በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ባገኙአቸው ዕድሎች በአገር ውስጥና በውጭ አገር ዕውቀት ለመቅሰምና የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት የቻሉ አንዳንድ ኢትዮጰያውያን ያገኙትን ዕውቀት ለወገኖቻቸው ለማድረስና አዳዲስ አሠራርንና አስተሳሰብን በሕዝባችን መካከል ለማስረጽ፣ አብዝተው የደከሙና ሕይወታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት የደረሱ ፋና ወጊ ግለሰቦች በርካታ ናቸው።
የማያልፍ ሥራ ሠርተው ስማቸው ሲወሳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል ከቀናት በፊት ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አንዱ ናቸው። ፕሮፌሰሩ ዕውቀት ከብስለት እና ከጥበብ ጋር ከሰመረላቸውና በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሕይወታቸው ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ከሰሩ ኢትዮጵያውያን መካከል እንደነበሩ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የተወለዱት መጋቢት 1942 ዓ.ም በሃዲያ ምስራቅ ባዶዋቾ ሾኔ ከተማ አቅራቢያ ባለችው ገጠራማ መንደር ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የምስራቅ ባደዋቾ ዋና ከተማ በሆነችው ሾኔ፣ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኩየራ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አዳማ በሚገኘው የቀድሞ አጼ ገላዎዴዎስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ-ሕይወት (Biology) የትምህርት ዘርፍ አግኝተዋል። አዳማ አፄ ገላውዴዎስ ሲማሩ በሳይንስ ክለብ አማካኝነት ያዩዋቸው ዶክተር አክሊሉ ለማ በሳይንስ ላይ የሠሩትን ሥራ አርአያ አድርገው ስለነበር ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የመረጡት የትምህርት ዘርፍ ላይ አስተዋጽኦ አድርጓል።
በዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውም የላቀ ውጤት በማምጣታቸው እዚያው ጀማሪ መምህር ሆነው ተቀጠሩ። ዩኒቨርሲቲው የውጭ መምህራንን ለመተካት ሲያደርገው በነበረው ጥረት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ወደ ውጭ ሀገር ሄደው እንዲማሩም ተደረጉ። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው ዊስኮንሰን ዩኒቨርሲቲ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውንም እዚያው አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው ቱለን ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ ጤና እና በተላላፊ በሽታዎች (Tropical Diseases) ሠርተዋል።
ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በ1970 ቀጥታ ወደ ሀገራቸው በመመለስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ጀመሩ። ከ1978 እስከ 1982 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነውም አገልግለዋል።
በተላላፊ በሽታዎች (Tropical Diseases) ላይ በርካታ ምርምሮችን ከሥራ አጋሮቻቸው እና ተማሪዎቻቸው ጋር አከናውነዋል። በተለይም በወባ በሽታ፣ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ላይ፣ በሳምባ ነቀርሳ፣ እንዲሁም በርከት ባሉ ሌሎች ሕዋስ ወለድ በሽታዎች ላይ ሰፊ ምርምር አድርገዋል።
ባልተሟሉ የቤተ ሙከራዎች እና ሁኔታዎች ውስጥ በተለይ ኤች አይ ቪ/ኤድስ ከሌሎች በሽታዎች ጋር ስላለው ግንኙነት እና በምድር ወገብ ሀገራት አካባቢ ስላለ በሽታ ወለድ ሕዋሳት ባህሪ በማጥናት ከአንድ መቶ በላይ በርካታ ምርምሮች በዓለም አቀፍ መድረኮች ይፋ አድርገዋል።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በርካታ ወጣት ተመራማሪዎችን በመምራት እና በማስተባበር ለውጤት ያበቋቸው ምርምሮች በሥነ ሕይወት ሳይንሱ ዘርፍ በዓለም አቀፍ እና በሀገር ቤት ባበረከቱት ድርሻም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል።
ባደጉበት አካባቢ ሕዝብ ላይ ይደርስ የነበረው ጭቆና እና የሕዝቡ በመሬቱ ላይ ባለቤት አለመሆኑ የመሬት ጥያቄን ሲያነሳ ወደ ነበረው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ተሳቡ። የፊት መሪ ባይሆኑም በነበረው እንቅስቃሴ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል።
በ1983 ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን መምራት ሲጀምር የፊት ለፊት ፖለቲካውን በግልጽ ተቀላቀሉ። በሽግግሩ ወቅት የትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሆነው ተሹመው የነበረ ሲሆን፣ የተወሰነ ጊዜ ካገለገሉ በኋላ ሥልጣናቸውን ለቅቀዋል። በዚህ የኃላፊነት ወቅት የሚታወቁበት አንድ ጉዳይም አለ። የግል ቤት ስላለኝ ቤትም ሆነ የቤት አበል አልቀበልም ማለታቸው እንደምሳሌ የሚነሳ ነው።
ግንቦት 1992 ዓ.ም በተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ በሃዲያ ዞን የምትገኘው ሾኔን በመወከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነዋል። የፓርላማ አባል በነበሩበት ወቅት ለአባላቱ የሚከፈላቸውን ደመወዝም ሆነ ቤት አልተቀበሉም፤ ለዚህም ምክንያታቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደመወዝ ስለሚከፈላቸው እና የግል ቤት ስላላቸው መሆኑን ራሳቸው ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ ጠላት ስለሌላት እጅግ ውድ ወጪ የሚጠይቅ አየር ኃይልም አያስፈልጋትም የሚለውን የኢሕአዴግ አቋም በመቃወም የአየር ኃይሉ ሕልውና እንዲጠበቅ በምክንያት ተከራክረው አሳምነዋል። ኢትዮጵያ በየብስ፣ በባህርም በአየርም ሠራዊት ሊኖራት እንደሚገባም ቀድመው ሲከራከሩ የነበሩ አርቆ አሳቢ ናቸው።
የሰብአዊ መብት አጠባበቅ፣ የመናገር እና የመጻፍ ነጻነት፣ የመደራጀት እና ከትጥቅ ትግል ውጭ የትኛውንም የፖለቲካ አመለካከት የመያዝ፣ የማራመድ እና የመደገፍ መብት እንዲጠበቅ በብዙ ተሟግተዋል፡፡
የሕዝብን ድምፅ ለማሰማት ያሉትን የጠበቡ እድሎች ታግሎ በማስፋት፣ ሰላማዊ መንገድን በመከተል ባለው አጋጣሚ በተገቢው ቦታ ለመገኘት መታገል እንደሚያስፈልግ የሚያምኑት ፕሮፌሰር በየነ ይህንኑ እምነታቸውን በተግባር ኖረው አስመስክረዋል።
ኢትዮጵያ ከፈተናዎቿ እና ከውጭ ጫናዎች መላቀቅ የምትችለው የውስጥ አንድነቷን ስታጠናክር መሆኑን የሚያምኑት ፕሮፌሰር በየነ፣ አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ተቆጥበው አያውቁም።
ኢትዮጵያ የሚገጥሟት ፈተናዎች አዲስ እንዳልሆኑ እና ፈተናዎቹን ለማለፍ ግን የሰከነ አካሄድ እና ቅድሚያ ለሚሰጡ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ ለችግሮች መፍትሔ እየሰጡ ስለመሄድ ሲናገሩ፣ “እኔ ኢትዮጵያ ዜጎቿን የማትጠቅም ሀገር ሆና ትቀጥላለች ብዬ አላምንም፤ ከእምነት አንፃር ተነስተው የሚናገሩ አሉ፣ ከእውነት አንፃር ተነስተው የሚናገሩም አሉ። እኛ ብቻ አይደለንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያለነውም እያለፍን ያለነውም፡፡
ስለዚህ ስለጎደለብን ነገር ብቻ እያብሰለሰልን መኖር አይገባንም። ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች በመጠቀም ወደ ፊት ለመሄድ መነሳት አለብን። ለጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት አለብን፤ በቅድሚያ መፍትሄ መስጠት የምንችለውን አሁን፤ በይደር እና በሂደት መፍትሄ የምንሰጠውን ጉዳይ በሂደት ለመፍታት የሚሰራ እና ትዕግስት ያለው ፖለቲከኛ ያስፈልገናል” ይላሉ።
ለኢትዮጵያ ስላላቸው ፍቅር ሲገልጹም፣ “በኢትዮጵያዊነቴ ያልኮራሁበት አጋጣሚ የለም፣ እኔ በኢትዮጵያ ጉዳይ ተስፋ አልቆርጥም። እዚህ እንድደርስ በርካታ ዘመዶቼ፣ ወዳጆቼ እና ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ አስተዋፅኦ አድርገዋል። እናም በሕይወቴ በኢትዮጵያዊነት ክብር የሚሰማኝ ሰው ነኝ” ይላሉ።
ፕሮፌሰር በየነ እጅግ የተለየ የሥራ ባህል ያላቸው ናቸው። “24 ሰዓት ለሁሉም ነገር በጣም በቂ ነው” የሚል እምነት ስላላቸው ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ጊዜ አጠረኝ የሚል እምነት እርሳቸው ጋር አይሠራም። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ጊዜ መምህር እና አማካሪነታቸው ለተማሪዎቻቸው፣ ለጥናት ወረቀቶች እርማት እና ግምገማ፣ ለሳይንሳዊ ምርምር ስራዎች በቂ ጊዜ መድበው ይሰራሉ።
ምርምሮችን በጥልቀት ይፈትሻሉ፤ ማሻሻያዎችን ለተማሪዎቻቸው ይሰጣሉ። ሙሉ የስራ ሰዓታቸውን ለመደበኛ ስራቸው ከማዋል በተጨማሪ ቤታቸውም ጊዜ ወስደው ያርማሉ ያስተካክላሉ። ይህን የማስተማር ኃላፊነታቸውን በሙሉ ጊዜ ከማከናወን ጎን ለጎን ነው እንግዲህ የፖለቲካ ተሳትፎአቸውን የሚያደርጉት።
ኢትዮጵያ ጥሪቷን አሟጣ ያስተማረቻቸው ልጆቿ ዝምታ እና የዳር ተመልካችነት የሚያንገበግባቸው ፕሮፌሰር በየነ፣ ምሁራን ሀገራቸውን የሚለውጥ ሥራ ላይ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ይመክራሉ፤ ሀገራቸው ያስተማረቻቸውን እውቀት እና የሰጠቻቸውን እድል በመጠቀም ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ይጎተጉታሉ።
ኑሮን ቀለል አድርጎ መኖር፣ የመንፈስ ስብራት፣ ላመኑበት ጉዳይ ዋጋ መክፈል፣ ትህትና፣ የመርህ ሰውነት፣ እውነተኛነት፣ ማኅበራዊ ተሳትፎ እና ወጥነት የፕሮፌሰር በየነ ባህሪያት እንደሆኑ ተማሪዎቻቸው፣ የሥራ ባልደረቦቻቸው እና አብሮ አደጎቻቸው ይመሰክራሉ።
ነሐሴ 2010 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት ላለመው የኢኮኖሚ ሪፎርም ከተቋቋሙት የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤቶች መካከል የፕራይቬታይዜሽን አማካሪ ምክር ቤት አባል ሆነው ተመርጠዋል።
ሀገርን የሚያስቀድም እና የሚጠቅም ከሆነ በቅርበት ለመሥራት ችግር የሌለባቸው ፕሮፌሰር በየነ ከጳጉሜን 04 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው መሥራታቸው ለዚህ አቋማቸው ዋቢ ነው፡፡
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በሕዝብ ተሳትፎ፣ በትምህርት እና በምርምር አመራር በርካታ ዓለም አቀፍና ሀገራዊ ሽልማቶችን እና የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝተዋል። 120 ሳይንሳዊ የጥናት ውጤቶቸን ለብቻቸው እና በጋራ በመሆን በተለያዩ ጆርናሎች ላይ ያሳተሙ ሲሆን፣ “Basic Principles of Biology” የተባለ ተወዳጅ መጽሐፍም አዘጋጅተዋል።
ኢትዮጵያን ሊለውጥ ይችላል ብለው የሚያምኑበትን ሃሰብ ለመቀበል ቅድመ ሁኔታ አያስቀምጡም። መምህርነት እና ፖለቲከኛነት አልተጋጨባቸውም። ትምህርት ቤት ሲሆኑ ምርጥ አስተማሪ እና ተመራማሪ፣ በፖለቲካው መድረክም የሃሳብ ተሟጋች ናቸው። ፖለቲካንም ሆነ አስተማሪነት ሳይቀላቅሉ በየራሳቸው መድረክ አሳምረው ይወጧቸዋል።
ከሦስት አሥርተ ዓመታት በተሻገረው የአደባባይ የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው ብዙ ችግሮችን በግጭት እና በጠመንጃ አፈሙዝ መፍታት መሞከር ልማድ በሆነባት ኢትዮጵያ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርገው በጠመንጃ መሸናነፍ ሳይሆን የሃሳብ ሜዳ የተሻለ መሆኑን በተግባር አስመስክረዋል፡፡
በመምህርነት እና ተመራማሪነት የብዙዎችን የሕይወት መንገድ አቃንተዋል፤ በፖለቲከኛነታቸውም ሕዝባቸውን ወክለው ተከራክረዋል፤ ባገኙአቸው መድረኮች ሁሉ ሳይሰለቹ የሕዝብን ትክክለኛ ጥያቄ አሰምተዋል።
ብዙ የቀድሞ ተማሪዎቻቸው የሚያውቁአቸው በታታሪ መምህርነታቸው እና የአርትኦት ሥራውን በሠሩት Introductory to Basic Biology በሚለው መጽሐፍ ነው። በርካታ የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን አማክረው አብቅተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቁት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በመምህርነት እንዲሁም በትምህርት ሚኒስትር ዴኤታነት ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሹመው ሲያገለግሉ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
እኛም በዚህ ለሕዝብና ለሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ አሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት የባለውለታዎቻችን አምድ እውቁን ፖለቲከኛ፣ መምህር ተመራማሪና የስነሕይወት ሊቅ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን ላበረከቱት መልካም አሻራ አመሰገንን። ሰላም!
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም