አባባሉ ልማዳዊ ስለሆነ የተባለበት ምክንያትም ልማዳዊ ነው፡፡ ወርሃ ጥቅምት በኢትዮጵያ አየር ንብረት ሁኔታ ሃይለኛ ብርድ ያለበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሙቀት ቦታ የሆነው አፋር እንኳን በወርሃ ጥቅምት ቀዝቀዝ ይላል፡፡ ከመሐል ሀገር ለሚሄደው ሰው መካከለኛ ሙቀት ሊሆን ይችላል፤ ለአፋር ነዋሪዎች ግን ‹‹ብርድ ልብስ የምንለብስበት ወር ነው›› ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ የጥቅምት ወር አፋር ድረስ እንኳን ይቀዘቅዛል ለማለት ነው፡፡
የጥቅምት ወር ጠዋት ሃይለኛ ብርድ እንዳለው ሁሉ ከረፋድ በኋላ ደግሞ ሃይለኛ ፀሐይ አለው፡፡ ብርዱም ፀሐዩም ሃይለኛ የሆነ ወር ነው፡፡ ይህ የሙቀትና ቅዝቃዜ መፈራረቅ ይመስላል በወርሃ ጥቅምት ጉንፋን ይበዛል። ይህ ወቅት እኔ ባደኩበት አካባቢ ‹‹አትንክ›› ይባላል። ጉንፋን እና ሳል የሚበዛበት ስለሆነ ነው። ‹‹ትክትክ›› ለማለት መሰለኝ፡፡ ይህ የትክትክ ወቅት ከመስከረም ወር መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ያለው ነው። በነገራችን ላይ በሳይንሳዊ መንገድም ቢሆን የመኸር ወቅት የሚጀምረው ከመስከረም 26 በኋላ ነው። በአጠቃላይ ጥቅምት ሃይለኛ ብርድ ያለበት ወቅት ስለሆነ ነው ‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት›› የተባለው፡፡
በብርድ ጊዜ ሰውነት ሃይል ይፈልጋል፡፡ ያንን ሃይል ለማግኘት ደግሞ ሃይል ሰጪ ምግቦች ያስፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ አባባሉ ልማዳዊ ብቻ ሳይሆን ሳይንሳዊ ምክንያትም ያለው ነው፡፡ ለምን እንደሆነ ለጊዜው ያገኘሁት የባለሙያ ማብራሪያ ባይኖርም በዚህ በጥቅምት ወር ብዙ ሰዎች ብረት ነክ የሆኑ ነገሮችን ሲነኩ እጃቸውን ይነዝራቸዋል፡፡ በተለይም የውሃ ቧንቧ ለመክፈት የጃኬታቸውን ወይም ሸሚዛቸውን እጅጌ የሚጠቀሙ አይቻለሁ፡፡ ብረት ነክ ነገር የሚነዝራቸው የደም ማነስ ያለባቸው ናቸው በሚል በልማዳዊ መንገድ ይነገራል፡፡
በአጠቃላይ ወርሃ ጥቅምት የክረምት መውጫ እና የመኸር ወቅት መቀበያ ስለሆነ አየሩ ለጉንፋን ይዳርጋል። በተመሳሳይ ጉንፋን የሚበዛበት ደግሞ የግንቦት ወር ነው፡፡ ግንቦት የበጋ ወቅት አልቆ ክረምት መጣሁ መጣሁ የሚልበት ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ወራት ከቅዝቃዜ ወደ ሙቀት እና ከሙቀት ወደ ቅዝቃዜ የምንሸጋገርባቸው ስለሆኑ ጉንፋን ይበዛባቸዋል፡፡
ወደ ዋናው ትዝብቴ ስሄድ፤ የተረሳውን ኮቪድ-19 ላስታውስ ነው፡፡ ኮቪድ-19 በዓለም አቀፍ ደረጃ ያደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ እንዳለ ሆኖ፤ በአንፃሩ ግን ብዙ ነገሮችንም አስተምሮናል። ከእነዚህ አንዱ የማስክ ጥቅም ነው፡፡ ምንም እንኳን ማስክ የተፈጠረውም ሆነ ጥቅም ላይ የዋለው በኮቪድ ጊዜ ባይሆንም የበለጠ የተዋወቀውና በብዙዎች ዘንድ ጥቅሙ የታወቀው ግን ከኮቪድ በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት በህክምና ተቋማትና በህክምና ባለሙያዎች አካባቢ ብቻ ነበር የሚታይ፡፡ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ግን አሁን ድረስ ማስክ የሚያደርጉ ሰዎች አሉ፡፡
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ለኮሮና ብቻ ሆኖ መቅረት የለበትም፡፡ ልብ ብላችሁ ከሆነ ያኔ ኮሮና አፍላ በነበረበት ወቅት ብዙ ሰዎች ‹‹በፊት ይይዘኝ የነበረው ጉንፋን እንኳን አልያዘኝም›› ሲሉ ነበር፡፡ ምክንያቱ ምንም ምርምር አያስፈልገውም፡፡ ለኮሮና መከላከያ የሚውሉ ነገሮች ጉንፋንንም ስለሚከላከሉ ነው፡፡ የመተላለፊያም ሆነ የመከላከያ መንገዶቻቸው ተመሳሳይ ስለሆኑ ነው፡፡ ዳሩ ግን ኮሮና አሁን ላይ አጀንዳ መሆኑ ሲቀር መከላከያዎቹን ለመሰል በሽታዎች እየተጠቀምነው አይደለም፡፡
በወቅቱ የህክምና ባለሙያዎች ሲሉ እንደነበረው፤ አብዛኞቹ የኮሮና መተላለፊያ መንገዶች ጉንፋን የሚተላለፍባቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቻችን የጉንፋን መተላለፊያና መከላከያ መንገዶችን ያወቅናቸው በኮሮና ምክንያት ነው፡፡ ከዚያ በፊት ምናልባትም በመጥፎ ሽታ እና በቀጥታ ትንፋሽ ብቻ ይመስለን ነበር፡፡ በሰላምታ ይተላለፋል፣ ልክ እንደ ኮቪድ-19 ቫይረስ በየትኛውም መገልገያ ዕቃ ላይ፣ ጉንፋን የያዘው ሰው የጨበጠው ነገር ላይ ይኖራል፡፡ ስለዚህ ለኮሮና ስንጠቀማቸው የነበሩ ነገሮችን መጠቀም ጉንፋንንም ይከላከላል ማለት ነው፡፡
ምናልባት በኮሮና ጊዜ እንደነበረው አስገዳጅ ይሁን ማለቴ አይደለም፡፡ ደረጃቸውም ይለያያል፤ ጉንፋን የለመድነው ነው፡፡ ዳሩ ግን በቀላሉ መከላከል ከተቻለ ያንኑስ ቢሆን ለምን እንታመማለን? ለምን ለሌላ ሰው እናስተላልፋለን?
ይህን ለማለት የቻልኩት ዛሬ ድረስ ማስክ የሚያደርጉ ሰዎች ስለማስተውል ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተገደው አይደለም፤ ማስክ ከሌለ አገልግሎት የለም (No Mask No Service) የሚለው የበፊቱ ሕግ አስገድዷቸው አይደለም፡፡ በአጭሩ ጥቅሙን ስለለመዱት ነው፡፡ ትራንስፖርት ውስጥ ወይም ሌላ ሕዝብ የሚበዛባቸው ቦታዎች ሲደርሱ የሚደርስባቸውን መጥፎ ሽታ ስለተከላከለላቸው ነው፡፡ በጉንፋን የተያዙ ሰዎችም በሚያስነጥሱበትና በሚያስሉበት ጊዜ ላለመሳቀቅ ነው፡፡
በአንዳንድ ካፌዎች ውስጥ ‹‹No Mask No Service›› የሚል ጽሑፍ እንዳልተነሳ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አይቼ አውቃለሁ፡፡ ምናልባት ረስተውት ይሆናል፤ በዚህም ምክንያት አንዳንድ ሰው ይስቅባቸው ይሆናል፡፡ ምንም እንኳን አሁን ላይ ማስክ ላላደረገ ሰው አገልግሎት አንሰጥም የሚል አስገዳጅ ሕግ መጠቀም ልክ ባይሆንም ማስክን ማስታወሱ ግን ችግር የለውም፡፡
ሌላው ከኮሮና መውሰድ ያለብን ልማድ እጅን በሳሙና መታጠብን ባህል ማድረግ ነው፡፡ ስለእጅ መታጠብ መናገር ሞኝነት ሊመስል ይችላል፤ ዳሩ ግን አሁንም እጅ የማይታጠቡ አሉ፡፡ በተለይ ምግብ ቤት አካባቢ ከተቀመጡበት ተነስቶ ወደ እጅ መታጠቢያው ላለመሄድ ከብርጭቆ ላይ ጣታቸው ላይ ውሃ ፈሰስ አድርገው የሚበሉ አሉ፡፡ ይሄ ለየትኛውም የውስጥ ህመም የሚዳርግ ነው፡፡ እጅ መታጠብ ከተነሳ ፤ አንድ በጣም የሚያናድደኝ ድርጊት አለ፡፡ ሆቴሎች፣ ካፌዎችና የትኛውም ምግብ የሚበላባቸው ቦታዎች ላይ መታጠቢያውን ወጥ በወጥ የሚያደርጉ ሰዎች ይገርሙኛል፡፡ እነዚህ ሰዎች በሁለቱም እጃቸው ይሆን የበሉ? ምግብ የሚጎረሰው በአንድ እጅ ነው፡፡ ታዲያ ምናለ ወጥ ባልካው እጃቸው ቢከፍቱት (ቢዘጉት)? ወጥ በነካ እጃቸው ከፍተውት ታጥበው ሲጨርሱ ለመዝጋት አይቸገሩም? ሲነኩት እጃቸው በድጋሚ ወጥ ነካ ማለት ነው፡፡
‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት›› የተባለውን ነገር በጥቅምት አንድ ማስክ ማለት ሳያስፈልግ አልቀረም። የጥቅምት ነፋስ በአፍና አፍንጫ እየገባ ከንፈርን ያደርቃል። ስለዚህ ጠዋት ጠዋት ማስክ መጠቀም መፍትሔ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ማስክ ወደ አፍና አፍንጫ የሚገባ ነገርን ለመከላከል ስለሆነ የግድ ለኮሮና ብቻ አይደለም፡፡ ‹‹ችግር ብልሃትን ይወልዳል›› እንደሚባለው በኮሮና ጊዜ የለመድናቸውን ነገሮች ጠቃሚ እስከሆኑ ድረስ እንደ አስፈላጊነቱ እንጠቀማቸው!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም