ሁሉም እንደሚያውቀው፣ ከእስከዛሬዎቹ የሙያና እውቀት ዘርፎች እጅጉን ከተጎዱት ቀዳሚው የትምህርቱ ዘርፍ ነው። እንዳይሆኑ፣ እንዳይሆኑ ከተደረጉት ቀዳሚው ይኸው ዘርፍ ነው። በመሆኑም፣ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በከፍተኛ ፍጥነትና ስር ነቀላዊ አካሄድ ወደ ለውጥ የገባው ይኸው የትምህርቱ ዘርፍ ነው።
በስመ “አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ” ሲጎሳቆል የኖረው ይህ የሀገሪቱ የትምህርት ዘርፍ በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ወደ ለውጡ በመግባቱ ምክንያት በርካታ ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን፣ አንዱም ከፈተና አመራር፣ አሰጣጥ፣ አፈታተንና ውጤት ጋር ተያይዞ የተሠራውና እየተከናወነ የሚገኘው ሥራ ነው።
የሰሞኑ የትምህርት ሚኒስቴር የ2015 ዓ.ም ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤትን በተመለከተ የወጣው “አስደንጋጭ” የጽሑፍ መግለጫ በመግቢያ አንቀፁ ላይ እንዳሰፈረው “ትምህርት ለማህበረሰብ ለውጥና ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ መሣሪያ ነው፡፡ ነገር ግን በሀገራችን ባለፉት ዓመታት የፖለቲካ ትግል መሣሪያ አድርጎ ለመጠቀም በተደረገው ያልተገባ ርብርብ የፈተና አስተዳደር ሥራ ላይ በርካታ ችግሮች ሲከሰቱ ቆይቷል፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው በትምህርት ሥርዓቱ ከሚስተዋለው ስብራት ላይ የፈተና አስተዳደር ችግር ሲደመርበት ዘርፉን በእጅጉ ጎድቶታል። የኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ሠርቲፊኬት ፈተና ውጤት ተፈታኞች አጠቃላይ ትምህርትን የሚያጠናቅቁበት፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያነት የሚገለገሉበትና ወደ ተለያየ ዘርፍ ሲሰማሩ የሚጠቀሙበት ከመሆኑ ውጪ ተሻግሮ ጥቂት በማይባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ለፖለቲካ ሴራ፣ የማህበራዊ ቀውስ መፍጠሪያ እና በማህበራዊ ሚዲያዎች ባልተገባ መንገድ ጥቅም ማግኛ ሆኖ ቆይቷል።”
“በመሆኑም” ይላል ይሄው መግለጫው፣ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ከመፈለግ አንጻር የፈተና አስተዳደር ሥራ ኮምፒዩተርን መሠረት ያደረገ እንዲሆን የተለያዩ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም ለሥራው የሚያስፈልጉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ባለመሟላታቸው ሳይተገበር ቆይቷል፡፡ ስለሆነም ከ2014 የትምህርት ዘመን አንስቶ የትምህርት ሚኒስቴር የፈተና ዝግጅት፣ ህትመት፣ ስርጭት፣ አሠጣጥና እርማት ሥራዎች ሚስጢራዊነታቸውና ደህንነታቸው የተረጋገጠ እንዲሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን በማስተባበርና በማቀናጀት ውጤታማ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በተለይም ፈተናው በፌዴራል የትምህርት ተቋማትና በዩኒቨርሲቲ መምህራን እንዲሰጥ መደረጉና በሂደቱ የነበሩ ውስጣዊና ውጫዊ ተጋላጭነትን በሚዘጋ አግባብ እንዲመራ ተደርጓል፡፡
የፈተና አስተዳደር ችግር በተለይም የፈተና ሌብነትና ኩረጃ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ሲያሳድር የነበረውን አሉታዊ ተጽዕኖ በመከላከል እንዲሁም በምትኩ ተፈታኞች የልፋታቸውን ውጤት ብቻ የሚያገኙበት፣ የትምህርት ማህበረሰብም ተማሪዎችንና ትምህርት ቤቶችን በቅርበት የሚደግፍበትና አዎንታዊ ሚና የሚጫወትበት ሥርዓት የመገንባት ሥራ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል፡፡ ለዚህም ለፈተና አስተዳደሩ እና ለትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ ሪፎርሞች መንግሥት ከፍተኛ ሀብት በመመደብ እና ከፍተኛ የሰው ኃይል በማሰማራት ለሁለተኛ ጊዜ ፈተናው ከፈተና ሌብነትና ኩረጃ በጸዳ መልኩ የተሳካ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።
ያለው እውነታ ይህንን ሲመስል፣ አጠቃላይ ውጤቱም፣ መግለጫውን የሰጡት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደ ተናገሩት፦
• የ12ኛ ክፍል ፈተና ካስፈተኑ 3 ሺህ 106 ትምህርት ቤቶች፤ 1 ሺህ 328 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ማሳለፍ አልቻሉም፤
• በትምህርት ዘመኑ ፈተናውን ከወሰዱት 845ሺ በላይ ተማሪዎች ውስጥ 50 በመቶና ከዛ በላይ ያመጡት 27 ሺህ 267 (3 ነጥብ 2 በመቶ) ተማሪዎች ብቻ ናቸው።
• በተፈጥሮ ሳይንስ እና በማህበራዊ ሳይንስ ለፈተና
ከተቀመጡ በድምሩ 845 ሺህ 677 ተማሪዎች 50 ከመቶና ከዚያ በላይ ውጤት ያመጡት 31 ሺህ 224 ተማሪዎች ብቻ ናቸው፤
• በተፈጥሮ ሳይንስ መስክ 200 ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት አምጥተዋል፤
• ማህበራዊ ሳይንስ መስክ 15 ተማሪዎች ብቻ ከ500 በላይ ውጤት አምጥተዋል፤
• እንደ መፍትሄ፣ ዩኒቨርሲቲዎች 160 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎችን በሬሜዲያል ፕሮግራም ይቀበላሉ፤
• በዘንድሮው ዓመት በተፈጥሮ ሳይንስ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት 649/700 ሲሆን፤ በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 533/600 ነው፤
• በማህበራዊ ሳይንስ መስክ 15 ተማሪዎች ብቻ ከ500 በላይ ውጤት አምጥተዋል፤
ተፈታኞችና ውጤታቸው ትምህርታቸውን ከተከታተሉበት መርሀ ግብር አኳያም የተገለፁ ሲሆን፣ በተሰጠው መግለጫ ላይ እንደሚከተለው ተቀምጦ ይገኛል።
መግለጫው አጠቃላይ ውጤቱን ከፆታ ስብጥር አኳያም የገለፀ ሲሆን፣ በተፈጥሮ ሳይንስ ከፍተኛው ውጤት 649 ሲሆን በአዲስ አበባ የልደታ ክሩዝ ትምህርት ቤት ተማሪ መሆኗን፤ በማህበራዊ ሳይንስ ከፍተኛው ውጤት 533 ሲሆን፣ ይህንን ውጤት ያስመዘገበውም የደብረ ማርቆስ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ መሆኑን አመልክቷል። እንዲሁም፣ አጠቃላይ ውጤቱን ከአጠቃላይ የተፈታኝ ተማሪዎች ፆታ አንፃር እንደሚከተለው አስቀምጦታል።
መግለጫው ከተሞችንም አስመልክቶ ያለው ነገር ያለ ሲሆን፣ በከተማ ደረጃ አዲስ አበባ፣ ሀረሪ እና ድሬዳዋ የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ ከተሞች ናቸው።
የትምህርት ቤቶችን ውጤታማነት በተለይ ያመላከተው የሚኒስትሩ መግለጫ አምስት ትምህርት
ቤቶች ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ ማሳለፋቸውን፤ እንዲሁም፣ ሌሎች አምስት ትምህርት ቤቶች ደግሞ ካስፈተኗቸው ውስጥ 95 በመቶ ተማሪዎቻቸውን ማሳለፋቸውን አመልክቷል።
ካስፈተኑት 3 ሺህ 106 መደበኛ ት/ቤቶች መካከል ከ50% እና በላይ ያስመዘገበ ተማሪ ያላቸው ት/ቤቶች ብዛት (ቢያንስ 1 ተማሪ) 1 ሺህ 778 (57.2%) ሲሆኑ፤ ከ50% እና በላይ ያስመዘገበ አንድም ተማሪ የሌላቸው ት/ቤቶች ብዛት 1328 (42.8%) ናቸው፡፡
ለተሻለ ለውጥ የልምድ ልውውጥ
ልምድ መለዋወጥን ወይም ከተሻሉ ተቋማት፣ ለውጥ ካመጡ የሥራ መስኮች ልምድ መቅሰምን ለትምህርት ሚኒስቴር ብቻ የሰጠው ማንም የለም። እንደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ካየነው፣ ልምድ መቅሰም የሚገባቸው ተቋማት፣ “ሁሉም” ለማለት ጥቂት ፈሪ ከመሆን በስተቀር በሙሉ ያስፈልጋቸዋል። ልምድ ደግሞ ቻይናና ህንድ ከመሄድ ብቻ የሚገኝ ሳይሆን፣ ከራስ ተግባርም ልምድ መውሰድ ይቻላል። ከራስ ሀገር ተቋማትም ተሞክሮ መውሰድ ይቻላል። እየሠሩ፣ ከሠሩት ሥራም በሂደት መማር ይቻላል። ዛሬ እጃችን ላይ ያለው ኮምፒውተር በአንድ ጊዜ የተደረሰበት ሳይሆን በዘመናት ሂደት እየተሻሻለ፣ ሁሉም ያለውን እየጨመረበት እዚህ የደረሰ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።
ከመግለጫው በግልፅ መረዳት እንደሚቻለው፣ ትምህርት ቤቶች ልምድ ሊለዋወጡ ይገባል (ለምሳሌ፣ ምንም ያላሳለፉት፣ ሙሉ በሙሉ ካሳለፉት – (እንዲሁም፣ ከፍተኛ አፈፃፀም ካሳዩት፣ 1. አዲስ አለማየሁ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ 2. ደሴ አዳሪ ትምህርት ቤት 3. ባህርዳር ስቴም ትምህርት ት/ቤት 4. ሀይራንዚ አዳሪ ትምህርት ቤት (ስልጤ ዞን) 5. ልጅ ጎጎ አዳሪ ትምህርት ቤት (ሀድያ) 6. ኦዳ አዳሪ ትምህርት ቤት (አዳማ) 7. ኮተቤ ሼርድ ካምፓስ 8. የኔታ አካዳሚ 9. ወላይታሊቃ አዳሪ ትምህርት ቤት እና 10. ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት) እንዴት ሊሆን ቻለ ከሚል ቁጭት በመነሳት ልምድ መውሰድ ይገባል።
ክልሎችና ከተሞች ከከተሞች ልምድ መውሰድ አለባቸው (ለምሳሌ፣ የተሻለ አፈጻጸም ካሳዩት አዲስ አበባ፣ ሀረሪ እና ድሬዳዋ ከተሞች)።
ትምህርት ቢሮዎች ልምድ ሊለዋወጡ ይገባል፤ መምህራን ልምድ ሊለዋወጡ ይገባል፤ የትምህርት አመራሮች ልምድ ሊለዋወጡ ይገባል፤ ወላጆች በወላጅ ኮሚቴዎች አማካኝነት ልምድ ሊለዋወጡ ይገባል፤ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ልምድ ሊለዋወጡ ይገባል፤ ሀገርም እንደ ሀገር ከሌሎች፣ ከተሳካላቸው ሀገራት ልምድ ልትቀስም ይገባል እንላለን።
በመጨረሻም፣ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ወቅታዊ መግለጫ በ2015 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከማንኛውም የፈተና ሥርቆትና ኩረጃ በጸዳ መልኩ ተሰጥቷል፡፡ ሆኖም የተመዘገበው ውጤት በተለይም 50% እና በላይ ያስመዘገቡ ተፈታኞች ብዛት ዝቅተኛ መሆኑ በትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ ያለው ስብራት አሁንም ብዙ ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅት በከፍተኛ ደረጃ ይፈልጋል፡፡ ችግሩ በሁለቱ ዙር በተደረገው ፈተና ይበልጥ ተጋለጠ እንጂ ለረጅም ዓመታት ሲንከባለል የቆየ ነው። መፍትሄውም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በመፍጠርና በመፍጠን እሳቤ ለውጥ ለማምጣት፤ በተለይም የትምህርት አመራሩ ቁርጠኛ አመራር ከመስጠትና በቅርበት ድጋፍና ክትትል ከማድረግ አንጻር የጋራ ርብርብ ይፈልጋል፡፡
ባለፈው ሰኞ፣ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ∙ም ትምህርት ሚኒስቴር በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው ተቋሙ ወደ ለውጥ (ሪፎርም) ከገባ ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን፣ በእነዚህ ሥራዎቹም የአጠቃላይ ማህበረሰቡን ድጋፍና ይሁንታ አግኝቷል። ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።
ለተሳካላቸውና ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገቡ ሁሉ መልካም የትምህርት ዘመን እንዲሆንላቸው፤ ላልተሳካላቸውም፣ ፈተና አንዱ መለኪያ እንጂ የሁሉም ነገር መጨረሻ ማለት አይደለምና የተሻለ ነገን እንመኛለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም