ለጤናማኑሮ – ጤናማ አዕምሮ

ሰዎች የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸውን የሕመም ስሜት ሲሰማቸው ወደ ዘመናዊ ሆነ ወደ ባህላዊ ተቋማት በመሄድ መድሀኒት ነው የሚባሉትን በመውሰድ ወደ ቀድሞ ጤናቸው ለመመለስ ይሰራሉ:: ይህን በራሳቸው ማድረግ የሚችሉት አእምሮ ጤናማ ሲሆን ነው፤ ሲታመምስ? ::

የአዕምሮ ጤናን እንደ አዕምሮ ህመም በቀላሉ ትርጓሜ ለመስጠት አስቸጋሪ እንደሆነ፤ ጤነኛ አእምሮ ማለት የአዕምሮ ሕመም ተቃራኒ ማለት እንዳልሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ:: በአዕምሮ ጤንነት ውስጥ የአዕምሮ ጤነኛ መሆን አንዱ መስፈርት ቢሆንም፤ በሱ የሚያበቃ አይደለም። ከዚህም ከፍ ባለ መልኩ፤ በሕይወት ደስተኛ መሆን፤ እያንዳንዱም ሰው ያለውን እምቅ አቅም አውጥቶ መጠቀምን የሚያካትት እንደሆ ይታማናል::

የአዕምሮ ሕመምን ከሌሎች ሕመሞች ለየት የሚያደርገው በዋናነት፣ በሕመሙ የሚጠቁ ሰዎች ሕመም እንዳለባቸውና እንደ ሌለባቸው የሚያገናዝቡበት፤ ሕመሙ የሚያስከትለውን ጉዳት የሚረዱበት የሰውነት ክፍል ራሱ መታመሙ ነው::

በዚህ ምክንያት በማሕበረሰባችን ውስጥ ሰዎች የአዕምሮ ሕመም ሲከሰት ሕመም የተከሰተ አድርጎ ያለመረዳት፤ በሕመም መያዛቸውን ያለማወቅ፤ ሕመሙ የሚያስከትለውን ተፅንኦ ያለመረዳት ሁኔታ ይስተዋላል::

የሚያስቡበት፤ የተለያዩ ስሜቶች እንዲሰሟቸው፤ የተለያዩ ፀባዮችን የሚመራው ዋናው የሰውነት ክፍል በሕመሙ መጠቃቱ ከሌሎች ሕመሞች የአዕምሮ ሕመምን በብዙ ይለየዋል:: የአዕምሮ ሕመም ለመከሰቱ ስነ-ህይወታዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ማሕበራዊ ምክንያቶች ያሉት ሲሆን፤ ሕክምናውም በነዚህ ዘርፎች የተከፋፈለ ነው::

በሽታው ዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት መሆን ከጀመረ ዓመታት እየተቆጠሩ ናቸው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአራት ሰዎች አንዳቸው በምድር ቆይታቸው የአእምሮ ህመም ይከሰትባቸዋል::

በሀገራችን ደግሞ 25 በመቶ የሚሆነው የሕብረተሰቡ ክፍል በእድሜ ቆይታው የአእምሮ የጤና እክል ያጋጥመዋል:: በዚህ ቁጥር ውስጥም አንዳንዶቹ ችግሮች እንደ አእምሮ ጤና ችግር ስለማይታዩ ከጥቂቶች ውጭ ብዙ ሰዎች እንብዛም ለአእምሮ ሕክምና ወደ ጤና ተቋማት አይሄዱም::

ሕሙማኑ ወደ ጤና ተቋማት የሚሄዱት የተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ የሕክምና አማራጮችን ሞክረው ተስፋ ሲቆርጡ በመሆኑ፤ ወደ ጤና ተቋማት የሚሄዱት በከፍተኛ ሁኔታ ከተጎዱ በኋላ ነው:: በተለይም የሕፃናት እና የአፍላ ወጣቶች የአእምሮ ሕመም ከተፈጠሮአዊ የእድሜ ባህሪ ጋር በማዛመድ/ በማመሳሰል ወይም ችግሮችን ቀለል አድርጎ በማየት የአእምሮ ጤና ችግሩ ስር እንዲሰድ ያደርጋል::

ለምሳሌ፣ ያክል እንደ አእምሮ ጤና ችግር ከማይቆጠሩት መካከል የተለያዩ ማሕበራዊ ሚዲያዎችን አብዝቶ መጠቀም ወይም ሱስ በሚባል ደረጃ ሲደርስ መመልከት፣ ልጆችን በጭምትነት፣ በረባሽነት እና ሌሎችም መሰል ባህሪያቶች መፈረጅ ለችግሩ እንደ ምክንያት ይቆጠራሉ::

በችግሩ ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ ለማስጨበጥና የአእምሮ ሕክምና አገልግሎት ለማስፋት (ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ) በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ መስከረም 29 ወይም እ.ኤ.አ October 10 የአእምሮ ጤና ቀን ተከብሮ ይውላል:: ቀኑ በኛም ሀገር ባለፈው ማክሰኞ ተከብሮ ውሏል።

ቀኑ በአእምሮ ጤና ዙሪያ ግንዛቤን ለማስጨበጥ እና መንግስታት፣ የባለድርሻ አካላት እና አጋር ድርጅቶች ለአእምሮ ጤና ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ ለማድረግ የሚታሰብ ነው:: ይህንኑ ዕለት አስመልክቶም በዓለም በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ይሰራሉ::

ዘንድሮም በአሉ ”ጤና ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ነው” በሚል መሪ ቃል ትናንት ተከብሯል፤ መሪ ቃሉ በውስጡ ሶስት መሰረታዊ የሰብአዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው::

1ኛ፣ የአእምሮ ጤና አገልግሎት ማግኘት ሰብአዊ መብት መሆኑ፤

2ኛ. የአእምሮ ሕሙማን አያያዝ ሰብአዊ ክብራቸውን የጠበቀ መሆን እንዳለበት (የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው የማሕበረሰብ ክፍሎች ከማንኛውም ጥቃት የመጠበቅ መብታቸው እንዲከበር፤

3ኛ የአእምሮ የሕሙማንን የመንቀሳቀስ መብታቸው እንዲጠበቅ፣ ማሕበረሰቡን እና የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ በማሳደግ የአእምሮ ጤና ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት መሆኑ እውቅና እንዲያገኝ ታስቦ ነው::

በርግጥ በአእምሮ ጤና ችግር ባለባቸው ማሕበረሰብ ክፍሎች ላይ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚደርሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ብዙ ናቸው:: እነዚህ የመብት ጥሰቶች መቆም የሚችሉት ሁሉም የባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት ሲችሉ ነው::

የአዕምሮ ሕመም በማንኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ ባለ ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል ቢሆንም፤ አብዛኞቹ ወይም ከባድና ፅኑ የአዕምሮ ሕመም የምንላቸው ሕመሞች መነሻቸው በወጣትነት እድሜ ክልል ነው:: ይህ እንደ ግለሰብ የሚያስከትለው ተፅንኦ እንዳለ ሆኖ፤ ችግሩ በቤተሰብ፣ ማሕበረሰብ እና በሃገር ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተፅንኖ ከፍተኛ ነው::

ለምሳሌ፣ ‘ስኪዞፌርኒያ’ እና ‘ባይ ፖላር’ የተሰኙት የአእምሮ ሕመሞች በአብዛኛውን ጊዜ ከሠላሳ ዓመት በታች ባለ የእድሜ ክልል /ምርታማ መሆን በሚጀምርበት ጊዜ ላይ የሚከሰቱ በመሆናቸው በስራ እና በማሕበራዊ ሕይወት ላይ ትልቅ ተፅእኖ ያሳድራሉ::

ይህ የአዕምሮ ሕመም በአብዛኛው በወጣትነት የዕድሜ ክልል ላይ ከሚከሰትባቸው ምክንያቶች አንዱ ስነ- ህይወታዊ በሆነ መልኩ በጉርምስና ዕድሜ እንደሚካሄዱ አካላዊ ለውጦች በተመሳሳይ ሁኔታ በአዕምሮአችን ውስጥ ከሚከሰት ለውጥ የሚፈጠር ነው::

በጉርምስና እድሜ ክልል ውስጥ በአእምሯችን ላይ የሚካሄዱት የለውጥ ሂደቶች በትክክለኛው መንገድ ሲቀጥሉ ጤናማ የሆነ የወጣትነት ዕድሜ ይኖራል፤ በተወሰኑ ሂደቶች ላይ ደግሞ ዕክል ወይም ችግር ሲያጋጥም ተፅንኦ ይኖረዋል:: የአእምሮ ሕመም እንዲከሰት ምክንያት ሊሆን ይችላል::፡

ከዚህም ባሻገር ከሱስ ጋር ያሉ ችግሮች የሚጀምሩት በአብዛኞቹ በወጣትነት ዕድሜ ላይ መሆኑ እና በተጨማሪም ከወጣትነት ዕድሜ በኋላ ሰዎች ቤተሰብ ስለሚመሰረቱና ኃላፊነት ስለሚሰማቸው ብዙ ጊዜ ሰዎች የወጣትነት ዕድሜን ካለፉ በኋላ የተረጋጋ ሕይወት ይኖራቸዋል:: ይህ ደግሞ የአዕምሮ ሕመም በቀላሉ እንዳይፈጠር፣ ቢፈጠርም በአፋጣኝ እንዲታከሙ ያስችላል::

የአዕምሮ ሕመም በወቅቱ ሕክምና ካላገኘ ለማከም አስቸጋሪ ቢሆንም፤ ሕክምናውን በቅድሚያ መለየትና ማከም ከተቻለ የአዕምሮ ሕመም እንደማንኛውም ሕመም ታክሞ መዳን ይችላል::

ለምሳሌ፣ የህጻንትን የአእምሮ ሕመምን ብንመለከት፤ በማሕበረሰባችን ውስጥ የአዕምሮ ህመም ችግሮች የሚያጋጥማቸው አዋቂዎችን ብቻ እንጂ ሕፃናት በአዕምሮ ሕመም የማይጠቁ አድርጎ የመውሰድ የተሳሳተ ግንዛቤ አለ:: የአዕምሮ ሕመም ሁሉም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችልና እንደ ማንኛውም ሕመም ሊረዳ (ሊታከም) የሚችል ነው::

የእእምሮ ሕመም በጉርምስና እድሜ ክልል ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሕፃናት ላይም ሊከሰት ይችላል:: ነገር ግን በሕጻናት ላይ የምናያቸው የአዕምሮ ሕመሞች በሌሎች እድሜ ክልሎች ላይ ከሚታዩት ሊለይ ይችላል:: አንዳንድ ጊዜም እንደ እድሜያቸው ክልል የተለያዩ ዓይነት ችግሮችን በብዛት ልናስተውል እንችላለን::

ለምሳሌ፣ ከእድገት ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮች (Neuro Developmental Disorder) የሚጠቀሱ ናቸው፤ እነዚህም የአዕምሮ እድገት ውስንነት (Au­tism)፣ መንቀዥቀዥ፣ ንግግር ወይም መግባባት ላይ የመዘግየት ሁኔታ በልጆች ላይ በብዛት ልናስተውል የምንችላቸው ናቸው። ከጭንቀትና ከፍርሃት ጋር የተያያዙ ችግሮችም ሌሎች ናቸው::

በዋናነት በአዋቂ ሰዎች ላይ በብዛት ጎልተው የሚታዩ፤ የባህሪ ችግር የአዕምሮ ህመም አይነቶች በህጻናትም ላይ ጎልተው ይታያሉ (Opposition­al Defiant Disorder)፤ እነዚህም እምቢተኝነት፣ መጨቃጨቅ፣ አለመታዘዝ፣ ሃይለኛ መሆን፣ መስረቅ ወዘተ ናቸው::

ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች አዋቂ ሰዎች ላይ የምናያቸው የአዕምሮ ህመሞች ልጆች ላይም ልናስተውል እንችላለን:: ለምሳሌ፣ የጭንቀት (Anxiety Disorder)፣ ድብርት (Depression)፣ ዕድሜያቸው ከፍ እያለ ሲመጣም (በጉርምስና ወቅት) የሁለት ተቃራኒ ጫፎች ተለዋዋጭ ስሜት (Bipolar Disorder)፣ ስኪዞፍሬኒያ (Schizophrenia) እና ለሱስ ተጋላጭ የሚሆኑበት ዕድሜ ስለሚሆን ከእርሱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የአዕምሮ ሕመም ችግሮች ሊኖራቸው ይችላል::

ግማሽ የሚሆነው የአዕምሮ ሕመም የሚከሰተው ከ18 ዓመት በታች በሆነ የእድሜ ክልል ውስጥ በመሆኑ ችግሩ ቀላል የሚባል አይደለም:: እነዚህ የአእምሮ ሕመሞች በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በማሕበራዊ፤ በአካላዊ ጉዳትና በባዮሎጂካል ለውጦች ሊከሰቱ ይችላሉ:: እነዚህ የአእምሮ ሕመሞች ሲከሰቱም በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት መሄድና ተገቢውን እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋል::

በዚህ መልኩ ችግሩ ሲከሰት ተገቢውን ክትትልና የሕክምና መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ ከቻልን፤ ለበሽታው ያለን ተጋላጭነት መቀነስ ይቻላል:: ለምሳሌ፣ የአዕምሮ ሕመም መምጫዎቹ ብዙ ቢሆኑም ሕመሙን ለማከምና ስርጭቱን ለመቀነስ ማሕበራዊ መስተጋብሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል::

ለአብነት፣ ባደጉት ሀገራት በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ:: ለዚህም እንደምክንያትነት የሚጠቀሰው የብቸኝነት ስሜት መኖር ነው፤ ይህ የሆነውም በብዛት ግላዊነት የበዛበት ኑሮ ስላላቸው ነው:: ይህ ጉዳይ በኛ ማሕበረሰብ ዘንድ እንብዛም ያልተለመደ በመሆኑ ሰዎች የሀዘን ጊዜያቸውን ሆነ የደስታ ጊዜያቸውን የሚጋሯቸው ወዳጅ፤ ዘመድና ጎረቤቶች አሏቸው::

ይህም ለአእምሮ ጤናቸው ከፍተኛ አስተዋጾ የሚኖረው በመሆኑ፣ ይህንን ጉዳይ ማስቀጠል ያስፈልጋል:: ከዚሁ ጋር ተያይዞም ሰዎች በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያጠፏቸውን ጊዜያት በመቀነስ ከቤተሰቦቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር የሚኖራቸውን ጊዜ ማጠናከር ይገባቸዋል::

ቤተሰብ ልጆች ላይ የባህሪ ችግር የሚመስሉ ባህሪያትን እና ልጆቻቸው የእድሜ እኩዮቻቸው የሚያደርጓቸውን ነገሮች ማድረግ ካልቻሉ፤ ማለትም ንግግር መጀመር በሚገባቸው ሰዓት ካልጀመሩ፤ መንቀሳቀስ መጀመር ባለባቸው እድሜ እንቅስቃሴ ካላሳዩ ወደ ጤና ተቋማት በመውሰድ የሕክምና እርዳታ የሚያገኙባቸውን መንገድ ቢፈልጉ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ያስችላል::

በተጨማሪም መንግስት ያለውን የአእምሮ ሕመም ስርጭት ለመቀነስና ሰዎች በአፋጣኝ ሕክምና እንዲያገኙ ለማስቻል የአገልግሎቱን ሰጭ ተቋማት ማስፋትና በዘርፉ የተማሩ ባለሙያዎችን ቁጥር ለመጨመር መስራት ይገባዋል:: በዚህ መልኩ ሁሉም የየራሱን ድርሻ ወስዶ ከሰራ፣ የአእምሮ ሕመም ችግርን መቀነስና የሚፈጥረውን ሁለንተናዊ ጫና መከላከል ይቻላል::

መክሊት ወንድወሰን አዲስ ዘመን  ጥቅምት 2/2016

Recommended For You