ውበት እንደ ተመልካቹ ነው ይባላል። ለአንዱ ሸጋ የሆነች ሴት ለሌኛው ደግሞ ፉንጋ ልትሆን ትችላለች። አንዳንድ ውበት ግን ያለክርክር በርካቶች ሲያሳምንና ምራቅ አስውጦ ልብን ትርክክ ሲያደርግ ይስተዋላል።
ከሰሞኑ ከወደ እንግሊዝ የተሰማ ዜና ውበት መከራ የሆነባት ሴት ስለደረሰችበት ውሳኔ አስነብቧል። ነገሩ እንዲህ ነው። በለንደን የሕግ ትምህርት ተመራቂ የሆነች የ33 ዓመት ኮረዳ አይን ከሚያስደነግጥና የልብ ትርታን የሚያጭር ውብት አላት።
የሩሲያ ተወላጅ የሆነችው ኢሪና ኮቫ የምትስኘው ይህች ሴት ስራ ለማግኘት ብዙ ብትደክምም ሊሳካላት ግን አልቻለም። ምክንያቱ ግን ለምትወዳደርባቸው ስራዎች በቂ የሆነ ልምድ አሊያም እውቀትን ሳታሟላ ቀርታ አይደለም። ይልቅስ ለስራ ቅጥር ለመወዳደር በምትሄድባቸው ተቋማት የውበቷን ፀዳል የሚመለከቱ ሁሉ እርሷን ለመቅጠር ማቅማማታቸው ነው።
ኮቫ እንደምትገልፀውም፤ የመልኳ ሳቢነት በስራ ህይወቷ ላይ ከባድ ተፅእኖ ፈጥሮባታል። በዚህም ምክንያት ብዙ ደክማለች። ስራ ለማግኘት የምታደርጋቸውን ሙከራዎች ለማሳካት ከራሷ አልፎ የሌሎችን እርዳታም አግኝታለች። በአማካሪ ባለሙያዎች ብትታገዝም ይህም ቢሆን ውጤት ማምጣት አልቻለም።
ኮቫ አዲስ ስራ ለማግኘት ብቻም ሳይሆን ቀደም ሲል የነበራትን ለማጣት የተገደደችው በውበቷ ምክንያት መሆኑን የዘገበው ኦዲቲ ሴንትራል፤ ቀደም ሲል ትሰራበት ከነበረው የንግድ ስራ ለመልቀቋም የውበቷ አማላይነት ዋነኛ ምክንያት እንደነበር አስነብቧል።
«ሳቢ ገፅታ ስላለኝ በለንደን ሥራ ማግኘት ቸገረኝ ፤ በተለይ ወንዶች ስራ ፈላጊ መስዬ አልታያቸውም›› ያለችው ኮቯ፤ የስራ ቃለመጠይቆች ብታልፍና ብትቀጠር እንኳን ወንዶች አለቆቿ ስራዋን በትጋትና በትኩረት ትሠራለች ብለው እንደማያምኗት አስረድታለች።
‹‹በሕግ ዲግሪ አለኝ፤ በቅጥር ሂደት ቁንጅና እንኳን ፈተና ሊሆን መንገዱን ያቃናል፤ይሁንና እኔ ለዚህ ባለመታደሌ፤ስራ ፍለጋ በምገባባቸው ተቋማት ሁሉ ወኪሌ የምትነግረኝ ለቃለ መጠይቅ ስቀርብ ወርቃማ ፀጉሬን በጥቁር ማቅለሚያ እንድቀባው ነው ስትልም ቅሬታዋን ገልፃለች።
በዚህ አይነት ለስራ ቅጥር ለመወዳደር በምትሄድባቸው ተቋማት ሁሉ አንድ አይነት አቋምና እሳቤን የሚያራምዱ ስለበዙባት፤በመጨረሻ ከመቀጠር ይልቅ በግሏ ለመስራት መወሰኗን የምትገልፀው ኮቫ፤የኋላ ኋላ በየግሏ የኦንላይን የጨርቃ ጨርቅ ጅምላ ማከፋፈያ ኩባንያ በመክፈት ሌሎች የነፈጓትን ስራ በራሷ ጥረት ማግኘቷ ታውቋል።
ወጣቷ ስራ ፈጣሪ ወንዶች በፍፁም እንዲቀጥሯት እንደ ማትፈልግ የዘገበው ኦዲቱ ሴንትራል፤ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቷ በእርሷ ምክንያት ስራ እንዳይስተጓጎል ስለምትፈልግ መሆኑን አስነብቧል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ