በመስከረም ወር የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት የኢትዮጵያን የተሟላ ገጽታ ለዓለም የሚገልጡ ናቸው

አዲስ አበባ፦ በመስከረም ወር የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት የኢትዮጵያ የተሟላ ውበት ለዓለም የሚገልጡ መሆናቸውን የቱሪዝም ከፍተኛ ባለሙያው አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) ገለጹ።

የቱሪዝም ከፍተኛ ባለሙያው አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በመስከረም ወር የሚከበሩ እንደመስቀል፣ የኦሮሞ ሕዝብ ትውፊታዊ መገለጫ እሬቻ፣ የወላይታ የዘመን መለወጫ ዮዮ ጊፋታ፣ የሀዲያ የዘመን መለወጫ ያ ሆዴ እና ሌሎችም የአደባባይ በዓላት የኢትዮጵያን የተሟላ ገጽታና ውበት ለዓለም የሚገልጡ ናቸው።

የአደባባይ በዓላት ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነው የሚያከብሯቸው በመሆኑ እርስበርስ ለመተሳሰር እና የየራሳቸውን ባሕልና ትውፊት ለሌሎች ለማስተዋወቅ ያገለግላሉ ያሉት አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር)፤ ለአብነት የመስቀል ደመራ በዓል በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስ ተመዝግቦ ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘ በመሆኑ በርካታ ቱሪስቶች እንደሚታደሙበት ገልጸዋል።

ሌሎቹንም የአደባባይ በዓላት ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ በማድረግ የቱሪስት ቁጥርን ማሳደግ ይገባል ያሉት አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር)፤ ይህም ለሥራ ዕድል፣ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት እና ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ የቱሪስት መስሕብ ሥፍራዎችን ለማስተዋወቅ እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት።

የአደባባይ በዓላቱን ለመታደም የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎችን ለማስተናገድ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ አለባቸው ያሉት አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር)፤ በዓላቱ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴታቸውን በሚያጎላ መልኩ እንዲከበሩ በትብብር መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተለይ የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ እና ባለድርሻ አካላት በዓላቱን ለዓለም ይበልጥ ማስተዋወቅ እንደሚኖርባቸው ገልጸው፤ የቱሪዝም ዘርፉ ይበልጥ ተጠናክሮ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው እያደገ እንዲመጣ እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዓላቱ ቱሪስቶችን ከመሳባቸውም በላይ በኢትዮጵያ ያለውን የቱሪዝም ዕምቅ አቅም ለማሳወቅና ሀገርን ለዓለም ለማስተዋወቅ ይረዳል። ሀገሪቱን በልማት ወደፊት ለማምጣት ቱሪዝም አንዱ መንገድ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህ ደግሞ ከመንግሥት በተጨማሪ ባለሃብቶችና ኅብረተሰቡ የጀመሩትን ጥረት ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን መስከረም 15/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You