በምርጫ ውጤትን አምኖ ያለመቀበል አባዜና ከስልጣን ለመውረድ ፍላጎት ማጣት በአፍሪካ የሚካሄዱ ምርጫዎች መገለጫ ስለመሆኑ ብዙ ዋቢ መጥቅስ አያስፈልግም። የአፍሪካ የዴሞክራሲ ዕድገት ሥጋት ውስጥ የሚወደቀውም የስልጣን ዘመናቸውን የጨረሱ መሪዎች ለመውረድ ፍላጎት ባለማሳየታው ነው፡፡ በተለይ አንጋፎቹ መሪዎች በስልጣን ዘመናቸው መካከል እድሜያቸውን ለማራዘም ሕግና ህገ መንግስታቸውን ለማሻሻል ብዙ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። አንዳንዶቹ ሲሳካላችውም ተስተውሏል።
ለዚህ አንዱ ማሳያ ኡጋንዳ ናት። የኡጋንዳ ፓርላማ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት የዕድሜ ገደብ የሚያስቀረውንና አምስት ዓመት የነበረውን አንድ የስልጣን ዘመን ወደ ሰባት ዓመት ከፍ በማድረግ፣ ከ30 ዓመት በላይ አገሪቱን ያስተዳደሩትን ዮሪ ሙሴቬኒንን የስልጣን ቆይታ ለማራዘም የህገ መንግስት ማሻሻያ አፅድቋል።
የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ሕግና ህገ መንግስታቸውን ለማሻሻል ቢጥሩም ስኬታማ መሆን ያልቻሉ የአህጉሪቱ አንጋፋ መሪዎችም አሉ። ለ20 ዓመታት አልጄሪያን ጸጥ ለጥ አድርገው የገዙትና ሕመምና እድሜ ተጭኗቸው ከወንበራቸው ለመነሳት አሻፈረኝ ያሉት የ82 አመቱ አብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካ፤ ለአምስተኛ የስልጣን ዘመን ለመወዳደር ፍላጎታቸው ፀኑ የነበረ ቢሆንም፤ ከወራት በፊት በዜጎቻቸው ተቃውሞ ስልጣናቸውን ለቀዋል።
ምንም እንኳን አሁን በይፋ ባይታወቅም፤የቻድ ፓርላማ እኤአ ከ 1991 ጀምሮ የስልጣን ርካብ የተቆናጠጡትን ፕሬዚደንት ኢድሪስ ዴቢን ፕሬዚዳንታዊ ቆይታ ለተጨማሪ ሁለት አምስት ዓመታት ማራዘም እየዳዳው ይገኛል። ከቀናት በፊት ከምዕራፍ አፍሪካዊቷ አገር ቶጎ የተሰማው ዜናም የአህጉሪቱ መሪዎች ስልጣን ለማስረከብ ያለመፈለግ በሽታ የተጠናወታቸው ስለመሆኑ በቂ ምስክር ነው ተብሎለታል።
ቶጎ ነፃነቷን ከተቀዳጀች ጀምሮ በወታደራዊ ኃይል ባካሄዱት መፈንቅለ መንግስት እ.ኤ.አ. ከ1967ዓ.ም አንስቶ ፕሬዚዳንት የሆኑት ጌናሲንግቤ ኢያዴማ ለ38 ዓመታት በስልጣን ቆይተዋል። ሰውየው እኤአ በ1992 በቶጎ ፕሬዚደንታዊ የስልጣን ዘመን ከሁለት ጊዜ በላይ እንዳይሆን የሚደነግግ ህግ ቢያወጡም ተግባራዊ ግን አላደረጉትም። ይልቁንስ ህጉ ከወጣ ከአስር ዓመት በኋላም ስልጣናቸውን አላስጠነቁም።፡
ይባስ ብሎም የተፈጥሮ ጥሪ ሆኖ እ.ኤ.አ በ2005 ህይወታቸው ሲያልፍም ስልጣናቸውን ለሌላ አካል ከማስረከብ ይልቅ ለልጃቸው ፌኡሬ ጌናሲንግቤ አውርስውታል። ጌናሲንግቤ ወደ ስልጣን የወጡት የአገሪቱ ህግ በማይፈቅደው መንገድና ህገ መንግስቱን ባልተከተለ መልኩ ነው፡፡ ድርጊቱ የበርካታ ወገኖች ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል።
በተለይ እኤአ ከ2017 ጀምሮ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር መንግስትን በመቃወም በየጊዜው ተቃውሞዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። የቀድሞዋ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ቶጎ አደባባይ በወጡ ዜጎቿ ስትዋከብ ታይታለች። በርካታ የተቃውሞ ንቅናቄዎች እና ሰልፎች በተደጋጋሚ ታይተውባታል።
በተቃውሞዎቹም ፕሬዚዳንቱ ስልጣናቸውን እንዲያስረክቡ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፣የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የስልጣን ቆይታ ሁለት አምስት ዓመታት እንዲሆን የሚደነግገው የ1992ቱ ህገ መንግስት ይመለስ የሚሉ ጥያቄዎችም ተሰምተዋል።
የአገሪቱ መንግስት ጠንካራ የተባለ አፀፋ ምላሽ በመስጠት ተቃውሞውን ለማፈንና አደባባይ የወጡትን ለመበተን ሃይል ተጠቅሟል። በዚህም የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉና በመቶዎች የሚቆጠሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ደጋፊዎችም ዘብጥያ መውረዳቸውም ታውቋል። ይህ ውጥረት ባሳለፈነው ዓመት በተካሄደው የፓርላማ ምርጫ ላይ ይበልጥ ግሎ ታይቷል። ክስተቱም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው አንሳተፍም በማለት እንዲወስኑ እስከማስገደድ ደርሷል።
የ52 ዓመቱ የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከ14 ዓመት በፊት ስልጣኑን ከአባታቸው ከወረሱ አንስቶ እስካሁን ለሶስት የስልጣን ዘመን አገሪቱን አስተዳድረዋል። ይህ ያንገሸገሻቸው ተቃዋሚዎችና የአገሪቱ ህዝቦችም ከሃምሳ ዓመታት በላይ የዘለቀው አገዛዝ እንዲያከትምና የፕሬዚደንቱ ስልጣንም እአአ በ2020 እንዲጠናቀቅ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
አንጋፋዎቹ መሪዎች የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ሕግና ህገ መንግስታቸውን ለማሻሻል ብዙ እንደሚደክሙት ሁሉ ፕሬዚዳንት ፌኡሬ ጌናሲንግቤ ይህንንም ፈፅመውታል። የአገሬው ፓርላማ አባላት በፕሬዚዳንቱ እድሜ ላይ የተጣለው ገድብ እንዲነሳ የአገሪቱን ህገ መንግስት ለማሻሻል የሚያስችለውን ውሳኔ ማፅደቃቸው ታውቋል።
ይህን ያስተዋሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ትንታኞችም ለጉዳዩ ሰፊ ትኩረት ሰጥተውታል። በዚህ ረገድ ሰፊ ትንታኔ የሰራው አልጀዚራ፤ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ፕሬዚዳንቱ ስልጣን እንዲያስረክቡ በተቃውሞ በሚጠይቁበት በዚህ ወቅት የአገሪቱ ፓርላማ ህገ መንግስቱን በማሻሻል የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ቆይታ እንዲረዝም እኤአ በ2020 እና 2025, በምርጫ መወዳደር እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ እያነጋገረ መሆኑን አትቷል።
ሮይተርስ በበኩሉ፤በምዕራብ አፍሪካዋ አገር ከቀናት በፊት የተሻሻለው ህገ መንግስት ፕሬዚዳንቱ ለተጨማሪ ሁለት አምስት ዓመታት በስልጣን እንዲቆዩ ፈቃድ መስጠቱ ላለፉት አምስት አስር ዓመታት የቆየውን የቤተሰብ ስልጣን ወደ ስድስት አስርት ዓመታት ያሽጋግረዋል ሲል ዘግቧል።
የተሻሻለው ህገ መንግስት ለፕሬዚዳንትነት የተቀመጠውን የእድሜ ገደብ ከማንሳት በተጨማሪ በአንቀፅ 75 ላይ ፕሬዚዳንቱ የምክር ቤቱ የህይወት ዘመን አባልና በስልጣን ዘመናቸውም ከማንኛውም አይነት ክስና ቅጣት ነፃ እንዲሁኑ ዋስትና ሰጥቷቸዋል።
ከ91ህግ አርቃቂ ድምፅ ሰጪዎች መካከል ዘጠና የሚሆኑት በፕሬዚዳንቱ የስልጣን ቆይታ ላይ የተቀመጠውን የእድሜ ገደብ መፍቀዳቸው የታወቀ ሲሆን፤የዘ ኢስት አፍሪካ ዘገባም አንድ ድምፅ ያልሰጡት ግለሰብ ሊኖሩ ያቻሉትም በእለቱ በፓርላማ ባለመኖራቸው መሆኑን አስነብብቧል። በእርግጥም የፕሬዚዳንቱ ፓርቲ አባላት ከአገሪቱ ፓርላማ ሁለት ሶስተኛ የሚሆነውን ወንበር ተቀምጠውበታል።
ተቃዋሚዎች በአንፃሩ፤ ከአንድ አመት በፊት አንስቶ የህግ አውጪዎችን ምርጫና የፕሬዚዳንቱን የስልጣን ዘመን ማራዘም ጭምጭምታን በመቃወም የፓርላማ መቀመጫቸውን ጥለው ወጥተዋል። ይህም በአሁኑ የህገ መንግስት ማሻሻያ ላይ ምንም አይነት የተቃውሞ ድምጽ እንዳይኖራቸው አድርጓል ነው የተባለው።
አፍሪካን አርጊውመንት የተሰኘው ጋዜጣ በህገ መንግስቱ ማሻሻያ ላይ ሰፊ ትንታኔ ካሰፈሩት መካከል አንዱ ነው። እኤአ በ1992 በወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጌናሲንግቤ ኢያዴማ የቶጎ ፕሬዚደንታዊ የስልጣን ዘመን ከሁለት ጊዜ በላይ እንዳይሆን የሚደነግግ ህግ አውጥተው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ኢያዴማ ይህን ህግ እንዳልተገበሩት ሁሉ፤ በሶስተኛ የፕሬዚዳንትነት የስልጣን እድሜው ላይ የሚገኙት ልጃቸውም ይህን ህግ አሽቀንጥረው ጥሎታል ሲል አስነብቧል። ለ52 ዓመታት የዘለቀው ቤተሰባዊ ስልጣንም እስክ መጪው 2030 ሊራዘም መሆኑን አመላክቷል።
አባት አገሪቱን ለ38 ዓመታት ካስተዳደሩ በኋላ ለልጃቸው ያወረሱት ስልጣን ቀጥሎ ቤተሰቡ አገሪቱን ለ 52 ዓመታት ማስተዳደሩንና ተጨማሪዎቹን አስር ዓመታት ሳያካትት ይህ ብቻውን በአፍሪካ የስልጣን ታሪክ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ረጅሙ የስርወ መንግስት ነው ብሎታል።
በአዲሱ የህገ መንግስት ማሻሻያ መሰረት ቶጎ ከፕሬዚዳንቷ ለመለያያት ተጨማሪ አስር ዓመታትን መጠበቅ ግድ እንደሚላት ያመላከተው ዘገባው፤ ምንም እንኳን አሁን ምንም ጥሩ የሚባል ዜና ባይኖርም፤ በተለይ C14 የተሰኘው የአገሪቱ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ ቀደም ሲል ከነበረበት የልዩነትና መከፋፈል ጉዞ ወጥቶ እኤአ በ2020 ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጠንካራ መሆኑ ለአገሬው ህዝብ ብቸኛ ተስፋው ስለመሆኑ ጠቁሟል።
እናም አሁን በርካታ ወገኖች ይህን በመቃወም አደባባይ እንደሚወጡ አትጠራጠሩ ያለው አፍሪካን አርጊውመንት ዘገባ፤ይህ ከሆነ እንደዚህ ቀደሙ አይነት የበርካታ ንፁሃን ዜጎች ህልፈት እንደሚኖር መጠራጠር እንደማያስፈልግም አመላክቷል።
በእርግጥም በአፍሪካውያን መሪዎች ዘንድ የምርጫ ውጤት አምኖ ያለመቀበል አባዜና ከስልጣን ለመውረድ ፍላጎት ማጣት ሲስተዋል፤ብቸኛው አማራጭ ህዝባዊ ተቃውሞ መሆኑ እርግጥ ነው። ለ20 ዓመታት አልጄሪያን ጸጥ ለጥ አድርገው የገዙት አብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካም ሆነ ለ30 ዓመታተ የዘለቀው የአልበሽር አገዛዝ ያከተመው በዚህ አይነቱ ለወራት በዘለቀ ህዝባዊ አመጽ ነው።
ለ52 ዓመታት የዘለቀው የቤተሰብ ዙፋን ወደ 62ኛው እንዳይሸጋገር የሚፈለጉ ቶጎአዊያንም ምናልባት ፕሬዚዳንታቸውን ለማውረድ ብቸኛው አማራጫቸው ይህ እንደሚሆን የሚያመላክቱም አልጠፉም። ይህ ደግሞ የነገ የአገሪቱን እጣ ፈንታ አሳሳቢ ያደርገዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2011
ታምራት ተስፋዬ