የትምህርት ጥራትን የማረጋገጡ ተግባር በአንድ ጀምበር ፍሬ አፍርቶ የሚታይ አይደለም

ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር ለትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት፤ በርካታ መዋዕለ ነዋይም ተመድቦለት የትምህርት ተደራሽነት በመላ ሀገሪቱ እንዲስፋፋ፤ መሃይምነትም እስከ ወዲያኛው አፈር እንዲለብስ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ዜጎች የትምህርት ዕድል ያገኙ ዘንድ ተሞክሯል።

ይህ የመንግሥት ጥረት የሚበረታታ ነው፤ ተግባሩ የተማረ የሰው ኃይልን በብዛት ሊያወጣ ይችል ዘንድ ታስቦ የተሠራ እንደመሆኑ መጠን ማንም በዚህ ደስ የማይሰኝ፤ ወይም፣ ያልተደሰተ ወገን አለ ለማለት ይከብዳል። ይሁን እንጂ፣ «በሁሉም አካባቢዎች የትምህርትን ተደራሽነት ከማረጋገጥ አኳያ የተሠራውን ሥራ ያህል ጥራቱ ላይ ምን ተሠርቷል?» የሚል መሠረታዊ ጥያቄ ያነሳን እንደሆነ በርካታ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑን መገንዘብ አያዳግተንም።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በሀገር አቀፍ ደረጃ 40ሺ የሚጠጉ የአንደኛ ደረጃና ከ3ሺ በላይ የሚሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል፡፡ በእነዚህ ትምህርት ቤቶችም ከ28 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከመሃይምነት ተላቀዋል፤ ወይም፣ የእውቀት ብርሃንን አግኝተዋል። ከአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ባሻገር በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተከፈቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) ብዛት ያላቸው ተማሪዎች በተለያዩ ደረጃዎች ተመርቀዋል።

ይህንን የትናንት ጉዟችንን፣ ዛሬ ላይ ሆነን ስንመዝናቸው እነዚህ ጥረቶችና ሥራዎች ብቻቸውን ውጤት አላመጡም። የትምህርት ተደራሽነትን የማስፋት ሥራው ላይ የተደከመውን ያህል በትምህርት ጥራት ላይ በቂ ትኩረት ተሰጥቶ ባለመሠራቱ ተመራማሪና ችግር ፈቺ ዜጎችን የማፍራቱ ሂደት ላይ ከፍ ያለ ተግዳሮት ተፈጥሯል።

ዛሬ፣ በተለይም አሁን ላይ እየታየ ያለው የተማሪዎች ውጤት በርካታ የቤት ሥራዎቻችንን ሳንሠራ፣ ባሉበት ከድነን ከላይ ከላይ ውጤት ያልሆነ ውጤት ስናስቆጥር እንደነበር ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል፡፡ ቀደም ሲል የነበረው የትምህርት ፖሊሲ ከጥራት ይልቅ ለብዛት ትኩረት አለመስጠቱ፣ ተማሪው በየደረጃው በቂ ዕውቀት ሳይጨብጥ ወደ’ ሚቀጥለው ክፍል እንዲያልፍ ሲደረግ እንደነበር በተጨባጭ ያመላከተ ነው ፡፡

ይህ ተማሪዎችን በገፍ የማሳለፍ ያልተገባ አካሄድ ዛሬ ላይ ሀገሪቱንም እንደ ሀገር፣ ዜጎችንም እንደ ዜጎች ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል። ጉዳዩን ከአጠቃላይ እውቀት ተነስተን ብንመዝነው፣ ጥራት የሌለው ትምህርት ጉዳቱ ብዙ ነው። ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በሌለበት ሀገር ላይ በየትኛውም ዘርፍ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎትን ለማግኘት መጠበቅ «ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ» እንደማለት ነው።

በርግጥ አሁን ላይ ያለፈ ስህተታችንን እናርማለን፤ ከብዛት ወደ ጥራት እንገባለን እያልን ነው። አዎ፣ ያለ ምንም ማመንታትና ማቅማማት በፍጥነት ከብዛት ወደ ጥራት መግባት ያስፈልጋል። ነገር ግን፣ «ወደ ምናልመው ግብ የሚያደርሱን ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ሥራዎችን ሠርተናል ወይ? የሚለው ጥያቄ አሁንም ተገቢውን ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል።

የለውጡ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ ማግስት ጀምሮ «ትምህርት ከነበረው የተዛባ አካሄድ መውጣት አለበት፤ ከሁሉም በላይ ሀገር የምትፈልገው ጥራት ያለው ትምህርት ነው » በሚል አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ከመቅረጽ ጀምሮ ፤ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ የመማር-ማስተማሩ ሂደት በአዲስ መልክ እንዲሄድ መደረጉ ይታወሳል።

እዚህ ላይ፣ «አዲሱ የትምህርት ሥርዓት ምን ያህል በሚመለከታቸው አካላት /ለትምህርት ባለ ድርሻ አካላት/ ተገቢው ትኩረት አግኝቷል? ለተግባራዊነቱስ ምን ያህል ቅድመ ዝግጅቶች ተደርጓል? የሚሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች ማንሳት ተገቢ ነው።

በተለይም ለአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ጉልበት ይሆናል ተብሎ የታሰበው የመጻሕፍት ዝግጅት ባልተጠናቀቀበት፤ ተማሪዎች መርጃ መጻሕፍት ሳያገኙ፣ ያላቸው በግላቸው እያሳተሙ በተማሩበት ሁኔታ ውጤት መጠበቃችን ለአምናውም ሆነ ለዘንድሮው ድንጋጤያችን ዋነኛ ምክንያት ይመስለኛል።

በርግጥ ተማሪዎች በዚህ ልክ ከውጤት መራቃቸው የሀገር ውድቀት ነው፤ ብዙ ቢሊዮን ብሮችን ሜዳ ላይ መበተን ነው። ነገር ግን ለውጤቱ መበላሸት የብዙ አካላት ሚና እንዳለበትም መዘንጋት አያስፈልግም።

መሬት የዘሩባትን ታበቅላለች፤ ተማሪም ያወቀውን በተግባር፣ በፈተና ይገልጻል። በፈተና ያለፈ ተማሪ ደግሞ ከክፍል ወደ ክፍል ይሸጋገራል፤ እውቀቱ በሚመጥነው ቦታ ላይ በመገኘትም የድርሻውን ይወጣል። ነገር ግን፣ ለችግሩ ተጠያቂ ተማሪውን ብቻ የምናደርግ ሰዎች ያልዘራነውን ለመሰብሰብ እየጠበቅን ስለመሆኑ በሚገባ ልንገነዘብ ይገባል፤ ይህ ደግሞ ራሱ ትልቅ ስህተት ነው ።

በወደቀው፣ ወይንም ዛሬ ላይ ዋጋ አስከፈለን ብለን በምናስበው ጥራቱን ያልጠበቀ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ አልፈው የመጡት ተማሪዎች በዚህ ሁለት አመት ውስጥ የገቡበት ችግር እኔ በግሌ ያሳዝነኛልም፤ ያሳስበኛልም። ምክንያቱ ደግሞ እነዚህ ተማሪዎች፣ ይነስም ይብዛ፣ 12 ዓመት ለፍተዋል ሀገርና ቤተሰብ ወጪ አውጥቶባቸዋል። ተስፋም ሰንቆባቸዋል።

እነዚህ ተማሪዎች በጠቀስናቸው እና ባልጠቀስናቸው ምክንያቶች ጨምሮ ከራሳቸው ቸልተኝነት ጋር ተዳምሮ ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል፤ በቀጣይ እነዚህ ወጣቶች ተስፋ እንዳያጡ ሌሎች መንገዶችን ማመላከትም ከቤተሰብ፣ ከመንግሥት፤ እንዲሁም ከሚዲያው የሚጠበቅ ዐብይ ሥራ ነው።

በተለይም በታችኛው የክፍል ደረጃ ላይ ያሉ ተማሪዎች በየደረጃቸው ብቃታቸው እየተረጋገጠ የሚሄዱበትን መንገድ ማመቻቸት፤ መምህራኖች ምን ያህል ለሚያስተምሩት ትምህርት ብቁ ናቸው የሚለውንም መፈተሽ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡

ካለፈው ዓመት ጀምሮም እየተሰጠ ባለው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተማሪዎች ብቁ በሚያደርጋቸው ውጤት ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ እያስቻለ ያለ መልካም ጅምር ነው ።

በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ከስር ከስር እየፈቱ፤ ተማሪው በራስ መተማመን በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ የሚጓዝበትን፤ በዚህም ለሀገር ትልቅ የለውጥ አቅም የሚሆንበትን አሠራር በመዘርጋት በቅርብ ዓመታት ውስጥ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል ።

በተለይም የትምህርት ጥራትን የማረጋገጡ ተግባር በአንድ ጀምበር ለፍሬ የሚበቃ ሳይሆን ረጅም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በቀጣይ ጥራት ያላቸው በርካታ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲዎችን የሚቀላቀሉበት ሂደት እየተፈጠረ እንደሚመጣ በማመን ቁርጠኛ ሆኖ መንቀሳቀስ ወሳኝ ነው።

ዛሬ ላይ ውጤታቸው ያላማረ ተማሪዎችንም ከመኮነን ወጥተን፣ እነዚህን ተማሪዎች በቀጣይ ፈተና ወስደው በተሻለ ውጤት ማለፍ እንደሚችሉ ማበረታታት፤ሕይወታቸውን ሊመሩባቸው የሚችሉባቸው ሌሎች አማራጮች እና በርካታ ዕድሎች እንዳሉም ማመላከቱ ከሁላችንም የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ።

እጸገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You