ሁኔታ የማይፈታው ስልታዊ ትብብርና ወዳጅነት

 ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እና የቻይና ግንኙነት በየጊዜው ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ እያደገ የመጣ ብቻ ሳይሆን፤ አሁን ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ ያለ ወዳጅነትና ትብብር ሆኗል። በዚህም የሀገራቱ ሕዝቦች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል፡፡ በቀጣይም ሀገሮቹ የሚኖሯቸው ግንኙነቶች በመተማመን ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ጠንካራ መሰረት ጥሏል።

የረጅም ዘመን የሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪክ ባለቤት የሆኑት ሁለቱ ጥንታዊ ሀገራት፣ አሁን የደረሱበት የግንኙነት ምዕራፍ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን እና አብሮ ማደግን መርህ ያደረ፣ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ራሳቸውን ሆነው ለማደግ መሻት ላላቸው የዓለም ሀገራት እና ሕዝቦች ተስፋ የሚሆን ውጤታማ ተሞክሮ ተደርጎም ይወሰዳል።

በተለይም ለዘመናት በድህነትና ኋላቀርነት ምክንያት ብዙ ዋጋ ለመክፈል ለተገደዱ፣ ከዛም በላይ ከድህነትና ከኋላቀርነት ለመውጣት የሚያደርጓቸው ጥረቶች በብዙ ተግዳሮቶች ሳቢያ ከስኬት ለራቀባቸው የአፍሪካ ሀገራት ሕዝቦች፣ ይህ አይነቱ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት በአዲስ መነቃቃት ነገዎቻቸውን ተስፋ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳ ነው።

ለዚህም የቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭ በአፍሪካ መሰረተ-ልማት እድገትና የንግድ ትስስር እንዲጎለብት እያደረገ ነው፤ በአፍሪካ በርካታ የስራ እድሎችን በመፍጠር ረገድም የጎላ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በአህጉሪቱ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት ሀገራት እርስ በእርስ እንዲተሳሰሩና ግንኙነታቸው እንዲጠናገር አድርጓል፣ ለአፍሪካ የመዘመን አጀንዳ አማራጭ የልማት ካፒታልን፣ ቴክኖሎጂንና ልምድን አምጥቷል።

ፍትሀዊነት የጎደለውን አሁነኛ የዓለም ስርዓት አግባብ ባለው መልኩ በመግራት፤ ዓለም ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ልትተዳደር የምትችልበትን፣ በብዙ ኢፍትሀዊነት የከፋ ዋጋ እየከፈሉ የሚገኙ የዓለም ሕዝቦች ካሉበት ሰቆቃ የሚወጡበትን ዓለም አቀፍ ስርዓት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ግብአት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ይህ ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ የሚገኘው የኢትዮ- ቻይና ግንኙነት ከሁለቱ ሀገራት ባለፈም ለቻይና አፍሪካ እና ለደቡብ- ደቡብ ትብብር ጉልበት የሚፈጥር፣ በቀጣይ ዘመናት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን በትብብር /በሕብረት /አሸንፎ ለመሻገር የሚያስችል ትልቅ አቅም መፍጠር የሚያስችል ተምሳሌነትም ነው።

በተለይም ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን በመሆን ካሉበት ድህነትና ኃላቀርነት ለመውጣት በእልህ ለጀመሩት ድህነትን ታሪክ የማድረግ የልማት ጉዞ ስኬት ትልቅ ተስፋ ይጣልበታል፤ ለዚህም እስካሁን የቻይና ባለሀብቶች በሀገሪቱ ስራ ላይ ያዋሉት መዋለ ነዋይ፤ በዚህም እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ መነቃቃትና እድገት በተጨባጭ ሊጠቀስ ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአይሲቲ፣ በማዕድን ልማት እና በቱሪዝም ዘርፍ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በማድረግ ላይ ያሉት ሰፊ ተሳትፎ ዘርፎቹን በተሻለ መልኩ በማልማት ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ስኬት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። የዘርፉን የቴክኖሎጂ ሽግግር በማፋጠን በኩልም ያለው አበርክቶ ከፍተኛ ነው።

የሀገሪቱ የፋይናንስ ተቋማትም ቢሆኑ ለልማታችን የሚያስፈልገንን ገንዘብ የፋይናንስ መርህን እና ወዳጅነትን ብቻ መሰረት ባደረገ መንገድ በማቅረብ/ይህን አድርግ አታድርግ በማይል መልኩ/ለሀገራችን ያላቸውን አጋርነት በተጨባጭ አሳይተዋል። በዚህም እንደ ሀገር ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያጋጥሙ የፋይናንስ ተግዳሮቶች እየቀነሱ ይገኛሉ።

አሁን ላይ የሁለቱ ሀገራት ግኝኙነት የሕዝቦቻቸውን የጋራ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ዓለም አቀፍ ተምሳሌት እየሆነ መጥቷል። የቻይና መንግስትም ሰሞኑን ይህ ሁሉን አቀፍ ፅኑ ግንኙነት፤ ሁኔታ ወደ ማይፈታው ስልታዊ ትብብር እና ወዳጅነት ደረጃ ከፍ ማለቱን አብስሯል። ይህ ደግሞ በእጅጉ የሚበረታታ ትልቅ የጋራ ተጠቃሚነት ስኬት ነው።

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You