በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መጠን በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል።በአሁኑ ወቅትም አሃዙ 52 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚሸፍኑት ልብና ልብ ነክ በሽታዎች መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የልብ በሽታ አስፈላጊው ሕክምናና ክትትል ከተደረገለት መዳን የሚችል ቢሆንም ሕክምናው ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ብዙዎች ለከፍተኛ ስቃይና ለሞት እየተዳረጉ ይገኛሉ። እነዚህን ህሙማን ለመታደግ የልብ ማዕከል በኢትዮጵያ ላለፉት አስር ዓመታት በሰራው ሥራ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ቢችልም፣ ዛሬም ድረስ በርካታ ወገኖች በከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛሉ። የልብ በሽታንና የማዕከሉን እንቅስቃሴ አስመልክተን የኢትዮጵያ የልብ ማዕከል ሜዲካል ዳይሬክተርና የልብ ፅኑ ህሙማን ስፔሻሊስት ከሆኑት ዶክተር ሄለን በፍቃዱ ጋር ቆይታ አድርገናል።
የልብ ሕመም እንዴት ይከሰታል?
የልብ ሕመም ልብንና ከልብ ጋር ተያይዘው ያሉ የልብ ቧንቧዎችን የሚያጠቃ ሲሆን፣ በዕድሜ የሕፃናትና የአዋቂ ተብሎ ይለያል። ሕፃናት ላይ የሚከሰተው በሁለት ይከፈላል፡፡ አንዱ ሲወለዱ በተፈጥሮ ይዘውት የሚመጡት የልብ ሕመም ሲሆን፣ ይህም በእርግዝና ወቅት እናቶች በቂ ክትትል ባለማድረጋቸው የሚከሰት ነው፤ በተለይም እንደ ስኳርና የደም ግፊት ያሉት በሽታዎች ሲኖሩ በአግባቡ ካለመታከማቸው ጋር ተያይዞ የሚከሰት ከቤተሰብ በዘር የሚተላለፍ የሕመም ዓይነት ነው።ሁለተኛውና በስፋት የሚታየው ደግሞ ከተወለዱ በኋላ ከጉሮሮ ህመም በተለይ ከቶንሲል ጋር ተያይዞ የሚመጣው ነው፤ ብዙ ጊዜ ለቶንሲል በሽታ ጤና ተቋማት ከመሄድ ይልቅ ፋርማሲ በመሄድ መድኃኒት በመስጠትና እሱንም ልጆቹ ትንሽ የመሻል ምልክት ሲያሳዩ በማቋረጥና የባህል ሕክምና በመጠቀም ቶንሲሉ በአግባቡ ባለመታከሙ ሲደጋገም የሚከሰት ነው።
በአዋቂዎች ላይ ደግሞ ከአምስት እስከ አስራ አምስት ዓመት የነበረባቸው የቶንሲል ችግር እያደገ መጥቶ የልብና የልብ ቧንቧ ችግር ይከሰታል፡፡በደም ግፊትና ስኳርን በአግባቡ ባለመቆጣጠርና ከአኗኗር ዘይቤ ጋር ተያይዞም ይከሰታል።
ከአኗኗር ዘይቤ ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የልብ ሕመም የአመጋገብ ሥርዓት ከተፈጥሮ ምግቦች በፋብሪካ ወደ ተመረቱት ሲያዘነብልና በአንፃሩ ለአካል እንቅስቃሴ ትኩረት ሳይሰጥ ሲቀር የሚመጣ የሕመም ዓይነት ነው። ይህም የሰውነት ክብደት በመጨመር የደም ዝውውር የተቀላጠፈ እንዳይሆን በማድረግ ስኳርና የደም ግፊት እንዲኖርና የኮሎስትሮል መጠራቀምን ተከትሎ የደም ቧንቧ መጥበብ እንዲከሰት በማድረግ ለልብ በሽታ ይዳርጋል።
ልብ በአግባቡ ደም መርጨት ካልቻለ ደግሞ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችንን ኩላሊትንና ጭንቅላትን ጨምሮ ለጉዳት የሚዳርግ ይሆናል። ችግሩ ሲከሰት የተለያዩ ምልክቶች የሚታዩ ሲሆን ከነዚህም መካከል የትንፋሽ ማጠር፤ በድካም ስሜት የተለመደውን የዕለት ከዕለት ተግባርን ማከናወን አለመቻልና አንዳንዴም ራስን ስቶ እስከ መውደቅ መድረስ ይታያል።
በሕፃናት ላይ ከላይ የተጠቀሰው ምልክት እንዳለ ሆኖ የሰውነት ቆዳ በተለይ ከንፈርና ጣት አካባቢ መጥቆር፣ ከዕድሜያቸው ጋር ተመጣጣኝ ክብደት አለመኖር ይከሰታል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጥቂት የአፍሪካና የፓስፊክ ሀገሮች በስተቀር ከቶንሲል ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የልብ ሕመም በጣም መቀነስ ችለዋል፤ ማጥፋት ደረጃም የደረሱ አሉ። ይህም ሊሆን የቻለው የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ለሕፃናት የሚሰጠውን የቶንሲል መድኃኒት በአግባቡ በመጠቀም በሽታውን ማዳን በመቻላቸው ነው። በአንፃሩ በእነዚህ ያደጉ ሀገራት ከኑሮ ዘይቤ ጋር ተያይዞ የሚመጣው የልብ ሕመም ከታዳጊ ሀገራት በበለጠ በበሽታ የመጠቃት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በገዳይነትም ከሚጠቀሱት አምስት በሽታዎች መካከል ይገኛል።
የልብ ሕመም ሕክምና በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ ለበሽታው ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት የተጀመረው ከ30 ዓመት በፊት ነበር።በ1981 ዓ.ም በዘውዲቱ ሆስፒታል በአንድ ትንሽ ኮንቴነር ውስጥ በልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል ነበር ሕክምናው የተጀመረው። ማዕከሉ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከ2ሺ500 በላይ የሚሆኑ ሕፃናት በሀገር ውስጥ ሊሰጥ የማይችለውን ሕክምና ውጪ በመሄድ በነፃ እንዲያገኙ ያስቻለ ሲሆን፣ ውጪ እየላኩ ማሳከሙ የትም እንደማያደርስ በመረዳትም ኅብረተሰቡንና ባለሀብቱን በማስተባበር በረጅም ጉዞ የልብ ማዕከል ለመገንባት ከሚያስችል ደረጃ አድርሷል።
ሕክምናው በተለያየ መንገድ የሚሰጥ ሲሆን የመጀመሪያው እንደ ሕመሙ ክብደት አንድም ሁለትም አንዳንዴም ከዚህ በላይ መድኃኒት እየተሰጣቸው ተመላላሽ ሕክምና የሚያደርጉበት ነው። ሁለተኛው ሕመሙ ጠንካራ ሲሆን የልብ ቀዶ ሕክምናና ‹‹ካቲተራይዜሽን›› (የጠበቡ የልብ ቧንቧዎችን ቧንቧ በሚመስል መሣሪያ በመግባት መክፈት እንዲሁም በተፈጥሮ የተከፈቱ የሕፃናትን ልብ መሸፈን) ነው። በሁለቱም ሕክምና ጊዜ የተጎዳ የልብ ክፍል በተገቢው መንገድ ካልዳነ ተመልሶ የመታመም አጋጣሚው ሰፊ ስለሆነ አስፈላጊውን ክትትል የማድረግና ግንዛቤ የማስጨበጡም ሥራ ለሕክምናው ወሳኝ ነው።
ሆስፒታሉ ተመርቆ ሥራ ከጀመረበት ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት አስር ዓመታት ከ4 ሺ 800 በላይ ለሚሆኑ የልብ ታካሚዎች በነፃ የልብ ቀዶ ሕክምና አድርጓል። ሆስፒታሉ አገልግሎት መስጠት ባይጀምር ኖሮ ምናልባትም ከ4ሺ 800 ህሙማን መካከል በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ውጪ ሄደው መታከም የሚችሉት ከ500 አይበልጡም። ይሄ ማለት ደግሞ ቀሪዎቹ በሕይወት የመኖራቸው ተስፋ የመነመነ ነበር ማለት ነው።
በአሁኑ ወቅትም ማዕከሉ በሳምንት ለሁለት ታካሚዎች የቀዶ ሕክምና እየሰጠ ነው፤ ለአንድ ቀዶ ሕክምና ከ15 ሺ እስከ 18 ሺ ዶላር ይፈጃል።
ሆስፒታሉ በቂ ቦታ፤ የሕክምና መሣሪያና ባለሙያዎች አሉት፤ ይሁንና ለሕክምና ከሚውሉት አላቂ መድኃኒቶችና መሣሪያዎች ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት በሀገር ውስጥ ገበያ የሌሉና ከውጭ የሚገቡ ውድ ናቸው።በዚህ የተነሳም የታካሚውን ቍጥር መጨመር አልተቻለም። እነዚህ ቢሟሉ በሳምንት ከአምስት እስከ ስምንት ለሚደርሱ ሕሙማን ሕክምናውን መስጠት የሚቻልበት ሁኔታ ግን አለ። የካቲተራይዜሽን ሕክምና በሳምንት ከሦስት እስከ ስድስት ለሚደርሱ ሕሙማን እየተሰጠ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከሰኞ እስከ አርብ ከ30 እስከ 40 ታካሚዎች አገልግሎት በማግኘት ላይ ናቸው። ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት በዚህ ሆስፒታል ብቻ ከ3 ሺ 500 በላይ ወረፋ የሚጠብቁ የልብ ሕሙማን አሉ።
ሕክምናውን ለማስፋፋት የሚሰሩ ሥራዎች
በተለያዩ የሪፈራል ሆስፒታሎች የልብ ሕክምና ይሰጣል።አብዛኛዎቹ የሚሰጡት ሕክምና በተመላላሽነት መድኃኒት በመስጠት የሚደረግ ሕክምና ነው። ነገር ግን በሀገሪቱ አብዛኛው ታካሚ ሕመሙ ከተባባሰና ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰ በኋላ ወደ ሕክምና ተቋማት ስለሚመጣ በሽታው በመድኃኒት ሕክምና ብቻ የሚቀረፍ አይደለም። በመሆኑም አንድም ቀዶ ሕክምና ወይንም ካቲተራይዜሽን ማድረግ ይጠበቃል።
በቅርብ ጊዜ የአዋቂ ቀዶ ሕክምና ከጀመረ አንድ ተቋም ውጪ የቀዶ ሕክምናውን በክልልም ሆነ በአዲስ አበባ የሚሰጥ ተቋም የለም። ካቲተራይዜሽኑንም ቢሆን ከሁለት የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች በስተቀር እየተሰጠ አይደለም። እስካሁን የቀዶ ሕክምናውን ሆነ ካቲተራይዜሽኑን ሙሉ ለሙሉ በነፃ እየሰጠ ያለው የልብ ማዕከል በኢትዮጵያ ብቻ ነው።
በጤና ሚኒስቴር በኩልም ቢሆን የተጀመሩ ግንባታዎች ቢኖሩም ወደ ሥራ አልገቡም። ነገር ግን ሕክምናውን ተደራሽ ለማድረግ ቢያንስ በዋና ዋና የክልል ከተሞች አንድ፣ በአዲስ አበባም አራትና አምስት ማዕከሎች ሊኖሩ ይገባል።
ሆስፒታሉ በነፃ ሕክምናውን መስጠቱ ብቻ ሳይሆን በፊት ሕክምናውን የጀመረው ሙሉ ለሙሉ በፈቃደኝነት ከውጭ በመጡ ባለሙያዎች ነበር። ተቋሙ ባለሙያዎችን ወደ ውጭ ልኮ በማሰልጠን በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ‹‹ኸርት ቲም ኢትዮጵያ›› የተባለ ያለ ማንም አጋዥነት ሙሉ ለሙሉ ራሱ ሥራውን መስራት የሚችል ሙሉ ቡድን ያሟላ መያዝ ችሏል። መስራት ከሚችለው ከአንድ ሦስተኛ በታች እየሰራ ይገኛል። በሌሎች ሆስፒታሎች ስፔሻሊስቶች ቢኖሩም ሁሉንም ዘርፍ የያዘ የለም።
ከዚህ በፊት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ብስራተ ገብርኤል አካባቢ በነፃ የሰጠው ቦታ ላይ በኅብረተሰቡና በባለ ሀብት እንዲሁም በጤና ሚኒስትር ትብብር ሁለት ባለ አምስት ወለል ሕንፃዎች ተገንብተው ተከራይተው ነው ገቢ
የሚያገኘው።አንድ ያልተጠናቀቀ ሕንፃም አለ፤ ይህንንም አጠናቆ ወደ ሥራ ማስገባት ይጠበቃል።
ሕክምናውን ለማስፋፋት ችግር የሆነው ሕክምናው የሚሰጥበት መድኃኒትና መሣሪያ በጣም ውድ በመሆኑ ነው። በግል ሆስፒታሎችም ሕክምናው የማይደፈረው ምናልባት ውድ በመሆኑ እና አትራፊ ስለማይሆን ይሆናል የሚል ግምት አለ። እንደ መንግሥትም ይሄንን ማድረግ ለሌሎቹም አንገብጋቢ የጤና ችግሮች ትኩረት መስጠት ስላለበት አዳጋች ሊሆን ይችላል።
ባደጉትም ሀገራትም የልብ ቀዶ ጥገና በየተቅማቱ አይሰጥም። በመሆኑም በአንድ ወገን ቅድሚያ ጥንቃቄ በማድረግና ምልክቶች ሲታዩ ተገቢውን ሕክምናና ክትትል በማድረግ በሽታው እንዳይከሰት ማድረግ ያስፈልጋል።በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝባዊ ተቋማት ተጠናክረው ሕክምናው ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆን የበኩላቸውን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ማዕከሉ በነፃ የሚሰጠውን አገልግሎት አጠናክሮ እንዲቀጥል ቋሚ ገቢ እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ድጎማው ለዕለት ፍጆታ ካልሆነ ዘላቂነት አይኖረውም፤ ሕክምናውን ማዳረሰም አያስችልም።ማዕከሉ የምርምርና የሥልጠና አገልግሎቱን ማስፋፋት ይኖርበታል።በእነዚህ ላይ ሁሉ ማዕከሉ 30ኛ የምስረታ በዓሉን ሰኔ ስምንት 2011 ዓ.ም ሲያከብር ለሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ ለመፍጠር የሚሰራ ይሆናል።
ለልብ ሕመም ሊደረግ የሚገባው ቅድመ ጥንቃቄ
ሕክምናው ውድ እና በቶሎ የማይገኝ መሆኑን በመረዳት መከላከሉ ላይ ትኩረት መስጠት አዋጭ ነው። በመሆኑም ልጆች የቶንሲል በሽታ ሲከሰትባቸው በወቅቱና በአግባቡ ማሳከም፣ የተሰጡ መድኃኒቶችን በትዕዛዙ መሠረት መጨረስ ያስፈልጋል።በተቻለ መጠን በተለይ ቢሮ ውስጥ የሚውልና አብዛኛውን ጊዜውን በተሽከርካሪ ላይ የሚያሳልፍ ሰው የአካል እንቅስቃሴና የእግር ጉዞ ማድረግ ይኖርበታል።
የአመጋገብ ሥርዓትን በማስተካከል በተቻለ መጠን ከፋብሪካ ምርቶች ይልቅ ተፈጥሯዊ ምግቦችን መጠቀም ይገባል። ሕመም ባይኖርም ጤናን ያለበትን ደረጃ በየወቅቱ በመመርመር ማወቅና በተለይም ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ሲታዩ በፍጥነት ወደ ሐኪም መቅረብ ይገባል ሲሉ ዶክተር ሄለን አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ