በ2022፤ 20 ሚሊዮን የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ እስከ 2022 ዓ.ም 20 ሚሊዮን የሥራ እድል ለመፍጠር አቅዳ እየሰራች መሆኗን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን አስታወቁ:: በሥራ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ላይ ትኩረት ያደረገው “እንቆጳ” የተሰኘው ጉባዔ መካሄድ ጀምሯል::

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን የ“እንቆጳ” ጉባዔን ትናንት በከፈቱበት ወቅት፤ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እየተስተዋለ ያለውን የሥራ አጥነት ሁኔታ ለመለወጥ እየጣረች ትገኛለች ብለዋል:: ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈተና እየሆነ የመጣውን የሥራ አጥነት ቁጥር ለመቀነስ በሀገር ደረጃ በ2022 ዓ.ም 20 ሚሊዮን የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ እንዳለም አመላክተዋል::

በብሄራዊ ሪፎርም ለሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ማሻሻያው ኢንተርፕራይዞቹ ምቹ የሥራ እድል እንዲፈጥሩና የንግድ ሥነ-ምህዳሩን ለማስፋት ያለመ እንደሆነ ጠቁመዋል:: ይህም ኢኮኖሚያዊ ሀብትን ለመፍጥር የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል::

መንግሥት፣ የግሉ ሴክተርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት በማድረግ በተለይ የዲጂታል ሥራ ፈጠራ አቅምን መጠቀም እንዳለባቸው ተናግረው፤ ይህ ካልሆነ ግን ሪፎርሙ የሥራ እድል ፈጠራንና የኢንተርፕራይዞች ልማትን ግብ በዘላቂነት ሊያሳካው እንደማይችል ተናግረዋል:: በዚህ ረገድ ሚኒስቴሩ ለሀገሪቷ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጠንካራ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥነ-ምህዳር ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሠራ ነው ብለዋል:: በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2022 ዓ.ም 20 ሚሊዮን የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ እንዳለ አመላክተዋል::

በብሔራዊ ዲጂታይላዜሽን ጥረቶች በመታገዝ የተጀመሩ ፈጠራዎች ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን ያመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል:: የዲጂታል ኢኮኖሚና የዲጂታል ሥራ አዲስ ክስተት እንደመሆኑ የግንዛቤ ፈጠራ፣ የሚዲያ ዘመቻና የፖሊሲ ቅስቀሳ እንደሚያስፈልገው ነው የጠቆሙት::

እ.ኤ.አ. በ2021 የኢትዮጵያን የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴ ለማስተዋወቅ እንቆጳ የተሰኘ ሀገራዊ ንቅናቄ እንደተጀመረ ያነሱት አቶ ንጉሡ፤ ቴክኖሎጂን ያፈለቁ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ተዋውቀው ድጋፍ የሚያገኙበት መድረክ እንደሆነም ተናግረዋል::

ጉባዔው የኢንዱስትሪ ኃላፊዎችን፣ የድርጅት ሥራ አስፈጻሚዎችን፣ መሐንዲሶችን፣ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችንና ምሁራንን ያሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል::

ትናንት የተጀመረው የእንቆጳ ጉባኤ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ለማሳደግና በሥራ ፈጠራ ኢትዮጵያ እንደ ትልቅ የኢንዱስትሪ ክስተት ያላትን ጸጋና አቅም ለማጋራት ያስችላታል ብለዋል:: ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ከፍተኛ የሥራ እድል ለመፍጠር ምቹ አጋጣሚ መሆኑንም ጠቅሰዋል::

በጉባዔው ከ26 ሀገራት የተውጣጡ አካላት የተሳተፉ ሲሆን፤ በዛሬው እለት እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ተችሏል::

“እንቆጳ” በግእዙ ቋንቋ “የወርቅ ጥሬ ሀብት” የሚል ትርጓሜ ያለው ሲሆን፤ የሥራ ፈጠራ ዘርፉ ያሉበትን ተግዳሮቶች በመቅረፍ በሚገባ ማንቀሳቀስ ከተቻለ ሊያብረቀርቅ የሚችል መልካም እድል ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው::

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You