የነፃነታችን ምልክት፣ የጥንካሬያችን ሐውልት የድላችን አርማ

አገር የእናት ተምሳሌት ናት። አገር ያለመስፈርት በሙሉ ልብ የምትወደድ የእናት አምሳያ ጌጥ ናት። የእናትና ሀገር ፍቅር አይለካም። ጥልቀትና ርቀቱም አይታወቅም። ማንም ጤነኛ አእምሮ ያለው እናቱ ምንም ትሁን ምን አክብሮ ያተልቃታል እንጂ ንቆ አያሳንሳትም። ጀርባውን አይሰጣትም።

ለኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ እናት እና የሕልውናቸው መሰረት ናት። እሷ ወድቃ እነርሱ አይቆሙም። እሷ እያዘነች እነሱ አይደሰቱም። እሷን ረስተው እነርሱ አይታወሱም። እሷ ከሌለች የእነርሱ በሕይወት መቆየት ትርጉም አልባ ነው።

ለኢትዮጵያውያን አገራቸው የነፃነታቸው ምንጭ ናት። የሚኖሩት በእሷ ተከብሮ መቆየት ውስጥ ነው። እርሷ ሰላሟን አጥታ ሕሊናቸው አትረጋጋም። ኢትዮጵያ ጎድሎባት እነርሱ አይሞላላቸው። እርሷ ዝቅ ብላ እነርሱ አይገዝፉም። የሚኖራቸው አገራቸው ሲኖራት ነው። ያለ ኢትዮጵያ የሚበሉት አይጣፍጣቸውም። የሚጠጡት አያረካቸውም።

አገር ውስጥ እንዳለው ሁሉ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊም ከምንም በላይ የአገሩን ፍቅር በልቡ ይዞ የሚኳትንና በአካል ርቆ ቢገኝም በመንፈስ ሁሌም ኢትዮጵያ የሚገኝ ነው። አብዛኛው አገሩን የሚወድ፣ አገሩ ተሻሽላና አድጋ ማየት የሚፈልግ፣ አንድ ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትኖር ከልብ የሚመኝና ለዚያም የሚታገል ነው።

ኢትዮጵያውያንም መቼም ቢሆን ለአገራቸው ያላቸው ፍቅርና አክብሮት የሚለወጥ አይደለም። ልባቸውን እንጂ ጀርባቸው የሚሰጡም አይደሉም። እድገቷን እንጂ ዝቅታዋን፣ ደስታዋን እንጂ ሃዘኗን፣ ክብራን እንጂ ውርደታን ፈፅሞ አይመኙም።

የኢትዮጵያውያን የሀገር ፍቅር ሁሌ እንደጋለ ሳይቀዘቅዝ የሚኖር ፍም እሳት ነው። ኢትዮጵያውያንም ሀገራቸውን የነኩባቸው ዕለት ትንታግና አይነኬ አራስ ነብር እንደሚመስሉ፣ በሀገራቸው ለመጣ ሞትን እንደ ሰርግ የሚቆጥሩ ህዝቦች ናቸው።

ኢትዮጵያውያን በሰላሙም ሆነ በጦርነቱ ወቅት ለሰንደቅ ዓላማቸው ያላቸው ጥልቅ ፍቅርና ልባዊ ክብር እጅግ አስደናቂ ነው። ኢትዮጵያ እንደቀዳሚና ገናና ስልጣኔዋ ሁሉ የረጅም ዘመን የሠንደቅ ዓላማ ታሪክ ያላት ሀገር ናት። ለበርካታ ሺ ዓመታት ከሰንደቋ ሳትፋታ፣ ከአርማዋ ሳትለያይ፣ ጠላቶቿን ድል እያደረገች ምልክቷን ከፍ አድርጋ እያውለ በለበች ዛሬ ላይ ደርሳለች።

እንደሚታወቅ ሠንደቅ ዓላማ የአንድ ሕዝብንና መንግስት ሉአላዊነት፣ ስልጣንና ነፃነት ምልክት ወይም ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። የሠንደቅ ዓላማ የአገር እና የሕዝብ ምልክት ነው። ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ምልክት በመሆኑ ከሰንደቅ ዓላማው ፊት በቆመ ቁጥር የሃገሩ ምስል የማይከሰትበት ሰው የለም። ከዓለም ታሪክ እንደምንረዳው ሃገራትና ዜጎች ከቀኝ ግዛት ተፅዕኖ ሲላቀቁ መጀመሪያ ከፍ አድርገው የሚያሳዩት ሰንደቅ ዓላማቸውን ነው።

ሕዝቦችና አገራት በሰላም አደባባይም ሆነ በጦር ሜዳ ውሎ ለድል ሲበቁ ቅድሚያ የሚሰቅሉት ሰንደቅ ዓላማቸውን ነው። ይህን በማድረግም ሉዓላዊነታቸውን ፍቅርና ክብራቸውን እጅግ ከፍ ባለ መልኩ ለሰንደቅ ዓላማቸው ይገልፃሉ።

የአንድን አገር ሕዝብ በውስጡ የተለያየ ሃይማኖት፣ ቋንቋና ነገድ ቢኖርም፤ በአንድነት የሚያቆመውና እንደ አንድ ጥላ ሆኖ ከሚያሰባሰበው አንዱ መለያ ዓርማው ወይም ምልክቱ ሰንደቅ ዓላማ ነው። ሰንደቅ ዓላማ ክቡር ነው። የእያንዳንዱ አገር ዜጋ ለሰንደቅ ዓላማው ክብር ይሞታል። ለሰንደቅ ዓላማቸው የተሰውም በክብር ይታውሳሉ። የክብር ሜዳሊያ ይሸለማሉ።

ለኢትዮጵያውያንም ሰንደቅ ዓላማ ትርጉሙ ረቂቅ፣ ዋጋውም የላቀ ነው። በኢትዮጵያ ሰንደቅ ውስጥ ጠላትን የሚያርድ ወራሪን የሚያርበተብት መግነጢሳዊ ኃይል አለ። ከፍ ሲያደርጉት አሸናፊነትን ዝቅ ሲያደርጉት ሽንፈትን የሚያላብስ፣ ያከበሩትን የሚያገን፣ የሚጠሉትን የሚያወርድ ረቂቅ ኃይል አለ።

ኢትዮጵያውያን በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ሰንደቃቸው፣ ልምላሜያቸውን፣ ተስፋቸውንና እንዲሁም ድል አድራጊነታችንን ይገልፁበታል። ለኢትዮጵያውያን ሰንደቃቸው በርካቶች ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸው ከስክሰው የጠበቁት የነፃነታቸው ትርጉም፣ የድላቸው አርማ፣ የኩራት፤ በራስ የመቆም፣ የአንድነታቸው ምስጢር ብሎም ምልክት ናት።

የኢትዮጵያ አርበኞች ኢትዮጵያን ከወራሪዎች ለመከላከል በየቦታው ሲፋለሙ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማቸውን አስቀድመው ነው። ሰንደቅ ዓላማውን ከነ ክብሩ ከትውልድ ትውልድ ለማስተላለፍ ብዙ ደምና አጥንት ተከፍሎበታል።

ብዙዎች ክብሯ እንዳይገፈፍ፣ ከከፍታዋ ዝቅ እንዳትል እና በወራሪ እንዳትዋረድ ከአንቺ በፊት እኔ በለው ደማቸውን አፍስሰውላታል። ጸሐፊያን በብዕራቸው፣ ሙዚቀኞች እና ከያኒያን በህልቆ መሳፍርት ጥበብ ብዙ ተቀኝተውላታል። አትሌቶቻችን በዓለም አደባባይ በድላቸው ክብሯን ከፍ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የቅኝ ግዛት ቀንበር መስበሪያ፣ የአፍሪካ የነጻነት ዓርማ፣ በርካታ ሀገራት እንደየራሳቸው አቀማመጥ ቀለሞቿን የተጋሩላትም ናት። የጀግንነት ዓርማ የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት ናት። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የነፃነትና የአልበገር ባይነት ዓርማ ተደርጎ ስለሚወሰድ በርካታ የአፍሪካ ሀገራትም ነፃነታቸውን ባገኙ ጊዜ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለምን በሰንደቅ ዓላማቸው ውስጥ አካተውታል።

የኢትዮጵያ ሠንደቅ የነጻነት ማህሌት፤ የትብብር መገለጫ የጭቁኖች አንደበት ናት። የሃይላችን አቅም የአንድነታቸው መዘውር ናት። የጥንት አባቶች ቅኝት የእናቶች ስሪት፣ የኢትዮጵያዊነት የነጻነቱ ጉልበት ናት። የነፃነትን ምልክት፣ የጥንካሬ ሃውልት፣ የድል አርማ ናት።

ሰንደቅ ዓላማ የሀገርና የህዝቦችን ፍላጎት፣ ራዕይ፣ ዓላማ፣ የተግባር እርምጃና ተጨባጭ ውጤት ዓርማ፡ በመሆኑም የእያንዳንዱ ዜጋ ፍላጐትና ሕይወት ይነካል። ሰንደቅ ዓላማ የሚለው መጠሪያ ከሁለት ቃላቶች የተመሰረተ ነው። ይህም “ሰንደቅ” እና ”ዓላማ” ከሚሉ ቃላቶች የተመሰረተ ነው።

የቃላቱ የተናጠል ትርጉም፡- ሰንደቅ፡- ማለት ምርኩዝ፣ ምሰሶ፣ በትር ማለት ሲሆን- ዓላማ፡- ማለት ምልክት፣ አቋም፣ ስብስብ እንዲሁም የነፃነት፣ የሉዓላዊነት ምልክት ማለት ነው። የሁለቱ ቃላት ጥምረት “ሰንደቅ ዓላማ” የሚለው ቃል በአንድ ላይ የአገር መታወቂያ፣ የሕዝብ አንድነት መጠበቂያ እንዲሁም የክብር መለያ ምልክት የሚለውን ትርጉም የሚሰጥ ነው።

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 3 ላይ ስለሃገሪቷ ሰንደቅ ዓላማ ተደንግጎ ይገኛል። በዚሁ አንቀፅ ስር የሃገሪቷ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሐሉ ብሔራዊ ዓርማ እንደሚኖረው ደንግጓል።

ከዚህም በተጨማሪ በሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ይገልፃል።

በሕገ መንግስቱ በጠቅላላ መርህ የተደነገጉትን ነገሮች በዝርዝር ለመፈጸም ይረዳ ዘንድም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ የሰንደቅ ዓላማ አዋጆችን አውጥቶ በስራ ላይ አውሏል። ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተሻሻለው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ እንደሚከበር ተደንግጓል።

ሰንደቅ ዓላማ ቀን ባለፉት ዓመታት በተለያየ መርሃ ግብር ሲከበር መቆየቱ ይታወሳል። ዘንድሮም ለ16ኛ ጊዜ ትናንት““የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለሕብረብሔራዊ አንድነታችንና ሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው!” በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ውሏል።

ባለፉት ዓመታት የሠንደቅ ዓላማ ቀን መከበርም የሕዝብና ሰንደቅ ዓላማ ይበልጥ በፍቅር ለማስተሳሰር የአገር ፍቅር ስሜትን ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉ ሁላችንንም የሚያስማማ ነው። ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ከሰንደቅ ዓላማ አያያዝና አጠቃቀም እንዲሁም ሥነ-ሥርዓቶች ጋር በተያያዙ የሚፈፀሙ የግንዛቤ ክፍተቶች፣ ድክመቶች ብሎም ጥፋቶችን መቀነስም አስችሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቀደም ባሉት ዓመታት ውዝግብ ከሚያስነሱት ምክንያቶች አንዱ፣ የአገር መሪዎች ከመቀየር ስር በስር ተከትሎ የሚደረገው የዓርማ ለውጥ እንደነበር እሙን ነው። የመንግስት ለውጡን ተከትሎ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ወገኖች ዘንድ ጉዳዩ እየተነሣና እየተጣለ የሚገኝበት አግባብ ይስተዋላል። ጉዳዩን በተመለከተ ያለው ግንዛቤና ሙግትም ተጣጡፋል።

ሠንደቅ ዓላማን መሠረት ያደረጉ ውዝግቦች ከተከሰቱ ዋል አደር ቢሉም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጉዳዩን አስመልክቶ በዝቅተኛ ደረጃ የሚታይ በተለያዩ ቡድኖች መካከል የሚከሰት እሰጣ ገባ ከፍ ሲልም ግጭት መስተዋልም ጀምሯል።

ሠንደቅ ዓላማን መነሻ ያደረጉ የተለያዩ ወዝግቦች በተለያዩ ወቅቶች ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ መከሰታቸውም አይካድም። ይሑንና ይህ አደገኛ አካሄድ ዛሬ በዝቅተኛ ደረጃ የሚታይ ይምሰል እንጂ አስቸኳይ መፍትሄ ካልተፈለገለት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንደማይሻገር እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

ይሁንና ለአገራችንና ለሰንደቅ ዓላማ ክብር ካለን መሰል ውጥረት አደገኛ መሆኑን ጠንቅቀን መረዳት ይኖርብናል። ልዩነቶችና ችግሮች እንኳን ቢኖሩ በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰብስቦ መፍትሄ መፈለግና ውይይትን ቀዳሚ አማራጭ ማድረግ ይገባል።

እኛ ያልነው ብቻ ልክ ነው ሌሎችን አትስሙ በሚል፣ ከግዙፉ ነጭ ይልቅ ነጥባን ጥቁር በማጉላት የአገርን ጉዞ ለማደናቀፍ የድንጋይን ሚና መያዝም ተገቢ አይደለም። ኢትዮጵያ ካሰበችው እንድትደርስ እንደ ጎልያድ መንገድ መዝጋትም አያዋጣም።

ኢትዮጵያ ክብሯ ተጠብቆ በዓለም ላይ ያላት ተሰሚነት ተጠብቆ እንዲኖር ጠንካራ ሀገራዊ አንድነት መገንባት ግድ ይላል። በተለይ ወጣቱ ትውልድም ከመለያየትና እርስ በርስ ከመገፋፋት ወጥቶ ለሀገሩና ለሰንደቅ ዓላማው ክብር ዘብ ሆኖ መቆም ይኖርበታል።

ስለ ምልክት ሳይሆን ስለሀገር ከልብ ልናስብም ልንጨነቅ ይገባል። ሰንደቅ ዓላማ መስቀል ብሎም ስለ ሰንደቅ ዓላማ መነጋጋር እና መከራከር የምንችለው ከሁሉ በላይ ሀገር ሲኖር ነው። ሀገር ከሌለ ግን ሰንደቅ ዓላማ ብቻውን ትርጉም የለውም።

ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት ከሚያፈርስ ይልቅ የሚያድስ፣ የመከፋፈል ፋሽን ተቀብሎ የመለያየትን ሰንደቅ ዓላማ የማያውለበልብ ትውልድ ትሻለች። ቀዳዳዋን ከመስፋት ይልቅ የሚያጠብላት ትውልድን ትፈልጋለች። የሚያፈርስ ሳይሆን የሚገነባት፣ ጥላቻን፣ መሃይምነትን፣ ቂም በቀልን እንትፍ የሚል በጎ ምግባርንና መልካም ስራን እፍ ብሎ የሚያቀጣጥል ትውልድ ትሻለች።

ሰንደቅ ዓላማ በዓልን ስናከብርም ምሬቷን በሀሴት ለመቀየር፣፡ መከፋቷን በደስታ ለመለወጥ፣ ዝቅታዋን ለሚመኙ ከፍታዋን ለማሳየት፣ ወዟን ከሚነጥቁ ውበቷንም ከሚሰርቁ ለመታግ የምንታገልለት ሊሆን ይገባዋል። በኢትዮጵያ ክብሯ የመጣ በሰብዕናችሁ እንደመጣ በማሰብ፣ እርሷን የነካ አይናችሁን የነካ እንደሆነ በመረዳት፣ እጅ ለእጅ ይበልጥ በመያያዝ አስተማማኝ ምርኩዝ ልንሆንላት ግድ ይላል።

ከትላንት እስከ ዛሬ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነፃነት በደማቸው ጠብቆ አቆይቷል፣ ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ አድርጓል። የዛሬ ትውልድ በአባቶቹ የሕይወት መስዋዕትነት ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ የቆየችውን ሀገር በላቡ ማፅናት ይጠበቅበታል።

የሰንደቅ ዓላማ በዓልን ስናክበርም ተናበንና ተደራጅተን በተባበረ ክንድ በተለይም ለብሔራዊ አንድነታችንና ሉአላዊነታችን ያለንን ቁርጠኝነት በሰንደቁ ፊት ዳግም ቃላችንን የምናድስበት ሊሆን ይገባል።

በመላ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ሆነ የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም ሆነ ነገ ከሚያስጎነብሷት በመጠበቅ፣ የተበተባትን ሰንሰለት መበጣጠስና የተቆለለባትን የሴራ ተራራ የመናድ ትግል ይበልጥ አጠንክረው መቀጠልን ሊዘነጉ አይገባም።

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር !

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2016

Recommended For You