ስለኢትዮጵያ በሚመለከት የሚወጡ መግለጫዎች መሬት ላይ ያለውን ሃቅ የሚያሳዩ ይሁኑ!

መንግሥት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሰላም ጋር በተያያዘ ያጋጠሙንን ችግሮች በውይይት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሰፊ ጥረቶችን አድርገናል። በተለይም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተፈጥሮ የነበረውን ደም አፋሳሽ ግጭት በሰላማዊ መንገድ በድርድር ለመፍታት ረጅም ርቀቶችን ተጉዟል።

ሀገራዊ የሰላም እሴቶቻችንን በመጠቀም ችግሩን በሰላማዊ መንገድ በሀገር ሽማግሌዎች በውይይት ለመፍታት ጥረት አድርጓል። የግጭት ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የሆኑ እናቶችን የሰላም ሐዋሪያት በማድረግ የሄደበት ርቀትም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የነበረውን ጠንካራ አቋም በአደባባይ በተጨባጭ ያሳየ ነበር።

ወደ ጦርነት ከተገባም በኋላ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የተደጋገሙ ጥሪዎችን በማድረግ እንደ ሀገር የትኛውም በግጭቱ ተሳታፊ የሆነ አካል ከግጭት ተጠቃሚ ሊሆን እንደማይችል በማሳሰብ፤ ሀገር እና ሕዝብን ከግጭት እና ግጭት ሊያስከትል ከሚችለው የከፋ ጥፋት ለመታደግ በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሷል።

በርግጥ የመንግሥት ጥረቶች ሰሚ አጥተው፤ እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ የከፈልንበት ጦርነት ውስጥ ገብተናል። በዚህም ከፍ ያለ ሰብአዊ፣ ሥነልቦናዊ እና ቁሳዊ ውድመት ለማስተናገድ ተገድደናል። ከችግሩም እስካሁን ማገገም የምንችልበትን አቅም መፍጠር አልቻልንም።

ገና ከጅምሩ ለሰላም ከፍ ያለ ፍላጎት ያሳየው መንግሥት፤ በተደጋጋሚ ስለሰላም ያቀረባቸው ጥሪዎች በሕወሓት በኩል ተቀባይነት አግኝተው በአፍሪካውያን ወንድሞቻችን አሸማጋይነት በደቡብ አፍሪካ ፣ ፕሪቶሪያ የሰላም ድርድር መጀመሩ ይታወሳል።

“ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ” በሚል መርህ በተካሄደው የሰላም ድርድር በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ስምምነት ማብቂያ ማግኘቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በዚህም አካባቢው ከጥይት ድምጽ ነጻ ሆኗል። ሕይወትም በአዲስ ተስፋ ቀጥሏል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎም ሰላሙን ዘላቂ ማድረግ የሚያስችሉ፤ በስምምነቱ ላይ የሰፈሩ ነጥቦች ተግባራዊ ተደርገዋል። በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከመመስረት ጀምሮ በክልሉ ሰላማዊ ሕይወት የሚቀጥልበት የተለያዩ ተጨባጭ ተግባራት ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ነው።

እንደ ሀገር የተሀድሶ ኮሚሽን በማቋቋም በግጭት ውስጥ የነበሩ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታትና ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ በአግባቡ እየተከታተለ ነው። ፍትህና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ውይይቶችን በማድረግ ቁርሾዎችን በመሻር የተሻለች ኢትዮጵያ ለመፍጠር እየተሠራ ነው።

በክልሉ በሁለንተናዊ መልኩ ሕይወትን ወደ ቀድሞ ስፍራው ለመመለስ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሰፊ የመልሶ ግንባታዎችን አቅዶ ወደ ተግባር ገብቷል፤ የክልሉ ሕዝብ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የደረሰበትን ሰብአዊ ፣ ሥነልቦናዊ እና ቁሳዊ ውድመት እንዲያገግም በሀገር አቀፍ ደረጃ እየሠራ ነው።

ለዚህም የፌዴራል መንግሥት ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በስፋት እየተንቀሳቀሱ ነው፤ እየተመዘገበ ያለውም ውጤት ተስፋ ሰጪ ነው።ይህ ውጤት ከሰላም ስምምነቱ ማግስት ጀምሮ እየተከናወኑ ባሉ ተጨባጭ ሥራዎች የተገኘ ስለመሆኑ በችግሩ ውስጥ ለነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የአደባባይ ምስጢር ነው።

ይህንን በተጨባጭ የሚታይ፤ የሰላም ስምምነቱ ለትግራይ ሕዝብም ሆነ ለመላው ሕዝባችን ይዞት የመጣውን እፎይታ አቅልሎ ማየት ሆነ ባልተገባ መልኩ በአደባባይ መካድ የሚቻል አይደለም።

በተለይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ ኢትዮጵያን በተመለከተ ሰሞኑን ያወጡት መግለጫ ይህንን ተጨባጭ እውነታ የዘነጋ ፣ በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ ኃላፊነት የጎደለውና መሬት ላይ ያለውን ሃቅ የካደ ነው።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2016

Recommended For You