‹‹በዚህች ሀገር መሣሪያ የመያዝ ሙሉ ኃላፊነት ያለው መንግሥት ነው››አቶ ግርማ ሰይፉ የኢዜማ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል

 የዛሬው የዘመን እንግዳችን አቶ ግርማ ሰይፉ ይባላሉ፤ ነጻነትን አጥብቀው ይሻሉ። የፖለቲካውን ዓለም ሲቀላቀሉም ዋና ትኩረታቸው ለአገራቸው የሚሰጡት አንዳች ነገር ካለ በሚል ነው። እንደ ተፎካካሪ የፓርቲ አባልነታቸው ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተፎካክረው የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል መሆን ችለዋል። ትልቁ ግባቸውም ኢትዮጵያን ወደተሻለው መንገድ ማስጠጋት ነው።

በተፎካካሪ ፓርቲ ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታ ላይ አገልግለዋል፣ የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርም ሆነውም ሰርተዋል። በፓርላማ ብቸኛው የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካይ ሆነው ድምጽ ሲያሰሙ እንደነበር ይታወሳል። በፖለቲካ ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍም ለንባብ ያበቁ ናቸው።

እንግዳችን በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት የከተማዋን ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኃላፊነት እንዲመሩ ሾሟቸዋል።

አዲስ ዘመን ስለ ሀገራዊ የምክክር መድረኩ፤ ኮሚሽኑ እያከናወነ ስላለው ስራና ወቅታዊ በሆኑ የአገሪቱ ሁኔታ ዙሪያ ከአቶ ግርማ ጋር ቆይታ አድርጎ እንደሚከተለው አቅርቦታል።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ዋጋ እያስከፈሉን ያሉ መሰረታዊ ችግሮቻችንና ምንጮቻቸው ምንድን ናቸው ብለው ያምናሉ?

አቶ ግርማ፡– የችግሮቻችን አንዱና ዋነኛው ምንጭ የሚነሳው ከሐሳብ መቀንጨር ነው የሚል እምነት አለኝ። በአገራችን ችግር እንዳለ ሁሉም ሰው የሚስማማበት ጉዳይ ነው። ችግር መኖሩን አውቆ ለችግሩ መውጫ የሚሆን መንገድ መፈለግ ላይ ሰነፎች ነን። የዚህ አይነት ስንፍና የሚመጣው ከሀሳብ መቀንጨር ነው ብዬ እንዳምን አድርጎኛል።

ለዚህም ነው በአሁኑ ወቅት ትውልድ ላይ መስራት አለብን ብለን ትምህርት ቤቶች ላይ እየተንቀሳቀስን የምንገኘው። ለዚህ ደግሞ ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ እንዲሁም በጨቅላ ሕጻናት ላይ መስራት ይጠበቅብናል። ይህችን አገር ለትውልድ አሻግራለሁ ብሎ የሚያስብና ትንሽም ቢሆን ከመቀንጨር የወጣ ሰው ይህን ማጤን አለበት።

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጥያቄ አሁን ካለንበትን ችግር እንዴት እንውጣ ብቻ ሳይሆን፤ ወደፊት ይህች አገር ከችግር ወጥታ አስተማማኝ መሰረት ያላት አገር እንድትሆን ምን መስራት አለብን የሚለውም ሊሆን ይገባል።

ለምሳሌ ዛሬ ድንገት ከባድ ዝናብ ቢጥል ከዝናቡ ለመጠለል መጠለያ፤ እንዲሁም ወንዝ ሞልቶ ከሆነ ደግሞ ወንዙን ለመሻገር የሚያስችል ግንዲላ/ማሻገሪያ/ እንጣል ይባላል። ይህ ማለት ጊዜያዊ መፍትሔ ነው። አሁን ለኛ የሚያስፈልገን እንዲህ አይነቱ ጊዜያዊ መፍትሔ ሳይሆን ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ነው።

ችግራችን አቀንጭራ ነው ያልኩሽ ለዚህ ነው። ምክንያቱ የማሰብና የማስተዋል፤ ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ መፍጠር ያለመቻል ነው። አሁን ላይ ስለልጆችም ሆነ ስለትምህርት ስናወራ የአገራችን ከችግር መውጫ መንገድን እያሰብን ነው። ችግሩ ግን እዛስ እንደርሳለን ወይ? የሚለው ነው።

መሳሪያ አንስቶ መፎከር ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ መሆን አይችልም። በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ቃለ ምልልስ በተደረጉ ጊዜ አንድ ነገር ሲናገሩ ሰምቻለሁ፤ ይኸውም ”አንድ አርሶ አደር አጣማጅ በሬ ሳይኖረው ጠብመንጃ ግን ይገዛል፤ ለምንድን ነው እንዲህ የምታደርገው? ሲባል ረሃብን እታገሰዋለሁ፤ ጥቃትን ግን እንደምን አድርጌ” የሚል ምላሽ መስጠቱን ጠቅሰዋል።

እኛ ኢትዮጵያውያን በዚህ አይነት ስነ ልቦና ውስጥ ሆነን የምንኖር ነን። ነገር ግን ረሃብንም ቢሆን መታገስ አይቻልም፤ በረሀብ ውስጥም መኖር የሚቻለው እስከተወሰነ ጊዜ ነው። ሰው ይነካኛል በሚል ስጋት ብቻ ሳይኖረን ጠብመንጃ ገዝተን የምንራብበትን አጉል ባህል መተው አለብን።

የሚያጠቃንና የሚገፋን ሰው ካለ ‹‹ለምን?›› ብለን መጠየቅ አለብን። ይህን ስናደርግ አንድ ‹‹ለምን?›› ብቻ መሆን የለበትም። አንድ ‹‹ለምን?›› ብቻ አይጠቅምም። የመጀመሪያው ‹‹ለምን?›› የሚነግረን ያለውን ስሜት ብቻ ነው።

ለምሳሌ አንድን ሰው ለምን ትኮሳተራለህ? ብዬ ብጠይቀው ‹‹ራሴን አሞኝ ነው›› የሚል ምላሽ ሊሰጠኝ ይችላል። ግን ራስ ምታት በራሱ በሽታ አይደለም። ራስን ለማመሙ ምክንያቱ ሌላ ሕመም ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ራስህን ያመመህ ለምንድን ነው? ስል ሌላ ‹‹ለምን?›› ማስከተል አለብኝ። በዚህ አግባብ ‹‹ለምን?›› የሚለውን ደጋግመን መጠየቅ ግድ ይለናል። በዚህ መልኩ የምንሔድ ከሆነ ወደ ትክክለኛው የችግሩ ምክንያት /መንስኤ/ ልንደርስ እንችላለን።

አንድ ሰው በደል አድርሶ ከሆነ ‹‹ዘራፍ!›› ብሎ ከመነሳት በፊት ‹‹ስለምን በደል አደረስክ? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው። በዚህ አግባብ ከ‹‹ዘራፍ!›› ‹‹ለምን?›› መቅደም መቻል አለበት። ይህን የምናደርግ ከሆነ የውይይት ሰዎች እንሆናለን። ስንወያይ ደግሞ ‹‹ለምን?›› ብለን የምንጠይቀው ከአራትና ከአምስት ጊዜ በላይ ስለሚሆን ጉዳዮች እየጠሩና ወደ መፍትሄያቸው እየቀረቡ ይመጣሉ።

በአገራችን በተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ ያሉ አብዛኞቹ ማሕበራዊ እሴቶቻችን ስለማንጠቀምባቸው ነው እንጂ ለችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ መሆን ሊሆኑን ይችሉ ነበር። ከነዚህ አንዱ የሆነው የሽምግልና እሴታችንን መውሰድ ይቻላል።

ሽምግልና የራሱ የሆነ የአካሄድ ስርዓት አለው። በአንድ ጀምበር ተጀምሮ ላይጠናቀቅ ይችላል፤ ከዚህ የተነሳ ቀጠሮዎች ይቀጠራሉ፤ ቀጠሮው በሚፈጥረው ምልልስ ውስጥ እርስ በእርስ የበለጠ የመተዋወቅ እድል ይፈጥራል። ይህ በምልልስ ብሎም በቅርርብ የሚገኝ ውይይት ነው። መፍትሄ በማፈላለግ ሂደት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

ከዚህ በተቃራኒ ያለው የ‹‹ዘራፍ!›› ነገራችን የሽምግልና እሴቶቻችንን እየበላው መጥቷል። በአሁኑ ወቅት ከጊዜ ወደጊዜ እየፋፋ የመጣው ‹‹የዘራፍ!›› ጉዳይ ነው። ስለዚህ የ‹‹ዘራፍ!››ን እሴት ማስታገስ ያለብን በእነዚህ መልካም በሆነ እሴቶቻን በመታገዝም ጭምር መሆን አለበት።

አዲስ ዘመን፡- ‹‹ዘራፍ!›› ለመባሉ የራሱ ምክንያት አይኖረውም ይላሉ ?

አቶ ግርማ፡– መልካም፤ ወደተነሳሽበት ጥያቄ ልምጣና የችግሮቻችንን ምንጭ መዘርዘር ይቻላል፤ ለምሳሌ የቅርቦቹን ችግሮች ብንጠቅሳቸው የተሳሳቱ ትርክቶች አሉ። ከትርክቶቹ አንዱ የማንነትና የብሔር ፖለቲካን እናስፋፋለን የሚሉ ኃይሎች የፈጠሩት ያልተገባ ቁጭት ተጠቃሽ ነው።

ለምሳሌ የትግራይ አርሶ አደርን ራቁቱን ያስኬደው፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መሬቱ አፈር እንዳይኖረው ያደረገው ‹‹አማራ›› ነው ብለው እንዲያምኑ አድርገዋል። የኦሮሞ ሕዝብ ጭቆና ደርሶብኛል ብሎ እንዲያምን እና የሚጨቁነው ደግሞ ‹‹ነፍጠኛ›› የሚባል ‹‹አማራ›› ነው ብለው እንዲያምኑ የሚያደርጉም አሉ። ሱማሌ ዘንድ ሔደው ደግሞ የደረሰብህ ጭቆና እንዲደርስብህ ያደረገው ‹‹አማራ›› ነው በሚል የተሳሳተ ትርክት እንዲፈጠር ተደርጓል። ይህ ትርክት ደግሞ ‹‹አማራ›› የሚባለውን ማኅበረሰብ ያለስሙ ስም አሰጥቶታል።

አማራ ‹‹ለምን?›› እንደዚህ አደረገ ተብሎ ቢጠየቅ በእርግጥ አማራ እንደዚያ አላደረገም። አንድ እንደቀልድ የሚወራ ነገር አለ። አንድ ፕሮግራም ውጫሌ ላይ እየሰራን ባለንበት ጊዜ ከሱማሌ ክልል ወደ አማራ ክልል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሱማሌ ተወላጆች አባይን ተሻግረው አማራ የተባለውን ማኅበረሰብ እያዩ ሲሄዱ ‹‹አማራ ማለት ይህ ነው?›› ሲሉ ጠየቁን። ‹አዎ!› የሚል ምላሽም ሰጠናቸው።

‹‹እነዚህ ናቸው በደሏችሁ ያላችሁን?›› ሲሉም ጠየቁንና መልሰው ‹‹ወላሒ! ይቅር ብለናል›› አሉን። ምክንያቱም እውነታው መሬት ላይ ሲታይ የለም። በዚህ አይነት ሌላው እንዲሁ ነው። ይህ አይነቱ የተሳሳተ ትርክት አሁን ላለንበት ግጭት አንዱ ምክንያት ነው። በዚህ መልክ ፍላጎታችን ‹‹ዘራፍ!›. እስከሆነ ድረስ ብዙ ነገራችን የግጭት መንስዔ ይሆናሉ።

ሌላው የችግሮቻችን ምንጭ ደግሞ መንግስት የማያቀርበውን ነገር ‹‹አቀርባለሁ›› ብሎ ማቅረብ አለመቻል ነው። ቃል የተገባለት ነገር ሳይቀርብ ሲቀር ዜጋው ይናደዳል፤ ለምሳሌ መንግስት ስኳር፣ ጤፍ፣ ማዳበሪያና ሌላም ነገር ‹‹አቀርባለሁ›› ይላል። ሳይቀርብ ሲቀር የቅሬታ ምንጭ ይሆናል። የመንግስትም የፖሊሲ ችግር የቅሬታ ምንጭ ሊሆን ይችላል። መንግስት ቃል ገብቶ የሚፈጠሩ ቁጭቶች እንኳን እዳው ገብስ ነው። ማለቴ ጥሩ ነው፤ በተለይ እንደ እኔ ላለ ተቃዋሚ መንግስትን ከስልጣን ለማስነሳት ይጠቅማል….ሃሃሃሃ….።

ነገር ግን የኅብረሰብ ግጭቶች፤ በተለይ ማንነትን መሰረት አድርገው የሚፈጠሩ ግጭቶችን የበለጠ የሚያባብሱና የሚያቀጣጥሉ አሉ። እነዚህ ኃይሎች ግጭትን የኑሯቸው መሰረትና የገቢያቸው ምንጭ ማድረጋቸውን ተረድተን እና ነቅተን መረባረብ ይጠበቅብናል።

በአስር ሺ ማይልስ ርቀት ላይ በሚገኝ አገር ተቀምጠው ይህ ብሶት እንዳይከስም እያራገቡ የሚያጋግሉ አሉ። እነርሱ በሰው አገር በነጻነት እየኖሩ ሌላው ከአንዱ ቦታ ወደሌላ ቦታ እንኳ በቅጡ እንዳይዘዋወር፣ አንድ ቦታ ላይ ብቻ በማንነቱ ተሸብቦና ተከርችሞ እንዲቀመጥ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የሚውሉ አሉ።

ይህንኑ ጉዳይ ብቻ ስራዬ ብለው የያዙ፣ ምንም ሙያ የሌላቸውና ምንም አይነት ኃላፊነት የማይሰማቸው አሉ። በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቦታ ይዘው ግጭት እየጠመቁ ያሉት እነርሱ ናቸው። የሚጠቀሙት ከዚህ ቀደም የነበሩ የተሳሳቱ ትርክቶችን ሊሆን ይችላል፤ ለእነርሱ ይህ የገቢ ምንጫቸው ነው።

ከምንመሳሰለው ይልቅ በጣም ጥቂት የሆነውን የማንመሳሰለውን ጉዳይ በማጉላት በዚያ ዙሪያ እንድንጣላ አጥብቀው የሚመክሩን ሰዎች አሉ። እኛ ኢትዮጵያውያን ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ብትሄጂ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብም ብታቃኚ ከምንለያይበት ይልቅ የምንመሳሰልበት ደምቆ የሚታይ ሕዝብ ነን። ልዩነቶቻችን ራሳቸው ቢሆኑ የሚያጣሉን አይደሉም።

በመጀመሪያ ደረጃ መታወቅ ያለበት በእኛ አገር ብዙ ማንነቶች እንዳሉ አስመስለው የውሸት ፖለቲካ የሚያስወሩ አካላት መኖራቸው ነው። የውሸት ብዙ ማንነት እንዳለ የሚያስመስሉ አሉ። ከእኛ በቅርብ ርቀት ያለችውና በሕዝብ ቁጥርም በጣም የምታንሰው ደቡብ ሱዳን ከእኛ የበለጠ ማንነት አላት።

ቢያንስ እኛ አንድ የሚያደርገን ኢትዮጵያዊ የሆነ ትልቅ ስም፣ ፊደልም ቋንቋም ያለን ሰዎች ነን። ፊደል ስል ሁሉም ሰው በግድ አማርኛ ይናገራል ማለት አይደለም። ነገር ግን ኢትዮጵያዊ ማንነት ውስጥ ያለ መሆኑን ስንረዳ ብንችል የመጣላታችን ምክንያት አይሆንም።

ብቸኛ አፍሪካዊት ፊደል ያላት አገር ተብሎ መጠራት እና በዚህ ጥላ ውስጥ መገኘት እንዴት ይጠላል? ስለዚህ የሚያቀራርበንና የሚያመሳስለንን ከምንወስድ ይልቅ የሚያጣላን ላይ እንድናተኩር ይጎተጉቱናል። ለመጣላት ሁሉንም ልዩነት ይሰብካሉ። ልዩነትማ ከተባለ በአንድ እናትና በአንድ አባት ልጆች መካከልም ቢሆን ልዩነት አለ፤ ችግሩ ልዩነት መኖሩ አይደለም፤ ልዩነታችንን እንዴት እናስቀጥለዋለን በሚለው ላይ መስማማትና መተጋገዝ አለመቻላችን ነው።

አዲስ ዘመን፡- እነዚህን ችግሮች በመፍታት የተሻለች ሀገር ለዜጎች ለመፍጠር ትኩረት ሰጥተን ልንሰራቸው የሚገቡን ስራዎች ምንድን ናቸው?

አቶ ግርማ፡- ከግጭት ለማትረፍ የሚተጉ ሰዎችን ማንነት አውቆ እነርሱን ንቆ መተው አንዱ ማድረግ የሚገባን ጉዳይ ነው። አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የእነርሱ ያልሆኑ ትውልድ መፍጠር አለብን። ያልቀነጨረ ወጣት መፍጠር መቻል አለብን። ካልቀነጨርን የሰው መባላትና መጋጨት የቢዝነስ ሐሳብ ሆኖ አይሰራም። እንድንጣላ ሌት ተቀን የሚተጉ አካላት አካሔዳቸው እናት አባት፤ እህት ወንድም ሞቶባቸው እድር ለመብላት እንደመፈለግ ነው። የእድር ገንዘብ አገኛለሁ ብሎ ሰው እንዲሞትበት የሚፈልግ አለ? ግጭት እየፈጠሩ ቢዝነስ የሚሰሩ ሰዎች ግን ከዚህ የሚሻሉ አይደሉም። ስለዚህ እነዚህን ንቆ መተው የተሻለ ነው።

በጣም አበዛኸው ካልተባልኩ በስተቀር እንደቻይና የራሳችንን የምንገናኝበትን ኔትዎርክ ከማበጀት ውጭ ከውጭ የሚተላለፉ የማሕበራዊ ትስስር ገጾች ቢዘጉ የሚል ሁሉ ሐሳብ አለኝ። እኔ በነጻነት በጣም የማምን ሰው ነኝ፤ ለነጻነት የምሰጠውን ዋጋ ያህል ለሌላ ነገር የምሰጠው ዋጋ የለኝም። ማንም ነጻነቴን እንዲጋፋ እንደማልፈልግ ሁሉ የማንንም ነጻነት መጋፋት አልፈልግም። ነገር ግን ከነጻነቶቼ አንዱ ሐሳቤን በነጻ መግለጽ ነው ብዬ ሰዎች እርስ በእርሳቸው እንዲጋደሉ ከፈለኩ እሱ ችግር ነው።

ለምሳሌ አንድ አካባቢ ኔትወርክ ተዘጋ ሲባል፤ ሕዝቡ መረጃ የማግኘት መብቱ ተነፈገ ብለው ሲጮኹ ይደመጣል፤ አንዳንዱ አካል ጩኹታቸው እውነት ይመስለዋል። በተለይ ደግሞ ፈረንጆቹ ጅሎች ሳይሆኑ አይቀርም ያስብላል። ለምሳሌ አማራ ክልል ያለ አርሶ አደር የዩቲዩብ ፍቅር አላስችል ስለሚለው ነው? እውን ለአርሶ አደሩ አዝነውለት ነው መረጃ የማግኘት መብት ተነፈገ ብለው የሚጮኹት? አይደለም።

አንዱ አንዱን ሲገድል ፊልም አንስተው ‹‹ይኸው እየተገዳደሉ ነው›› ብለው ሊያሳዩ ነው እንጂ። ይህ ቢዝነስ ነው። ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በዩቲዩብ ተከታዮቻቸው ብዛት ገንዘብ ያገኛሉ። ስለዚህ ማለት የሚጠበቅባቸው ሱቃችን ወይም ገበያችን ተዘጋብን ነው እንጂ የዩቲዩብ መዘጋት ለአማራ አርሶ አደር ምንም የሚያመጣው ፋይዳ ኖሮት አይደለም። በኦሮሚያም ሆነ በሌላው ቦታ እንደዚያው ነው።

ለምሳሌ በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ የኢሬቻ በዓል ተከበረ፤ እኔ የአዲስ አበባ ነዋሪ ነኝ። ተወልጄ ያደግሁትም ሆነ ከ50 ዓመት በላይ የኖርኩት አዲስ አበባ ውስጥ ነው። ስለዚህ ከእኔ የበለጠ ስለአዲስ አበባ የሚያገባው ሰው ያለ አይመስለኝም። ታዲያ ኢሬቻ አዲስ አበባ ውስጥ በመከበሩ እኔ ምን እጎዳለሁ?

‹አዲስ አበባ ውስጥ ኢሬቻ ተከበረ፤ የማንነት ጫና ሊፈጠርብህ ነው፤ እንትን ሊሆን ነው›› እያሉ ጠብ ማጫር የያዙ አካላት ዓላማቸው ምን እንደሆነ ራሱ አይታወቅም፤ አዲስ አበባ ውስጥ ጨምበላላም፣ ጊፋታም፣ ሌላው ቀርቶ ከአገራችን ውጭ ያሉ ፌስቲቫሎች በየተወሰነ ጊዜ መጥተው ቢከበር ምንድን ችግሩ? እኔ የሚታየኝ ከበዓሉ መከበር በተጓዳኝ ገቢው ነው።

በእርግጥ በዓሉ ሲከበር መንግስት ጣልቃ ገብቶ የሚያደርገውን ቢያቆም ደስተኛ ነኝ። መንግስት የእኔ ነው የሚለውን አቁሞ ለኅብረተሰቡ ቢተውለት እወዳለሁ። ከዛ ውጭ ግን በአዲስ አበባ በዓመት አንዴ ብቻ የሚከበር በዓል ሳይሆን ለምን ሶስት አራቴ እንኳ አይሆንም? መከበሩ ችግሩ አይታየኝም።

ይህ የበዓላት መከበር የከተማ ባህሪ ነው፤ አዲስ አበባ የምታድገው በኢንዱስትሪ አይደለም። አዲስ አበባ የምታድገው በቱሪዝም ነው። መሆን ያለባትም የቱሪዝም ማዕከል ነው። የቱሪዝም ከተማ ሰዎች የሚመላለሱበት እና የሚዝናኑበት ነው። መሆን ያለበትም ይህ ነው። አዲስ አበባ የአየር ንብረቷም ምቹ እንደመሆኑ 24 ሰዓት መንቀሳቀስ የሚያስችል የቱሪስት ከተማ መሆን አለባት።

ይህ ግጭት እንዲነሳ የሚቀሰቅሱና አዲስ አበባ ውስጥ ‹‹‹ለምን የኢሬቻ በዓል ይከበራል?›› የሚሉ አካላት በአሜሪካ አገር ‹‹የኢትዮጵያ ቀን!›› በሚል የሚያከብሩ አካላት ናቸው። ‹‹ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም!›› እያሉ በአሜሪካ አገር ድንኳን ጥለው እየጨፈሩ ያሉ ሰዎች ናቸው።

እንዲህ ስል በኢሬቻ በዓል ከበዓሉ ዓላማ ውጭ ያልተገባ ነገር ያደረጉ አካላት ልክ ናቸው የሚል መታወቂያ እየሰጠሁ አለመሆኑ ልብ ይባልልኝ። ኢሬቻ አከብራለሁ ብሎ አደባባይ ወጥቶ ለሌላው አካል ማስጠንቀቂያ የሚሰጠው ልክ ነው እያልኩ አይደለም። ኢሬቻ፣ ጥምቀት፣ ታላቁ ሩጫና ሌላውም ሲከበር አላስፈላጊ መልዕክት ለማስተላለፍ የሚገቡ ባለጌዎችን የሚያካትት አይደለም።

በአሜሪካ አገር ‹‹የኢትዮጵያ ቀን!›› ብለው ለማክበር ወጥተው የሚሰዳደቡ አሉ፤ በዓሉ እነዚያን ባለጌዎች የሚያካትት አይደለም። በእኔ አመለካከት እንደ እነዚህ አይነት ችግሮችን መፍታት ያለብን አርቀን እያሰብንና እየተቻቻልን መሆን አለበት።

አዲስ ዘመን፡- ለችግሮቻችን መፍትሄ ከማፈላለግ አንጻር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ምን ተስፋ ይዞ መጥቷል?

አቶ ግርማ፡- እኔ ለምን ተስፋ ቆርጣለሁ? አንድ ነገር ሰው ለመስራት ሲፈልግ በመጀመሪያ መነሳት ያለበት ተስፋ አድርጎ ነው። ተስፋ እንደሌለው የሚያስብ ሰው ካለ ራሱ ተስፋ የቆረጠ ስለሆነ ያንን ሰው መስማት አያስፈልግም ባይ ነኝ። እያንዳንዷ ትንንሽ ነገር የምትደረገው ለበጎ እና ለመልካም ነገር የምትደረግ ከሆነ መስራት ያለብን እዛ በጎ ነገር ላይ ምን ባዋጣ ይሻላል ብለን ነው።

እኔ ይህንን በምሳሌ ለመግለጽ አንድ በጽኑ ሕመም ያለን ሕመምተኛ እያከመ ያለ ሐኪም ታማሚው ተስፋ የለውም ብሎ ከጀመረ ለምን ጓንትስ ያደርጋልን? ስለዚህ የአገራችንን ችግር ይፈታል ብለን ተስማምተን እያለ አይሆንም ሊባል አይገባም።

ስለዚህ ምክክር መድረኩ ብዙ ተስፋ ያለው ነው። እኔም ደግሞ በዛ ውስጥ የማዋጣው ብዙ ነገር አለኝ ብዬ አምናለሁ። ተስፋ የለውም የሚሉ ካሉ እነርሱ ለእኔ የከሸፉ ሐኪሞች አይነት ናቸው። ተስፋ የለውም የሚል አባባል የሰነፎች መገለጫ ነው። ሰነፎች ደግሞ በምክክር መድረኩ ምንም ተስፋ የለም ብለው ሌላ ቦታ ደግሞ በሁለት ዓረፍተ ነገር ጽሁፍ ጽፈው ሕዝብን ሲያበጣብጡ የሚስተዋሉ ናቸው።

እንዲህ አይነቱ ሰነፍ ሰው በእርግጥ ተረት ለመናገር ምንም ችግር የለበትም። ወይም ደግሞ የቀድሞውን የተሳሳተ ትርክት እንደ ቀልድ በማህበራዊ ትስስር ገጽ ለማስፈር አያፍርም። እንደዚህ አይነት ሰው ደግሞ ቁስል ላይ እንጨት የሚሰድ ነው።

አዲስ አበባ፡- ለኮሚሽኑ ተልእኮ ስኬታማነት ከማን ምን ይጠበቃል?

አቶ ግርማ፡– ከሁሉም አካላት የኮሚሽኑ እንቅስቃሴ ስኬታማ ይሆን ዘንድ አለመበጥበጥ ይጠበቃል። ከዚህ ጎን ለጎን ለምክክሩ ስኬታማነት ሁሉም የሚጠየቀው የሚችለውን እንዲያደርግ ነውና የሚችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርበታል ። ትልቁ ችግራችን አንዱ ሲደክመው አገር ሁሉ የደከመው መምሰሉ ነው። እሱ እንቅልፉ ስለመጣ ብቻ ሁሉም መተኛት ያማረው መምሰሉ ነው። የደከመው ካለ ወይም እንቅልፉ የመጣበት ካለ ማድረግ ያለበት ማረፍ ወይም መተኛት እንጂ ሌላውን ይዤ ልረፍ አሊያም ልተኛ ማለት አይደለም። ኑ! እንተኛ ማለት አይሰራም። የሚያበረክተው ነገር ከሌለው እጁን መሰብሰብ ይጠበቅበታል።

ሌላው አብዛኛው ሰው ወይም አብዛኛው ባለድርሻ አካል ሚናውን መለየት አለበት። በማያገባው ነገር አለመግባት ያስፈልጋል። አሁን ላይ አብዛኛው ሰው በማያገባው ከመግባት አልፎ ፖለቲከኛ ሆኗል። አንድ ሐኪም በሰለጠነበት የስራ መስክ መስራት ቢችል ምናለበት? ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች መተው ተገቢ ነው።

ምክንያቱም ሁሉም ሰው ፖለቲከኛ መሆን አይጠበቅበትም።፡ ‹‹አይ…እኔ ፖለቲከኛ እሆናለሁ›› የሚል ከሆነ የምሩን ፖለቲከኛ መሆን አለበት እንጂ ባልኮኒ በመደገፍ፣ ቡና እየጠጣ እና ማሕበራዊ ትስስር ገጽ ላይ በመጣድ ፖለቲከኛ መሆን አይቻልም። ፖለቲካ ሲባል መሰጠትን የሚፈልግ ነው፤ ዋጋ መክፈልንም የሚጠይቅ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። ለዛ የሚመጥን እውቀትና ብቃት ያለው ሰው መሆን የግድ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ችግር ፖለቲካ የእውቀት ሳይሆን የደፋሮች መሆኑ ነው። ደፋሮች ደግሞ ብዙ ጊዜ እውቀት አልባ ናቸው። እውቀት የሌለው ሰው ደግሞ ፖለቲከኛ ልሁን ሲል በጣም አደገኛ ነገር ይፈጠራል። የፖለቲካውን ቁንጮ የሚጨብጥ ሰው ትልቁን ነገር የያዘ ማለት እንደሆነ የሚታወቅ ነው፤ እሱን ደግሞ የሚይዘው ያለአዋቂ ሰው ከሆነ በስሌት ሳይሆን በስሜት የሚንቀሳቀስ ስለሚሆን ከባድ ጉዳት ሊፈጠር ይችላል።

ስለዚህ ሁሉም በየተሰማራበት ዘርፍ መስራት አለበት። የኢትዮጵያ ፖለቲካ የደፋሮችና የደንቆሮዎች መሆን የለበትም። ፖለቲካ በባህሪው ሁለገብ እውቀት የሚጠይቅ ነው። በአንድ ነገር ብቻ ስፔሻላይዝድ በማድረግ ስኬታማ መሆን የማይቻልበት ነው። በመሆኑም ፖለቲካ በምን አገባኝ ለደፋሮች ሊተው አይገባም። ሁሉንም ሊያርቅ የሚችል ኃይል በመሆኑ ጥንቃቄ የሚያሻው ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከታሪክ ትርክቶች ጋር በተያያዙ የሚነሱ አለመግባባቶችንና ቁርሾዎችን ማከም የሚያስችል እንዴት ነው ይላሉ ?

አቶ ግርማ፡- ቁርሾውም ትርክቱም ሆነ ሌላ ሌላውም ነገር አለ፤ አስቀድሜ ልገልጽልሽ እንደሞከርኩት የእነዚህ መድኃኒት ‹‹ዘራፍ!›› አይደለም። ‹‹ለምን?›› ማለት ነው። ለምሳሌ እኔ በደል ደርሶብኝም አድርሼም አላውቅም። ፖለቲካ ውስጥም የገባሁት በቁጭት ሳይሆን ለአገሬ ማበርከት የሚገባኝ ነገር አለ በሚል ነው።

ተበድያለሁና አንድ የበደለኝን አካል ፈልጌ ቁጭቴን ልወጣ በሚል ሒሳብ ለማወራረድ አይደለም። ወይም ደግሞ ቆስያለሁና ገብቼ ልታከም በሚል ስሌት አይደለም። ፖለቲካ በመሰረቱ የቁጭት ማብረጃ ሊሆን አይገባም። እንዲህ አይነት ሰዎች ካሉ መሄድ ያለባቸው ማገገሚያ ማዕከል ነው፤ ለእነርሱ ኒውከሌር ወይም ባንክና ታንክ አይሰጥም። ከተሰጣቸው የሚያስቡት ቁጭታቸውን ለማወራረድ ነው።

እኔ ከፖለቲካ ትርፍ አልፈልግም። የምሳተፈው የምሰጠው ስላለኝ ነው። ፓርቲ ውስጥም ስሳተፍ ብቻ ለብቻ ከምንሆን በጋራ የተሻለ ነገር ለአገር እናበረክታለን በሚል ስሌት ነው። መቆጨት ካለብን አገራችንን የተሻለ ለማድረግ ነው። ስለዚህ ከ‹‹ዘራፍ!›› ወደ ‹‹ለምን?›› እንምጣ እላለሁ።

ለችግሮቻችን ከስር መሰረቱ መፍትሔ ሊሆን ሚችል መድሀኒት ያስፈልገናል። ለራስ ምታት ሁሌ አስፕሪን በመውሰድ፤ ለጉበት በሽታ መዳረግ አይገባም። የራስ ምታቱ መነሻ ምን እንደሆነ በአግባቡ መታወቅ አለበት፤ ይህን ማድረግ ሲቻል ነው ራስ ምታቱን ለዘለቄታው መዳን የሚቻለው፤ የኛም ጉዳይ በዚህ መልኩ ሊታይ የሚገባ ነው።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ አመራርነቶ እና እንደ አንድ ዜጋ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ምን መደረግ ይኖርበታል ብለው ያምናሉ ?

አቶ ግርማ፡- እንደሚታወቀው እኛ እንደ ኢዜማ የጸጥታ መዋቅር የለንም። በጣም ትልቁ የምናደርገው ነገር የፓርቲያችን አባላት በምንም መልኩ የአገርን ሰላም በሚያደፈርስ አጀንዳች ውስጥ እንዳይሳተፉ ማድረግ ነው። ይህን እንዳያደርጉ ምክርም እንሰጣለን።

የፓርቲያችንም አባላት ሰዎች እንደመሆናቸው ሌላው ሊሰማው የሚችል አይነት ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። ነገር ግን ከስሜት እንዲወጡ እና ተረጋግተው እንዲያስቡ እናደርጋለን።

ቢያንስ እኛ እንደ ፓርቲያችን የችግር አባባሾች መሆን የለብንም ብለን እናምናለን። ከሁሉም በላይ ግን ለጸጥታው መደፍረስ ከውጭም ከውስጥም የሚሳተፈው አካል ረጋ እንዲል ምክራችንን እንለግሳለን።

ለምሳሌ መንግስት መሳሪያ ይዞ አስቸግሮ ከሆነ መንግስትን በጋራ ሃይ! ለማለት እንጥራለን፤ ግን ደግሞ መሳሪያ ተይዞ ፖሊስ ጣቢያ በመውረር እስረኛን ለማስለቀቅ መጣር አግባብነት የሌለው ተግባር ነው፤ ሌባን የሚጠብቀውን ፖሊስ ጣቢያ መውረር የመብት ታጋይ ምናምን መባሉ ይቀርና ሌባ መሆን ነው።

ፖሊስ ጣቢያ ወርሮ እስረኛ ማስለቀቅ አሁን አሁን ትልቅ ፋሽንና ጀብዱ ሆኗል። ስለዚህ ይህ ማለት ከተማ ውስጥ ሌባ ማሰማራት ማለት ነው። እንዲያ ከሆነ ደግሞ ሕገ ወጥነት ነው።

በዚህች አገር መሳሪያ የመያዝ ሙሉ ኃላፊነት ያለበት መንግስት ነው። በነገራችን ላይ ግለሰቦች መሳሪያ ለምን ይይዛሉ የሚል ሙግት የለኝም፤ እኔ በግሌ መሳሪያ አልይዝም። ቢያንስ የግል መሳሪያ መያዝ መብት ነው፤ ነገር ግን መሳሪያ የያዙ ሰዎች በአንድ ቀበሌ ውስጥ ተሰብስበው ራሳቸውን በሆነ ቡድን ሰይመው መንቀሳቀስ ግን በፍጹም መፈቀድ የሌለበት ጉዳይ ነው።

መሳሪያ እየታጠቁ የፈለጉ ቀን እየወጡ ታክስ የሚሰበስቡ፤ የፈለጉ ቀን ደግሞ ‹‹ወንድ የሆነ በዚህ ያልፋል›› ለሚሉ መፈቀድ የለበትም። በግል ደረጃ ግን መብት ነውና መፈቀድ አለበት፤ መንግስትም ያንን የከለከለ አይመስለኝም። እንዲያውም ምናልባት አካባቢያቸውን በመጠበቅ ተባበሩኝ ሊላቸው ይችላል። ለመንግስትም ስራ ያቀላሉ።

ነገር ግን በጎጥ በመደራጀትና መሳሪያ በመያዝ ከዚያኛው ጎጥ ጋር ግጥሚያ እና ዘራፍ ዘራፍ አይሰራም። እሱ ጸረ ሰላምነት ስለሆነ እኛ እንደ ፓርቲ እሱን አናበረታታም። ከዚህ ጎን ለጎን የምክክር ኮሚሽኑን ከመጀመሪያው ጀምሮ እየደገፍነው ነው። ያለንንም እያበረከትን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።

አቶ ግርማ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2016

Recommended For You