በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ወንድም ኢሳያስ ዳኘው፣ ኮሎኔል አሰፋ ዮሃንስ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩት ያሬድ ዘሪሁን፣ ተስፋዬ ኡርጌ፣ የኢትዮ ቴሌኮም የሴኪውሪቲ ዲቪዥን ኃላፊ የነበሩት ኮሎኔል ጉደታ ኦላና እና ሌሎች ሦስት ተጠርጣሪዎች ትናንት ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ተጠርጣሪዎቹ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ነው የቀረቡት።
ፍርድ ቤቱ በበለስ አንድ ፕሮጀክት ያለአግባብ ለሁለት የውጭ ድርጅቶች የግንባታ ውል በመስጠት ከፍተኛ የህዝብና የመንግስት ሃብት እንዲባክን በማድረግ የተጠረጠሩት ኮሎኔል አሰፋ ዮሃንስ ላይ ፖሊስ የቀረውን ምርመራ አጠናቆ እንዲያቀርብ 10 ቀን በመስጠት ለታህሳስ 5 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የፖሊስ ምርመራን በማደናቀፍ እና ተገቢ ያልሆነ ሃብት በማከማቸት ወንጀል በተጠረጠሩት ኮለኔል ጉደታ ኦላና ላይ ፖሊስ ከጀመረው ምርመራ በተጨማሪ ቀሪ ምርመራ አጠናቆ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ከህዳር 20 ጀምሮ በሚቆጠር የ14 ቀን ጊዜ ፈቅዶ ለታህሳስ 4 ቀን 2011 ዓመተ ምህረት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ከአዲስ የሜቴክ ሰራተኞች ጋር ተመሳጥሮ ከሁለት የውጭ ድርጅቶች 2 ሺህ 500 ትራክተር በድለላ በመግዛት ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ለግላቸው አውለዋል የተባሉት አቶ ረመዳን ሙሳም ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፥ ፖሊስ የተጠረጠሩበትን ጉዳይም አስረድቷል።
አቶ ረመዳን ሙሳ ላይ ፖሊስ ሦስት ምስክር የተቀበለ ሲሆን ፥የኦዲት እና ትራክተሮች ቆጠራ ለማድረግ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን ጠይቋል።
ተከላካይ ጠበቃ በበኩሉ ፖሊስ ሰነድ ሰብስቧል በዋስ ቢወጡ የሚፈጥሩት ጉዳት የለም ብሏል።
ሆኖም ፖሊስ በተከላካይ ጠበቃ የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ተቃውሟል።
ፍርድ ቤቱም የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ ለዛሬ ከሰዓት ትዕዛዝ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
እንዲሁም ፖሊስ በቀድሞው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ኃላፊ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አቶ ያሬድ ዘሪሁን ላይ ከዚህ በፊት በተሰጠው ምርመራ ጊዜ ውስጥ በባለቤታቸው ወይዘሮ አዳነች ስም አገኘሁ ያለውን ሃብት ዘርዝሯል።
በዚህም በባለቤታቸው ስም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤት እና በባለቤታቸው እናት በኢንቨስትመንት ፍቃድ የተመዘገበ 3 ሚሊየን 300 ሺህ ብር ካፒታል ማግኘቱን ገልጿል።
እንዲሁም በኦሮሚያ ህብረት ባንክ በባለቤታቸው ስም 2 ሚሊየን 742 ሺህ ብር ማግኘቱንም ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
በተጨማሪም ፖሊስ በእሳቸው ትዕዛዝ የሰው ህይወት ማለፉንና የአካል ጉዳት መድረሱን ጠቅሶ፥ የሰው ማስረጃ ያገኘ በመሆኑ የ14 ቀን ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል።
የአቶ ያሬድ ጠበቃ በበኩላቸው ተጎጂዎቹ እነማን ናቸው፣ ተጎጂዎችን ፖሊስ ገና እያፈላለገ ባለበት ሁኔታ ሰነድ ያሸሻሉ ማለቱ ተገቢነት የለውም፣ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ሃብት አከማችተዋል መባሉ በማስረጃ አልቀረበም ብለዋል።
በተጨማሪም አቶ ያሬድ ህመምተኛ ናቸው በዋስ እንዲወጡ ይፈቀድ ሲል ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል።
ፖሊስ የዋስትና ጥያቄውን በመቃወም ለተለያዩ ተቋማት በሳቸውና ባለቤታቸው የተመዘገበ ሃብትን ተጨማሪ ለማጣራት ደብዳቤ መላኩንና ተጨማሪ ጥቆማም እየደረሰው መሆኑን ጠቅሶ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱም የምርመራ መዝገቡን ነገ ጠዋት ተመልክቶ ከሰዓት ትዕዛዝለ መስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በሌላ በኩል ፖሊስ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ካቀረበው ከሰኔ 16ቱ የቦምብ ፍንዳታ በተጨማሪ ግለሰቦችን ያለአግባብ በማሰር፣ በማሰቃየት እና በማስፈራራት እንዲሁም 6 ሚሊየን ብር እና 200 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በመቀበል በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ሃብት በማከማቸት እንደጠርጠራቸው ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል።
እንዲሁም ፖሊስ በአቶ ተስፋዬ ላይ ተጨማሪ በ6 ነጥቦች ምርመራ ለማድረግ ተጨማሪ 14 ቀን ይሰጠኝ ብሏል።
አቶ ተስፋዬ የስራ ኃላፊነቴ በጸረ-ሽብር መምሪያ ኃላፊ ነኝ እንጂ ሰዎችን የማሰርም ሆነ የማሰቃየት ኃላፊነት የለኝም ሲሉ ፍርድ ቤቱ ኃለፊነታቸውን እንዲመዘግብ ጠይቀዋል።
የአቶ ተስፋዬ ጠበቃም በሰኔ 16ቱ ቦምብ በማስተባበር ብሎ በፍርድ ቤት እየታየ በድጋሚ ፖሊስ ካለመያዣ ነው አሁን ይዞ የሚመረምረው፤ ይህ ተገቢነት የለውም ብለዋል።
ፖሊስ በበኩሉ ይህ ከሰኔ 16 ቦምብ ጋር የሚገናኝ አይደለም ምርመራው የተለየ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱም መዝገባቸውን መርምሮ ትእዛዝ ለመስጠት ለዛሬ ከሰዓት በይደር ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ወንድም ኢሳያስ ዳኘው ላይ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ባለፈው በጽሁፍ ያቀረበውን የምርመራ ውጤትን በቃል አሰምቷል።
በሜጄር ጄነራል ክንፈና ወንድማቸው ኢሳያስ ላይ በቀረበ ምርመራ ጠበቃዎቹ የምርመራ መቋወሚያ አቅርበዋል።
በዚህም በተራ ቁጥር 1፣ 2፣ 4፣ 7 እና 12 ላይ የተጠቀሰው የምርመራ ውጤት ከበፊቱ የተለየ አዲስ ነው፤ ይህም ፖሊስ እንደፈለገው በየጊዜው አዳዲስ ማቅረቡ አግባብነት የለውም ብለዋል።
በሜጀር ጀነራል ክንፈም ላይ በፊት አውሮፕላን ግዢ እና የህዳሴ ግድብ ምንጣሮ ተብሎ ነበር የቀረበው አሁን ላይ አዲስ ምርመራ መቅረቡ ተጠርጣሪዎችን አስቀድሞ ቅጣት እንዲያወራርዱና ንጹህ ሆነው የመገመት መብታቸውን የሚጎዳነው፤ ፍርድ ቤቱ እልባት ሊሰጥ ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ከመንግስት መስሪያ ቤት ለሚሰበሰብ ሰነድ ተጠርጣሪዎችን አስሮ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቁ አግባብነት የለውም፤ ከዚህ በተጨማሪ በጠቅላይ አቃቤ ህግ በደረሰው ጉዳት ኦዲት አድርጌ ጨርሿለው ብሏል፤ ለዚህም በሲዲ የተደገፈ ማስረጃ አለን ብለዋል ጠበቆቻቸው።
በሜጀር ጀነራል ክንፈ ላይ መንግስት አስቀድሞ መግለጫ የሰጠበት በተለይም ኦዲት ስራ ሰርቶ ምርመራ ማጠናቀቁን በገለጸበት ሁኔታ ፖሊስ ተጨማሪ እንድመረምራቸው 24 ቀን ይፈቀድልኝ ማለቱ አግባብነት የለውም፤ ፍርድ ቤቱ በመንግስት መግለጫ ላይ ያለንን ማስረጃችንን ይመልከትልን ሲሉ አመልክተዋል።
ጠበቆቹ ሜቴክን ከማስታወቂያ ጋር በተያያዘ ለቀረበው ክስ ድርጅቱ መተዋወቅ አልነበረበትም ወይ ሲሉ የጠየቁ ሲሆን፥ ድርጅቱ ከሚያገናኘው ስራ ጋር በተያያዘ እንደ ወንጀልም ሊቀርብ አይገባም ብለዋል።
አቶ ኢሳያስም ቢሆኑ የፕሮግራም ኃላፊ እንጂ የፓወር ተከላ ፕሮጀክት ያለአግባብ ሰጥተዋል መባሉ አግባብነት የለውም ሲሉ ተቃውሞ አቅርበዋል።
በጀነራል ክንፈ ላይም በተመሳሳይ ሜቴክ ከተቋቋመ ጀምሮ የተሰራ ስራን በማይመለከታቸው ጉዳይ እሳቸውን ተጠያቂ ለማድረግ ለቀሪ ምርመራ ተብሎ መቅረቡ አግባብነት የለውም ብለዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ዘገባን በተመለከተ ማሳሰቢያ ይሰጥልኝ ያሉ ቢሆንም፥ ፍርድ ቤቱ የቀረበ ማስረጃ አለመኖሩን በመጥቀስ ሁሉም ሀላፊነቱን አውቆ እንደሚሰራ ይገባናል ብሏል።
ፖሊስ በበኩሉ በጠበቆች መቃወሚያ ላይ ምላሽ የሰጠ ሲሆን፥ በዋናነት አቶ ኢሳያስ ተጣምረው በአንድ መዝገብ መቅረባቸው ለምን አስፈለገ ለሚለው ጥያቄ፥ አቶ ኢሳያስ ውል አሻሽለው የፓወር ተከላ በሶማሌ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በተከናወነ የኢትዮ ቴሌኮም ፓወር ተከላ ውልን በ2011 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ160 ሳይቶች በራሳቸው 18 ሳይት በመጨመር ቀደም ሲል 204 ሚሊየን 981 ሺህ 630 ብር የነበረውን ውል በማሻሻል በድጋሚ ከፍ በማድረግ 321 ሚሊየን 710 ሺህ 404 ብር ከ51 ሳንቲም በማድረግ 322 ሚሊየን ብር እንዲከፈል በማድረጋቸው በዚህ መነሻ መጠርጠራቸውን አስረድቷል።
የሁለቱ መዝገብ በአንድ የተጣመረውም ወንጀሉ ተመሳሳይ በመሆኑ ነው ብሏል።
የሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘውን በተመለከተ በየጊዜው በምርመራችን ላይ አዳዲስ የወንጀል ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ የምርመራ ባህሪ ነው፤ በቂ ፍንጭ ስናገኝም ለፍርድ ቤቱ እያቀረብን ነው፤ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ይህን ይገንዘብልን፤ እኛ አለአግባብ ለማሰር ሳይሆን ቢወጡ ማስረጃ ሊያሸሹብን፣ ምስክር ሊያባብሉብንና ከሀገር ሊሸሹ ስለሚችሉ በሚል ነው የዋስትና ጥያቄውን የምንቃወመው ሲል አስረድቷል።
ማስታወቂያን በተመለከተ እንደ ፍፁም የሺጥላ የሜቴክ አባል ሳይህኑ አባል ናቸው ተብሎ አሜሪካ የተላኩበትና ተማሪዎችን ሜቴክን አስጎብኝተው ስፖንሰር ተብሎ መከፈሉ በሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው መሆኑን ማስረጃ በማግኘታችን ነው፤ እንዲሁም 104 ሚሊየን ብር ለስፖንሰር ተብሎ ለበርካታ ተቋማት የተከፈለውንም በማስረጃ እየቀየርን ነው፤ ስለዚህ በማይመለከተው የማስታወቂያ ጉዳይ ማለታችን መነሻ ስላለን ነው፤ ይህንንም ፍርድ ቤቱ ይወቅልን ብሏል።
ለመገናኛ በዙሃን መረጃ ይሰጣሉ መባሉን ተከትሎ ህዝቡ በየጊዜው የምናደርገውን የምርመራ ውጤት የማወቅ ህገመንግስታዊ መብት አለው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ኤፍ ቢ ሲ እንደዘገበው ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤትም የምርመራ መዝገቡን ጠዋት ተመልክቶ ትእዛዝ ለመስጠት ለዛሬ ከሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።