ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ/ር) – ውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ
ዳር እስከዳር(ዶ/ር) ታዬ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ እና የኢስያ ፓስፊክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ናቸው፡፡ በተለያዩ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሁፎችን በማቅረብና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ የሚታወቁ ናቸው፡፡ በዓባይ ውሃና በቀይ ባህር ከባቢያዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ምሁራዊ ሃሳቦችንም በማንሳት ይታወቃሉ፡፡
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በኢትዮጵያ የወደብ ተጠቃሚነትና በቀይ ባህር አካባቢ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከእኚሁ ምሁር ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡– አሁን ላይ ያለውን የዓለም ፖለቲካ አካሄድ እንዴት ያዩታል ?
ዳርእስከዳር(ዶ/ር)፡– በአሁኑ ወቅት ዓለም በለውጥ ምህዋር ውስጥ ናት፡፡ ይህ ለውጥ ደግሞ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ መልኩ ሥርዓታዊ ለውጥ እየታየበት ነው። አንድ ሀገር አደገ፤ አንዱ ወደቀ የምንለው አይነት ሳይሆን አጠቃላይ ሥርታዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አይነት ነው።
በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ የተወሰኑ ሀገራት በዓለማችን አዲስ ሥርዓት እውን እንዲሆን እየተጉ ነው፤ ሌሎቹ ደግሞ የነበረው ሥርዓት እንዲቀጥል የሞት ሽረት ትግል እያካሄዱ ነው፡፡ አሁን ያለው የዓለም ሥርዓት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አሸናፊ በሆኑ ሀገራት በተለይም በአሜሪካ መሪነት የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ላለፉት 70 ዓመታት የበላይነቱን አስጠብቆ ቆይቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን ቻይና፣ ህንድ እና ሩስያን የመሳሰሉ ሀገራት አቅማቸውን እያጠናከሩ በመምጣታቸው ለ70 ዓመታት ቆየውን ነባሩን ሥርዓት ለመቀየር በመገዳደር ላይ ይገኛሉ፡፡ ሥርዓት መቀየር ማለት የተባበሩት መንግሥታትን ሪፎርም ማድረግ ወይም ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትን መለወጥ ላይ ብቻ የሚያቆም አይደለም። ሌላ አይነት አዲስ አስተሳሰብና አሠራርን ተግባራዊ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም ነባሩ ባለበት ለመቀጠል አዲሱ ደግሞ ከቻለ የራሱን ሥርዓት ለማንበር ከልሆነም ለማሻሻል የበኩላቸውን ጥረት የሚያደርጉበት ወቅት ላይ እንገኛለን ፡፡
ስለዚህ በሁለት ትላልቅ ጎራዎች መካከል የማያባራ ፍትጊያ አለ ማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– በዚህ የዓለም የፖለቲካ አካሄድ ውስጥ የአፍሪካ ሀገራት እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
ዳርእስከዳር(ዶ/ር)፡– በዚህ ፍትጊያ ውስጥ ሁለቱም ጎራዎች አፍሪካ ሀገራት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እየሞከሩ ነው፡፡ ነባሩ ሥርዓት በዚህ መጠን ተግዳሮት ይገጥመዋል ብሎ ያሰበ የለም፡፡ ሆኖም በተለይ እኤአ ከ2016 ወዲህ አዳዲስ ሀገራት በዓለም ላይ ተጽዕኗቸውን ማሳየት የጀመሩበት ጊዜ ነው፡፡ በተለይ ቻይና ቀደም ብላ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የጠበቀ ግንኙነት መፍጠር በመቻሏ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት መልካም የሚባል ንግድ እና ዲፕሎማሲ ግንኙነት አዳብረዋል፡፡
በእርግጥ የቻይና እና የአፍሪካ ወዳጅነት በርካታ የሚያስተሳስሯቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ አንዱ ሁለቱም አካላት የቅኝ ግዛት ሰለባ መሆናቸው የጋራ ሥነ-ልቦና እንዲጋሩ ያስችላቸዋል፡፡ ቻይና ወደ አፍሪካ ስትመጣ የቅኝ ገዢ እና ተገዢ አስተሳሰብ ይዛ አይደለም፡፡
ሌላው ቻይና ወደ ጸጥታው ምክር ቤት እንድትገባ በተደረገው እንቅስቃሴ አፍሪካ ትልቁን ሚና ተጫውታለች። በአጠቃላይ እኤአ በ1970ዎቹ አፍሪካ ድጋፍ ለቻይና አስፈላጊና ጠቃሚ ነበር፡፡
የቅርብ ጊዜውን ስንመለከት የቻይና ኢኮኖሚ ከአፍሪካ ጋር ተሳስሮ ያደገበትና ለጋራ ዕድገትም ሲሠሩ የቆዩበት ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም አፍሪካ የምታወጣቸውን የልማት ዕቅዶች ከመደገፍ፣ መሠረተ ልማቶችን ከማስፋፋት እና በአጠቃላይ አፍሪካ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት በማገዝ ላይ ትገኛለች፡፡
ቻይና ከአፍሪካ ጋር ጥብቅ ግንኙነት በፈጠረችበት ወቅት ነው ምዕራባውን የቻይናን እንቅስቃሴ የመግታት ፍላጎት ያደረባቸው፡፡ የቻይናን ትኩረት ለማስቀየስ ደግሞ አፍሪካውያን ላይ ትኩረት ማድረግ ጀመሩ፡፡ ‹‹ከእኛ ጋር ወይም ከቻይና ጋር ሁኑ›› በሚል የአፍሪካ ሀገራት አንዱን እንዲመርጡ የሚያስገድድ አካሄድ መከተል ጀምረዋል፡፡
በአንድ በኩል የአፍሪካ ሀገራትን የፖሊሲ ነጻነትን የሚነኩ አካሄዶች መከተል ከዚሁ ጎን ለጎን አፍሪካ ሀገራትን ለማማለል የሚያስችሉ ሃሳቦችን ይፋ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ልክ ቻይና “ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭን” በጀመረችበት መንገድ አሁን የአውሮፓ ህብረትና የ “ጂ. ሰቨን” ሀገራት አዳዲስ ማማለያዎችን ይፋ አድርገዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ የአውሮፓ ህብረት “ግሎባል ጌት ዌይ” የሚል ኢኒሼቲቭ ይዞ መጥቷል፡፡
“ግሎባል ጌት ዌይ” የቻይናው “ቤልት ኤንድ ሮድ” ኮፒ ቢመስልም ልዩነቱ ግን “ቤልት ኤንድ ሮድ” መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ በአውሮፓ ህብረት የሚተገበረው “ግሎባል ጌት ዌይ” በአካባቢ ጥበቃና መሰል ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡
ስለዚህም አሁን ባለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔ እየተፈጠረ ያለው ለአፍሪካ ስጋትም ዕድልም ነው፡፡ እንደ ስጋት የሚነሳው የፖሊሲ ነጻነትን እስከ መጋፋት የሚደርሰውና “ወይ ከእኛ ወይ ከቻይና ምረጡ” የሚለው የምዕራባውያን ግትር አካሄድ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ የአፍሪካ ሀገራት ከፈለጉት ጋር ወዳጅነት የመመሥረት እና ይጠቅመኛል የሚሉትን ፖሊሲ የመተግበር ነጻነታቸውን የሚያሳጣ ነው።
ያው እንደሚታወቀው አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት የፋይናንስ አቅማቸው ደካማ በመሆኑ ለተጽዕኖ መጋለጣቸው አይቀሬ ነው፡፡ አብዛኞቹ የፋይናንስ አቅራቢዎቹ ደግሞ ምዕራባውያን ከመሆናቸው ጋር ተያይዞም ተግዳሮቱ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
በጎ ጎኑን ስንመለከት ደግሞ የአፍሪካ ሀገራት አማራጫቸው እየሰፋ መጥቷል፡፡ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ የጥናትና ምርምር እገዛዎችን ከብዙ አቅጣቻዎች እንዲያገኙ በር ይከፍትላቸዋል፡፡
ስለዚህም የሀገራቸውን የውስጥ ሁኔታ ማስተካከል የቻሉና ጸጥታና ደህነታቸውን ያረጋገጡ ሀገራት ከተፈጠረው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ የመጠቀም ዕድላቸው የሰፋ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ከዚህ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን እራስን ማዘጋጀት ይጠይቃል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ የምትገኝበትን የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አሁን ካለው ዓለም አቀፍ ፖለቲካ አንጻር እንዴት ይመለከቱታል ?
ዳርእስከዳር(ዶ/ር)፡– የአፍሪካ ቀንድ የበርካታ ሃያላን ሀገራትን ትኩረት የሚስብ ስትራቴጅክ ስፍራ ነው፡፡ በተለይም አካባቢው በቀይ ባህር እና በናይል ውሃ ተፋሰስ መሃል መገኘቱ የበርካታ ሀገራትን ቀልብ ሊስብ ችሏል፡፡ የቀይ ባህር እና የናይል ፖለቲካ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በማወዳጀትም ሆነ በማራራቅ ከፍተኛ ሚና ያለውን ያህል አካባቢውን በቁጥጥራቸው ለማዋል ህልም ያላቸውም ሀገራት የሚራኮቱበት ነው፡፡
ከአክሱም ሥልጣኔ ጀምሮ የቀይ ባህር አካባቢ ትኩረት ያገኘ ስፍራ ነው፡፡ በየዘመናቱ የነበሩ ኃያላን ቀይ ባህርን ሳይዙ ኃያልነታቸውን ማረጋገጥ የሚታሰብ አልነበረም፡፡
ቀይ ባህር በተለይ ከስዊዝ ካናል መከፈት ጋር ተያይዞ የዓለም የንግድ ኮሪደር ለመሆን ችሏል፡፡ ቀይ ባህርን የመቆጣጠር ፍላጎት የዓለም ኃያልን ሀገራት ሁሉ ምኞት ነው፡፡ ይባስ ብሎም ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ጅቡቲ ላይ በርካታ ኃያላን ሀገራት የጦር ቤዝ እየመሠረቱ መጥተዋል። በእዚህ አካባቢ የጦር ቤዝ ያለው ሀገር ከየትኛው አካባቢ የሚነሳን ጥቃት ፈጥኖ ለመመከት ከማስቻሉም በላይ የመርከብ ላይ ዘረፋን ለመከላከል ትልቅ እገዛ አለው፡፡
በሌላም በኩል የዓባይ ውሃ የግጭት እና የአለመግባባት ምንጭ ሆኖ ለዘመናት ኖሯል፡፡ እስከዛሬም ድረስ የዘለቀው ይኸው ነው፡፡ ስለዚህም የምስራቅ አፍሪካ አጠቃላይ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ የሚወሰነው በእነዚህ ሁለት የውሃ አካላት ነው፡፡ ተጽዕኖውም የሚመጣው ከእነዚህ ውሃ አካላት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል የቀጣናው ሀገራት በሚደርስባቸው ተፅእኖ አንድ ጊዜ ሲዳከሙ ሌላ ጊዜ ሲበረቱ የሚስተዋለው፡፡
በአካባቢው ባለው ተጽዕኖ ደካማ መንግሥታት ወይም መንግሥት አልባ ሀገራት ሲፈጠሩ እናስተውላለን። ሶማሊያ መንግሥት አልባ ሆና ዘልቃለች፡፡ አሁን ሱዳን ለሁለት ተከፍላ ወደ መንግሥት አልባነት እያመራች ነው።
አዲስ ዘመን፡– ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ያላትን ተቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን እንዴት ያዪዋቸዋል ?
ዳርእስከዳር(ዶ/ር)፡– እኔ የለውጡ መንግሥት ሠራቸው ብዬ ከማስባቸው ታላላቅ ሀገራዊ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ የነበራትን ተሰሚነት ለማስመለስ እያደረገው ያለው ጥረትን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ከቀይ ባህር እንድትርቅ ተደርጋለች፡፡ ይህ ደግሞ እንደሀገር የሚያስቆጭና የሚያንገበግብ ነው፡፡
የለውጡ መንግሥት ይህንኑ በመረዳት አይነኬ የሚመስለውን የቀይ ባህር ፖለቲካን ቢያንስ በአሁን ደረጃ የመወያያ አጀንዳ ማድረግ ችሏል፡፡ ሁኔታዎች በፈቀዱ መጠንም ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር መመለሷ አይቀርም። ከአምስት ዓመታት በፊት እኮ ስለባህር በር ማውራት እንደተስፋፊነት እና ጠብ ጫሪነት ነበር የሚቆጠረው፡፡ ስለቀይ ባህር ማውራት እራስን ለጦርነት እንደማዘጋጀት፤ ጦርነትን እንደመቆስቆስ ነበር የሚታሰበው፡፡
ሆኖም በአሁኑ ወቅት 120 ሚሊዮን ህዝብ በ2050 አካባቢ ደግሞ በእጥፍ የሚያድግ ህዝብ ተይዞ “ስለቀይ ባህር እና ስለ ወደብ አታንሳ፤ ዝም ብለህ ተቀመጥ” የሚል አፋኝ አመለካከት ሊኖር አይገባም፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት ስለ ወደብ እና ቀይ ባህር ማንሳት እንደወንጀል የሚቆጠር ነበር፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት ስለወደብ የተጻፈ አንድ አንድ መጽሀፍ ነው፡፡ ‹‹አሰብ የማነች?›› ከሚለው የዶክተር ያዕቆብ ወልደማርያም በስተቀር ሰዎች እውነታውን እያወቁ ለመጻፍ እንኳ አይደፋፈሩም ነበር። መጻፍ እና መናገር ቀርቶ ማሰብ እንኳን የሚያስወነጅል ጉዳይ ነበር፡፡
የጥበብ ሥራዎችም ቢሆኑ ታፍነው ኖረዋል፡፡ የተሠሩ ፊልሞችም ለዕይታ እንዳይበቁ ተደርገዋል፡፡ በዚህ ደረጃ ስለቀይ ባህር እና ወደብ ማንሳት አስፈሪ ጉዳይ ነበር፡፡ አሁን ግን ቢያንስ መወያየትና ሃሳብ መስጠት ተችሏል። ይህ ትልቅ ጅምር ነው፡፡ ሃሳቡን ሁሉም ሲገዛው አንድ ቀን ኢትዮጵያ ወደታሪካዊ ቦታዋ መመለሷ አይቀርም፡፡
ስለዚህም መንግሥት አሁን በዚህ ዙሪያ ሃሳብ እንዲሸራሸር በሩን ከፍቶታል፡፡ ሃሳብ ማንሸራሸር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር የትምትመለሰብትንና የወደብ ባለቤት የምትሆንባቸውን አማራጮች በጥናት በመለየት ላይ ይገኛል፡፡ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትም እየሠራው ያለው ይህንኑ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ ከእነዚህ የውሃ አካላት ተጠቃሚ ለመሆን ምን ማድረግ አለባት?
ዳርእስከዳር(ዶ/ር)፡– የኢትዮጵያን እድገት ከሚወስኑት አበይት ጉዳዮች መካከል ዋነኖቹ የቀይ ባህርና የዓባይ ውሃ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ጋር ይያያዛል፡፡ ኢትዮጵያም በአካባቢው ላይ የራሷን ተጽዕኖ ለማሳረፍና በአካባቢው ላይ ድርሻ እንዲኖራት ስትጠር ቆይታለች፡፡ በአንጻሩ ሌሎች ሀገራት ኢትዮጵያን ከአካባቢው ለማራቅ ሲሞክሩ ኖረዋል፡፡
ሆኖም በእነዚህ ሁለት የውሃ አካላት መካከል የምትገኘው ኢትዮጵያ የጥቅሙ ተጋሪ ለመሆን መጣሯ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ የዓባይ ውሃ አመንጪ ሀገር ብትሆንም ለዘመናት ተጠቃሚ እንዳትሆን በርካታ ሴራዎች ተሰርተውባታል፡፡ የዓባይን ውሃ እንዳትጠቀም ችግሮች ደጋግመው እንዲመጡባት ይደረጋል፡፡
ሆኖም ኢትዮጵያ የሚመጡባትን ችግሮች እየተሻገረች የዓባይ ግድብን ወደ ማጠናቀቁ ደርሳለች። በተለይም በየጊዜው እየጨመረው ከሚመጣው የህዝብ ቁጥሯ ጋር ተያይዞ የዓባይንም ሆነ ቀይ ባህርን ውሃዎች ካልተጠቀመች ህዝቧን መመገብ አትችልም፡፡ ማደግም የሚታሰብ አይሆንም፡፡
ወደ ቀይ ባህርም ካልገባህ በነጻነት ከዓለም ጋር መነገድ አትችልም፡፡ ስለዚህም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በዙሪያዎቿ ካሉት ሀብቶች የመጠቀም መብቷን ማረጋገጥ አለባት። ከጎረቤቶቿ ጋር በሰላም እና በፍቅር የውሃ ሃብቶቹን የምትጠቀምበትን ስትራቴጂ መንደፍ አለባት፡፡
አዲስ ዘመን፡– ሰላማዊ በሆነ መንገድ ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት እንድትሆን የሚያደርጓት አማራጮች አሉ? ካሉስ የትኞቹ ናቸው ?
ዳርእስከዳር(ዶ/ር)፡– ኢትዮጵያ እያደገ ከሚሄደው የህዝብ ቁጥሯና ኢኮኖሚዋ ጋር ተያይዞ የባህር ባር እንደሚያስፈልጋት እሙን ነው፡፡ ከያዘችው የህዝብ ቁጥር እና እያስመዘገበች ካለችው ኢኮኖሚ አኳያ በአንድ ወደብ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና መቀጠል አትችልም፡፡ ከዛሬ 30 ዓመት ጀምሮ በአንድ ወደብ ላይ ጥገኛ ሆና ዘልቃለች፡፡ ይህ ከነበረው የህዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ ዕድገት አንጻር ብዙም ተጽዕኖ ሳያመጣ ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡
አሁን ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ጨምሯል። ኢኮኖሚዋም በምስራቅ አፍሪካ በግዙፍነቱ አንደኛ ሆኗል። ስለዚህም አሁን ካለውና በቀጣይ ከሚኖረውም ግዙፍ ኢኮኖሚ አንጻር አንድ ወደብ ብቻ ገቢና ወጪ ዕቃዎችን ሊያስተናግድ አይችልም፡፡ ወጪና ገቢ ዕቃዎች ከጅቡቲ ወደብ አቅም በላይ እየሆነ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ታዲያ አማራጩ ምንድን ነው ?
ዳርእስከዳር(ዶ/ር)፡– ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል ሲባል ብዙዎች ጉዳዩን ከጦርነት ጋር ያያይዙታል፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ አማራጮቹ በርካታ ናቸው፡፡ በኪራይ ተጨማሪ ወደቦችን በማግኘት፣ ወደብ በጋራ ማልማት፣ የአካባቢ ልውውጥ በማድረግ፣ ኢትዮጵያ እያከናወነቻቸው ልማቶች ውስጥ የተወሰኑትን በመስጠት እና በምትኩ ወደብ በማግኘት ማካካስ ይቻላል፡፡ ከህዳሴ ግድብ ተርባይኖች ውስጥ የተወሰኑትን በመስጠት ወደብ በምትኩ ማግኘት ይቻላል፡፡ ሌላም ሌላውንም እንዲሁ ማድረግ ይቻላል፡፡
ለአብነት ሶማሊያ በሺዎች ኪሎ ሜትር የሚቆጠር የባህር በር አላት፡፡ ግን ይህ ሁሉ ኪሎ ሜትር ለሶማሊያ ወደብ ሆኖ ሊያገልግል የሚችል አይደለም፡፡ ስለዚህም ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለገች ወደብ ከኢትዮጵያ ጋር ማልማት ትችላለች። ወይንም ደግሞ ለም መሬት ወስዳ በምትኩ ወደብ ልታቀርብልን ትችላለች፡፡ ብቻ አማራጩ ብዙ ነው፡፡
ዘይላ ሶማሊያ እንደሀገር ከመፈጠሯ በፊት ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የባህር በር ነው፡፡ ከዛግዌ መንግሥት ጀምሮ ኢትዮጵያ በወደቡ ስትጠቀም ኖራለች፡፡ ለኢትዮጵያ ቅርበት አለው፡፡ ከሞቃዲሾ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የሚርቅ ስለሆነ ሶማሊያ ልትጠቀምበት አትችልም፡፡ ስለዚህም መነጋገር ከተቻለ በቅርብ ርቀት ላይ
የሚገኘውን የዘይላን ወደብ ኢትዮጵያ ብትጠቀምበትና ሶማሊያም በምትኩ ጥቅም ብታገኝ ሁለቱም ሀገራት አሸናፊ መሆን ይችላሉ፡፡
በተመሳሳይም ከኤርትራ ጋር በተፈጠረው መልካም የሰላም አጋጣሚ የአሰብን ወደብ በሰላማዊ አማራጭ ለመጠቀም ውይይት ማድረግ ይቻላል፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ የምትፈልጋቸው አቅርቦቶች ይኖራሉ፤ እነሱን በመስጠት አሰብን መጠቀም ይቻላል፡፡
ወደ ሶማሌ ላንድ ስንመጣ የበርበራ ወደብን በጋራ ማልማትና መጠቀም ይቻላል፡፡ ከዚህ ቀደም የኢምሬት መንግሥት 51 በመቶ፣ የሶማሊላንድ አስተዳደር 30 በመቶ እና የኢትዮጵያ መንግሥት 19 በመቶውን በማልማት ወደቡን በጋራ የማልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚችል ነው፡፡
በአጠቃላይ ግን የኢትዮጵያ ማደግ ለጎረቤት ሀገራት ዕድል ይዞ የሚመጣ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ ሲመጣ ተጨማሪ ወደቦች ያስፈልጓታል፡፡ ጎረቤት ሀገራትም ወደቦችን በማከራየት፣ በጋራ በማልማት ወይንም ከኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ምርቶችን እና አገልግሎቶችን በማግኘት ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ፡፡
ለምሳሌ ሲዊዘርላንድን ብትመለከት የባህር በር የሌላት ሀገር ነች፡፡ ነገር ግን የአካባቢው ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት የሚያምኑ ስለሆኑ በገበያ ዋጋ ለስዊዘርላንድ ወደባቸውን በቀላሉ እያከራዩ እየተጠቀሙ ነው፡፡ ለእነሱ የወደብ ጉዳይ ብዙም አወዛጋቢ አይደለም፡፡
ወደ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ ስትመጣ ግን ከአስተሳሰብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ታስተውላለህ፡፡ በጋራ ከመሥራት ይልቅ የመከልከልና ጥቅም ላይ ሳይውል ዝም ብሎ የማስቀመጥ እሳቤ ይታያል፡፡ የመንግሥታት ባህሪ ከትብብር ይልቅ መገፋፋትን የመምረጥ ነገር ይታያል፡፡ ሆኖም በሂደት አካባቢው እየሠለጠነ ሲመጣ ስዊዘርላንድና ጎረቤቶቿ በሚሄዱበት መንገድ መሄዳችን አይቀርም፡፡
ምክንያቱም መንግሥታት ከራሳቸው ስሜት ወጥተው የጋራ እድገትን ሲሹ ከኢትዮጵያ እድገት ለመቋደስ መሞከራቸው አይቀርም፡፡ ሶማሊያም ማደግ ትፈልጋለች፤ ጅቡቲም ማደግ ትፈልጋለች ፤ ኤርትራም ማደግ ትፈልጋለች፡፡ ስለዚህም አጓጊ ከሆነው የኢትዮጵያ እድገት ለመሻማት እራሳቸውን ማዘጋጀታቸው የሚቀር አይሆንም። አሁን ያለውን በመንግሥታት ደረጃ ያለውን ግንኙነት ተቋማዊ ማድረግ ከተቻለና የበለጠ መተማመን ከተፈጠረ የአሰብን ወደብ በጋራ የምንጠቀምበት ሁኔታ አይኖርም ብዬ አላስብም፡፡
ከጅቡቲ ጋር በተያያዘ እስካሁን የመጣንበት መንገድ
በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ላለፉት 30 ዓመታት በብቸኝነት የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ዕቃዎች ሲመላለሱ የቆዩት በጅቡቲ ወደብ ነው፡፡ ስለዚህም የጅቡቲ መንግሥትና ህዝብም ምስጋና የሚገባቸው ናቸው፡፡
ይህ ግን የበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ መልካም አጋጣሚ ሆኖ የጅቡቲና የኢትዮጵያ ህልውና የተሳሰረ በመሆኑ ግንኙነቱ የበለጠ ይጠናከራል ብዬ አስባለሁ። የጅቡቲ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ኢትዮጵያ ወደቡን እስከተጠቀመች ድረስ ነው፡፡
ጅቡቲዎችም ውሃና ኤሌክትሪክ የሚያገኙት ከኢትዮጵያ ነው፡፡ ይህ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተው ግንኙነት ሁለቱንም ተጠቃሚ እስካደረገ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ሆኖም አሁን ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጅቡቲ ወደብ ብቻ የሚስተናገድ አይሆንም፡፡ ስለዚህም ከጅቡቲ ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት ማጽናትና ሌሎች አማራጮችን ማማተር የግድ ይላል፡፡ ለደቡቡ የሀገራችን ክፍል ደግሞ የኬንያውን የላሙ ወደብ መጠቀም ይቻላል።
ከአካባቢው ሀገራት ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር እና ፍላጎትን ማጣጣም ከተቻለ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ አማራጮችም አሉ፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን የቻይና መንግሥት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በመሠረተ ልማት የማስተሳሰር ፍላጎት አለው። የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግሥትም ወደቦችን የማልማት ፍላጎት አለው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ የባህር በር በማጣቷ ምክንያት ምን ያህል ዋጋ ከፍላለች ?
ዳርእስከዳር(ዶ/ር)፡– ኢትዮጵያ የባህር በር ካጣችበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ዋጋ ከፍላለች፡፡ በየዓመቱ ለወደብ ከምናወጣው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በተጨማሪ ለሀገር ስትራቴጂክ የሆኑ ዕቃዎችን ለማስገባት ስትፈልግ የግድ ወደብ የሚያከራየው ሀገር ማወቅና መፍቀድ አለበት፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ምስጢር ነው ብላ የምትደብቀው ነገር አይኖራትም ማለት ነው። እንደሀገር የምትይዛቸው ምስጢሮቿ ሁሉ በወደብ ሰጪው ሀገር ዕውቅና ውስጥ የሚያልፉ ናቸው ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ አስፈላጊ የጦር መሣሪዎች ኢትዮጵያ ማስገባት ብትፈልግ በወደቡ ባለቤት ዕውቅና ማግኘት አለበት፡፡ በአጠቃላይ ጉዳዩ ከኢኮኖሚ እስከ ደህንነት ድረስ ነው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ዓለም አቀፉ ሕግ ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት እንድትሆን ምን ያህል ይደግፋታል?
ዳርእስከዳር(ዶ/ር)፡– ዓለም አቀፉ ሕግ በስምምነት እና በትብብር ያምናል፡፡ ሀገራት እስከተስማሙ ድረስ ወደብ አልባ ሀገሮች ወደብ አልምተው እንዲጠቀሙ ያበረታታል፡፡ ነገር ግን ከዓለም አቀፉ ሕግ በላይ ሊደግፈን የሚችለው ዲፕሎማሲያዊ አቅማችን ነው። ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላትና ኢኮኖሚዋም በፍጥነት እያደገ ያለች ሀገር ተቆልፎባት ትቀመጥ የሚል እሳቤ አይኖርም፡፡ ነገር ግን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይህን ማስረዳትና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡
በተለይም ደግሞ ውስጣዊ ሰላምን ማረጋገጥ ከተቻለ እና ኢኮኖሚውን በቀጣይነት ማሳደግ ከተቻለ ሁሉም ሀገር ከኢትዮጵያ ጋር መሥራት ይፈልጋል። ስለዚህም ሰላማችንን ካረጋገጥን የሌሎቹንም ሀገራት ቀልብ መግዛት ብዙም ከባድ አይሆንም፡፡
አዲስ ዘመን፡– ቀደም ሲል በመሪዎች ደረጃ ሳይቀር ወደብ ሸቀጥ ነው ሲባል ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያን ህልውና የሚወስን ጉዳይ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ እርስዎ በእነዚህ ሃሳቦች ላይ ምን ይላሉ?
ዳርእስከዳር(ዶ/ር)፡– ይህንን ጥያቄ በቀጥታ ከመመለሴ በፊት አንድ ሀገር ወደብ አለው ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን መመልከቱ ይሻላል፡፡ ወደብ አለህ ማለት በቀላሉ ከሌላው ዓለም ጋር ባሻህ ጊዜ የመገናኘት መብት አለህ ማለት ነው፡፡ ወደብ የለህም ማለት ሁልጊዜ ከሌላው ዓለም ጋር የምትገናኘው የወደብ አገልግሎት በሚሰጥህ ሀገር እስከፈቀደ ድረስ ነው፡፡ ስለዚህ ዕቃ የማስገባትና የማስወጣት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡
በጣም ምስጢራዊ የሆኑ ዕቃዎችን ለማምጣት ብትፈልግ ቢያንስ ቢያንስ ወደብ የፈቀደው ሀገር ማወቅ አለበት፡፡ ሀገር በጠላት ብትወረርና መሣሪያ ከውጭ ለማስገባት ቢሞከር ያንን መሣሪያ በምስጢር ማስገባት አይቻልም፡፡ ስለዚህም የምታስገባው መሣሪያ ምስጢር በቀላሉ በጠላት እጅ ሊወድቅ ይችላል፡፡ የሀገር ህልውና አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ አቀማመጧ ቋሚ የሆኑ ስጋቶች ያሉባት ሀገር ነች፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ቀይ ባህርና የዓባይ ውሃ ለኢትዮጵያ የእድገቷ ምንጮች ወይም የውድቀቷ መነሻዎች የሚሆኑ ናቸው፡፡ ስለዚህም ከእነዚህ ሁለቱ የውሃ አካላት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ስጋቶችን ለመቋቋም በነጻነት የምታዝበት ወደብ ያስፈልጋታል። ስለዚህም ወደብን እንደሸቀጥ መቁጠር አግባብ አይደለም። ለኢትዮጵያውያን ወደብ የህልውና ጉዳይም ጭምር ነው፡፡ ቁጥር አንድ የብሄራዊ ደህንነትም ጉዳይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ። ዳርእስከዳር(ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም