ለሰላም ተገቢውን ዋጋ እንስጥ

 ዓለም ዘወትር የሚያቀነቅንለት፣ የሚገጥምለት፣ የሚደረስለትና የሚያወራለት የሶስት ፊደላት ጥምር የሆነው ሰላም (peace) የሚለው ቃል ነው። ቃሉ ብቻውን የያዘው የመልዕክት ክብደት ዓለም ካሏት ውድ ሀብቶች ሁሉ የሚልቅ ነው። ዋጋውን ለመተመን ብዙ መመራመርም አያስፈልግም። እሱን ማጣት በቂ ነው። በዚህም ብዙ ሀገራት ለከፋ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ተዳርገዋል፤ ፈራርሰዋል።

ሰላም ከፈጣሪ በታች የሁሉም ጠባቂና ተንከባካቢ የሆነ የማይዳሰስ የሃሳብ ቁርጠኝነት ነው። ከዚህ የተነሳም ሰላም የችግሮች መፍቻ ቁልፍ በመሆኑ ዓለም በአንድ ድምጽ እንዲዘምርለት ሆኗል። በሀገራት ታሪክ ውስጥም የሰላም የመኖርና ያለመኖሩ ጉዳይ የታሪክ ትርክቶችን ፍጹም የተለያዩ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

በርካታ ሀገራት ሰላም ማስቀደም ተስኖቸው ወደ ግጭት በመግባት ለውድመትና ለብዙ ምስቅልቅሎች እንደተዳረጉ ሁሉ፤ ሰላምን ማስቀደም የቻሉ ሀገራት የተሻሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ መስተጋብሮች ባለቤት መሆን ችለዋል። በዚህም ለዜጎቻችው የተሻለ የመኖሪያ አካባቢ መፍጠር ችለዋል።

በርግጥ ለግጭቶች ምክንያት የሆኑ ችግሮች ብዙ ናቸው። ትልቁ ጉዳይ ምክንያቶቹ ሳይሆኑ፤ ዋናው ችግሩን ለመፍታት የሚኬድበት መንገድ እንደሆነ ይታመናል። በተለይም ችግሮችን በኃይል ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ለሰላም መታጣት አልፋና ኦሜጋ ናቸው።

የራሳችን ሀገር ጉዳይ እንኳን እንደ ምሳሌ ብንወስድ ለሰላም እጦታችን በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ለሰላም ቅድሚያን አለመስጠት ነው። በሀገሪቱ እስከ አሁን እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች ሰላማዊ መፍትሔን ከማስቀደም ይልቅ ነገሮችን በኃይልና በጠመንጃ ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ውጤት ናቸው።

በመላ ሀገሪቱ ምላሽ የሚጠይቁ የተለያዩ ጥያቄዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ከችግሮቹ ምንነት፣ ከመጡበት መንገድ፤ ከዛም ባለፈ ለዘለቄታው ምላሽ እንዲያገኙ ከማስቻል አንጻር ከኃይል ይልቅ በውይይትና በምክክር ለመፍታት መሞከሩ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነው።

በርግጥ እኛ ከመጣንበት የግጭት መንገድ አንጻር የሰላም ዋጋ ምንያህል እንደሆን ነጋሪ የሚያስፈልገን ሕዝቦች አይደለንም። በቀደሙት ዘመናት ጭግሮቻችን ከኛ በልጠው ሳይሆን ከችግሮቻችን መብለጥ አቅቶን ብዙ ዋጋ ለመክፈል ተገድደናል።

በቅርቡ እንኳን በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተካሄደው ጦርነት የደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ምን ያህል የከፋ እንደሆነ ለማንኛችንም የተሰወረ አይደለም። ጦርነቱ ከፈጠረው ቁስል ገና በወጉ አላገገምንም። ከሀዘኑ አልወጣንም። ብዙ እናቶች፣ አባቶች፣ ጎረቤቶች፣ ቤተሰቦች አሁንም በሀዘን ላይ ናቸው።

ጦርነቱም ለማስቀረት የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። ከነዚህ ተጠቃሽ የሚሆነው፤ በሀገር ሽማግሌዎች፣ በእምነት አባቶችና በታዋቂ የሀገር ልጆች የተደረገውና ሳይሳካ የቀረው የሰላም ጥረት ነው።

በዚህም በርካታ መንገዶች፣ ድልድች የውሃና መብራት መሰረተ ልማቶች፣ የቴሌኮም አገልግሎቶች ትውልድን የሚቀርጹ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች ወድመዋል።

እነዚህን ተቋማት መልሶ የመገንባቱ ሄደት ከፍያለ ሀብትና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው። ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄን ማስቀደም ቢቻል ኖሮ ትሩፋቱ ምን ሊሆን እንደሚችል፣ ተሞክሮውም ለመጪ ትውልዶች የሚኖረው ፋይዳ ከፍያለ ስለመሆን መገመት የሚከብድ አይሆንም።

ጦርነት አውዳሚ ነው፣ አውዳሚነቱ በተለይ እንደኛ ባሉ ድህነት እና ኋላ ቀርነት ብዙ ዋጋ እያስከፈላቸው ላሉ ሕዝቦች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው። አንዴ ወደ እዚህ አውዳሚ ግጭት ከገቡ በኋላ በሚፈጠረው ምስቅልቅል መቆጨት “የፈሰሰ ውሃ አይታፈስ” እንደሚባለው አንዳች ፋይዳ አይኖረውም።

በየትኛውም መመዘኛ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር መፍታት የሚደገፍና የሚበረታታ ነው። ለዚህ ደግሞ የሰላም ዋጋ በአግባቡ መረዳት ከሁሉም ይቀድማል። በተለይም ፖለቲከኞቻችን ልዩነታቸውን ዘመኑን በሚዋጅ መንገድ ለመፍታት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።

በየትኛውም ማሕበረሰብ ውስጥ አለመግባባቶች አይኖሩም አይባልም ይኖራሉ፤ ግራና ቀኝ እግር እንኳን የሚጋጭበት ሁኔታ እንዳለ አበው ይናገራሉ፤ ዋናው መሆን ያለበት ችግሮች/አለመግባባቶች ለምን ተፈጠሩ አይደለም፤ እንዴት በሰላማዊ መንገድ/በውይይት ሊፈቱ ይችላሉ የሚለው ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን ለሰላም ዋጋ የሚሰጡ የተለያዩ ወግ፣ ባህልና የአኗኗር ስርዓት ያለን ህዝቦች ነን። እነዚህን ሀገራዊ አቅሞቻችንን በአግባቡ ተረድተን በተጨባጭ በእለት ተእለት ሕወታችን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ገና ብዙ ይቀረናል። በተለይም ፖለቲከኞቻችን በዚህ በኩል ያለባቸው ክፍተት አሁን ላይ እያጋጠሙን ላሉ የሰላም ተግዳሮቶች ዋነኝ ተጠቃሽ ነው።

አሁን ላይ እያጋጠመን ያለው የሰላም እጦት ተማሪው በውጤቱ እንዲያሽቆለቅል፣ ገበሬው ምርቱን በአግባቡ ሰብስቦ ለገበያ እንዳያቀርብ፣ ለፍቶ አዳሪ እንደልብ ተንቀሳቅሶ የዕለት ጉርሱን እንዳያገኝ እንቅፋትን ፈጥሯል። ፋብሪካዎች ስራ እንዲያቆሙ የሀገር ኢኮኖሚ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ገፊ ምክንያት በመሆን የዜጎችን ሕይወት ፈተና ውስጥ ከቷል።

ሁላችንም ያለችን አንድ ሀገር ነች፤ እንደ ሕዝብም እህትማማቾች እና ወንድማማቾችን ነን። የአንዱ ሕመም የሚያመን የሌለው በደል የሚቆረቁረን ነን። አንዳችን ለአንዳችን አቅም እና ድጋፍ ነን ፤ ይህንን ጠብቀን ለመሄድ ለሰላማችን በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅብናል። እንደ ሕዝብ የተጋመድንበትን ገመድ በሰላምና በፍቅር አጠንክረን መቀጠል ይገባናል።

ለሰላም ተገቢውን ትኩረት በመስጠት፤ ትኩረታችንን ወደ ጀመርነው የለውጥ መንገድ ማድረግ ኖርብናል። የጀመርነው ልማት የብዙ ጥያቄዎቻችን ተጨባጭ ምላሽ ይዞ የሚመጣ፤ ሰላማችንን የበለጠ የሚያገዝፍ ነው። ለመጪዎቹ ትውልዶችን ብሩህ ተስፋ ፈንጣቂ ነው።

ለሰላሙ ተገቢውን ትኩረትና ቅድሚያ በመስጠት ባልተገቡ ግጭቶች ሊከሰቱ የሚችሉ የሚደርሰውን ሰቆቃዎችን ከወዲሁ ማስቀረት ይገባል። ለዚህም ከሁሉም በላይ መላው ሕዝባችን ለሰላሙ በሁለንተናዊ መልኩ ዘብ ሊቆም ይገባል። የሀገር ሽማግሌዎች፣ የእምነት አባቶች የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማሕበረሰብ ተቋማት ደግሞ ሰላምን በመስበክ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር የበኩላቸውን ማዋጣት ይኖርባቸዋል።

ጠመንጃ በማንሳት ግጭት ውስጥ የገቡ አካላትም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጠመንጃውን በማስቀመጥ በምትኩ የሰላም ምልክት የሆነውን ነጭ ባንዲራ በመያዝ ወደ አስከፊ ጉዳት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ሊገቱ፤ መንግስትም ለሰላም የሚደረገውን ጥሪ አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባል።

 አለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You