ታንዛንያ የቱሪስቶችን ቁጥር ለመጨመር በአፍረካ ረጅሙ በሆነው በኪሊማንጃሮ ተራራ ላይ በኤሌክትሪክ ገመድ የሚወጣ ተሽከርካሪ ለማሠራት አስባለች። ለዚህም ፕሮጀክት ስኬት ይሆን ዘንድ የቻይናንና የምዕራባውያን ኩባንያን እያነጋገረች ነው።
የኪሊማንጃሮን ተራራ በዓመት 50ሺ ቱሪስቶች የሚወጡ ሲሆን፤በኤሌክትሪክ ገመድ ወደ ተራራው እንዲወጣ የታሰበው ተሽከርካሪ ተግባራዊ ከሆነምይህን ቁጥር በሃምሳ በመቶኛ እንደሚጨምረው ታውቋል።
«የታንዛንያ ውጥን ተራራው መውጣት እየፈለጉ መውጣት ላልቻሉት ምቹ አጋጣሚ ይሆናል ያሉት» የሀገሪቱ የቱሪዝም ምክትል ሚኒስትር ኮምስታንቲን ካንያሱ፤የፕሮጀክቱ አዋጪነት ጥናትም እየተደረገበት ስለመሆኑ አስታውቀዋል።
መንግስት የቢዝነስ ዕቅዶችን አቅም ያላቸው ባለሀብቶችንና ትርፎችን እየዳሰሰ መሆኑ የዋጋና የምህንድስና ጉዳዮች ጨምሮ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማም እንደተካሄደበትም ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱን ለመተግበር ፍላጎት ያሳደሩ ሁለት ኩባንያዎች መኖራቸውንና አንደኛው ከቻይና መሆኑ ታውቋል። በዓለም ላይ ቀዳሚ ያልሆነው የኬብል ተሽከርካሪ በጣልያን፣ በስዊድንና በሂማሊያ ይገኛል።
ጎብኚዎችን ወደ ተራራው ጫፍ የሚወስዱት አስጎብኚዎች ቡድን በአንፃሩ፤ ፕሮጀክቱን የተቃወሙት ሲሆን፤ የኬብል ተሽከርካሪዎቹ ወደ ተራራው የሚወጡ ሰዎችን ብዛት ይቀንስብናል የሚለውም ዋነኛ ምክንያታቸው ሆኗል።
«በተለመደው መልኩ ጎብኚዎች ተራራውን ለመውጣት አንድ ሳምንት ይፈጅባቸዋል ያለው፤ የታንዛንያ አጓጓዦች ድርጅት ሊቀመንበር ሎይሺዬ ሞሌል፤ በኪሊማንጃሮ በሜሩና አቅራቢያው የሚገኝ አንድ ተራራ 20 ሺ የሚደርሱ አጓጓዦች እንደሚኖሩ ጠቁሞ፤ አዲስ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሲሆንም በማጓጓዝ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ብዛትና ገቢ በእጅጉ እንደሚቀንስው ተናግሯል። እናም «የግድ ተራራው እንደ ነበር ነው መተው ያለበት» ብሏል።
በታንዛንያ የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር በመጨመሩ ሀገሪቱ ከቱሪዝም የምታገኘው ገቢ ባለፈው ዓመት ከ7 ነጥብ 13 በመቶ ጨምሯል። በዚያው መጠን ገቢውም አድጓል። ለታንዛንያ ቱሪዝም የውጭ ምንዛሪ ዋነኛ ምንጭ ሲሆን፤ በባህር ዳርቻዎቿ በዱር እንስሳት ጉብኝትና አደን በኪሊማንጃሮ ተራራ ትታወቃለች።
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ