‹‹አይበገሬ የሳይበር ደህንነት አቅም ለሀገር ሉዓላዊነት››

‹‹የዘመነ ዲጅታል›› ፈተናዎች ከሚባሉት አንዱ የሳይበር ጥቃት ነው። ጥቃቱም ሆነ ተብሎ ያልተፈቀዱ የኮምፒውተር ሥርዓቶች ፣ መሰረተ ልማቶች፣ ኔትዎርኮች ላይ አጥፊ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም በሕገወጥ መንገድ ዳታዎችን፣ መበዝበዝና አገልግሎት በማስተጓጎል የሚፈጸም ነው። ዲጅታላይዜሽን እየተስፋፋ በመጣ ቁጥር የሳይበር ጥቃት በዚያው ልክ ይከሰታል። ጥቃቱ መመከት ሳይቻል ቀርቶ ከተከሰተ ደግሞ የሚያስከትለው ውድመት ከፍተኛ ነው፤ በተለይ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል። ለዚህም ሀገራት ዲጅታላይዜሽን ከማስፋፋት ጎን ለጎን ጠንካራ የሳይበር ጥቃት መመከት የሚያስችል አቅም መገንባት እንደሚጠበቅባቸው የዘርፉ ምሁራን ያመላክታሉ።

ኢትዮጵያ በሀገሪቱ የሚሰነዘሩ ማንኛውንም የሳይበር ጥቃት ለመመከት የሚያግዛት አቅም ለመፈጠር እየሰራች ትገኛለች። ይህ ኃላፊነት የተሰጠው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር(ኢንሳ) ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ኃይል በመገንባት የሳይበር አቅም በመፍጠር ፣የሀገሪቱን ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን መሠረተ ልማት ከሳይበር ጥቃት በመከላከል የሀገሪቱን ዲጅታል ሉአላዊነት በማስጠበቅ ረገድ የበኩል ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።

ተቋሙ የሳይበር ሉአላዊነት ከማስከበር ሥራ በተጎዳኝ ጥልቅ የሆነ እሳቤ ይዞ በርካታ ሥራዎች እየሰራ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ይጠቅሳሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ የቴክኖሎጂና የእውቀት ባለቤትነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ተቋሙ ለዚህም ክልከላ ያለባቸውን ቴክኖሎጂዎች በማልማት ለሀገሪቱ የዲጅታልና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስፋፋት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ሶፍት ዌሮችን እና ሀርድ ዌሮችን በማልማትና የጸጥታና ደህንነት እንዲሁም የልማትና የመንግሥት ድርጅቶችን በማስታጠቅ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው።

‹‹ የሳይበር ምህዳር እጅግ በጣም ውስብስብ፣ ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች፤ ደርማሳዊና ድንበር የለሽ መሆኑ ይታወቃል›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህም አውድ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅሞችን ማስከበር እጅግ በጣም እልህ አስጨራሽና ፈታኝ ጉዳይ ነው ይላሉ። ለዚህ ተቋማትና ዜጎች ርብርብ ማድረግ አለባቸው በሚል ከፍተኛ የሆነ ንቅናቄ ሲካሄድ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህም የሳይበር ጥቃት በመመከት ረገድ ያለው አቅም እንዲጨምር አስችሏል ብለዋል።

በዚህም በባለፈው በጀት ዓመት (2015 በጀት ዓመት) በሀገራችን ላይ የተቃጣውን የሳይበር ጥቃት 96 በመቶ መከላከል ተችሏል ። ይህም በገንዘብ መጠን ሲሰላ 23 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ማዳን የተቻለበት ነው። ይህ ሥራ በሀገር ላይ ሊደርስ የነበረው ከፍተኛ ኪሳራ የተመከተበት እና ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ የተቻለበት እንደሆነ አመላክተዋል።

‹‹ የሳይበር ጥቃት በባህሪው አውዳዊና ደርማሳዊ የሆነ ጥቃት ነው። ኢንሳም የሀገር ኢኮኖሚና ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የመከላከል ሥራ እየሰራ ነው›› የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ‹‹የመከላከል አቅማችን ቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሚባሉ (የቴሌኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማት፣ የአየር መንገድ፣የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችንና መሠረተ ልማት የኤሌክትሪክ ኃይልና አገልግሎትን እና ሌሎች) በጥብቅ እንከታተለን። ጉዳት ቢደርስባቸው ዜጎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት ሊያደርሱና ቀውስ ሊፈጥሩ በሚችሉት ላይ ትኩረት አድርገን እንከታተላለን ›› ብለዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ፤ የጥቃት ቀጠና ለሆነው የፋይናንስ ዘርፍ በከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል። የሚዲያ ተቋማትን፣ የጤናና የትምህርት ተቋማትን፣ የጸጥታና ደህንነት ተቋማትና የመሳሰሉት የመንግሥት ተቋማት ትኩረት ተደርጎባቸው ክትትልና ጥበቃ ይደረጋል ። ይህንን በጥብቅ በመፈጸሙ የሳይበር ጥቃት በሀገራችን ላይ ሲደርስ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ ሆኗል። ‹‹96 በመቶ ራሳችን ተከላክለናል ስንል ከፍተኛው የሀገሪቱን ሀብት መጠበቅ ችለናል ማለት ነው። ይህ ለከፍተኛ ኪሳራ የሚዳርግ ወጪ እንዳይደርስ ተከላከልንበት ነው። ከፍተኛው የሀገሪቱን ሀብት መጠበቅ ችለናል›› ይላሉ።

እነዚህ በሀገር ላይ የተቃጡ ጥቃቶቹ ቢደርሱ ኖሮ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሱ እንደነበር ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያስታወሱት። እሳቸው እንዳሉት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ እና የማይታወቁ የሳይበር ጥቃት አይነቶች አሉ። የማይታወቁ በድንገተኛነት የሚከሰቱ ሪፖርት የሚደረጉ ጥቃቶችም አሉ። ይህ ጥቃት እዚህ ጋር ድንገተኛነት ጥቃት ደርሶብኛል ብለው ግለሰቦች ፣ተቋማት ሪፖርት ሊያደርጉት የሚችሉት አይነት ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ እንኳን የማይታወቅ አይነት ጥቃት ሲደርስ ደግሞ የእኛ የሳይበር ሰራዊት ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ ይከላከላሉ። ሆኖ ግን ጉዳቱ ሊደርስ ይችላል። እንደሀገር ግን በጣም ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ የሚችለው(በመሠረተ ልማትና በፋይናንስ ሴክተር የተከሰተው) በመከላከል ሊደርስ የነበረው ኪሳራ ማዳን ተችሏል ብለዋል።

ተቋሙ ሲቋቋም የሳይበር ደህንነት የመከላከል አቅም ለመጨመር የቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን አለብን በሚል መርህ ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ‹‹ስለዚህም ክልከላ ያለባቸውን ቴክኖሎጂ እናለማለን ፤ለራሳችንንና ለጸጥታና ደህንነት ተቋማት እናስታጥቃለን። በዚህም ሊወጣ የነበረው ከፍተኛ መዋለ ነዋይ እንቀንሳለን ። የዲጅታል ትራንስፎርሜሽኑን የሚያሳልጡ የተወሰኑ ተቋማት አውቶሜት የማድረግ ሥራም ይሰራል›› ብለዋል።

በሳይበር ምህዳር ዜጎችና ተቋማት ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ለሳይበር ደህነነት መረጋገጥ ጎልህ አስተዋጽኦ አለው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህም ተቋሙ በየዓመቱ አለም አቀፍ የሳይበር ቀን አስመልክቶ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብሮች እንደሚያካሄድ አመላክተዋል። በዚህም ዘሪያ የተለያዩ ሁነቶች በማዘጋጀት ዜጎች በሳይበር ዙሪያ በቂ እውቀት እንዲኖራቸው በማድረግ፣ ግለሰቦችና ተቋማት ራሳቸውን እንዲጠብቁ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚሰሩ አብራርተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ፤ባለፈው ዓመት በተደረገው የሳይበር ደህንነት ሁነት ላይ በ100 የሚቆጠሩ የግልና የመንግሥት ተቋማት መሳተፋቸውን አስታውሰዋል። መድረኩ ስለሳይበር ደህንነት በሀገራችንን በአጠቃላይ ለ50 ሚሊዮን ዜጎች ተደራሽ መሆን የተቻለበትና ከፍተኛ የሆነ የትስስርና የቅንጅት ሥራ የተሰራበት እንደሆነም አመላክተዋል። ያለፈው አመት ሥራ ለዘንድሮ ጽኑ መሠረት የጣለ እና ቱሩፋት ይዞ የመጣበት ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ‹‹የተቀናጀ የሳይበር ደህንነት ለሀገር ሉዕላዊነት›› በሚል መሪ ቃል መካሄዱን አስታውሰዋል፤ ዋና ትኩረት ያደረገው የሳይበር ደህንነት ጉዳይ በአንድ ተቋም ብቻ የሚመጣ ሳይሆን የግሉንም ዘርፍ ትኩረት እንደሚፈልግ ለማሳየት ታሰቦ እንደሆነ ይናገራሉ።

ዘንድሮም የሳይበር ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ ጊዜ ፤በሀገራችን ለአራተኛ ጊዜ ‹‹አይበገሬ የሳይበር ደህንነት አቅም ለሀገር ሉዕላዊነት›› በሚል መሪ ቃል በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ይከበራል። ‹‹ይህ መርሀ ግብር ዓምና ላይ የፈጠረነውን አቅም ዘንድሮ እጅግ አልቀነው እና ከፍ አድርገን ለሀገራችን ዲጅታል ሉዓላዊነት የየበኩላችንን ድርሻ የምንወጣበት ይሆናል ›› በማለት ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የዘንድሮ የሳይበር ወር በአምስት የተለያዩ አይነት ሁነቶች እንደሚከበር የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በመክፈቻው ዕለት ጥቅምት 4 በአስተዳደሩ የተዘጋጀው ስውር ውጊያ የሚል ፊልም ለእይታ እንደሚቀርብ ተናግረዋል፤ / ፊልሙ በእለቱ ለእይታ ቀርቧል/ ፊልሙ ሀገር እንዴት እንደምትጠበቅና ትውልድ እንዴት እንደሚገነባ የሚያሳይ እውነተኛ ሁነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጸው፣ የፊልሙ ኢንዱስትሪውን የሚያልቅ እንደሆነ አመላክተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ሁለተኛው ሁነት ጥቅምት 12 የሚካሄደው ሲሆን ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ስጋት ጥናት ይፋ የሚደረግበት ነው። ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለብን የሳይበር ስጋት ምን ይመስላል የሚለውን በደንብ የሚተነተንበት ይሆናል። ከጥቅምት 12 እስከ ጥቅምት 15 ድረስ ለአራት ቀናት በዲጅታልና በሳይበር ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት እና የዘርፉ ተጠቃሚዎች አገልግሎታቸውንና ምርቶታቸው የሚያስተዋዋቁበት አውደ ርዕይ ይካሄዳል።

ሦስተኛው ሁነት ጥቅምት 19 የሚካሄደው ነው። ይህም የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ጥናት ውጤት ይፋ የሚሆንበት ነው። እንደ ሀገር የሳይበር ንቃተ ህሊናችን ምን ላይ እንዳለ የሚቀርበበት ነው። በጥናቱ የዜጎች ፣ የተቋማት፣ አጠቃላይ የማህበረሰቡ የዘርፉ ንቃተ ህሊና ምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚለውን የሚያሳይ ይሆናል።

አራተኛው ሁነት ጥቅምት 22 የሚካሄደው ሲሆን፣ የሳይበር ተደራሽነትን ሰፋ ለማድረግ በሳይበር ፖሊሲና ስታንዳርድ ዙሪያ በበይነ መረብ የሚደረግ ቨርችዋል የሚካሄድበት ነው። በውይይቱም የክልል ርዕስ መስተዳዳሮችና የሚመለከታቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የሳይበር ደህንነት የሚያስተዳደሩ ቢሮች እና የዘርፉ ምሁራንና ዩኒቨርሲቲዎች ይሳተፋሉ።

ጥቅምት 29 የሚካሄደው ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ምርምር ኮንፍረንስ አምሰተኛው ሁነት ነው። ይህም የዘርፉ የጥናትና ምርምር ተቋማት እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎች ያደረጓቸው ጥናቶችና የመጧቸው ውጤቶች የሚቀርቡበት እንደሆነም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት ይህ የሳይበር ደህንነት የምርምር ኮንፈረንስ በተቋም ደረጃ መካሄዱን አስታውሰው፤ ዘንድሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሳይበር ደህንነት ወር እንደሚካሄድ ይናገራሉ። በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን እናደርጋለን ብለዋል።

የሳይበር ደህንነት በመከላከል ረገድ ያለውን ግንዛቤ በማስፋት እያሳደግን ሀገራዊ አቅምን እየፈጠርን መጥተናል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህ ሀገራዊ አቅም ለሀገር ሉዓላዊነት የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ይናገራሉ። ‹‹ዓለምአቀፋዊ ስናደርግ ደግሞ በዓለም አቀፍ አውድ ለሰው ልጆች ሁሉ እንደሀገር ማድረግ የምንችለውን የምናበረክትበትና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚህ ዘርፍ የሀገራችንን ስም የምናስጠራበት ቁመና ለመትከል ይሄ ጽኑ መሠረት ይሆናል››ነው ሲሉ ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያብራሩት።

በእነዚህ አምስቱም የሳይበር ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች ከሁሉም ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች፣ ከጸጥታና ደህንነት ተቋማት፣ ከፋይናንስ ተቋማት፣ ቁልፍ የመንግሥት መሠረተ ልማት ከሚያስተዳደሩ የልማት ድርጅቶች እንዲሁም በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ላይ ከተሰማሩ ተቋማት የሚመጡ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንደሚሳተፉ አብራርተዋል። የማህበረሰቡን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና በማሳደግ በኩል ከፍተኛ ሚና ያላቸው የሚዲያ ተቋማትና የኪነጥበቡ ማህበረሰብ አባላትም እንደሚሳተፉበት ዋና ዳይሬክተሩ አስታወቀዋል።

ተቋሙ የሀገሪቱን የሳይበር ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ለመወጣት ንቃተ ህሊናን ለማስፋት የሚያስችሉ መርሀ ግብሮችን እንደሚያከናወን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ተቋማት የሳይበር ደህንነት ማረጋገጥ ሥራ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን በመረዳት የሳይበር ደህንነትን ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ ንቃተ ህሊና ላይ በዘላቂነት እንዲሰሩ የሚያስችል ማነቃቂያ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ስኬታማነት እየሰራች መሆኗን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም ዘርፉን ከሚመሩት ተቋማት /ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ኢትዮ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ ከአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዮት/ ጋር ያለንን ቴክኖሎጂዎች በማውጣት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሊያስወጡ የሚችሉት ቴክኖሎጂዎችን በሀገር አቅም በማልማት እንገኛለን ብለዋል።

በዚህ ጥረት ውስጥ የግሉ ዘርፍ ተሳታፊ እንዲሆን ፍሬም ወርክ ተዘጋጅቶ ዘንድሮ ወደ ሥራ እንደሚገባ አስታውቀዋል። ከጥቅምት 12 እስከ 15 በሚካሄደው አውደ ርዕይ ላይ የሚሳተፉ የግል ኩባንያዎች ከተቋሙ ጋር በበጀት ዓመቱ በዲጅታል 2025 በሚደረጉ ፕሮጀክቶች ለመሳተፍ እድል ያገኛሉ ብለዋል። በዚህም የግሉን ዘርፍ ለማነቃቃት እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ የግል ኩባንያዎች በተጠቀሰው ጊዜ እንዲሳተፉና ያላቸውን አቅም እንዲያሳዩ ከተቋሙ ጋርም ትስስር እንዲፈጥሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2016

Recommended For You