ሰላም የሚሻው የቱሪዝም ዘርፍ

በኢትዮጵያ በቱሪስት መስህብነት የሚታወቁ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ስፍራዎች በርካታ ናቸው።በመልክአ ምድር አቀማመጡና በተፈጥሯዊ ውበቱ፣ መንፈስን በሚያድሱ ምቹ አየርና አፍን በእጅ የሚያስይዝ ምትሃታዊ የውበት ጥግ የሚታወቁ በርካታ የመስህብ ቦታዎች አላት።

ሀገሪቱ በቱሪዝም ሀብቷ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ከሆኑ ሀገሮች መካከል አንዷ ብትሆንም ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም ግን አላገኘችም። በጎብኚዎች መዳረሻነት ከሚታወቁት ሀገራት ተርታ በቀዳሚነት መሰለፍም አልሆነላትም።

በተለይ የዘርፉን የመዳረሻ ስፍራዎች በማልማት፣ በማስተዋወቅ፣ ጎብኚዎችን በመሳብና አዳዲስ መዳረሻዎችን በመፍጠር ተጠቃሚነትን ማጎልበት ረገድ ግልፅ ድክመት እንዳለባትም በርካቶች ይስማሙበታል።

የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር የመሰረተ ልማትና የማረፊያ ቦታዎች ምቹነት እጅጉን ወሳኝ ነው። ሌሎች ሀገራት ያልታደሉት ተፈጥሯዊም ሆነ መልክአ ምድራዊ ሀብት ብትታደልም ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎቻችንን ማልማት ሳትችል ቆይታለች።

በየቱሪስት መዳረሻዎች በቂ የሚባሉ የእንግዳ ማረፊያዎች ባይኖሩም ያሉትንም በሚፈለገው ደረጃ በማደራጀት ለጎብኚዎች ምቹ መስተንግዶና አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ውስንነትም ጎልቶ ይታያል።

የአይሁድ ዝርያና የደች ዜግነት ያለው ታዋቂው የፍልስፍና ጠቢብ ባሩች ስፒኖዛ Baruch Spinoza ‹‹ If you want the present to be different from the past, study the past/ዛሬ ከትናንቱ የተሻለ እንዲሆን ከፈለግክ የትናንቱን በሚገባ አጢነው/››የሚል አባባል አለው። ይህን አባባል ዛሬን ከትናንት ለማብለጥ በተለይ ካለፈው ልምድና ተግባራችን ትምህርት መቅሰም እንደሚገባ ያስገነዝባል።

የቱሪዝም ዘርፉ ከትናንት ይልቅ ዛሬ ላይ የተሻለ ቁመና ላይ ቆሞ ለመመልከት ከተፈለገ ይህን አባባል ጠንቅቆ መረዳት የግድ ይላል።በቱሪዝም ዘርፉ ማግኘት የሚገባንን ማግኘት ያልቻልነው ለምን ይሆን ብለን መጠየቅም ተገቢ ነው።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉ እድገት ማነቆ የገባው ይመስላል።ዘርፉን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ለማድረግ የመዳረሻ ስፍራዎች በማልማት፣ በማስተዋወቅ፣ ጎብኚዎችን በመሳብና አዳዲስ መዳረሻዎችን በመፍጠር ተጠቃሚነትን ማጎልበት እንደሚቻል አምኗል።

የሀገሪቱን የቱሪስት መዳረሻነት ለማሳደግ እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ይገኝበታል። ገበታ ለሀገር በሚል ፕሮጀክት ቀደም ሲል ትኩረት ያልተሰጣቸው ቦታዎችን በመምረጥ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ነው። በዚህም ትኩረት ተነፍጎት የቆየው የሀገሪቷን የተፈጥሮ ሀብት የማልማት ሥራ በጎርጎራ፣ በኮይሻና በወንጪ አካባቢዎች በመከናወን ላይ ይገኛል።

የእነዚህእና የሌሎች ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ታዲያ የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ አቅም ይበልጥ በማጎልበት ከዘርፉ የሚገኘውንም ጥቅም ከፍ ለማድረግ ሁለንተናዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ የሚያከራክር አይሆንም።

ይሁንና የቱሪዝም ተስፋ እንዲሰምር የመዳረሻ ስፍራዎች በማልማት፣ በማስተዋወቅ፣ ጎብኚዎችን በመሳብና አዳዲስ መዳረሻዎችን ከመፍጠር ባሻገር የዘርፉን እንቅስቃሴ ሰላማዊ መንገድ ላይ ማራመድ የግድ ይላል።ለቱሪዝም ዘርፍ ልማት፣ እድገትና ተጠቃሚነት ከሁሉ በላይ ሰላም የማይተካ ሚና አለው።

ሰላም ከጥንት ፈላስፎች እስከቅርብ ጊዜ ሊቃውንት የተጠበቡበት ለሰው ልጆች በጣም አስፈላጊ የሆነ እሴት ነው። ስለ ሰላም ዋጋ የጦርነት አውዳሚነት በመጥቀስ በርካቶች ሰብከዋል። ጽፈዋል። ከእነዚህ መካከል ዕውቁ ግሪካዊ ጸሐፊና የታሪክ ሰው ሔሮዶቱስ የጦርነትን አስከፊነት እና ሰላም የውሃና የአየር ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲህ ሲል ገልጾታል።

“ In peace, sons bury their fathers. In war, fathers bury their sons!” (በሰላም ጊዜ ልጆች አባቶቻቸውን ይቀብራሉ፤ በጦርነት ጊዜ አባቶች ልጆቻቸውን ይቀብራሉ ) ሲል ይህ ግሪካዊ የታሪክ አዋቂ አባባል የጦርነት እጅግ አስከፊ ገጽን ብቻ ሳይሆን የሰላምን ጥቅም አድማሳዊነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል።

በሀገራችን ያለው ሰላም መደፍረስ ሕይወት ከመቅጠፍ ባለፈ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ ጥቁር ጥላ ማጥላት ከጀመረ ዋል አደር ብሏል።ይህን ጠንቅቆ ለመረዳትም ደግሞ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ቀላል ነው።

ለአብነትም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረውን ግጭት ተከትሎ እስካሁን ለጎብኚዎች ክፍት ያልሆነው የአክሱም ሐውልት በሰላም እጦት ከተጎዱት ውስጥ አንዱ መሆኑን መጥቀስ ይችላል።

ከወጥ አለት የተሰራውና ዓለም ስለህንጻ ንድፍ ሳይገባው አያቶቻችን ቀድመው ከላይ ወደታች ያነጹት የላሊበላ ቤተክርስቲያን በሰላም እጦት ጎብኚዎች “ጉብኝት ሰላም ሲኖር ነው” ብለው ርቀውታል። በጎንደር የሚገኘው የፋሲል ቤተመንግሥትም ዕጣ ፋንታው ተመሳሳይ ነው።

ግጭትና ጦርነት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካባቢዎች የሕገወጦች መበራከትም ለቱሪዝም ዘርፉ ከባድ አደጋ ነው። ይህ የጎበዝ አለቆች መበራከትና እኩይ ተግባርም በተለይም በብዙ ዓመታት መልካም የእንግዳ አያያዝና መስተንግዶ የተገነባው የኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይነት ሥም የሚያጎድፍ ነው።

ሰዎች በተፈጥሯችን ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ከምናገኘው መረጃ ይልቅ የቅርባችን ሰው ሲነግረን የበለጠ እናምናለን። ለቱሪስቶችም የሚሠራው ይሄ ነው። አንድ ቱሪስት ጎብኝቶ በወደደው ሀገር ቆይታውን ያራዝማል፤ ከቻለ ተመልሶ ይመጣል።ለወዳጅ ዘመድ እንዲጎበኙት ይነግራል።

በተቃራኒው በተለያዩ ምክንያቶች በሄደበት ሀገር ደስተኛ ካልሆነ የጉዞ እቅዱን ሳያጠናቅቅ አቋርጦ በፍጥነት ይመለሳል። እንኳን ለሰው ሂዱ ብሎ ሊመክር ሊሄዱ ያሰቡም ካገኘ ውሳኔያቸውን እንዲቀይሩ ጫና ያሳድራል።

ይህ እንደመሆኑም የቱሪዝም ዘርፉን የመዳረሻ ስፍራዎች በማልማት፣ በማስተዋወቅ፣ ጎብኚዎችን በመሳብና አዳዲስ መዳረሻዎችን በመፍጠር ተጠቃሚነትን ለማጎልበት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን ሰላምና መረጋጋት በማስፈንም ይበልጥ ሊታጀቡ ይገባል። የዜጎችንም ሆነ የጎብኚዎችንም በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ በሰላም የመንቀሳቀስ መብት በተጨባጭ ማረጋገጥም የግድ ነው።

ዓለም እንደ ድሮው በእንግዳ ተቀባይነት ያውቀን ዘንድ ሁላችንም ለሰላማችን ዘብ ልንቆም የግድ ይላል። ችግሮችንም በሠለጠነ መንገድ በመቀራረብ፣ በመነጋገርና መደራደር መፍታት ቀዳሚ አማራጭ ማድረግ ተገቢ ነው። ሀገር ሰላም ስትሆን ኢኮኖሚው ይነቃቃል። ቱሪዝማችንም ይጎለብታል። ከዘርፉ በሚገባን መልኩ ተጠቃሚ መሆንም ቀላል ይሆናል።

ከትዝታ ማስታወሻ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2016

Recommended For You