የሁሉ ነገር መሰረት የሆነውንትምህርት ከስብራት ለመታደግ

የማንኛውም ችግር መፍቻ ዘዴና ብልሃቱ ትምህርት ለመሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም:: በዓለም ላይ ለሚታዩ ለውጦች ሁሉ ጉልህ ሚና የመጫወት አቅሙ ትልቅ ነው:: ለአንድ አገር ዕድገትና ለውጥ ሁለንተናዊ የሆነ መፍትሔዎችን ያነገበ በመሆኑ ለተጠቀመበት የችግሮች ሁሉ ፍቱን መድሃኒት ከመሆን ባለፈ የአገር ካስመን የሚያጸና ነው:: ለዚህም ነው ትምህርትን በአግባቡ የተጠቀሙ እና ውጤታማ የትምህርት ሥርዓትን የተከተሉ የዓለም አገራት በተለያዩ ዘርፎች ቀዳሚ ሆነው የምንመለከተው::

በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ከድህነት ለመውጣትና እንደ ሀገር ለማጽናት ብቸኛው መንገዳቸው ትምህርት ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም:: ‹‹ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ›› እንዲሉ የሁሉ ነገራችን መሰረት ከስር መሰረቱ የጸና ይሆን ዘንድ እንደ አገር ትምህርትን ጠበቅ አድርጎ መያዝና ውጤታማ የትምህርት ስርዓትን መከተል አገርን ወደፊት ለማሻገር ይበጃል::

በተቃራኒው ደግሞ አገርን የኋሊት ለመጎተትና ለማጥፋት ዘመናዊ መሳሪያን ከመጠቀም ይልቅ የትምህርትን ዋጋ መቀነስ፣ ትምህርትን ማሽመድመድና ስብራት እንዲገጥመው ማድረግ በራሱ ብቻ በቂ እንደሆነ ይታመናል:: በዚህ ሂደት ትልቅ ዋጋ የከፈሉ ሀገራትም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ከአብዛኞቹ ኋላቀር ደሀ ሀገሮች አሁነኛ ሀገራዊ እውነታ በስተጀርባ ጎልቶ የሚታየውም ይሀው ነው።

አንድ አገር ትምህርትን በተገቢው መንገድ መጠቀም፤ ውጤታማ የትምህርት ስርዓትን መከተል ካልቻለ በትምህርት የሚገኙ ትሩፋቶችን ለማግኘት አይችልም:: ይህ ማለት ደግሞ ለመጪው ትውልድ የምናሻግረው አገርና ሕዝብ አይኖረንም ማለት ነው:: ለዚህም ነው ትምህርት ላይ በብዙ መሥራት የግድ የሚሆነው::

እርግጥ ነው እኛ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ስድስት አስርቶች እንደ አገር በርካታ ስብራቶች አጋጥመውናል:: አሁንም እየፈተኑን ያሉ ለቁጥር የበዙ ስብራቶች ያሉብን ህዝቦች ነን፤ ከስብራቶቻችን ሁሉ የከፋው ግን በትምህርት ዘርፍ የገጠመን ለመሆኑ አያጠያይቅም:: ለዚህም ደግሞ ከሰሞኑ ይፋ የተደረገው ብሔራዊ የ12ኛ ክፍል ውጤት አንድ ማሳያ ነው:: የውጤቱ አስደንጋጭነት የትምህርት ዘርፉን ከሚመራው ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈ መላውን ሕዝብ ያነጋገረና ያስደነገጠ ጉዳይ ነው::

የትምህርት ሚኒስቴሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የ2015 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤትን ይፋ ባደረጉበት ወቅት በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ፤ በትምህርት ዘመኑ ፈተናውን ከወሰዱት 845 ሺ በላይ ተማሪዎች ውስጥ 50 በመቶና ከዛ በላይ ያመጡት 27 ሺ 267 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህም ከአጠቃላይ ተማሪዎች ሶስት ነጥብ ሁለት በመቶ የሚሸፍን ነው፤ ተማሪዎቻቸውን ካስፈተኑ ሶስት ሺ 106 ትምህርት ቤቶች መካከልም አንድ ሺ 328 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ማሳለፍ እንዳልቻሉ ተናግረዋል:: ውጤቱ እንደ አገር በዘርፉ ውድቀት ላይ መሆናችንን የሚያሳይ ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም።

ተማሪዎቹ ከታች ጀምረው የመጡበት መንገድ የተጣመመና የተወላገደ ለመሆኑ ይኸው ውጤት ይናገራል:: ለጊዜው ለውድቀቱ ተጠያቂው ማነው የሚለውን ወደ ጎን በመተው እንደ አገር የደረሰብንን ስብራት ለመጠገን በሚያስችለን ጉዳዮች ዙሪያ እያንዳንዳችን ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል::

በርግጥ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ለቁጥር የበዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ስብራቶቻችንን ለመጠገን አገር ወገቧን ታጥቃ ያለ ስስት ብዙ ርቀት ተጉዛለች:: በዚህም ውጤት የታየባቸው ዘርፎች ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አይደሉም::

የሁሉም ነገር መሰረት በሆነው በትምህርት ዙሪያም አገር እንደ አገር ብዙ ሥራዎች ሰርታለች:: በዘርፉ ያጋጠመውን ስብራት ለመጠገን በትምህርት ፍኖተ ካርታ ኮንፈረንስና አገራዊ ጥናት በማካሄድ አገርን ለመጪው ትውልድ ለማቀበል ብዙ ደፋ ቀና ብላለች::ይህም ሆኖ

 ግን ውጤት አስደንጋጭ ሆኗል:: እርግጥ ነው ዛሬ ያስደነገጠን ውጤት የዛሬ አምስትና ስድስት ዓመታት ሥራ አይደለም ከዛም በላይ ተከማችቶ የቆየ ችግር ነው::

እሱ ሳይማር ልጆቹን የሚያስተምር ወላጅ ባለበት በእኛ አገር ደግሞ ውጤቱ ከማስደንገጥ በላይ ይሆናል:: ወላጆች የነገዋን ኢትዮጵያ በማሰብ ብዙ ዋጋ ሲከፍሉ ኖረዋል:: ችግሮቻቸውን ሁሉ ዋጥ ስልቅጥ አድርገው ባለ በሌለ አቅማቸው ምሳ ቋጥረውና የትምህርት ቁሳቁስ አሟልተው አገርን ከውድቀት ለመታደግ ተማር ልጄ በማለት ከዕውቀት ገበታ ሲልኩና ሲቀበሉ ለዓመታት ደክመዋል::

ተማሪዎችም እንዲሁ ካቅማቸው በላይ የሆነ ቦርሳ ተሸክመው ከትምህርት ቤት ተመላልሰው ከክፍል ክፍል ሲዘዋወሩ ኖረዋል:: እዚህ ጋር ቆም ብሎ ማሰብና ለመፍትሔው መትጋት እንደ አገር ከሁሉም የሚጠበቅ ነው። በተለይም ከምሁራኑና ከፖለቲካ ኢሊቱ ብዙ ሥራ ይጠበቃል::

ምንም እንኳን ለዛሬው ስብራታችን ትናንትናችን ተወቃሽ ቢሆንም፤ የትናንቱ ችግራችን እስከመቼ ነው ለዛሬው ውድቀታችን ምክንያት ሆኖ የሚቀጥለው የሚለው ግን መልስ ሊሰጠው የሚገባው የብዙዎቻችን ጥያቄ ነው:: ትናንትናችን ውስጥ የቱንም ያህል ችግሮች ቢኖሩ ዛሬም ያልተሻገርናቸው እጥረቶች ስለመኖራቸው መካድ አይቻልም::

ለአብነትም ከዚህ ቀደም አንድ ለአምስት የነበረው የተማሪዎች መጽሐፍ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከተማሪዎች ቦርሳ ውስጥ አልታየም:: ለተማሪዎች ዕውቀትን ማቀበል ያለበት የተማረ ኃይል እንደመሆኑ የመምህራኑ አቅምም እንዲሁ ሊፈተሽ የሚገባው ጉዳይ ነው:: እነዚህና መሰል ችግሮች ከትናንትናችን ጋር ተደምረው አስደንጋጭ የሆነውን የ12ኛ ክፍል የተማሪዎች ውጤት አስታቅፈውናል::

ውጤታማ ባልሆነ የትምህርት ስርዓት ውስጥ ያለፈ ተማሪ ነገ ከነገ ወዲያ መምህር፣ ሀኪም፣ መሀንዲስ፣ ኢኮኖሚስትና ሌላም ሌላም መሆን አይችልም:: ምንም መሆን ቢችል እንኳ ተሳስቶ የሚያሳስተን እና እንደ አገር አጥፍቶ የሚያጠፋን መሆኑ አይቀሬ ነው::

ትምህርት የሁሉ ነገር መሰረት እንደመሆኑ ትምህርት ላይ የተበላሸ ነገር ሁሉ ጥፋቱ የበዛ ነው፤ አገር እንደ አገር እንዳትቀጥል ማድረግ የሚያስችል አቅም ይኖረዋል:: በተመሳሳይ ትምህርትን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለና ውጤታማ የትምህርት ሥርዓትን መከተል ከተቻለ የአገር ካስማን በማጽናት በተለያዩ ዘርፎች ቀዳሚና ተጠቃሽ ያደርጋል::

በትምህርት የታገዘ ማሕበረሰብ አምራችና ውጤታማ በመሆን አገር እንድትቀጥል ዋስትና የሚሰጥ በመሆኑ ደግመን ደጋግምን ለትምህርት ጥራት ዋጋ መስጠት ይጠበቅብናል:: ለትምህርት የተሰጠው ዋጋ በዕውቀት ላይ የተመሠረተና ሁሉን አቀፍ ዕድገት ማምጣት የሚያስችል እንዲሆንም የትምህርት ስርዓታችን በሁለንተናዊ መንገድ መመርመር ወሳኝ ነው::

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You