መልቀቂያ ፈተናውን የወደቅነው ሁላችንም ነን ፤

ዘንድሮም እንደ አምናው በባሰና በከፋ ሁኔታ በየዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ውጤት እንደ ሀገር፣ ሕዝብና ተቋማት ደባብቀን ያቆየነውን ገመናችንን አደባባይ በማስጣት አንገታችንን አስደፍቶናል። አሸማቆናል። ከዚህም ባሻገር ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ እኛም እንደ ሀገር፣ ሕዝብና ተቋም ከተፈታኞች እኩል መውደቃችንን አርድቶናል። የዘራነውን አሳጭዶናል። በዚህ አሳፋሪ ውጤት የተማሪዎች፣ የአስተማሪዎች፣ የወላጆችና አጠቃላይ የትምህርት ማሕበረሰቡ ቅስም ተሰብሯል። ውጤቱ በቁጭት ሁሉንም ለተሻለ ስራ ሊያነሳሳው ይገባል።

በትምህርቱ ላይ የሚታየው ልብ ድካም የሀገራችንና የሕዝባችንን ሕመም ነውና የሚያሳየው እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ መነሳት አለብን። የመማር ማስተማሩ ሒደት ከምንም ነገር በላይ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን እንዲሁም የኑሮ ውድነቱን ማስተካከል ያሻል። የፈተናው ውጤት በሌላ በኩል የመጣንበትን መንገድ ቆም ብለን እንድናብሰለስል አድርጎናል።

የትምህርት ስርዓቱ ወሳኝ መታጠፊያ ላይ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል። በእልህና በቁጭት በመነሳሳት ድክመታችንን በማረም የወደቀውን የትምህርት ጥራት በአንድነት ማሻሻል የመጀመሪያው ወሳኝ መታጠፊያ ሲሆን፤ መጭውን ጊዜ ራስን ከተጠያቂነት ለማሸሽ ጣት በመቀሳሰር ማሳለፍ እና ሌላ ትውልድ ይዞ እንደገና መውደቅ ሁለተኛው ወሳኝ መታጠፊያ ነው። መቼም የአብዛኛዎቻችን ምርጫ የመጀመሪያው ወሳኝ መታጠፊያ ነውና በእልህና በቁጭት በመነሳት ይሄን ሀገራዊ ስብራት አጅለን ውጤታማ እናደርገዋለን ብዬ አምናለሁ።

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት የደረስንበትን ሁለንተናዊ ስብራት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ስብራቱ የትምህርት ማሕበረሰቡንና ወላጁን ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ በሽታውን የሚያሳይ ነው። በትምህርት የወደቀ ሀገር እንደ ሀገር ለመቀጠል ያዳግተዋል። ጥራት ባለው ትምህርት ሀገር ተረካቢ ትውልድ ካልተፈጠረ ደግሞ የሀገር መጻኢ እድል አሳሳቢ ይሆናል።

ትምህርት የሁሉም ነገር መሠረት ነው። ይህ መሠረት በጠንካራ አለት ላይ ካልተገነባ ሀገር በአሸዋ ላይ እንደተቀለሰ ሰቀላ ነው የምትሆነው። በቀላሉ ንፋስ የሚጥላት። የትምህርት ጉዳይ የአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጉዳይ አይደለም የሚባለው ለዚህ ነው። ለመግቢያ ያህል ይሄን ካልሁ መጀመሪያ አመዳችንን ቡን ወዳደረገው የዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት፤ በማስከተል ደግሞ ለዚህ ውጤት የዳረገንን ውሽልሽል የትምህርት ስራችንን መለስ ብዬ እቃኛለሁ።

የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤትን አስመልክተው ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ የማለፊያ ነጥብ ያመጡት 27 ሺህ 267 ተማሪዎች ወይም 3 ነጥብ 2 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው። ከፍተኛ ውጤት ከተፈጥሮ ሳይንስ 649 በአዲስ አበባ ከተማ ሲመዘገብ፤ በማሕበራዊ ሳይንስ ደግሞ 533 በደብረ ማርቆስ ከተማ ተመዝግቧል።

አምስት ትምህርት ቤቶች ያስፈተኗቸውን ተማሪዎችን በሙሉ ማሳለፋቸውን፤ ከተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች ውስጥ 205 ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን፤በማሕበራዊ ሳይንስ ደግሞ 15 ተማሪዎች ከ500 በላይ ውጤት ማምጣታቸውን፤ የፈተና መመሪያ እና ደንብ በመጣስ በግል 483 ተማሪዎች እንዲሁም በቡድን 376 ተማሪዎች መቀጣታቸውን አንስተዋል።

ባለፈው ዓመት ለፈተናው ከተቀመጡት አጠቃላይ ተማሪዎች መካከል ከግማሽ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ከአራት በመቶ በታች ናቸው። የተመዘገበውን ውጤት “አስደንጋጭ” ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፈተናውን ከወሰዱት ከ980 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል ወደ 30 ሺህ የሚጠጉት ብቻ ናቸው ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ማግኘት የቻሉት። በተደጋጋሚ በብሔራዊው ፈተና ይከሰታል ሲባል የቆየውን የፈተና ስርቆት ለማስወገድ በሚል የትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው ዕቅድ መሠረት ተማሪዎቹ ፈተናውን ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ መውሰዳቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም ቀደም ሲል ከነበረው የፈተና አሰጣጥ በተለየ የተፈጥሮ ሳይንስ እና የማሕበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ተማሪዎች በተለያየ ጊዜ በተናጠል ፈተናውን ወስደዋል። ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ተግባራዊ በተደረገው አዲስ አሠራር መሠረት በፈተና ወቅት ምንም ዓይነት ስርቆት አልተፈጸመም ። ባለፈው ሐሙስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ይፋ የተደረገው ውጤትም በፈተና ወቅት የኮርጁ ተማሪዎችን ሳያካትት በሥርዓቱ መሠረት የተፈኑ ተማሪዎች ውጤት ብቻ ነው።

ለፈተናው ለመሳተፍ በአጠቃላይ 985,384 ተማሪዎች ተመዝግበው ተፈትነው ውጤት የተያዘላቸው ተማሪዎች ደግሞ 896,520 ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ ለፈተናው ተመዝግበው ያልተፈተኑ 77,098 ተማሪዎች እንዲሁም 20,170 የሚሆኑት ደግሞ በፈተናው ላይ ተገኝተው “በተለያዩ የደንብ ጥሰቶች እንዳይፈተኑ የተደረጉ እና ፈተናውን ትተው የሄዱ” መሆናቸውን ፕሮፌሰር ብርሀኑ ገልጸዋል። በአማራ ክልል በፈተናው ወቅት የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ 12 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎች ፈተናውን ላለመውሰድ ወስነው ትተው የወጡትንም ያካትታል።

ከ50 በመቶ በታች ያመጡ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደማይገቡ ሚኒስትሩ ገልጸው፤ ነገር ግን የዩኒቨርሲቲዎችን የመቀበል አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት በውጤታቸው መሠረት ተጨማሪ ተማሪዎችን በመቀበል ለቀጣይ ዓመት ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚያስችላቸውን ውጤት እንዲያገኙ ይሠራል። በመቶኛ ሲሰላ የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል የተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ተፈታኞች ከ50 በመቶ በላይ ውጤት በማስመዝገብ ከማሕበራዊ ሳይንስ አቻዎቻቸው የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል።

ከ339,642 የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች መካከል 6.8 በመቶው እንዲሁም የማሕበራዊ ሳይንስ ፈተናን ከወሰዱት 556,878 ተማሪዎች መካከል ደግሞ 1.3 በመቶው ብቻ ከ50 በመቶ በላይ ነጥብ አግኝተዋል። በዚህም መሠረት ከ50 በመቶ በላይ ነጥብ ያስመዘገቡ 30 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎች በቀጥታ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማም ገብተው ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ይሆናል።

ከዚህ ባሻገር ደግሞ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የመቀበል አቅምን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት “የተሻለ ውጤት ያመጡት ተመርጠው ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ የሚደረግ ቢሆንም እነዚህ ተማሪዎች በቀጥታ የዩኒቨርሲቲ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች እንደማይሆኑ” ተናግረዋል። ከዚያ ይልቅ ተማሪዎቹ ደካማ ውጤት ያስመዘገቡባቸውን የትምህርት ዓይነቶች ለአንድ ዓመት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲማሩ ተደርገው፤ የሚሰጣቸውን የመመዘኛ ፈተና የሚያልፉ ከሆነ የአንደኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ይጀምራሉ።

የትምህርት ሚኒስትሩ አሁን ለታየው የተማሪዎች የውጤት ማሽቆልቆል “ለዓመታት ሲንከባለል የቆየ የበርካታ ችግሮች መገለጫ እና ተሸፍኖ የቆየውን እውነተኛ የትምህርት ሥርዓት ያለበትን ደረጃ ያመለከተ ነው” ብለዋል። ለዚህ ችግር መፍትሄ ይሆን ዘንድ አጠቃላዩን የአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ለመለወጥ የሚያስችል ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቀደም ባለ አንድ ተያያዥ መጣጥፌ አበው፣ ተምሮ የማይፅፍ፣ አክፍሎ ማይገድፍ፤ የሚል ወርቅ ይትበሀል፤ ፍልስፍና እንዳላቸው ለማስታወስ ሞክሬ ነበር። አዎ ! ተምሮ ! ተምሮ ! ካልፃፈ ! ካላነበበ ! ፈተና ካላለፈ፣ በተጠየቅ ! በአመክንዮ !፣ በጥበብ ! ካልተጓዘ፤ ካልተመላለሰ፤ ማሰብ ማሰላሰል ከተሳነው፤ ምኑን ተማረው ! ? ፊደል መቁጠሩ፤ መማር መመራመሩ መና ቀረ ! ፉርሽ ሆነ ! ቀኑን ሙሉ ፆሞ፣ አክፍሎ ማይገድፍ፣ ፆም ማይፈታ ከሆነ ደግሞ የከፋ ነው።

በመንፈሳዊ አውድ ካየነውም ፀሎቱ፣ ልመናው፤ አልሰመረም፤ ወደሚል እሳቤ ይወስዳል። የተማሪውም፤ የአክፋዩም ቃል ኪዳን፣ ውል በምክንያትና በውጤት የታሰረ ነው። ከተማረ ፈተና በማለፍ/ከተማረ በመፃፍ፤ ካከፈለ በመግደፍ። ተማሪውም አጠቃላይ የትምህርት ማሕበረሰብም ይሄን ቃል ኪዳን ባለመጠበቁ ከፍ ብሎ የተገለጸውን አሳፋሪ ውጤት አስመዝግቧል።

በተለይ ባለፋት 30ና ከዚያ በላይ ዓመታት በብዙ መቶ ቢሊዮን ብር የሚገመት የሀገር የሕዝብ ሀብት በማፍሰስ ወደ ሀምሳ የሚጠጉ ዩኒቨርሲቲዎች፤ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የ1ኛና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል። ለመምህራን ስልጠና፣ ለመፅሐፍ ሕትመት፣ ለቤተ መፅሐፍትና ሙከራ ግንባታም ቀላል የማይባል የሀገር ሀብት ባክኗል።

ከዚህ ሁሉ ጊዜ፣ ድካምና ሀብት ብክነት በኋላ ግን ከ1ኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ በየደረጃው ካሉ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ ተማሪዎች፣ ሰልጣኞች መመዘኛው፣ መስፈርቱ የሚጠይቀውን ያህል የማይፅፋ፣ የማያነቡ፣ የማያገናዝቡ፣ የማያንሰላስሉና የማያመዛዝኑ ናቸው። የአንዳንድ ጥናቶች ግኝትም ይሄን ከማረጋገጥ አልፎ የሚያስደነግጥ ነው። ቢዘገይም የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተነድፎ፤ ስራዎች እዚህም እዚያም እየተሞካከሩ ይገኛል። የችግሩን መነሻ ማወቅ የመፍትሔው አካል ነውና አንድ ሁለት ነጥቦችን ላነሳሳ፦

1ኛ . የተደራሽነት ተረክ፦ ለሀገራችን ትምህርት ጥራት መውደቅ ግንባር ቀደም ምክንያት ጥራትን ወደ ጎን ገሸሽ አድርጎ ተደራሽነትን ብቻ የሙጥኝ ብሎ በፖለቲካ ቅኝት ሲመራ የኖረው የተንጋደደ የመንግስት የትምህርት ፖሊሲ ነው። ትምህርትን ተደራሽ ከማድረጉ ጎን ለጎን ጥራት ላይ አለመሰራቱ ዛሬ በየደረጃው ለተከሰተው ሀገራዊ የትምህርት ጥራት ቀውስ ዋናው ምክንያት ነው። መንግስት በማሕበራዊ ሚዲያዎች የታዘብናቸውን የዛፍ ጥላ፣ የጎጆና የሰቀላ እንዲሁም በየ”ቀበሌው ተሰሩ ! “ የተባሉ ት/ቤቶችን እንዲሁም ተማሪዎቻቸውን እየቆጠረ በአኃዝ ዕድገት ሲመፃደቅ፣ ሲጀነን ጥራቱን ለተደራሽነት መስዋዕት አድርጓል።

የጥራት ጉዳይ ከተደራሽነት ጎን ለጎን ሊሰራ ሲገባው ይሄን ያህል ዓመታት ችላ መባሉ ቀውሱን አባብሶታል። እንደ አንዳንድ የትምህርት ጥናት ጥቆማዎች፤ የጥራት ጉዳይ ቢያንስ ከአስር ዓመታት በፊት ትኩረት ሊያገኝ ይገባ ነበር። ሆኖም ዛሬ ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ትኩረት ያገኘ ይመስላል። ኩረጃን ባስቀረ አግባብ የተሰጠው የዩኒቨርሲቲ መግቢያና ሰሞኑን ይፋ የሆነው ውጤት፤ ከፈተና ውጤትነት በላይ የስርዓተ ትምህርቱ የሲቲ ስካን ምርመራ ውጤት አድርጌ ነው የወሰድሁት። የበሽታውን ደረጃ ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናልና። ይሄን የሚያክም መድኅኒት መቀመም የሁላችንም ኃላፊነት ነው።

2ኛ . ጥራተ መሰዋት፦ የቁጥር፣ ጨዋታ በራሱ የጥራት መለኪያ፤ የጥራት መገለጫና ግብ ባይሆንም እንደ ጥራት መመዘኛ ተደርጎ ተወስዷል። የትምህርት ጥራትን በተለይ የሚለካ፣ የሚመዝን ሳይንሳዊ ስነ ዘዴ መሬት ላይ አልነበረም። ቢኖርም በአግባቡ ስራ ላይ አልዋለም ነበር። ወጥነት በጎደለውና በተዝረከረከ ሁኔታ አልፎ አልፎ ጥራትን ለማስጠበቅ የሚደረግ ጥረት ቢኖርም አልዘለቀም። አንድ ተማሪ ወደ ቀጣዩ ደረጃ ለመዘዋወር ምን ማሟላት፤ ምን ያህል ዕውቀት መገብየት እንደሚጠበቅበት የሚለካበት፣ የሚመዝንበት ስልት አልነበረም።

ቢኖርም ስራ ላይ አልዋለም። ምንም እንኳ የተማሪዎች የፈተና ወጤት ከጥራት መስፈርቶች አንዱ ቢሆንም፤ ተቋማው አስተዳደራዊ እየሆነ በመጣው ኩረጃ የተነሳ መመዘኛነቱ አፈር ድሜ በልቷል። ኩረጃው ሲቀር ውጤቱ ምን እንደሆነ ደግሞ ዘንድሮ በአይናችን በብረቱ አየነው። ምክንያቱም ት/ቤቶች ይወዳደሩት የነበረው ባሳለፉት ተማሪ ብዛት እንጂ በሚሰጡት የትምህርት ጥራት ደረጃ ስላልሆነ፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መምህራን፣ የትምህርት አመራሩ ከፍ ሲልም የአስተዳደር አካሉ የተሳተፉበት የተደራጀና ተቋማዊ የሆነ ኩረጃ በተማሪዎች መካከል እንዲካሄድ፤ ከፍ ሲልም መምህራን የፈተና መልስ ሰርቶ በማደል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተማሪ በማሳለፍ ትምህርት ቤታቸውን ተሸለሚ ለማድረግ የሚካሄድ “ ከንቱ ውድድር ! “ ጥራቱን ይባስ ሲገድለው ኖሯል።

በትምህርቱ ደከም ያለን ተማሪ ክፍል ማስደገም ሀብት እንደማባከን እና እንደመምህራን ድክመት ስለሚቆጠር መምህራን ተማሪዎችን ለማስደገም አይደፍሩም ። ተማሪ እንዲደግም ያደረጉ አንዳንድ” ደፋር…! “ መምህራንም እንደ ድክመት ተቆጥሮባቸው ይገመገሙ ነበር። እንዲሸማቀቁም ተደርጓል። ከፍ ሲልም በትምህርት አመራሩ ግፊትና አስገዳጅነት የደገሙ ተማሪዎችን እንዲያሳልፉ ይታዘዛሉ፤ ይህን ትዕዛዝ የማይቀበሉ መምህራን ደግሞ ስራቸውን እንዲለቁ ጫና ይደረግባቸው ነበር።

3ኛ . የትምህርት ነፃነት አለመኖር ፦ በሀገራችን በየደረጃው ለተፈጠረው የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል አንዱ ምክንያት በትምህርት ተቋማቱ የቀለም ትምህርት ነፃነት ስላልነበር (violation of acadamic freedom) ነው። የትምህርት ስራውን በነፃነት ከመምራት ይልቅ በየደረጃው ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ይስተዋልበት ነበር። የትምህርት አስተዳደር አመራሩ፣ ርዕሰ መምህሩ፣ የፈረቃ መሪው ሳይቀር፤ በየደረጃው የሚመደበው በብቃቱ ተወዳድሮ ሳይሆን በፖለቲካ ታማኝነቱ ስለነበር፤ መምህራን በት/ቤቱ በነፃነት ሀሳባቸውን እንዲገልፁ፣ እንዲጠይቁ፣ እንዲሞግቱ ምቹ ሁኔታ አለመኖሩ፤ ተማሪዎች ስለትምህርታቸውም ሆነ ስለሀገራቸው በነፃነት እንዲመክሩ አለመፈቀዱ፤ በትምህርት ስራ ማሕበረሰቡ ላይ ተጭኖ የነበረው መዋቅራዊ አፈና መምህሩ፣ የትምህርት ስራ አመራሩ፣ ተማሪው የትምህርት ፖሊሲውንም ሆነ፤ ስርአተ ትምህርቱን በነፃነት ከስር ከስር እንዲተች እንዲታረም ስለማይደረግ ችግሩ እየተሽፋፈነ እና በፈጠራ የአፈፃፀም ሪፖርት እየተኳኳለ ዛሬ ለደረስንበት ቀውስ ዳርጎናል።

በነፃነት የመማር ማስተማር፣ የምርምር፣ የመሰብሰብ፣ የመወያየት፣ ነፃነት ከሌለበት ዩኒቨርሲቲ እንዴት ብቃት፣ ጥራት ያለው ምሩቅ ማፍራት ይቻላል? ብቁ መምህራን በሌሉበትት፣ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ዝግጁነት የሌለው ተማሪን ይዞ፤ የመማሪያ መፅሐፍት የይዘት ጥራት ባልተሟላበት፤ የትምህርት መሰረተ ልማት በአግባቡ ባልተሟሉበት፤ የወላጅ ተሳትፎ ዝቅተኛ በሆነበት፤ በተለያዩ ምክንያቶች የተከሰቱ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች መባባስ፤ ለምሩቃን ምቹ የስራ ዕድል አለመመቻቸት፤ ማሕበረሰቡ ስለ ትምህርት የነበረው በጎ አመለካከት መሸርሸሩ፤ በየደረጃው ለሕብረተሰቡ ምሳሌ፣ አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ዜጎች አለመፈጠራቸው፤ ተምሮ ጥሮ ሳይሆን በአቋራጭ ዘርፎ መበልፀግ እንደ ጀግና የሚቆጠርበት ዘመን መፈጠሩ በአንድም በሌላ በኩል ለሀገራችን የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል ሌላው ምክንያት ነው። ከፍ ብሎ የትምህርት ሚኒስትሩ እንዳሳሰቡት በሀገራችን የትምህርት ጥራት ላይ የተከሰተውን አሳሳቢ ቀውስ ለመቀልበስ ስር ነቀልና ከፖለቲካዊ ተፅዕኖ ነፃ የሆነ፤ መላ ሕዝቡን ያሳተፈ ሀገራዊና ሁሉን አካታች የትምህርት ዘርፍ መዋቅራዊ ክለሳ ሊካሄ ይገባል።

ሻሎም ! አሜን ።

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2016

Recommended For You