በኢትዮጵያ በማእድን ዘርፍ እየተከናወኑ ካሉ ተግባሮች አንዱ ለሲሚንቶና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች በጥሬ እቃነት የሚያገለግለውንና ከውጭ ሲመጣ የኖረውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚደረገው ጥረት ነው:: በዚህም በሀገሪቱ በማህበራት ተደራጅተው የድንጋይ ከሰል እያመረቱ ካሉት ማህበራት በተጨማሪ ኩባንያዎች የድንጋይ ከሰል በማምረትና በማጠብ ሥራው እየገቡ ናቸው::
ከማእድን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ በሀገሪቱ ከውጭ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ምርት ሙሉ ለሙሉ ለመተካት የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ነው:: የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ለማምረት ፈቃድ የወሰዱ ትልልቅ ኩባንያዎች ወደ ምርት እንዲገቡ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል:: ሌሎች ኩባንያዎችም ወደ ዘርፉ እንዲገቡ የሚያደርግ ሥራም እየተሠራ ነው::
የማዕድን ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወቀ ተስፋው በቅርቡ እንደገለጹልን፤ ከፌዴራል መንግሥት ስምንት ኩባንያዎች የድንጋይ ከሰል ለማምረት የሚያስችላቸውን ፈቃድ ወስደዋል:: በክልሎችም የድንጋይ ከሰል የማምረት ፈቃድ ወስደው በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራትና ኩባንያዎች በርካታ ናቸው::
ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰልን በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አቶ አወቀ ጠቅሰው፣ በ2015 በጀት ዓመት በሀገር ውስጥ ከተመረተው 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል ምርት ማግኘት ተችሏል ብለዋል:: በዚህም ከ 7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል:: የ2016 በጀት ዓመት ሁለት ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ለማምረት መ ታቀዱን ነው የሚናገሩት::
በሌላ በኩል ደግሞ ከደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ በክልሉ 15 አነስተኛ ደረጃ አምራቾች እና ሦስት በከፍተኛ ደረጃ አምራቾች በአጠቃላይ 18 አምራቾች በማዕድን ዘርፍ በተለይ በድንጋይ ከሰል ልማት ሥራ ፈቃድ ወስደው ተሰማርተዋል::
ከክልሉ በ2015 በጀት ዓመት 748 ሺ24 ቶን ያህል የድንጋይ ከሰል ለማምረት ታቅዶ፤ 209 ሺ398 ቶን ለማምረት ተችሏል:: ከገቢም አንጻር 30 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማስገባት ታቅዶ፤ 29 ነጥብ3 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ተችሏል:: በድንጋይ ከሰል ምርት ብቻ ለ600 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ፣ ለ525 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ተፈጥሯል::
በክልሉ የዳውሮ ዞን በድንጋይ ከሰል ማምረትና እጥበት ሥራ ከተሰማሩት ከፍተኛ ደረጃ አምራቾች ውስጥ አንዱ የኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማህበር ነው:: አክሲዮን ማህበሩ በድንጋይ ከሰል እጥበት ሥራ ለመሥራት በ2014 ዓ.ም ነው ፈቃድ ወስዶ ወደ ሥራ የገባው::
አክሲዮን ማህበሩ በአሁኑ ወቅት በድንጋይ ከሰል እጥበት ሥራ ለመሥራት የሚያስችለውን ፋብሪካ እየገነባም ይገኛል:: ይህ በዳውሮ ዞን ተርጫ የሚገኝ የድንጋይ ከሰል ማበልፀጊያ ፋብሪካ በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በተሰናዳውና በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል በቅርቡ በተደረገው የሚዲያ ባለሙያዎች ጉብኝት ወቅትም ተጎብኝቷል:: በወቅቱም የፋብሪካው ተወካይ አቶ ወንድሙ ምትኩ ፋብሪካው በዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል በማጠብ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች በማቅረብ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ያድናል ብለዋል::
የድርጅቱ ሥራ ሀገሪቱ ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ስታስገባ የኖረችውን የድንጋይ ከሰል ምርት በማስቀረት ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት አዲስ ዘመን ጋዜጣ በስልክ ያነጋገራቸው እኚሁ የአክሲዮን ማህበሩ ተወካይ አቶ ወንድሙ ምትኩ ገልጸዋል::
እሳቸው እንደሚሉት፤ ይህ ኩባንያ በማዕድን ሚኒስቴር በማእድን ዘርፍ ላይ እንዲሠሩ ከተመረጡት ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነው:: የኩባንያው ዋና ዓላማ ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝቶ የሚመጣውን የታጠበ ድንጋይ ከሰል ምርት በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ለሲሚንቶና ብረታ ብረት ፋብሪካዎች ማቅረብ ነው::
‹‹የድንጋይ ከሰል የሚያመርት ፋብሪካ ለመገንባት ከመታሰቡ በፊት በዳውሮ አካባቢ ያለውን የድንጋይ ከሰል ክምችት ምን ያህል ነው በሚል አዋጭነቱ በሚገባ በጥናት ተረጋግጧል›› ያሉት ተወካዩ፣ ይህ ታውቆ ወደ ፋብሪካ ግንባታ መገባቱን አስታውቀዋል:: ዞኑ በቂ የድንጋይ ከሰል ማእድን ክምችት እንዳለው ጠቅሰው፣ እኛ ባረጋገጥነው መሠረት በዳውሮ ዞን ያለው የድንጋይ ከሰል ክምችት ሠላሳ ዓመታት ያህል የሚያሠራ ነው ሲሉም አብራርተዋል:: አጎራባች በሆኑት ኮንታና ጎፋ ዞኖችም ላይ ቢያንስ እስከ 60 ዓመታት ያህል የሚያሠራ የድንጋይ ከሰል ክምችት ስለመኖሩ አረጋግጠናል›› ብለዋል::
አቶ ወንድሙ እንዳሉት፤ ፋብሪካው በሰዓት 150 ቶን የድንጋይ ከሰል የሚያመርት ሲሆን፤ በዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል ማምረት ይችላል:: ፋብሪካው በሰዓት በሚያጥበው 150 ቶን የድንጋይ ከሰል እንዲሁም በዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል የሚያጥብ በመሆኑ በሀገር ውስጥ ካሉት የድንጋይ ከሰል የሚያጥቡ ፋብሪካዎች የተለየ ያደርገዋል:: ከውጭ የሚመጣው 75 በመቶ የሚሆነው የድንጋይ ከሰል ምርትንም ይሸፈናል ተብሎ በመንግሥት አቅጣጫ የተቀመጠበት ፋብሪካ ነው ብለዋል:: ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ደረጃ እንደሚጠቀምም ተናግረዋል::
አሁን ፋብሪካው ስላለበት ደረጃ አቶ ወንድሙ ሲያብራሩ እንዳሉትም፤ የፋብሪካው የፋውንዴሽን ዲዛይን ሥራ ተሠርቶ ተጠናቋል:: የዲዛይኑ ደረጃም በቱርክ ባለሙያዎች እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጂኦሎጂስቶች ተረጋግጧል:: የፋብሪካው የጥገና ክፍል፣ መጋዘን፣ የውጭ ሀገር ዜጎች የሚያርፉበት (ገስት ሀውስ) ፤ የአስተዳደር ህንጻ እና ለጋራዥ አገልግሎት የሚውል ህንጻ ፣ መኪናዎች ሲወጡና ሲገቡ የሚመዘኑበት የሚዛን ቦታ ፣ የሠራተኞች ማደሪያ ህንጻና ለካፍቴሪያ አገልግሎት የሚውሉ ህንጻዎች ግንባታ ተጠናቅቋል::
የመንገድ ሥራን ጨምሮ በአብዛኛው በሚባል ደረጃ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ጠቅሰው፣ አሁን ላይ የፋብሪካው ግንባታ ሥራ ከ85 በመቶ በላይ መድረሱን አመልክተዋል:: ቀሪ ሥራዎች ከውጭ የመጡ ለፋብሪካው አገልግሎት የሚውሉ መሣሪያዎች ተከላ መሆናቸውንም አብራርተዋል::
እነዚህን ቀሪ ሥራዎች ለመሥራት የሚያስፈልጉት የውጭ ሀገር ሙያተኞች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል ያሉት አቶ ወንድሙ፤ በጥቂት ቀናት ውስጥ ፋብሪካው ወደ አለበት ቦታ ላይ መጥተው የመሣሪያዎቹን ተከላ እንደሚያከናወኑም ጠቁመዋል:: የተከላ ሥራው እንደተጠናቀቀም ወደ ሙከራ ማምረት ሥራ እንደሚገባ ተናግረዋል:: ከመጪው ህዳር ወር በኋላ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ወደ ማጠብ ሥራ ይገባል ሲሉም አስታውቀዋል::
ከሥራ እድል ፈጠራ አንጻር ፋብሪካው አሁን በደረሰበት ደረጃ ቀንና ማታ በፈረቃ እያሠራ ለ410 ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠሩንም አቶ ወንድሙ አስታውቀዋል:: ፋብሪካው ተጠናቅቆ በሙሉ አቅሙ የማምረት ሥራ ሲጀምር ለ 400 የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ቋሚ የሥራ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ በጊዜያዊነትም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ይናገራሉ::
የዳውሮ ዞን ለድንጋይ ከሰል ምርት ተመራጭ የሆነበት በርካታ ምክንያቶች እንዳሉም ጠቅሰው፣ አካባቢው ላይ የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ክምችት ብቻ ሳይሆን የድንጋይ ከሰሉ ፋብሪካው ከተቋቋመበት አካባቢ በቅርበት ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑም ነው ይላሉ::
አቶ ወንድሙ የልማቱ ተግዳሮት ያሏቸውንም ጠቅሰዋል:: ከውጭ ሀገር ተገዝተው ወደ ሀገር ውስጥ እየተጓጉዙ ያሉትን ማሽነሪዎች ከወደብ ወደ ዳውሮ ዞን ለማምጣት ከወላይታ ሶዶ እስከ ዳውሮ ዞን ያለው መንገድ ምቹ አለመሆን ችግር እንደሆነባቸው ይጠቅሳሉ::
‹‹ማሽነሪዎችን በተሳቢ መኪናዎች በኮንትራት ስናመጣ በመንገድ ችግር ለመቆም እየተገደዱ ናቸው፤ በዚህ የተነሳም በኩባንያው ላይ በቀን አምስት ሺ ብር ኪሳራ እየደረሰ ነው›› ይላሉ:: አንድ ኮንቴይነር የፋብሪካ እቃ ሲመጣ ከድሬዳዋ ወይም ከአዲስ አበባ ማዕከል 290ሺ ብር ይከፈላል፤ ከዚያ እዚህ እስከሚደርስ ደግሞ ያለው ከፍተኛ የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር በአምስትና ስድስት ቀናት መድረስ ያላባቸው መኪናዎች መንገድ ላይ 20 ቀናትና ከዚያ በላይ እንዲቆዩ እያደረገ ነው ሲሉ ያብራራሉ:: ይህ ሁሉ ድርጅቱን ለኪሳራ እየዳረገው መሆኑን ይጠቁማሉ::
ይህ ሁሉ ችግር በፋብሪካው ግንባታ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ መፍጠሩን ጠቅሰው፣ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ በእቅድ የተያዘውን የፋብሪካውን ሥራ ወደ አንድ ዓመት እንዲጓተት ማድረጉን ይናገራሉ:: ይህ ደግሞ የፋብሪካውን ሥራ ሊያስተጓጉል እንደሚችል ገልጸዋል::
የመብራት ኃይል ማነስ ሌላው ችግር መሆኑንም አቶ ወንድሙ ጠቁመዋል:: ፋብሪካው ያለበት ዳውሮ ተርጫ አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለአካባቢው ከጊቤ ሁለት የተዘረጋው የመብራት ኃይል በጣም ከፍተኛ ችግር ያለበት በሳምንት ሁለት ጊዜ አልያም ሦስት ጊዜ ብቻ ብቅ የሚል መሆኑን ያመለክታሉ:: ‹‹ የፋብሪካውን ግንባታ አጠናቅቀን ወደ ማምረት ሥራው ስንገባ፣ አሁን ባለው ሁኔታ በጣም ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት እጥረት ይገጥመናል›› ሲሉ ስጋታቸውን ይጠቁማሉ:: በዚህ ሁኔታ የራሳችንንም፣ የመንግሥትን እቅድ ለማሳካት እንቸገራለን ሲሉም ይገልጻሉ:: የሃይል አቅርቦቱ ከጊቤ ሦስት የሚገኝ ከሆነ የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት ፋብሪካውን የሚያግደው እንደሌለም ተናግረዋል::
እሳቸው እንዳሉት ፤ የድንጋይ ከሰል ማምረቱ ሥራ ከገበያ አንጻር ምንም ችግር አይኖርም:: የድንጋይ ከሰል ፍላጎትና አቅርቦቱ በንጽጽር የሚቀርብ አይደለም:: ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ ነው፤ አቅርቦቱ በጣም ዝቅተኛ ነው:: የአቅርቦቱን መጠን ለማመጣጠን ይህ ፋብሪካ ወሳኝ ሚና ይጫወታል:: የሲሚንቶ ዋጋ ንረትን ለማረጋጋትም የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ መመረቱ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል::
‹‹በያዘነው እቅድ መሠረት በ2016 ዓ.ም እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ ግንባታውን እንጨርሳለን ብለን ነበር›› ያሉት አቶ ወንድሙ፤ ፋብሪካው ያለበት አካባቢ ሙቀታማ መሆኑም ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ጠቅሰዋል:: ከውጭ ሀገር የመጡት ባለሙያዎች ከሙቀቱ ጋር ተያይዞ በህዳር ወር( ከህዳር 15 እስከ 30 ባለው ጊዜ) ውስጥ ሠርተን እናስረክባል የሚል ሃሳብ እያቀረቡ እንደሆነም ተናግረዋል::
ድርጅቱ በአክሲዮን የተቋቋመና በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተመሠረተ መሆኑን ጠቅሰው፣ እንደ ሀገር የድንጋይ ከሰል ምርት በሀገር ውስጥ ለማምረት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል::
ከውጭ ይመጣ የነበረውን የድንጋይ ከሰል ምርት በሀገር ውስጥ ምርት የመተካቱ ሥራ በራሱ ለሀገሪቱ ትልቅ እምርታ መሆኑን አቶ ወንድሙ ጠቅሰው፣ የማዕድን ሀብትን በማስተዋወቅ በሀገር ውስጥ ያለውን እምቅ አቅም አጎልቶ በማሳየት በኩል የሚዲያ ተቋማት ትልቅ ድርሻ መውጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2016