ለኮሚሽኑ ተልዕኮ ስኬት ዜጎች ለአካባቢያዊና ሀገራዊ ሰላም ተግተው ሊሠሩ ይገባል!

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉት አለመግባባቶች እና ግጭቶች በሰከነ መንፈስ ቁጭ ብሎ ካለመነጋገር የመነጩ ናቸው። በተለይም በፖለቲከኞች እና በልሒቃን መካከል ያለው አለመተማመን እና ጥርጣሬ የችግሩ መሠረታዊ ምንጭ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ይህ ደግሞ ሀገሪቱ በየወቅቱ የምታደርገውን የዴሞክራሲ የሽግግር ሂደት ፈታኝ አድርጎታል።

ይህንን ሀገራዊ ችግር ለዘለቄታው ለመፍታትና ሀገሪቱን ከግጭት አዙሪት ለመታደግ፤ መንግሥት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ አቋቁሞ ወደ ሥራ የሚገባበትን የተመቻቸ ሁኔታ ፈጥሯል። ኮሚሽኑም ከተቋቋመ ማግስት ጀምሮ ከፍ ባለ ኃላፊነት መንፈስ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ለሥራው ስኬታማ የሆኑ ሰፊ ሥራዎችን በማከናወን አሁን ላይ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

ኮሚሽኑ ሆነ የኮሚሽኑ አባላት ምንም አይነት የፖለቲካ ወገንተኝነት በሌላ መልኩ፣ ከማንኛውም የመንግሥት ወይም ሌላ አካል ተጽዕኖ ነጻ ሆነው መንቀሳቀስ የሚችሉበት ሕጋዊ ሰውነት ተላብሰው እንዲቋቋሙ መደረጉ ተልዕኳቸውን ስኬታማ በሆነ መልኩ በታማኝነት እንዲወጡ ትልቅ አቅም ሆኗቸዋል።

የኮሚሽኑ ምሥረታ ሆነ ሀገራዊ እንቅስቃሴው በአገሪቱ መተማመን የሰፈነበት የፖለቲካ ሥርዓት ለመመሥረት አንድ ትልቅ ርምጃ ተደርጎ እየተወሰደ ነው፤ አካታችና ውጤታማ ሀገራዊ ምክክር በማድረግ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሥርዓት ዘመኑን በሚዋጅ ፅኑ መሠረት ላይ ሊያዋቅር እንደሚችልም ብዙ ተስፋ ተጥሎበታል ፡፡

ይህንን እውነታ ታሳቢ በማድረግም፤ መላው ሕዝባችን የኮሚሽኑ ተልዕኮ ውጤታማ እንዲሆን፣ በተሳትፎ አጋርነቱን እያረጋገጠ ይገኛል። ለዚህም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተሳታፊዎች ምልመላ ዙሪያ የሚታየው የነቃ ተሳትፎ ተጨባጭ ማሳያ እንደሆነ ይታመናል ።

ከዚህ በተጨማሪም የሀገሪቱ የቆዩና አሁነኛ ችግሮች በሰላማዊ ውይይት ዘላቂ መፍትሔ ሊኖረው እንደሚችል የሚታመኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ ለመሥራት እያሳዩት ያለው ቀና ትብብር፤ ለኮሚሽኑ ተልዕኮ ስኬት ዋነኛ አቅም ስለመሆኑ ብዙም የሚያጠያይቅ አይሆንም ።

በኢትዮጵያ ሊኖር የሚችል ሰላማዊ እና የተረጋጋ የፖለቲካ ምሕዳር ለቀጣናው ሀገራት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብር ትልቅ አቅም ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። ከዚህ የተነሳም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለኮሚሽኑ ተልዕኮ ስኬታማነት ከምሥረታው ጀምሮ እያበረከተ ያለው አስተዋፅዖ ከፍ ያለ እውቅና ሊሰጠው የሚገባና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የኮሚሽኑን መቋቋም ከመደገፍ አንስቶ፣ ከ10 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። የገንዘብ ድጋፉ ኮሚሽኑ ለሥራ ማስፈጸሚያ የሚፈልገው ገንዘብ አንጻር ብዙ ነው የሚባል ባይሆንም፤ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው።

ከገንዘብ ድጋፍ ባሻገር ተመድን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቀማት ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለኮሚሽኑ የእውቀት፣ የሀሳብ፣ የበጀት እና ሌለችንም ሁለንተናዊ ድጋፎች እያደረገ ያለበት ሁኔታ፤ እንደ ሀገር ለችግሮቻችን በራሳችን መፍትሔ ለማፈላለግ ለጀመርነው ጥረት ስኬት ትልቅ አቅም ነው፡፡

ይህ ጥረታችን ስኬታማ እንዲሆን ግን ከሁሉም በላይ አሁናዊ ሰላም የሚኖረው አስተዋፅዖ የማይተካ ነው። ከዚህ የተነሳ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሰላም እናቶችና ወጣቶች፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች/ ሁሉም ዜጎች ከምንጊዜውም በተጠናከረ መልኩ አካባቢያዊና ሀገራዊ ሰላም ለማስፈን ተግተው ሊሠሩ ይገባል ።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2016

Recommended For You