“ዩኒቨርሲቲው የመምህራንን ክብር የሚመልሱ ተመራቂዎችን ማፍራት ይጠበቅበታል”ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር

አዲስ አበባ፡– የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የመምህራንን ክብር የሚመልሱ ተመራቂዎችን ማፍራት ይጠበቅበታል ሲሉ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ፡፡

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደገለፁት፤ ዩኒቨርሲቲው በማኀበረሰቡ ዘንድ መምህራን ያጡትን ክብር የሚመልስ ተማሪ ማፍራት ይጠበቅበታል።

የትምህርት ዩኒቨርሲቲው በማስተማር ተግባሩ ጠንካራ የሞራል መሰረት ያላቸው፣ ሙያቸውን የሚያከበሩ መምህራንን ለሀገሪቱ ማብቃት ይጠበቅበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ዋነኛ ትኩረታቸውን የሚያደርጉት ህንፃ መገንባት ላይ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲው ይህን አካሄድ በመቀየር ዕውቀት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይኖርበታል ብለዋል::

ፕሮፌሰር ብርሃኑ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የተማሩ ሰዎች ቁጥር በርካታ ቢሆንም ከጥራት አንጻር ሲታይ ክፍተቶች ይታያሉ:: በመሆኑም የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ብዛት ላይ ሳይሆን ጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይኖርበታል::

ትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮ በጀት ዓመት የመምህራን ጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ለሚኒስቴሩ የሥራ ስኬት የዩኒቨርሲቲው አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን አመላክተዋል።

የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የበቁ መምህራንን ለማፍራት በሚያደርገው ጥረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን አብረሃ (ዶክተር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት ዓለም ለትምህርት ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሠራ ይገኛል::

የሀገሪቷን የትምህርት ዘርፍ ለማሻሻል ባለፉት ዓመታት መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ዶክተር ሰሎሞን አስረድተዋል።

በሀገሪቱ የተማረ ሰው ኃይል ከ32 ሚሊዮን ማለፉን ጠቁመው፤ 51 የመንግሥት እና አምስት የግል ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በርካታ የግል ኮሌጆች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አስታውቀዋል።

የትምህርት ዘርፉን በማስፋት ረገድ ስኬታማ የሚባሉ ዓመታት ቢኖሩም፤ የሀገሪቱ የትምህርት ጥራት ሲገመግም በሁሉም ዘርፍ ማሽቆልቆል ይታያል ሲሉ አስረድተዋል::

ትውልዱ ያገኘውን ፀጋ ለሀገር ግንባታ እንዲያውልና ሀገር ወዳድ በመሆን ያለውን አቅም ለሕዝብ እንዲያበረክት የሚደግፍ መምህር ያስፈልገዋል ያሉት ዶክተር ሰለሞን፤ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በዚህ ረገድ ጠንካራ ሥራ ማከናወን ይጠበቅበታል ሲሉ ገልጸዋል::

መንግሥት ጥራቱን የጠበቀ የትምህርት ሥርዓት እንዲኖር የተለያዩ ሪፎርሞችን በማስጀመር እየሠራ ይገኛል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ መወለድ አንዱ የለውጡ አካል ነው ብለዋል::

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You