ሚኒስቴሩ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የጀመረውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል !

የአስራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት አሁንም ብዙዎችን እያስደነገጠና እያሳዘነ ያለ ሀገራዊ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል። ከአስደንጋጭና አሳሳቢነቱ ባሻገር ያለው እውነታ ግን ከሁሉም በላይ በትምህርት ዙሪያ ያለው ስብራት የቱን ያህል የከፋና ብዙ መስራት የሚጠይቅ አንደሆነ በግልፅ ያመላከተ መሆኑ ነው።

በተለይ ላለፉት ሶስስት አስርት ዓመታት የሀገሪቱን የትምህርት ዘርፍ ሲከታተል ለነበረ ዜጋ ጉዳዩ ብዙም አዲስ ላይሆንበት፤ ላያስደነግጠውና ላያሳዝነው ይችላል። ዛሬ ላይ ችግሩ በግልጽ ከመነገሩ ውጪ በየወቅቱ ችግሩ ምን ያህል እየገነገነ እንደሄድ በአደባባዮች ሳይቀር ብዙ ተብሎበታል።

በተለይም በትምህርቱ ዘርፍ በቋንቋ ክህሎትና በሂሳብ ትምህርት እንደ ሀገር የእውቀት ክፍተት መፈጠር ከተጀመረ ረጅም ጊዜ ተቆጥሯል። በትምህርት መስክ ከተደራሽነት ውጪ በጥራት ረገድ የተጀመረው የቁልቁለት ጉዞ ከንጉሱ ዘመን በኋላ በግልጽ እየታየ፤ በደርግ በተለይም በኢህአዴግ ዘመን እየተባባሰ መምጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው።

በመሰረቱ ዛሬ የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ልጆች ላስመዘገቡት አሳፋሪ ውጤት ከዛሬ አስራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ያለው የትምህርት ዘርፍ ጉዞቸው ዋንኛ ተጠቃሽ ምክንያት ስለመሆኑ አፍ ሞልቶ ለመናገር የሚከብድ አይደለም። ምክንያቱም ውጤቱ የመጡበት መንገድ ፍሬ ነው።

በርግጥ ውጤቱ በተማሪዎችና በተማሪዎች ቤተሰብ ላይ ሊፈጥር የሚችለው ሀዘን፣ ድንጋጤ እና ጭንቀት ከፍ ያለ ቢሆንም፤ እንደሀገር በዘርፉ የተፈጠረው ስብራት ግን ከሁሉም በላይ የተሻለች ሀገር ለመፍጠር እየተደረገ ባለው ጥረት ላይ ሊያሳድር የሚችለው አሉታዊ ተጽእኖ በቀላሉ ሊታሰብ የሚችል አይደለም።

ችግሩ የተፈታኝ ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን በአጠቃለይ በትምህርት ዘርፍ የተሳተፉ የመንግስትም ይሁን የግል ዘርፍ ባለ ድርሻ አካላትን የሚያካትት ነው። ችግሩ የሚገባውን ያህል በቂ ትኩረት ካልተሰጠው ዘንድሮ ወደ ትምህርት ቤት በሄዱና እያስተማሩ ባሉ ተማሪዎች ላይ ዳግም ላለመከሰቱ ምንም ማስተማመኛ ሊኖር አይችልም።

ይሄ መሰል ስር የያዘ ችግር ደግሞ በአንድ ወገን ጥረት የሚፈታ ሳይሆን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አንዲሁም የሕዝብን አይንና ጆሮ የሚጠይቅ ነው። በተለይም ከመንግስት/ከትምህርት ሚኒስቴር/ብዙ ይጠበቃል። ችግሩን በግልጽ ለአደባባይ እንዳበቃው ሁሉ፤ ችግሩን ለመፍታት ጠንካራ እርምጃዎችን በተጨባጭ መውሰድ ይጠበቅበታል።

በተለይም ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በዓመታት ውስጥ እየገነገነ የመጣውን፤ በዓመታት ውስጥ በሂደት እንደመጣ በሂደት ሊቀረፍ የሚችለውን፤ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ለማከም እየሄደበት ያለው የሚበረታታ መንገድ እና ቁርጠኝነት አጠናከሮ ሊቀጥልበት ይገባል።

በመሰረቱ ዘመናዊ ትምህርት በኢትዮጵያ ከተጀመረ አንስቶ የትምህርት ፋይዳ አምብዛም የማይታያቸው አባቶችና እናቶች ምንም ሳይማሩ በጣታቸው እየፈረሙ ስንት ምሁራን ባፈሩበት ሀገር በዚህ የተማረና ትምህርት ቤት በበዘባት ዘመን ይህ ውጤት መመዝገቡ ሁላችንንም አንገት የሚያስደፋ ነው።

እንደ ትምህርት ተቋም አስራ ሁለት ዓመት ካስተማርናቸው ተማሪዎች፤ 3ነጥብ 2 ከመቶ የሚያልፉበት ሀገራዊ እውነታ እየተስተዋለ ባለበት ሁኔታ፤ በውጤቱ ማዘን፣ መደንገጥና እና መጨነቅ፤ ከዛም በላይ መሸማቀቅ ያለባቸው ተማሪዎች እና ወላጆቻች ብቻ ሳይሆኑ የትምህርት ተቋማቱንና እነሱን የሚቆጣጠሯቸውን አካላት ሊሆኑ ይገባል።

ለትምህርት ዘርፍ ውጤታማነት በቀዳሚነት ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች፤ በሁለንተናዊ መልኩ ለመማር ማስተማሩ ብቁ የሆኑ መምህራን፣ የትምህርት ግብአቶች እና ቁሳቁሶች ወሳኝ ናቸው። ትምህርት ስርዓቱ የሚመራበትን የቁጥጥር ስርዓት ማጠናከርም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው።

ከዚህም ባለፈ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር የሚሰራው ስራ ስኬታማ እንዲሆን በትምህርት ፖሊሲው እና ፖሊሲውን በማስፈጸም ሂደት ውስጥ ለሚከሰቱ ችግሮች በቂ ትኩረት መስጠትን፤ ፖሊሲዎችን በየወቅቱ በመገምገም የማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባል። ለዚህ ደግሞ በበቂ ሁኔታ መዘጋጀትን ጨምሮ ቁርጠኛ ሆኖ መንቀሳቀስን ይጠይቃል!።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2016

Recommended For You