“የግድብ ስራችንን በአሸናፊነት ጀምረን እዚህ እንዳደረስን ሁሉ የወደብ ጉዳያችንንም ለማሸነፍ ጠንካራ ዲፕሎማቶች ያስፈልጉናል”ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል

 ጥንታዊው የኢትዮጵያ ስልጣኔ በሁሉም ዘርፎች ላይ አስደናቂና እመርታዊ ለውጥ የታየበት ስለመሆኑ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት የሚያስረዱት ሀቅ ነው። እነዚህ ያልተቋረጡ የታሪክ አካሄዶች ደግሞ ዛሬም ድረስ ያልደበዘዙ የታሪክ አሻራዎች ናቸው። እነዚህ ነባራዊ ሀቆችም ኢትዮጵያን በዓለማች ላይ ከሚገኙ ጥንታዊና ያልተቋረጠ የስነ መንግስት ታሪክ ካላቸው አገሮች መካከል አንዷ እንድትሆን አስችሏታል።

በተለይም በኢዛናና በካሌብ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በነበራት ከወርቅ ከብርና ከነሐስ በተሰሩ መገበያያ ገንዘቦች በቀይ ባህር ላይ በምታንቀሳቅሳቸውና በምታዛቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጦርና የንግድ መርከቦች በመታገዝ ከደቡብ አረብ አገራት እስከ ሕንድ ውቂያኖስና የአሁኗ ቻይና ድረስ በሰፊው የተዘረጋ የኢኮኖሚ የንግድ የዲፕሎማሲና የመንግስታት ግንኙነት በተጠናከረ መልኩ ታካሂድ እንደነበረ ከጥንት ስልጣኔዋ የከፍታ ልኬት አንጻር የተሰነዱ ነባራዊ የታሪክ ድርሳናት አስረጂዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ ለአያሌ ዓመታት ታስተዳድረው በነበረው የቀይ ባሕርና የባሕር በሮቿ ግዛቶችም ከላይ ከተጠቀሱት አገራት ጋር የዝሆን ጥርስ የቅመማ ቅመም ምርቶችን የሙጫ ተክሎችን እንዲሁም ሌሎች ወጪና ገቢ ሸቀጦችን አልባሳት ሽቶና ጌጣጌጦችን በመላክና ወደአገር ውስጥ በማስገባት የተቀላጠፈ የንግድ እንቅስቃሴ ታካሂድ እንደነበርም የአባቶቻችን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ይህ ብቻም አይደለም የቀይ ባሕር ወደብን እንደ አሸዋ ትናኝበት በነበረበት ጊዜ ከየመን እስከ ሕንድ ከሶሪያ እስከ እስራኤል ከሳውዲ አረቢያ እስከ ግብጽ ከቻይና እስከ አውሮፓና ኤዤያ ድረስ ጠንካራ የመንግስታት ግንኙነትን በመፍጠር የልዕለ አያልነት አስፈሪነቷን ለዓመታት እንደቆየችበት የአገሪቱ የዲፕሎማሲ ታሪክ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው እውነት ነው።

ይህም በዘመኑ በቀይ ባሕር ቀጠና ከፍ ያለ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማሕበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ብልጽግናን ካነገሱ አገራት ቀዳሚዋና ፋና ወጊ ሲያስብላት ቆይቷል። በዚህ ገናናነቷ ዓለምን ሊቀይር የሚችል አቅምን መፍጠርን እንደቻለችም በብዙ የውጭ አገር ዲፕሎማቶች ሳይቀር ዛሬም ድረስ የምትታወስ አገር ስትሆን የዚህ ታላቅነቷ ምስጢር ሲገለጽ ደግሞ ግርማቸው ከሩቅ የሚያስፈራ በጥበብም ቀድመው የነቁ የበቁ መሪዎችና በስነ ምግባር በአገር መውደድና አርቆ በማሰብ ውስጥ የነበሩ ተመሪ ሕዝቦችም የነበሯት አገር እንደነበረች የሚያሳይ ነው።

በአንጻሩ የአገሪቱን የቀዳሚነት መንገድ ይዞ ካለመዝለቅ የመነጩ ክስተቶችን ያስተየናገደችው ኢትዮጵያ በተለይም ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በኋላ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ መቀየር በራሷ በአገሪቱም የመሪዎች መለዋወጥ ምክንያት አገሪቱን ካለወደብ በሚያስቀር ውል ኤርትሪያ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ሆነ። ይህ መሆኑ ደግሞ የአገሪቱን ፖለቲካዊ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ኩነቶች በመቀያየር አገሪቱን ወደብ አልባ ከማድረጉም ባሻገር ከቀይ ባሕርና ከኤደን ባሕረሰላጤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነቷ ውጪ እንድትሆን አስገድዷታል።

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ አገር በመሆኗ በወጪ ገቢ ምርቷ ላይ የሌላ አገር ጥገኛ እንድትሆን አስገድዷታል። ይህም ለራሷ ታውለው የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማቀጨጭ በኢኮኖሚዋ ላይ እድገት እንዳይመዘገብ የፊጥኝ አስሯታል። ከቀይ ባሕር በ60 ኪሊ ሜትርና ከሕንድ ውቂያኖስ በ2 መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ቢሆንም እነዚህን አካባቢዎች ተጠቅማ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን እንዳታደርግ የማግለል ሁኔታዎች ፈጥረዋል።

የአፍሪካውያን የነጻነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ በጥንታዊው ስልጣኔዋና ገናናነቷ ከቀይ ባሕር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ የነበራትን ኃያልነት መርምሮ ዘመኑን ታሳቢ ባደረገ ዓለም አቀፍ የወደብ አጠቃቀም መርህን ፈትሾ የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ፖለቲካዊ አካሄድ ተረድቶ በሰላማዊ ንግግርና ምክክር የኢትዮጵያም የወደብ መጠቀም መብት ሊከበር የሚገባበት ወቅት አሁን ነው።

የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።

 አዲስ ዘመን ፦ .በቅድሚያ ኢትዮጵያን እንዴት ይገልጿታል?

ረዳት ፕሮፌሰር አደም፦ ኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜ የነጻነት ታሪክ ያላት ከመሆኗም በላይ በጸጥታው ምክር ቤት እኤአ በ1945 ሲመሰረት ከመስራቾቹ አንዷ ነበረች። በሌላ በኩል ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት እኤአ 1963 ሲመሰረት ከመስራቾቹ አለችበት። አፍሪካውያን በሙሉ በቅኝ ግዛት አጣብቅኝ ውስጥ ገብተው በተከፋፈሉበት ወቅት ከዛም ነጻነታቸውን ባገኙበት ጊዜ በኢኮኖሚም በፖለቲካም በኩል ነጻነታቸው የተከበረ እንዲሆን ለማድረግ ትልቅ ጥረትን አድርጋለች።

በዚህም እነ ኔልሰን ማንዴላ ሳይቀሩ ሚሊተሪ እውቀትን እንዲጨብጡ በማሰልጠን በኩል ሚናዋ የጎላ ከመሆኑም በላይ እሷም በራሷ ለቅኝ ገዢዎች ያልተበገረችና ያልተደፈረች ሆና ቆይታለች።

ጣሊያኖች ለአምስት ዓመት ያህል በቅኝ ለመግዛት ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው እንዲቀር ከማድረጓም በላይ ጥቁሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ነጮችን ያሸነፉበት ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ ደግሞ በዓለም አደባባይ አስደማሚ ከመሆኑም በላይ የመላው ዓለም መነጋገሪያ ሆኖ የቆየም ነው። ይህ ደግሞ መላው ጥቁር ሕዝብን አበረታቶ ለኢትዮጵያ ድጋፍ እንዲያደርጉ ከመገደዳቸውም በላይ በራሳቸው ከፍተኛ የሆነ የሞራል ልዕልናን እንዲይዙም ያደረጋቸው ታሪክ ነው።

በዚህም አፍሪካውያን ነጻነታቸውን ካገኙ በኋላ ለአገራቸው መለያ ሰንደቅ ዓላማ (ባንዲራ) እንኳን የእኛን የሰንደቅ ዓላማ ቀለም መነሻ አድርገው ነው እየተጠቀሙ ያሉት። ይህ ደግሞ የአገራችንን ልዕልናና ክብር የሚያመላክት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በሙስሊሙ ዓለም ልዩ ከበሬታ ያላት ናት። በዓለማችን ከሁለት ቢሊየን በላይ ተከታዮችን ያፈራው የእስልምና ሀይማኖት መነሻ ከመሆኗም በላይ የነጃሺ የቢላል አገር ነብዩ ሙሀመድ ያከበሯት አገር ስለሆነች ልዩ ክብር ይሰጧታል። ሕገ ሀይማኖት በሆነው ቁራንም ላይ ኢትዮጵያን 30 ቃላቶች በላይ በኢትዮጵያና በግዕዝ ቋንቋ ተመዝግቦ እናገኛለን። ከዚህም በላይ ነብዩ ሙሀመድ ሲያልፉ ኢትዮጵያን አትንኩብኝ ብለው ልዩ ኑዛዜን ያስቀመጡላትም አገር ናት።

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በአፍሪካም ይሁን በሙስሊሙ ዓለም ልዩ ከበሬታ ያላት ናት። እዚህ ላይ የማይረሳውና የዓለምን ሕዝብ እስከ አሁን ድረስ እንዳነጋገረ የቀጠለው የአድዋ ድልም የሚረሳ አይደለም።

አዲስ ዘመን፦ ከዚህ ታሪኳ ተነስተንስ በቀጠናው በተለይም በቀይ ባሕር አካባቢ የነበረውን የኢትዮጵያ ሚና እንዴት ይገልጹታል?

ረዳት ፕሮፌሰር አደም፦ አሁን ላይ ያለው ትውልድ የአገሩን የረጅም ዓመት ታሪክ በቅጡ የማይረዳ መሆኑ በበኩሌ ያሳዝነኛል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የተከበረችው እና ያልተደፈረችው የቀይ ባሕር ባለቤት ስለሆነች ነበር። ነገር ግን ምክንያቱን በውል በማናውቀው ሁኔታ እንደ እኔ ሀሳብ ደግሞ የውጭ እጅ ሊኖር ይችላል ወደቧን አጥታለች። በተለይም ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ የሚባለው ግብጻዊ የተባበሩት መንግስታትን ለአራት ዓመት በመራበት ወቅት ኤርትራም ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ትልቅ ሚናን የተወጣ ነው። እኔም በወቅቱ አብሬያቸው ስለነበርኩ ስለሁኔታው በደንብ አውቃለሁና ይህንን ተግባሩን ለመፈጸምም ከጅቡቲ እስከ ሱዳን ድረስ በጀት አስሶ አዲስ በምትወለደው የአረብ ሊግ ላይ ኤርትራን አባል ማድረግ አለብን በማለት ብዙ ሰርቷል።

ግን መላው ሕዝብ ይህንን ያወቀና ያነበበ አይመስለኝም ፤ በመሆኑም ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለቤት በነበረችበት ጊዜ ምርቷ በሙሉ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚከፋፈል ነበር። ለዘመናት የቀይ ባሕርና የበርካታ ወደቦች ባለቤት የነበረች ኃያልና ክቡር አገር አሁን ላይ ወደኋላቀርነት ድህነት የገባችበት ሁኔታ ነው ያለው።

አዲስ ዘመን፦ እንዴት በቀይ ባሕር ላይ የነበራትን የበላይነት ልታጣ ቻለች ?

ረዳት ፕሮፌሰር አደም፦ የአፍሪካ ቀንድ የበርካታ ኃያላን ሀገራትን ትኩረት የሚስብ ስትራቴጂክ ስፍራ ነው። በተለይም አካባቢው በቀይ ባሕር እና በናይል ውሃ ተፋሰስ መሃል መገኘቱ የበርካታ ሀገራትን ቀልብ ሊስብ ችሏል። የቀይ ባሕር እና የናይል ፖለቲካ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በማወዳጀትም ሆነ በማራራቅ ከፍተኛ ሚና ያለውን ያህል አካባቢውን በቁጥጥራቸው ለማዋል ሕልም ያላቸውም ሀገራት የሚራኮቱበት ነው።

ከአክሱም ስልጣኔ ጀምሮ የቀይ ባሕር አካባቢ ትኩረት ያገኘ ስፍራ ነው። በየዘመናቱ የነበሩ ኃያላን ቀይ ባሕርን ሳይዙ ኃያልነታቸውን ማረጋገጥ የሚታሰብ አልነበረም።

ቀይ ባሕር በተለይ ከስዊዝ ካናል መከፈት ጋር ተያይዞ የዓለም የንግድ ኮሪደር ለመሆን ችሏል። ቀይ ባሕርን የመቆጣጠር ፍላጎት የዓለም ኃያልን ሀገራት ሁሉ ምኞት ነው። እነዚህ ሀገራት ኢትዮጵያ እንዳትቀናቀናቸው የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ከአካባው እንድትርቅ አድርገዋታል።

ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ይዛ በቆየችበት ወቅት ማን ነበረች? ምን ነበረች? የሚለውን ጠለቅ ብሎ መዳሰስ ያስፈልጋል፤ ታሪክ ላይም መደራደርና መወያየት እንደዛው አስፈላጊ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ጠለቅ ያለ የዲፕሎማሲ ስራንም መስራት ይጠበቅብናል።

በአሁኑ በወቅት የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ጠቃሚ አይደለም፤ እሱ የሚጠቅመው ለመሳሪያ ነጋዴዎች ብቻ ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን መጀመሪያ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ላይ የውስጥ አንድነታቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል። የአባይን ግድብ በሕብረት እንደሰራነው እዚህ ላይም ተጠናክረን የወደብ ጉዳያችን ላይ ጠለቅ ብሎ ማየት መወያየት እንዲሁም በሳል የሆኑ ዲፕሎማሲዎችን መመስረት ጠንካራ ውይይት ማድረግ አሸናፊ ያደርገናልና ሙስሊም ክርስቲያን ሳይባል ሴት ወንዱ ተጋግዞ በውይይት ለመፍታት መጣር ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን ፦ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ያላት ሚና እያሽቆለቆለ መጥቷል። ይህ ሚናዋ እየቀጨጨ መምጣቱ እንደሀገር ምን አሳጥቶናል ?

ረዳት ፕሮፌሰር አደም፦ ለድህነት; ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ፍልሰት እንዲሁም ለኑሮ ውድነት ነው ዳርጎናል። ኢትዮጵያ እንኳን 120 ሚሊየን ቀርቶ 270 ሚሊየን ሕዝብ ቁርስ ምሳ እራት ሳይቸገር በልቶ ጠጥቶ ጠግቦ ሊያድርባት የምትችል አገር ናት።

ኢትዮጵያ ያልተነካ ድንገል መሬት ያላት የውሃ ሃብት ያላት 70 በመቶ የሚሆን የወጣት ኃይል ያላት ከመሆኗ አንጻር ያለችበት ደረጃ የማይመጥናት ከመሆኑም በላይ ከሽንኩርት አቅም እንኳን እንዲህ ሰማይ ነክቶ ብዙዎችን ባላማረረ ነበር።

የውሃ እጥረት የተፈጥሮ ሀብት ችግር የለብንም ;ግን ደግሞ ዜጎቿ አገራቸውን የማወቅ ሁኔታቸው ከ ዜሮ በታች ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ማቀራረቡ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ አንጻር መሪዎችም ትልቁ የትኩረት አቅጣጫቸው ሊያደርጉት ይገባል።

ኢትዮጵያ ማን ናት? ለኢትዮጵያውያን ምን ነበረች? ወደፊትስ ምን መሆን አለባት? የሚለውን ትኩረት መሰጠት ያለበትና በዚህም መሰረት ሁሉም ትምህርት ቤቶች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ሀይማኖት ድርጅት ሚና ነው። በዚህ መልኩ ብንሰማራ ደግሞ አስገራሚ ውጤትን እናስመዘግባለን።

አዲስ ዘመን፦ በተለይ ከለውጡ ወዲህ በቀጠናው ላይ የኢትዮጵያን ሚና ለማጎልበት እየተሰራ ያለውን ስራ እንዴት ይመለከቱታል ?

ረዳት ፕሮፌሰር አደም፦ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን እናያለን ፤ የእኛ ዋናው ነገር ግን ጦርነትን እንደ አማራጭ መወሰድ እንደሌለበት ትልቅ ግንዛቤ መውሰድ ነው። ምክንያቱም ሶማሌያን የአንድ እምነት ተከታዮችና አንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ነበሩ:: ሶሪያም የመንም እንደዛው ::ነገር ግን በገቡበት አላስፈላጊ ጦርነት ምክንያት ዛሬ ላይ ከዜሮ በታች ወርደው ያሉ አገራት ሆነዋል። የቅርብ ጊዜው የሱዳን ሁኔታም ትልቅ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ክስተት ነው።

ዛሬ ላይ ሱዳን በሁለቱ አንጃዎች መካከል እየሆነ ያለው ነገር ለአገሪቱም ለሕዝቧ አስጊ ሆኗል:: በተለይም የእነዚህን አካላት ፍልሚያ ተከትለው ነጋሪት እየጎሰሙ የሚገቡት የውጭ ጣልቃ ገቦች ነገሩን እያባበሱት ነው። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሲጠቃለሉ ደግሞ ለእኛም ትምህርት የሚሰጥ ነው። የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ለሁሉም አስፈላጊ በመሆኑ፤ ለምሳሌ ሱዳናውያን አንድ እንዲሆኑ በእኛ በኩል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ አምባሳደር ሙሀመድ ድሪር ብዙ ጥረቶችን አድርገው ሰላም አምጥተውላቸው ነበር። አልተጠቀሙበትም እንጂ። ወደራሳችን ስንመለስም ወደብ ያስፈልገናል ?አዎ ነገር ግን አካሄዱ ሰላምን የተከተለ የማይሆን ከሆነ ሁላችንም ችግር ውስጥ የሚከትና የሚበላንም ይሆናል። በመሆኑም ጉዳዩን በጦርነት ካደረግንላቸው አውሮፓውያኑም ደስታቸው ነው። በመሆኑም ዓለም ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም ካለንበት ደረጃ ትምህርት በመውሰድ ማሰብ ጥቅሙ የጎላ ነው።

አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ የ120 ሚሊዮን ሕዝብ ባለቤት ሆና እና ከባሕር ጠረፍ ከ60 ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ እየተገኘች የወደብ ባለቤት አለመሆኗ አግባብ እንዳልሆነ የሚናገሩ ምሁራን አሉ። ከዓለም አቀፍ ሕግና ተሞክሮ አንጻር እርስዎስ ምን ይላሉ ?

ረዳት ፕሮፌሰር አደም፦ እኛ እኮ ለዚህ ነው ታሪካችንን አላወቅንም የምንለው። ኢትዮጵያ የአካባቢው ባለቤት በነበረችበት ወቅት ምን ያህል በኢኮኖሚው ምን ያህል አያል እንደነበረች ታሪክን ማገላበጥ ያስፈልጋል። የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ነዳጅ እንጂ ምንም አይነት የእርሻ ምርት ስለሌላቸው ሁሉንም የምትመግበው ኢትዮጵያ ነበረች። የዚህ ሁሉ ባለቤት የነበረችው አገር ዛሬ ለድህነት ለረሀብ ስትጋለጥ አሳፋሪ ነው። በአባቶቻችንና በአያቶቻችን የተከበረች አንድነትና ሀያልነት የነበራት አገር ዛሬ በዚህ ትውልድ ለድህነትና ኋላ ቀርነት መጋለጧ እጅግ አሳፋሪ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ቀጥላ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ ናት ። ግብጾችም ቢሆኑ ይህ ነገር ነው የሚያሳስባቸው፤ በመሆኑም ለኢትዮጵያ መዳከም የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም። በመሆኑም አሁን ላይ የውጭ ጠላታቸን ማነው? ምን እያሴረብን ነው? የሚለውንም ከግምት ማስገባት ይገባናል።

በመሆኑም የግድብ ስራችንን በአሸናፊነት ጀምረን እዚህ እንዳደረስን ሁሉ የወደብ ጉዳያችንንም ለማሸነፍ ጠንካራ ዲፕሎማቶች ያስፈልጉናል። በተለይም ለመካከለኛው ምስራቅ አረብኛ የሚችሉ ተናግረው የሚያሳምኑ የሚጽፉ ዲፕሎማቶችን ማሰማራቱ እጅግ ይጠቅመናል። ዲፕሎማቶቹም በአረቡ ዓለም ምን እየሆነ ነው? የሚለውን ነገር መመርመርና መፈተሽ ለእሱ የሚሆን በቂ ምላሽ ይዞ ለመቅረብ መዘጋጀት አለባቸው። ስራውም ከውጭ ጉዳይ ባለፈ የደህንነት የእስልምና ጉባኤውና የሀይማኖት ድርጅቶችም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።

አዲስ ዘመን፦ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት እንድትሆን የሚያደርጓት አማራጮች አሉ ?ካሉስ የትኞቹ ናቸው ?

ረዳት ፕሮፌሰር አደም፦ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሲያነሱ እንደነበረው በርካታ አማራጮች አሉ። ወደብን በጋራ ማልማት፤ ኢትዮጵያ ከምታለማቸው መሰረተ ልማቶች ጥቂቱን ሰጥቶ ወደብ ማግኘት፤ የቦታ ቅይይር ማድረግና የመሳሰሉትን በመጠቀም ኢትዮጵያን የወደብ ባለቤት ማድረግ ይቻላል። ይህንን ሁሉ ስናደርግ ሰላማዊ ሂደትን በመከተል ነው።

ከዚህ ሁሉ በፊት ግን ውስጣዊ ሰላም ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ምን ጊዜም ቢሆን የአገር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት መደረግ አለበት። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል። ሌላው ደግሞ በእያንዳንዱ ዜጋ ውስጥ የአገር ፍቅር ስሜት ዘልቆ ሊገባ ይገባል። በተለይም በአሁኑ ወቅት የትም መሰደጃ የሌለን ሕዝቦች በመሆናችን አገራችንን ማወቅና መጠለያችን መኖሪያችን መቀበሪያችን ለሆነችው እናት አገራችን ምን መምሰል አለባት የሚለውን ከብሔር ከጎሳና ከሀይማኖት ጭምልቅልቅ ወጥተን አገራችንን ማስቀደም ይገባል።

እኛ አሁን ባለው ሁኔታ የሚዲያ ችግራችን ከፍ ያለ ነው። ሚዲያዎቻችንን ትኩረት መስጠት ላለባቸው የአረብኛ ቋንቋ ትኩረት አይሰጡም። በመሆኑም አገራችን አሁን ላይ ያለችበትን ሁኔታ በመረዳት በአረብኛ ቋንቋ የውይይት መድረኮችን እየከፈቱ ምን አለ የሚለውን በትጋት መከታተል ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፦ ሰላማዊ አማራጮችን በመጠቀም የወደብ ባለቤትን ለማረጋገጥ የተወሰዱ ዓለማቀፋዊ ተሞክሮዎች ካሉ ቢያብራሩልን ?

ረዳት ፕሮፌሰር አደም፦ በጣም ብዙ ተሞክሮዎች አሉ። በጦርነትም በሰላማዊ መንገድም ተግባራዊ ያደረጉ የዓለም አገራት አሉ። ምክንያቱም የሕዝብና የአገር ጥቅም ከወደብ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ሁሉን መስዋዕትነት ከፍለው አረጋግጠዋል። ለምሳሌ አውሮፓ ወደ በርካታ አገራት የተከፋፈለችው በወደብ ምክንያት ነው። ይህ ለእኛ እንግዳ ሊሆን ይችላል እንጂ ለሌላው ዓለም አዲስ ነገር አይደለም።

ለምሳሌ ቦስኒያ፤ ምስራቅና ምዕራብ አውሮፓ በወደብ ምክንያት የነበሩበትን ችግር ማንሳት ይቻላል፤ እንግሊዝና ፈረንሳዮችም በወደብ የተነሳ ለክፍፍል በቅተው ነበር፤ ኋላ ላይ ሁሉም ሀያል ሲሆኑ በጋራ እንጠቀም ብለው በመወሰን ችግሩን ፈትተውታል።

አዲስ ዘመን፦ በዚህ ረገድ እንደ ሀገር ያለውን ተስፋስ እንዴት ያዩታል ?

ረዳት ፕሮፌሰር አደም፦ ኢትዮጵያዊነት በውስጣችን ከተረጋገጠ አሸንፈን የምንወጣበት እድል በጣም ሰፊ ነው። ግን ደግሞ ኢትዮጵያዊነት እውነት ልባችን ውስጥ አለ ወይ ? የሚለው ቀዳሚ ጥያቄ ሊሆን ይገባል። እስከ አሁን አልሆነም ከዚህ በኋላ ግን ትንሹም ትልቁም ሴቱም ወንዱም ኢትዮጵያ ማን ናት? ምን ነበረች? አሁንስ? የሚለውን ነገር በጣም መገንዘብ ይገባዋል። ይህንን ካደረግን በራሱ ሀይልና እንቅስቃሴ አገሩን የቀደመ ማንነቷ ላይ ያስቀምጣታል።

በመሆኑም አሁን ላይ ብሔርን ከማግነንና ከማቆለጳጰስ በመውጣት እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለውን ነገር ልክ እንደ አርማችን አጉልተንና ከፍ አድርገን ልንይዘው የሚገባ ነገር ነው። ይህንን ካደረግን ደግሞ ማንም አይደፍረንም ብቻ ሳይሆን የቀደመ እኛነታችንንም መልሰን ከኋላቀርነት ከስደትና ከርሃብ ነጻ የሆንን ሕዝቦች እንሆናለን።

አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ጊዜ በጣም አመሰግናለሁ።

ረዳት ፕሮፌሰር አደም ፦ እኔም አመሰግናለሁ

 እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You