ከወደቅንበት ተነስተን አቧራችንን እናራግፍ

ግለ ሂሳዊ መራር ወግ፤

“የድልና የስኬትህን ዜናና ትርክት አዘግይተህ፤ በተሸነፍክበት ውድቀትና ድካም ላይ በርትተህ ጀግን!” የሚለውን ብሂል አዘውትረው የሚጠቀሙበትና ለሕይወታቸውም እንደ ዋና መርህ የሚገለገሉበት “የእስያ ነብሮች” ወይንም “የእስያ ድራጎኖች” በመባል የሚታወቁት የሩቅ ምሥራቆቹ የደቡብ ኮሪያ፣ የሲንጋፖር፣ የታይዋንና የሆንግ ኮንግ ሀገራት ዜጎች ናቸው።

በኢኮኖሚ ግስጋሴያቸውና በእድገታቸው ሽምጥ እየጋለቡ ያሉትን እነዚህን ሀገራት እግር በእግር እየተከተሉ ያሉት “ታዳጊዎቹ የነብር ደቦሎች ‹ግልገሎች›)” (ታይላንድ፣ ፊሊፒንስና ኢንዶኔዢያን የመሳሰሉት ሀገራትም) በእርምጃቸው ፈጠን ፈጠን እያሉ “በአቦ ሸማኔ ፍጥነት” ሽምጥ እየጋለቡ ያሉትን ጎረቤቶቻቸውን ሳይርቁ በቅርበት ሊደርሱባቸው በግስጋሴ ላይ ናቸው። ስለዚህም ነው በነብር ግልገልነት የተመሰሉት።

ከላይ የተጠቀሱት “ነብሮች ወይንም ድራጎኖች” በመሮጫቸው መም ላይ ቆመው ኢኮኖሚያቸውን ወደፊት ለማስፈንጠር ቃል ኪዳን በመግባት ለዕድገታቸው የመሠረት ድንጋይ የጣሉበትን እ.ኤ.አ 1960 ዓ.ምን መነሻ ብናደርግ እንኳን እነዚህ ሀገራት ዛሬ ለደረሱበት ከፍተኛ የኢኮኖሚና የተጽእኖ ፈጣሪነት ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት በስድስት ዐሠርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ መሆኑን ታሪካቸው ምስክር ነው። የዕድገታቸው ምሥጢር ደግሞ ለትምህርት ሥርዓታቸው የሰጡት ተቀዳሚ ትኩረት ነው።

ሀገራቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ እድገታቸው የሚሞካሹትና አንቱታን ያተረፉት በሚከተሉት ዋና ዋና ምክንያቶች መሆኑን የጥናት መረጃዎችን ጭምቅ ሃሳብ (Summary) ዋቢ ማድረግ ይቻላል፡- “Hong Kong and Singapore are among the most prominent worldwide financial centers, while South Korea and Taiwan are essential hubs for the global manufacturing of automobile and electronic components, as well as information technology…these Tigers share common characteristics, including a sharp focus on exports, an educated populace, and high savings rates.”

በዓለም ቀዳሚ የኢኮኖሚ የዕድገት ደረጃ ሠንጠረዥ ውስጥ በሁለተኛነትና በሦስተኛነት የተሰለፉት ቻይናና ጃፓንም እንዲሁ ከላይ የተጠቀሰውን ብሂል ሕዝባቸው በመርህነት እንዲመራበት “ስላሰለጠኑት” እነሆ ለራሳቸው በቅተው ለእኛም እስከ መትረፍ ደርሰዋል። ሀገራቱ በአብዛኛው ትርክቶችን ሲቀምሩ ውለው የሚያድሩት የትምህርት ሥርዓታቸውን ሌት ተቀን እያዘመኑ እድገትና ብልጽግና እንዴት የሀገራቸው እሴት እንደሚሆን እንጂ እንደኛ ካለፈው ታሪክ የማያግባባ ትርክቶችን በመፈልፈል ራሳቸውን እየተበተቡ አይደለም። በእኛ ዘንድ ዋጋ አጥቶ የረከሰው “መማር ያስከብራል፤ ሀገርን ያኮራል” የሚለው ዓይነት “የጥንት” እንጉርጉሮ ለእነርሱ “እንደ ብሔራዊ መዝሙር” በየዕለቱ የሚያቀነቅኑትና የሚግባቡበት ብሂል ብቻ ሳይሆን የዕለት ተዕለቱን ሕይወታቸውን የሚመሩበት መርሃቸው ጭምር ነው።

ልዩነቱ እኛ ከትናንት ታሪኮቻችን ውስጥ በእንክርዳድ የምንመስላቸውን የነበር ዘለላዎች እየመዘዝንና እየነቀስን አዳዲስ የሚያጋጩና የሚያናንቁ “አስካሪ” ትርክቶችን ስንጠምቅ፤ እነርሱ ግን ነባር ታሪኮቻቸውን በክብር አቆይተው ሲጨነቁና ሲመክሩ የሚውሉት ለዛሬውና ለነገው እድገታቸው የሚረዷቸውንና የሚያግዟቸውን አዳዲስ ሃሳቦች እንዴት በተግባር ላይ እንደሚያውሉ ነው።

እኛ ያልኖርንበትን ዘመን፣ የዘመኑን ታሪክና “ታሪክ ሰሪዎቹን” የዘመኑን ሰዎች ፍርድ ቤት ካላቆምን እያልን ያዙኝ ልቀቁን እያልን ለገላጋይ ስናስቸግር እነርሱ ግን “የነበራቸውን” በአግባቡ እየተፈተሹ ዛሬያቸው ላይ ታሪክ በመሥራት ተጠምደዋል። እኛ ግባ መሬታቸው ከተፈጸመ ሙታን አጽሞች ጋር “ይህንንና ያንን ሠርተው አልፈዋል” በማለት ግብግብ ካልገጠምን እያልን መቃብራቸውን ስንቆፍር እነርሱ ግን ለህያዋን ዜጎቻቸው ሕይወታቸውን ለማስዋብ ይጨነቃሉ።

ይህ ጸሐፊ አራት ዓመታትን በውጭ ሀገር አብሮ ከተማረው የኮሌጅ ጓደኛው የቀሰመውን አንድ እውነት ለመመስከር ርዕሰ ጉዳዩ ስለሚፈቅድለት እዚህ ቦታ ቢያስታውሰው ተገቢ ይሆናል። ይህ ታይዋናዊ ጓደኛው ቺሆንግ ከ. ይባላል። ይህ ሰው ቀንም ሆነ ሌሊት እረፍት ነስቶት የሚያብከነክነው የሀገሩ ሥልጣኔና እድገት ጉዳይ ነበር። ከትምህርት ሰዓት ውጪ ውሎው ፋብሪካዎችንና ኢንዱስትሪዎችን መጎብኘት፣ የቴክኖሎጂ ተቋማትን ማሰስ፣ አዳዲስ የሸቀጥ ምርቶችን ማጥናትና አሠራራቸውን መመርመር ነበር። በተለየ ሁኔታ ግን ለአዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የነበረው ፍቅርና አትኩሮት በልዩ ሁኔታ የሚያስገርም ነበር።

የዚህን የጓደኛዬን ጥረትና ትጋት አዘውትሬ ስለማስተውልም፡- “ከትምህርትህ እኩል ትኩረት የምትሰጥበት ይህ የዕውቀት ኀሠሣ ትጋትህ ምክንያቱ ምንድን ነው?” ብዬ በጠየቅሁት ዕለት የሰጠኝ መልስ እንዲህ የሚል ነበር፤ “ሀገሬ ታይዋን አሜሪካን ድረስ ልካ ያስተማረችኝ የወረቀት ማስረጃ ይዤ እንድመለስ ብቻ ሳይሆን ለሀገሬ እድገትና ብልጽግና የሚበጅና የሚረዳ የቴክኖሎጂ ዕውቀት ቀስሜ እንድመለስ ጭምር ነው።

ትምህርት ብቻ ቢሆንማ በሀገሬ ያሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በምንም መልኩ በጋራ እየተማርንበት ካለው ከዚህ ዩኒቨርሲቲ የሚተናነሱ አይደሉም። የእኔ ተልዕኮ በአንድ የዕውቀት ዘርፍ ሰልጥኖ መመረቅ ብቻ አይደለም። ሀገሬ ምን ይዘህ መጣህ ብላ ለምትጠይቀኝ ጥያቄ መልስ ማዘጋጀት ስላለብኝ አንዲትም ደቂቃ ቢሆን ጊዜዬን ለማባከን አልፈልግም።”

ይህ “ትንግርተኛ” ጓደኛዬ ትምህርቱን ጨርሶ እንደተመለሰ በርግጥም ሀገሩ የተቀበለችው በከፍተኛ ክብርና አድናቆት መሆኑን ከምንጻጻፈው እውነታ ተረድቻለሁ። የእኔ ሀገር ግን ተምረውም ሆነ በግላቸው ሀብት ትንሽም ቢሆን ለሀገሬ አስተዋጽኦ ላድርግና ላገልግላት ብለው የባዕድ ሀገር ኑሯቸውን እርግፍ አድርገው የሚመጡትን ልጆቿን እንኳንስ በክብር ልትቀበላቸው ቀርቶ እንደ ጥፋተኛ ሕጻን “ምን ልትፈይዱ ሀገር ብላችሁ ተመለሳችሁ?” በማለት “በቢሮክራሲና በንቀት ልምጭ ቆሌያቸውን ገፋ” ፊት እንደምትነሳቸው ከዚህ ጸሐፊ በተጨማሪነት የብዙዎችን ተመሳሳይ ምስክርነት ማድመጥ ይቻላል። ይህን ጉዳይ ለጊዜው “በሆድ ይፍጀው” ትዕግሥት በይደር ማስተላለፉ ይበጃል።

“ሀገሬን ካልጎበኘህልኝ” በማለት በስንት ውትወታ ገፋፍቼ የጋበዝኩት ሌላኛው የተሳካለት አሜሪካዊ ወዳጄም እንዲሁ ለኢትዮጵያ በጎ ለመዋል አስቦ ፕሮጀክቶች ቀርጾና ሀብቱን ይዞ አደራ ያልኩትን ሕዝቤን ለማገልገል ጨክኖ መጥቶ በሙስናና በክፋት የቆሸሸው ቢሮክራሲ አላላውስ ብሎት ተስፋ መቁረጡን የገለጸልኝ እንዲህ በማለት ነበር። “ሀገርህ በውብ ታሪኮች ያሸበረቀች መሆኑ እውነት ቢሆንም የቢሮክራሲያችሁ ቆሻሻ ግማት ግን እንኳን ለባዕዳን ቀርቶ ለእናንተ ለተወላጆችም የሚከረፋው ሽታ የሚያስቀርብ ስላይደለ ፕሮጀክቴን ወደ ኬኒያ ለማዘዋወር ተገድጃለሁ።” በእጅጉ ልብ ሰባሪ ክስተት ነበር።

እንደ ክፉ ልክፍት የተጠናወተን ብሔራዊና መልከ ብዙ የመገፋፋትና የመናናቅ አዚም መገለጫው የትዬለሌ የሚባል ዓይነት ስለሆነ ልክ እንደ ቅዱስ መጽሐፉ ናቡከደነፆር “ሕልሙም ፍቺውም ጠፍቶብን” ሕልም ተርጓሚዎችን የምንፈልግባቸው ጉዳዮቻችን ብዙዎች ናቸው። ከብዙዎቹ መካከል በአቧራ የሚመሰለውን አንድ ጉዳይ ብቻ አስታውሼ እንደተለመደው ኢትዮጵያችን ወደ ዕድገት ማማ ከፍ እንዳትል ያሽመደመዳትን ልክፍት ለማሳያነት በማመላከት አንድም ፈጣሪ ፊቱን መለስ እስኪያረግልን፣ አንድም ቅጥ አንባሩ የጠፋበት ወፈፌው ፖለቲካች ሰክኖ እስኪያሰክነን ድረስ በቁዘማ እህህ ማለትን እንቀጥል።

የትምህርት ሥርዓታችን “መጭ”፤

መጭ ሳይፈለግ የሚበቅል ኑግ መሰል ባዕድ የአዝዕርት አይነት ነው። “ሀገር ሲያረጅ መጭ ያበቅላል” መባሉም ስለዚሁ ነው። “ሀገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል” የሚለው ብሂልም የላይኛው አባባል መንትያ ጓደኛ ነው። የሀገሬ የትምህርት ሥርዓት ዛሬ ላይ ጣፋጭ ፍሬ ከማፍራት ይልቅ “የመጭ አዝመራ” ወደ ማምረት ደረጃ ላይ የተሸጋገርንበትን ምክንያት መመርመሩ ጊዜ የማይሰጠው ብሔራዊ ጉዳያችን ይመስለናል። የትምህርቱ ሥርዓት የወረሰውን አቧራ አራግፈን በተቻለ መጠን ተንገዳግደንም ቢሆን በመቆም ሀገሪቱን ካልታደግን በስተቀር የነገዋ ኢትዮጵያ መልክ ምን ሊመስል እንደሚችል ለመተንበይ አይገድም።

በቅርቡ ለሁለተኛ ጊዜ ድፍረት ተሞልቶበት ይፋ የተደረገው የሀገሪቱ የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ሀገርን ብቻ ሳይሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወላጆችንና ዜጎችን ማቅ ያለበሰ ብሔራዊ ሀዘን ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከወላጆችም አልፎ ተርፎ ዋነኞቹን ባለጉዳዮች ተማሪዎችን፣ መምህራንንና የትምህርት አስተዳደር ባለሙያዎችን አንገት ያስደፋና መሳለቂያ ያደረገ ውጤት ነው ቢባልም ግነት አያሰኝም። አንድ ሁለት ዓለም አቀፍ ዜናዎች እየተሳለቁብን የሠሩትን ዜና እንዳልደግመው “ከሰደበኝ መልሶ የነገረኝ ገደለኝ” እንዳይሆንብኝ ጉዳችንን አምቄ መያዙን መርጫለሁ።

“በ2015 ዓ.ም ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱት 845,099 የሀገሪቱ ተማሪዎች መካከል 50 ከመቶና በላይ ያመጡት ተማሪዎች ቁጥር 27,267 ወይንም 3.2% ብቻ ነው። ብሔራዊ ፈተናውን ካስፈተኑ 3,106 ት/ቤቶች መካከል 1,328 (42.8%) ት/ቤቶች አንድም ተማሪ ማሳለፍ አልቻሉም” የሚለው ሪፖርት የተደመጠበትን ዕለት እንደዚህ ጸሐፊ እምነት ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እየተውለበለበ የሀዘን ቀን ሆኖ ቢውል ተገቢ ነበር ብዬ አምናለሁ። ለሀዘኑ ከፍታ ለመጨመር ካስፈለገም መምህራኑና በየደረጃው ያሉ የትምህርት ሥርዓቱን የሚመሩት ኃላፊዎችም ጥቁር በጥቁር ለብሰው ለቅሶ መቀመጥ ነበረባቸው።

መቼም ብሔራዊ ማመካኛ ስለማይጠፋ ብዙ ሰበብ አስባቦች መስጠትን ስለተካንበት እንጂ እንዲህ ዓይነት ብሔራዊ ውድቀት ሲከሰት ቁንጮዎቹ የትምህርት አመራሮች በሕዝቡ ፊት በይፋ ንስሐ ገብተው ኃላፊነታቸውን በመልቀቅ ራሳቸውን ማዋረድ ነበረባቸው። ዳሩ “ማንን ወንድ ብለሽ” እንዳለችው ሆደ ባሻ እንስት መሆኑ በጃቸው።

ይህ ጸሐፊ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጠንከር ብሎ ለመሄስ ብዕሩን ያደፋፈረው ለትምህርት ሥርዓቱ ይነስም ይብዛ የዜግነቱን አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ስለሚሰማው ነው። በዘመነ ወጣትነቱ በሁለት የሀገራችን ተጠቃሽ ትምህርት ቤቶች (ጄኔራል ዊንጌት እና ሕይወት ብርሃን የልጃገረዶች ትምህርት ቤት) በትርፍ ሰዓት በመምህርነት ለዓመታት ያህል አገልግሏል። ከዝቅተኛ ክፍሎች እስከ ከፍተኛ ክፍሎች ዛሬም ድረስ በአገልግሎት ላይ ያሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍት ሲዘጋጁም በአስተባባሪነትና ራሱም ጸሐፊ በመሆን አገልግሏል።

ምንም እንኳን በስም እንጂ በግብር እንደሚገባ ባይሰራበትም “የፀረ ኩረጃ አምባሳደር የመሆን ማዕረግም” ከወቅቱ የፈተናዎች ኤጀንሲ አደራ ተሰጥቶት አሰሪ በመጥፋቱ ማዕረጉ በከንቱ ባክኗል። በዚህ አንጋፋ ጋዜጣ ላይም በሀገራችን የትምህርት ጉዳይ ላይ የአቅሙን ያህል ሃሳብ ከመሰንዘር አልቦዘነም። ስለዚህ አስተያየቱ ጠንከር ቢል ምክንያት አለው ለማለት ነው።

ለመሆኑ ለሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት እንዲዚህ ለመዝቀጡ ተጠያቂዎቹ እነማን ሊሆኑ ይገባል? ወፈፌ ፖለቲካችን ነው? የካሪኩለም ቀረጻና አተገባበሩ ነው? ተገቢ የትምህርት መሣሪያዎች አቅርቦት ችግር ነው? ከፈተና አዘገጃጀትና ከምዘና ጋር ያልተጣጣመ መርህ ውጤት ነው? የወላጆች ችግር ነው? የተማሪዎች የሥነ ልቦና አገነባብ፣ የሰብዕና ግንባታ መዛነፍና በነገ ተስፋቸው ላይ እምነት ማጣት ነው? የትምህርት አስተዳደሩ አንካሳነትና የመምህራኑ አቅም ማነስና ከሙያ ፍቅር ጋር የተያያዘ ችግር ነው? ወይንስ ሌላ የተሰወረብን ብሔራዊ ዓይነ ጥላ ተጠናውቶናል?

ምንም እንኳን በፈተና የመውደቅና የማለፍ ጉዳይ ያለ፣ የነበረና ወደፊትም የሚኖር እውነታ ቢሆንም “በጅምላ” ወድቃችኋል ተብሎ የተፈረደባቸውን የሀገሪቱን ልጆች ሞራል እንደምን ማስጠበቅ ይቻላል? “አንድም ተማሪ ማሳለፍ አልቻላችሁም” ተብለው አንገት የደፉት የ1,328 ትምህርት ቤቶች የወደቀ ሞራልስ በምን ዘዴ ተገንብቶ “ዳግመኛ ት/ቤት ሊባሉ” ይችላሉ። የተማሪዎች ወላጆች፣ መምህራንና የትምህርት አስተዳደሩ ጉዳይስ መፈተሽ የለበትም? የእስከዛሬ የፈተና ምዘናው የጉዞ እርምጃ በዚሁ መቀጠል ይኖርበታል? የትምህርት መሣሪያዎች አቅርቦት ችግርስ “ብሔራዊ የማመካኛ ሰበብ” ሆኖ እስከ መቼ ሊቀጥል ይችላል?

መቼም ፈታኝም ቢሆንም በሚመጥነው ልክ በጥያቄዎች ሊሞገት ስለሚገባው የትምህርት ሥርዓታችንን የወረሰው አቧራ እንዲራገፍ ካስፈለገ በእነዚህና በመሳሰሉ “ብሔራዊ አቧራዎቻችን” ላይ ሳንሽኮረመም ተወያይተን መፍትሔው ላይ መስራት ይኖርብናል። “መማር ያስከብራል ሀገርን ያኮራል” እያሉ ያስጨበጨቡን የጥንቶቹ ዘማሪዎች በሕይወት ኖረው ከሆነ ዛሬ በስተእርጅና ዘመናቸው የትምህርት ውድቀታችንን መርዶ በሰሙ እለት ምን ብለው ይሆን? ሰላም ለሀገራችን፤ ለዜጎችም በጎ ፈቃድ።

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2016

Recommended For You