እምቅ የቱሪዝም ሀብታችንን ለማልማት ቆርጠን እንነሳ

ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት የበርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች ባለቤት፤ ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች ሀገር ናት። እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች የየራሳቸው መለያ የሆኑ ባሕላዊ እሴቶች፣ ቅርሶች፣ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ሥነ- ቃል፣ ወግ፣ ዕምነት፣ እሴትና ሥነ-ጥበብ አሏቸው።

ይህም ሀገሪቱን በሚዳሰሱ (ታንጀብል) እና በማይዳሰሱ (ኢንታንጀብል) ባሕላዊ ቅርሶች ሀብት የበለጸገች አድርጓታል፡፡ በዚህ ረገድ ሀገሪቱ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርሶች መዝገብ ዘጠኝ የሚዳሰሱ (ታንጀብል) እና አራት የማይዳሰሱ (ኢንታንጀብል) ባሕላዊ ቅርሶችን በድምሩ 13 ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ናት።

ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ የቅድመ ሰው ዘር መገኛ ሀገርም ናት። የኢትዮጵያውያን ብሎም የዓለም ሕዝብ ቅድመ አያት የሆነችውን የሦስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዓመት እድሜ ባለቤት ድንቅነሽ (ሉሲ)፣ የአራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዓመት እድሜ ባለቤት አርዲና የሦስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዓመት እድሜ ያስቆጠረችው ሰላም የቅድመ ሰው ዘር መገኛ፤ የቅድመ ታሪክ ቅርሶች ባለቤት ናት።

የነዚህ ሁሉ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከፍ ያለ አቅም ሊሆኑ የሚችሉ ሀብቶች ባለቤት ብትሆንም፤ እነዚህን ሀብቶች በማልማት ተጠቃሚ በመሆን ያላት ተሞክሮ ግን ሲታይ፤ ከዚህ ግባ የማይባል የቱሪዝም ሀብት ካላቸው ሀገራት ያነሰ ስለመሆኑ መረጃች እና የተለያዩ ጥናቶች በስፋት ያሳያሉ።

ለአብነት ከኤስያ ሀገሮች አንዷ የሆነችው ታይላንድ ያላትን ብርቅየ የነብር ዝርያ ላይ ትንሽ ኢንቨስት በማድረግ ለዓለም ሕዝብ በስፋት በማስተዋወቅ፤ የምታገኘው ገቢ ኢትዮጵያ ከጠቅላላው የቱሪዝም ዘርፏ ከምታገኘው ገቢ በእጅጉ ይልቃል።

እንደ ዓለም ቱሪዝም ድርጅት መረጃ የብርቅየ ነብር ዝርያ መገኛ የሆነችው ታይላንድ እ.ኤ.አ በ2019 ብቻ 39 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዓለም አቀፍ ቱሪስት ጎብኝቷታል። በዚህም 60 ሺህ 521 ሚሊዮን ዶላር ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ደረሰኝ (Internation­al tourism receipts) ወይም ገቢ አግኝታለች።

ሌላኛዋን የኤስያ ሀገር ቻይና በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ግንባታ ላይ ማኅበረሰቡ በተለያየ መንገድ እንዲሳተፍ በማድረግ የቱሪስት መዳረሻዎቹዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት እንዲተዋወቁ ማድረግ ችላለች፡፡ በዚህም የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶቿን/ሀብቶቿን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ በዘርፉ ከፍ ያለ ተጠቃሚ ሆናለች፡፡

በአንድ ሰማይ እልፍ ከዋክብት እንደሚደምቁ ሁሉ፤ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር እልፍ የቱሪዝም ሀብት እያሉ በአግባቡ ማየት፣ ማልማት እና ማስተዋወቅ ባለመቻላችን ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ማግኘት ሳትችል ቀርታለች ።

የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ፣ የ900 ዓመት ብራና ቅርስ፣ የራሷ የዘመን አቆጣጠር፣ …ወዘተ ዘርፈ ብዙ የባሕልና የቱሪዝም ሀብት ባለቤት የሆነችው ሀገራችን፤ የ200 ዓመት ታሪክ እንኳን ከሌላቸው ሀገራት እኩል ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም።

ለዚህም ደግሞ የአሜሪካንን እና የፈረንሳይን ተጨባጭ እውነታ መቃኘት በቂ ነው፤ እንደ ዓለም ቱሪዝም ድርጅት መረጃ አሜሪካ እ.ኤ.አ በ2022 ብቻ 50 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዓለም አቀፍ ቱሪስት ጎብኝቷታል። ከዚህም 135 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ደረሰኝ (International tourism receipts) ወይም ገቢ አግኝታለች።

በፈረንሳይ የቱሪዝም ዘርፉ እ.ኤ.አ በ2013 ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) 79 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዩሮ በቀጥታ አበርክቷል። ይህ ከኛ ሀገር ጋር ሲነጻጻር /በተያዘው በጀት ዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ከተያዘው እቅድ ጋር ሲነጻጸር/ምን ማለት እንደሆነ ለማገናዘብ የሚከብድ አይደለም።

ሀገሪቱ ባሏት የቱሪዝም ሀብቶች አሁን ላይ በሀገሪቱ ፈተና እየሆነ ያለውን የሥራ አጥነት መቅረፍ የሚያስችል የሥራ ዕድል መፍጠር፣ በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የሥራ ባለቤት ማድረግ እንደሚቻል ይታመናል። ሀገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በምታደርገው ጥረትም ዘርፉ ሊኖረው የሚችለው አበርክቶ ከፍ ያለ ነው።

ስለዚህ በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር በመቅረፍ፤ ሀገሪቱ እንደ ሀገር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ከሁሉም በላይ በዘርፉ ያላትን ሀብት ማወቅ፤ ማልማትና ማስተዋወቅ ይገባል።

ከዚህ አኳያ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን ሀገር አቀፍ የቱሪዝምና የሆስፒታሊቲ ዐውደ- ርዕይን በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ “አሁን ጊዜው ድህነትን የምንታገልበት ብቻ ሳይሆን በተለይ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት በማውጣት በጋራ የምንለማበት ወቅት ነው።

…. እኛ ከቅንነትና ከትጋት በስተቀር ያጣነው የለም። ስለዚህ ዓይናችን ገልጠን ማየት፣ ያየነውን በማልማት እንዲወጣ ከማድረግ ባለፈ ማስተዋወቅና የአገልግሎት አሰጣጣችን ማሳደግ ከቻልን በጋራ እንለማለን” ብለዋል።

በመሆኑም በተለይ የለውጡ መንግሥት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የመዳረሻ ስፍራዎች በማልማት፣ በማስተዋወቅ፣ ጎብኚዎችን በመሳብና አዳዲስ መዳረሻዎችን በመፍጠር ከኃያላኑ ተርታ የሚያሰልፍ ጠንካራ ኢኮኖሚ መፍጠር እንደሚቻል አምኖ፤ በዘርፉ እያከናወነ ያለውን ልማት አጠናክሮ ማስቀጠል ይኖርበታል። ነገ ላይም የልማቱ ግንባር ቀደም ተጠቃሚ የሚሆነው ማኅበረሰቡ በመሆኑ ልማቱን በሚችለው ሁሉ ሊደግፍ ይገባል።

ከዚህ በተጨማሪ ከአዳዲሶቹ የመዳረሻ መስሕብ ስፍራዎች ባሻገር፤ ነባር ባሕላዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ ሃብቶችን እንዲሁም ያልተዳሰሱ አዳዲስ የቱሪዝም መስሕቦችንና ዘርፎችን ከተቀበሩበት አውጥቶ በሚገባ አልምቶ፣ አስተዋውቆና ጠብቆ የሀገርንና የዜጎችን ገቢ ማሳደግ ለነገ የማይባል የሁሉም ዜጋ የቅድሚያ ቅድሚያ ሥራ መሆን ይኖርበታል።

 ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2016

Recommended For You