በሀገሪቱ የተከሰተው የኑሮ ውድነት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የማኅበረሰብ ክፍል የከፋ አደጋ ውስጥ እንዳይከተው መንግሥት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ሸቀጦች ላይ ድጎማ ማድረግ ከጀመረ አመታት እየተቆጠሩ ነው። በዚህም እየተመዘገበ ያለው ውጤት ዜጎች በተወሰነ መልኩ ችግሩን መቋቋም የሚያስችል አቅም እንዲገነቡ ረድቷቸዋል። እንደ ሀገርም ችግሩ ሊያስከትል የሚችለውን ምስቅልቅል ትርጉም ባለው መልኩ እየቀነሰው ይገኛል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በሸቀጦች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ግሽበት፤ እንደ ሀገር ከውጭ በምናስመጣቸው ሸቀጦች እና ከውጭ በሚመጡ የፋብሪካ ግብአቶች ላይ በፈጠረው የዋጋ ንረት ምክንያት የሸቀጦች ዋጋ ዕለት ዕለት እየጨመረ የዜጎችን የመግዛት አቅም ችግር ውስጥ ከትቷል። ችግሩ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የማኅበረሰብ ክፍል አልፎም መካከለኛ የሚባለውን የማኅበረሰብ ክፍል እየተፈታተነው ይገኛል።
የሀገሪቱ የንግድ ሥርዓት የመጣበት የተበላሸ መንገድ ለችግሩ ተጨማሪ አቅም በመሆን፤ ችግሩን ለመፍታት በመንግሥት ደረጃ የሚደረጉ ጥረቶች የሚጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳያመጡ ትልቅ ተግዳሮት በመሆን ላይ ይገኛል። ይህም የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት ፈተና ውስጥ በመክተት ሕዝባችን ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል እያስገደደው ነው።
«በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንደሚባለው ችግሮችን በውይይትና በድርድር ከመፍታት ይልቅ፤ በኃይል ለመፍታት የሞከሩና እየሞከሩ ያሉ ኃይሎች በፈጠሯቸው አላስፈላጊ ግጭቶች፤ የተፈጠሩ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎች፤ ችግሩ መልከ ብዙ መገለጫ እንዲኖረው በማድረግ ዜጎች በከፋ መልኩ የችግሩ ሰለባ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
መንግሥት ይህንን ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ችግር አቅምን ታሳቢ ባደረገ መንገድ ለመፍታት ረጅም ርቀት ሄዷል። ለዜጎች በዋንኛነት የሚያስፈልጉ እንደ ዘይትና ስንዴ የመሳሰሉ ሸቀጦችን ቢሊዮን ብር በመደጎም ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲከፋፈሉ አድርጓል። የሀገር ውስጥ ገበያውንም በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል በተወሰነ መንገድ ሥርዓት ለማስያዝ ጥረቶችን አድርጓል።
ከዚህም ባለፈ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የማኅበረሰብ ክፍል ከሸቀጦች መወደድ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ጫናዎች እንዲቀንሱለት ለማድረግ የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ተግባራዊ አድርጓል። እስካሁንም መንግሥት በሚያወጣው ታሪፍ የሚተዳደሩ 197ሺህ 389 የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች የድጎማው ተጠቃሚ ሆነዋል። ለድጎማውም ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል።
የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ትግበራ ነዳጅ ያለመቆራረጥ እንዲቀርብ ከማድረግ ባለፈ፤ ሀገሪቱ ከነዳጅ ጋር በተያያዘ ሊኖርባት የነበረው ዕዳ አሻቅቦ ነዳጅ ማስገባት ከማትችልበት ደረጃ ላይ ትደርስ እንደነበር ይታመናል። በተተገበረው ሥርዓት ከ190 ቢሊዮን ብር በላይ የነበረውን ዕዳ ወደ 120 ቢሊዮን ብር እንዲወርድ ማድረግ ተችሏል።
ይህም ሆኖ የትራንስፖርት ዘርፍ አጠቃላይ በሆነው የሀገር ኢኮኖሚ ላይ ካለው ከፍያለ አስተዋጽኦ አንጻር ድጎማው ኅብረተሰቡን በብዙ መልኩ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ቢታመንበትም፤ ኃላፊነት በማይሰማቸው ግለሰቦች የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል። ድጎማ ተቀብለው ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ ብሎም ከነጭራሹ ስምሪት ላይ የማይሳተፉ ተሽከርካሪዎች ተስተውለዋል።
ይህ ሥርዓተ አልበኝነት የትራንስፖርት ዘርፉን ፈተና ውስጥ ከመጨመር አልፎ፤ በድጎማ መልኩ ወጪ የሚደረግ የሕዝብ ሀብት ያለ አግባብ እንዲባክን አድርጓል። ከድጎማው ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የማኅበረሰብ ክፍልም ኑሮው የበለጠ እንዲከብደው በማድረግ፤ የሕይወት ጫናውን አክብዶታል፤ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ እንዲቀንስ አድርጎታል።
በትራንስፖርቱ ዘርፍ ላይ የታየውን ይህን ሥርዓተ አልበኝነት መስመር ለማስያዝ፤ ዘርፉ ከሁሉም በላይ ለሕግና ሥርዓት ተገዥ እንዲሆን ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት፤ በተለይም የፌዴራል የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን እና የክልል የትራንስፖርት ቢሮዎች የሚጠበቅባቸውን ከፍ ያለ ኃላፊነት በቀና መንፈስ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በዘርፉ የሚታየው ኃላፊነት የጎደለው አሠራር እና በአደባባይ የሚስተዋለው ሙስና በጠንካራ እርምጃ ሊስተካከል ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም