የታመነን ማመስገን የላቀ ኃላፊነት የሚሰማውታማኝ ዜጋን ይፈጥራል!

 የአንድ ሰው ታማኝ መሆን ለራስ ብቻ ሳይሆን፤ ለቤተሰብ፣ ለማሕበረሰብ ብሎም ለሀገር ያለውን ከፍ ያለ ፍቅር፣ ክብር እና ስለነዚህ አካላት ከፍ ያለ ኃላፊነት የመሸከም ልዕልናን መግለጫ ነው:: ምክንያቱም ታማኝነት ለራስ ከፍ ያለ ክብርና የስብዕና መግለጫ ከመሆኑም ባሻገር፤ ከፍ ያለ ኃላፊነት የመሸከምና የመወጣትም አቅምን ብቻ ሳይሆን፤ ለሕግ፣ ለሞራል እና ለየማኀበረሰብ እሴቶች ተገዢነትን ማሳያ ነው::

አንድ ሰው ሲታመን ለራሱም ለቤተሰቡም ክብር ነው፤ በቤተሰቡ ውስጥ መታመንን የተለማመደ ትውልድ ደግሞ ለማሕበረሰቡም ለሀገር የታመነ ይሆናል:: ለዚህ ነው ቤተሰብ ላይ የሚሰራ ሥራ ሀገርን መገንባትም፣ ማፍረስም የሚችል ምግባር የተላበሰ ትውልድን እንደሚፈጥር በብዙ መልኩ ሲገለጽ የሚሰማው::

የመታመን መገለጫዎች ደግሞ ዘርፈ ብዙ ናቸው:: ከእነዚህ መካከል ለዛሬው ለሀገርና ሕዝብ መታመን ውስጥ የሚገለጸውን የታማኝ ግብር ከፋይነት ይገኝበታል:: በተለይ ግብር ለአንድ ሀገር እና ለሀገረ መንግስት ሕልውና ከሚኖረው አይተኬ አበርክቶ አኳያ፤ በየትኛውም ሀገር የግብር ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነው::

ምክንያቱም አንድ ሀገር ማሕበራዊም፣ ኢኮኖሚያዊም፣ ፖለቲካዊም ሆነ የደኅንነትና ሉዓላዊነት ጉዳይዋ መሠረት ሊኖረው የሚችለው፤ እነዚህን ጉዳዮች ማራመጃ የሚሆን የገንዘብ አቅም፣ የፋይናንስም ምንጭ ሲኖር ነው:: የሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ደግሞ፣ የአንድ ሀገር መንግስት ትልቁ የሀብት ምንጭ ግብር ነው::

በኢትዮጵያም ይሄው የግብር ጉዳይ እንደየወቅቱ የአሰባሰብ ሂደቱ ይለያይ እንጂ ለሺህ ዓመታት የነበረ፤ አሁንም ከዘመኑ ጋር ራሱን እያወዳጀ የቀጠለ ተግባር ነው:: ይሄ በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ሕልውናዋ ተጠብቆ፤ መንግስትም እንደ መንግስት ሀገርን የማስተዳደር፤ የሕዝቦችን ጥያቄ የመመለስ አቅም ፈጥሮ ዘልቋል::

ይሁን እንጂ የግብር አሰባሰቡ ሂደት ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖ የሚከወን ነው ማለት አይደለም:: ይሄ ደግሞ አንድም ከግብር ሰብሳቢው አካል፤ በሌላም በኩል ከግብር ከፋዩ ማሕበረሰብ ባሕሪ እና ፍላጎት ጋር የሚያያዝ ነው:: ይሄ የባህሪና ፍላጎት ጉዳይ ደግሞ ታምኖ ግብር የመሰብሰብና ያለመሰብሰብ፤ ታምኖ ግብር የመክፈልና ያለመክፈል ተቃርኖዎችን ይፈጥራል::

ለሀገርና ሕዝብ ታምኖ ግብር መሰብሰብና መክፈል እንዳለ ሁሉ፤ በአንጻሩ ከሀገርና ሕዝብ ሸሽጎ ለራስ ጥቅምና ፍላጎት በማድላት የሚገለጥ ብልሹ ባህሪ ምክንያት ግብርን በመሰወርና ለዚህ ተባባሪ በመሆን ውስጥ በሚታይ አለመታመን በእጅጉ ሀገርንም መንግስትንም የሚፈትኑ ጉዳዮች ናቸው::

እነዚህ በመታመንና አለመታመን ውስጥ ያሉ ሁለት ተቃርኖዎች ደግሞ፤ የዜጎችን ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር የሚገልጹበት፤ ካልሆነም ግላዊ ፍላጎታቸውን ተከትለው የሚነጉዱበት ነው:: ከዚህም ባለፈ አንዱ ታምኖ የከፈለውን ክብር ሌላኛው ባልተገባ መንገድ መልሶ የሚወስደው፤ ሀገርና ሕዝብ የሚፈልጉትን እንዳያገኙም፣ እንዳይጠቀሙም የሚያደርግ አሰራር ነው::

ይሄን መነሻ በማድረግም፣ ግብር ሰዋሪዎችንና በመሰል ተግባር የሚገለጹትን የማረምና ወደ መስመር የማስገባት ርምጃዎች ለመውሰድ ተሞክሯል:: በዚህም የተወሰነ ለውጥም ማምጣት ተችሏል:: ይሁን እንጂ ታምነው ግብር የሚከፍሉ እና በሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን የሚወጡ ግብር ከፋዮች የሚበረታቱበት ሥርዓት አልነበረም::

ይሄም መልካም መሥራት የሚያስመሰግንና የሚያሸልም ስላይደለ፤ እንዲህ አይነት ታማኞችን ለማፍራት የሚደረገው ጥረት ላይ የራሱን ጫና መፍጠሩ አልቀረም:: ይሁን እንጂ ከለውጡ ማግስት ይሄንን ስሜት የሚቀይር አዲስ አሰራር እውን ሆነ:: ግብር ሰዋሪዎችን የማረም ብቻ ሳይሆን፤ በታማኝነት ግብራቸውን የሚከፍሉ አካላትን በአደባባይ ማመስገንና መሸለም ተጀመረ::

በ2012 ዓ/ም ላይ አንድ ብሎ የጀመረው ይሄ የእውቅናና ሽልማት መርሃ ግብር፣ ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ ተካሂዷል:: በመጀመሪያው ዙር .. ታማኝ ግብር ከፋዮችን የማመስገንና የመሸለም ተግባሩ ያሳደረው መልካም ሂደት፤ በሁለተኛው ዙር 200፣ በሦስተኛው ዙር 300፣ በአራተኛው ዙር 400 እንዲሁም በአምስተኛው ዙር 500 ታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅናና ሽልማት አግኝተዋል:: በዚህ መልኩ ታማኝ ግብር ከፋዮችን የማመስገንና የመሸለም ሂደቶች ደግሞ ታማኝ ብቻ ሳይሆን የማይታመኑትን የሚያጋልጡ ዜጎች እንዲፈጠሩ ዕድል የሰጠ ሆኗል::

ለምሳሌ፣ በአራተኛው ዙር የዕውቅና እና ሽልማት መርሃግብር 400 ታማኝ ግብር ከፋዮች የተሸለሙ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል 40ዎቹ የፕላቲኒየም፣ 120ዎቹ የወርቅ እና 240ዎቹ የብር ደረጃ ተሸላሚዎች ናቸው:: 14 ግብር ከፋዮች ደግሞ ለሦስት ተከታታይ ጊዜ እና ከዛ በላይ በመሸለም በልዩ ተሸላሚነት፤ አንድ ግብር ከፋይ ደግሞ ሙስናና ብልሹ አሰራርን በማጋለጥ ተሸላሚ ሆነዋል::

በአምስተኛው ዙር የታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅናና ሽልማት መርሀግብርም 50 በፕላቲኒየም፣ 150 በወርቅ፣ 300 በብር ደረጃ እንዲሁም፤ 14 ልዩ ተሸላሚዎች ምስጋናና እውቅና ተበርክቶላቸዋል:: ይሄን መሰሉ ታማኞችን የማመስገን ተግባር ደግሞ የታመኑትን የበለጠ እንዲታመኑ፣ በመታመናቸውም ክብርና ኩራት እንዲሰማቸው ከማድረጉም በላይ፤ ሀሰተኛ ግብር ከፋዮች ከእኩይ መንገዳቸው እንዲመለሱና የተሻለ ስብዕናን ተላብሰው ወደ ታማኝ ግብር ከፋይነት መስመር እንዲገቡ የሚያደርግ ነው!

 አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You