባቡ እንዳይዘጋጁ እክል እንደፈጠረባቸው ነግረውኛል። ›› ብላ የሰማችውን ሃሳብ ሰነዘረች።

መምህርት ማርታ ቀጣዩን ዕድል ወሰደች። ‹‹በአጠቃላይ ያለመማሪያ መጽሐፍት አቅርቦት የተሻለ የመማር ማስተማር ሂደት መፍጠር አዳጋች ነው። በተለይም እንደኢትዮጵያ ባሉ ዝቅተኛ የትምህርት ጥራት ባለባቸው ሀገራት የመማሪያ መጽሐፍት በወቅቱ አለማዳረስ በቋፍ ላይ ያለውን የትምህርት ጥራት ይባሱኑ ወደ አዘቅት ውስጥ መክተት ስለሚሆን ሳይውል ሳያድር ችግሩን የሚመጥን መፍትሔን መፈለግ ግድ ይላል። ይህም የእኛም የትምህርት ባለሙያዎች ሃሳብ ነው።

በቂ የሆነ ግብዓት ባልተዘጋጀበት ሁኔታም ከተማሪዎች ውጤት መጠበቅም ብዙ ርቀት የሚያስኬድም እንዳልሆነም አምናለሁ። በተለይም አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ባለበት ጊዜ ይህን መሰሉ የመጽሐፍት አቅርቦት ችግር መፈጠሩ እንደሀገር በርካታ ዕውቀትና ሃብት የፈሰሰበትን ፖሊሲን ስንኩል የሚያደርገው ይሆናል። ይህም እንደባለሙያ ያሳስበኛል።

ሆኖም እንደእኔ እምነት መንግሥት ችግሩ ሳያስበው ቀርቶ ሳይሆን ከሕትመት ጋር የተያያዘ ችግር ገጥሞት ነው። እናም ችግሩ እንደተፈታ ልጆቻችንን መጽሐፍት እንደሚያገኙ እምነቴ ነው›› ብላ ወደ ዘነበች ተመለከተች።

ዘነበች ከእሷ የሚጠበቅ ሃሳብ እንዳለ በመረዳቷ ‹‹መምህርት ማርታ ያለችው እንዲሆን ሁላችንም ምኞት ነው። ነገር ግን የተማሪዎች የመማሪያ መጽሐፍት ጉዳይ ቀጣይነት ያለውና የመማር ማስተማሩ ሂደት አንዱ አካል በመሆኑ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግን ይጠይቃል። ችግሩ ሰፊና ውስብስብ በመሆኑን ከመንግሥት ባሻገር በሕትመት ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ አካላትን በሀገር ውስጥ መሳተፍና ማጠናከርን ግድ ይላል። ›› ብላ መምህርት ማርታን በጨረፍታ ተመለከተቻት።

መምህርት ማርታ ለሮማን እድሉን ለመስጠት በመፈለግ ጓደኛዬ እኛ ስንጨቃጨቅ ዝም አልሽ እኮ። አንድ ነገር ብለሽ ገላግይን እንጂ ብላ ወደ ጨዋታው ዳግም ጋበዘቻት።

‹‹አይ፤ ብዙ የምለው ነገር ስለሌለኝ ነው። ደግሞም ሁለታችሁም በአግባቡ ገልጻችሁታል። ሆኖም ያለመጽሐፍት አቅርቦት የመማር ማስተማር ሂደቱን ማስቀጠል አግባብነት አለው ብዬ አልወስድም። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የመጽሐፍት ሕትመት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባ ነበር። በእርግጥ መጽሐፍቱ በጥራት ስለሚታተሙ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ዋጋቸውም ውድ ስለሚሆን ገንዘብ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል።

ምንም ሆነ ምን ግን ሁለት እና ሦስት ዓመት ሙሉ ያለመጽሐፍት ተማሪዎች እንዲማሩ ማድረጉ በእኔ በኩል ተቀባይነት የለውም። መንግሥት ተማሪዎችን ዩኒፎርም እያለበሰ፤ ደብተር እየገዛና እየመገበ ብዙዎችን አስደስቷል። ሁላችንም እንደ ወላጅ ሸክማችን ቀሎናል። ነገር ግን የመጽሐፍት ስርጭቱ ላይ ትኩረት ቢያደርግ ጥረቱን ሙሉ ያደርግለታል።

እንዴውም እናንተ አላነሳችሁትም እንጂ ከመጽሐፍቱ ባልተናነሰ ደብተር ለተማሪው በወቅቱ አለመድረሱም አሳሳቢ ነው። በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ደብተር የሚሟላላቸው በመንግሥት ነው። ነገር ግን በተሟላ መልኩ ደብተር አልተከፋፈለም። ስለዚህ ተማሪዎች መንግሥትን በመጠበቅ ጊዜያቸውን እያባከኑ ነው። ከውጭ የሚመጣውን ደብተር ማዳረስ ካልቻለ የሀገር ውስጥ ምርትን መጠቀሙ አንዱ አማራጭ ነው። በዚህም ተባለ በዚያ ግን ደብተር የሚሰጥበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል።

ዩኒፎርምም ቢሆን ሁሉም ትምህርት ቤት በተሟላ ሁኔታ አልተዳረሰም። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ አልደረሰንም ሲሉ ዜና ላይ አዳምጫለሁ። ሌሎቹ ደግሞ በከፊል እንደተሟላላቸው ሲናገሩ አዳምጫለሁ። ስለሆነም መንግሥት የሚያደርጋቸው ጥረቶች የተሟሉ እንዲሆኑ የተጓደሉትን የትምህርት አቅርቦቶችን በፍጥነት ሊያሟላ ይገባል። እንደዚያ ሲሆንም ወላጆች በሙሉ ልባቸው እፎይ ይላሉ። ያለበለዚያ ግማሽ መላጣ፤ ግማሽ ጎፈሬ አይነት ጉራማይሌ ይሆናል። ›› ብላ ሃሳቧን ቋጨች።

መምህርት ማርታ ሙያዋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሃሳቡን እንድታጠቃልለው ዘነበችና ሜሮን ወደ እሷ አንጋጠጡ። መምህርት ማርታ በፈገግታ ከተመለከተቻቸው በኋላ ንግግሯን ቀጠለች።

“በአጠቃላይ ግን በ2015 የትምህርት ዘመን ያጋጠመውም የተማሪዎች የመጽሐፍት እጥረት ተማሪዎች ተገቢውን እውቀት እንዳይጨብጡ እንቅፋት ከመሆኑም ባሻገር በቀጣይ የትምህርት አቀባበላቸውም ላይ የራሱን የሆነ ተጽዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው። በ2015 የትምህርት ዘመን የተፈጠረው የመጽሐፍት አቅርቦት ችግር ዘንድሮም እንዳይቀጥል ትምህርት ሚኒስቴርና በየክልሉ የሚገኙ የትምህርት ቢሮዎች ከወዲሁ ሊያስቡበት ይገባል።

በሌላም በኩል ደብተርና ዩኒፎርም የተባሉትም ትኩረት የሚያሻቸው ናቸው። በዚህ ላይ ትኩረት እንዲደረግ የበኩሌን ጥረት አድርጋለሁ። እንደምገምተው የተባሉት ችግሮችን መንግሥት በውል ስለሚያውቃቸው ቶሎ መፍትሔ ይሰጣል ብዬ አምናለሁ›› ብላ ንግግሯን አሳረገች።

ሦስቱም ጓደኛሞች በመስማማት ስሜት በፈገግታ ተያዩ። ዘነበችም‹‹ ወይ እኔ ነገር በነገር ጠመድኳችሁና ቡና እንኳን ጠጡ ሳልላችሁ ›› ብላ እየተጣደፈች ወደ ጓዳ ገባች። ማርታና ሜሮንም እየሳቁ የሚወዱት የዘነበች ቡና እስኪመጣ በግል ወሬያቸው ተጠመዱ።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You