ሀገር ወዳድነት የሀገር ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ከማክበር ይጀምራል!

ሀገር ያለ ሕዝብ፤ ሕዝብም ያለ ሀገር አይገለጡም። ሀገር ያለ ነዋሪ፤ ነዋሪም ያለ ሀገር መልክም፣ ስምም አልባ ናቸው። ይህ ስምና መልክ ደግሞ የጋራ ወካይ ዓርማ አለው። ሀገር እንደ ሀገር፣ ሕዝብም እንደ ሕዝብ በዓለም አደባባይ የሚወክሉበትና የሚገልጹበት ይህ ዓርማ (ምልክት) ሰንደቅ ዓላማ ነው።

የሰንደቅ ዓላማ ውክልና ከስም በላይ ፤ የሀገር ሉዓላዊነት፤ ክብር፣ ጀግንነት፤ ብልጽግና እና ኃያልነት የሚገለጽበት፤ በዘመናት ሂደት ውስጥ አንድ ሀገርና ሕዝብ ያላቸውን ከፍታ እና ነጻነት፤ እድገት እና ልዕልና፤… የታሪክ ትርክት ተሸክሞ በውክልና ከፍ ብሎ የሚውለበለብ የሁለንተናዊ ማንነት መገለጫ ነው።

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንም በዚሁ አግባብ የሚወከሉበት ብቻ ሳይሆን፤ ዘመን የማይሽረው፣ ትውልድ ሳይዘነጋ የሚዘክረው፣ ዓለም በደማቁ በታሪክ ድርሳኑ ከትቦ ያኖረውን ዘርፈ ብዙ ገድል የፈጸሙበትን መወድስ ነጋሪ ሰንደቅ ዓላማ ባለቤት ናቸው። በዚህም ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ከትናንት እስከ ዛሬ በዘመን ሂደት ውስጥ ትውልድ እየተቀባበለ በሉዓላዊነት ከፍታው ላይ ባኖረው ዓርማ እየተገለጹ የኖሩ/የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው።

ብርሃናማ ጨረር ያለው ሰማያዊ ዓርማ (በእኩልነት ያጌጠውን የኢትዮጵያውያንን ብዝሃነት አመልካች የሆነ) ያፈረበት በአረንጓዴ (ልምላሜን ገላጭ)፣ ቢጫ (ተስፋን ወካይ) እና ቀይ (በመስዋዕትነት የመጽናትን ልዕልና) ገላጭ በሆኑ የሰንደቁ ሦስት ቀለማት ደምቆ የሚገለጸው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ፤ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር፣ ኢትዮጵያውያንንም እንደ ሕዝብ በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጎ የሚገልጽ ሕያው ምልክታቸውና መልካቸው ነው።

ይህ ምልክት ስለ ሀገር ሉዓላዊነትና ነጻነት ሲባል ዋጋ የተከፈለበት፤ ስለ ልማትና ብልጽግና፣ ስለ አብሮነትና እኩልነት፣ ስለ ሰላም እና ዴሞክራሲ፣… ሲባል ከፊት ቀድሞ የተውለበለበ የማንነት ማሰሪያ፣ የሕልውና ማብሰሪያ ነው። ኢትዮጵያውያን ለአብሮነታቸው በአብሮነት ዋጋ የከፈሉበትን፣ ስለ ሉዓላዊነታቸው በሕብር የተዋደቁበትን የመስዋዕትነታቸውን ገድል ሰንዶ የያዘ ነው።

ይህ ስለክብርና ነጻነት፤ ስለ አብሮነትና ብልጽግናቸው ሲሉ ከፊታቸው የሚያስቀድሙት፤ በፍቅር የሚጠብቁት ሰንደቅ ዓላማቸው፤ ከልብ በመነጨ የእኔነት ስሜት በብዙ አርበኞች የተጋድሎ የመስዋእትነት ታሪክ ከትናንት ዛሬ ደርሷል፤ ሀገርን ከመውደድና ከማስቀደም በሚመነጨው ብሄራዊ ማንነት እዚህ ደርሷል።

ኢትዮጵያውያን ሰንደቃቸውን በመዝሙር አጅበው ከፍ ሲያደርጉ እንባ የሚቀድማቸው፤ በዓለም መድረክም ከበዙ ሀገራት ዓርማ መካከል የራሳቸውን ሰንደቅ ፈልገው ሲያገኙ ደስታን በተመላ ፈገግታ ፊታቸው ደምቆ የሚታየው፤ በትውልዶች መንሰላሰል ብዙ ዋጋ የተከፈለበት የማንነታቸው ማሕተም የሆነው ሰንደቅ ዓላማቸው በልባቸው ስለታተመ ነው።

ይህ የራስም የሀገርም ገጽ የሆነ ሰንደቅ ዓላማ፤ በብዙ መስዋእትነት ትናትን በክብር ከፍ ብሎ ለዛሬ ደርሷል። ዛሬም ስለ ሀገር ልዕልና በሚከፈል ዋጋ ከፍ ብሎ እየተውለበለበ ነው። ነገም በዚሁ ክብርና ከፍታ እንዲዘልቅ ማድረግ ይገባል። ይህ እንዲሆን ደግሞ የሰንደቅ ዓላማን ክብር፣ የሰንደቅ ዓላማን ልዕልና፣ የሰንደቅ ዓላማን ውክልና፣… ለትውልዱ በወጉ ማስገንዘብ አስፈላጊ ነው።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሲከበርም ዓላማው ትውልዱ ስለ ሰንደቁ እንዲያውቅ ማስቻል ነው፤ ግቡም ሰንደቅ ዓላማውን በወጉ ተገንዝቦና አውቆ ተገቢውን ክብር የሚሰጥ፤ ለሰንደቁ መክፈል የሚገባውን ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጀ ትውልድ መፍጠር ነው።

‹‹እኔ የምወክለው በሰንደቅ ዓላማዬ ነው፤ ሀገሬም የምትገለጸው በሰንደቋ ነው›› የሚል ትውልድ መፈጠር ለአንድ ሀገር ሁሉን አቀፍ ብልጽግናና ልዕልና እውን መሆን ወሳኝ ነው። ከዚህ የተነሳም ሰንደቁን የሚያውቅም የሚያከብርም ትውልድ መፍጠር፤ ስለ ሰንደቁ ከፍታ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ትውልድ መገንባት የግድ ነው።

የሰንደቅ ዓላማ ቀንን እንደሀገር ስናከብር፤ የሀገር ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ከመውደድና ከማክበር፤ ባለፈ ለክብሩና ለሕልውናው የሚፈለገውንም ዋጋ ለመክፈል እራስን በማዘጋጀት ሊሆን ይገባል !

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2016

Recommended For You