የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ፤ የስብራቶቻችን ሁሉ መፍቻ ነው !

ትምህርት ለሰው ልጆች ኑሮ ቅልጥፍና፣ ለሀገራት ዕድገትና ልማት፣ ባሕልንና እውቀትን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል ስለመሆኑ ብዙ ተብሎለታል። የትምህርት አንዱ ባሕሪ መሠረታዊ እውቀት በማስጨበጥ በግለሰብም ሆነ በኅብረተሰብ የችግር ፈችነት አቅምን ችሎታን፤ ባሕልን ማጎልበት ነው ።

ትምህርት የሰው ልጅ በኑሮ ትግል ያከማቻቸውን ግኝቶችና ተሞክሮዎችን ማስተላለፊያና አዲስ ግኝቶችን ማፍለቂያ ሂደት እንደሆነ ይታመናል። ግለሰቦችን በእውቀት፣ በግንዛቤ፣ በአስተሳሰብ፣ በአመለካከት፣ በሥነ ውበትና በእሴት እንዲሁም በችሎታና በክህሎት በማነጽ ለራሳቸውና ለኅብረተሰቡ ሁለንተናዊ እድገት ፍሬያማ ተሳትፎ ለማድረግ እንደሚያስችላቸው በትምህርት ላይ የተሠሩ ጥናቶች ያመለክታሉ።

የትምህርት ሂደት በግለሰብና በኅብረተሰብ ተስተጋብሮት ለአጠቃላይ ኅብረተሰብ ሕልውናና እድገት ቁልፍ ሚና አለው ። ዓለማችን አሁን ለደረሰችበት የእድገት ደረጃ ትምህርት የተጫ ወተው ሚና ከፍተኛ ነው፤ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ሚና እንደነበረው እና እንደሚኖረው የሚያጠራጥር አይደለም።

እውቁ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ በአንድ ወቅት ስለትምህርት ሲናገሩ፣ “ትምህርት ዓለምን ለመለወጥ ልትጠቀ ምበት የምትችለው በጣም ኃይለኛ መሣሪያ ነው” ብለው ነበር ። ትምህርት ዓለምን ለመለወጥ ቁልፍ መሣሪያ ነው የሚለውን መርሕ የዓለም ሀገራት የሚስማሙበት በመሆኑ ፤ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡታል።

በኢትዮጵያም የቀደሙት አባቶቻችን በትምህርት ልቆ ለመገኘት የአቅማቸውን ሞክረ ዋል፤ ጥረዋል። በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሀገራችን ዘመናዊ ትምህርት ከጀመሩት ዳግማዊ ምኒልክ አንስቶ፤ በትውልድ ቅብብሎሽ አገርን በእውቀት መሠረት ላይ ለማቆም አቅማቸው የፈቀደውን አድርገዋል።

በዋናነት በአገሪቱ ዘመናዊ ትምህርት መስፋፋትን ተከትሎ፤ በማኅበረሰቡ ውስጥ ስለ ትምህርት የነበረው አስተሳሰብ ከመቀየር ጀምሮ፤ ትውልዶችን በተሻለ የትምህርት መሠረት አንጾ ለማውጣት እንደ ሀገር ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። ከባለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት ወዲህ ያለውን ብንመለከት፤ በጊዜው የነበረው መንግሥት ለትምህርት ዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የትምህርት መሠረተ ልማቶችን ከማስፋፋት ጀምሮ፤ ተደራሽነት በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሥራ ሠርቷል።

አንድ ዩኒቨርሲቲ የነበረው ሀገር ወደ 47 አድጓል፡፡ ውጤቱ ከተደራሽነት አንጻር ሲለካ ጥልቅ ቢሆንም፤ ትምህርትን በአግባቡ ለለውጥ መጠቀም በመቻል ረገድ ግን ከፍ ያለ ክፍተት ከዛም ባለፈ ውድቀት እንደነበር በዘርፉ ምሑራን በስፋት ይነሳል። ለዚህም የትምህርት ሥርዓቱ ከፖለቲካ ነፃ አለመሆኑን እንደ ጥልቅ መከራከሪያ ያነሳሉ። ይህም ከሁሉም በላይ በትምህርት ጥራት ላይ ያልተገባ ጥፋት ማስከተሉን ይሞግታሉ።

በርግጥም በኢትዮጵያ የትምህርት ክህሎት አጎናጻፊነት፤ የትምህርት የእውቀት ማዕድነት፤ የትምህርት የምርምርና የፈጠራ መድረክነት፤ የትምህርት በእውቀትም በክህሎትም በሥነ ምግባርም ትውልድን አንጾ የሀገር አሻጋሪ ራዕይ ያላቸው ተተኪዎችን የመፍጠሪያ ኃይልነቱ ከእለት እለት እየኮሰመነ መጥቷል። ለዚህ አሁም ያለው ሀገራዊ ፈተና እንደ አንድ ማሳያ ሊታይ የሚችል ነው ።

ትምህርት ቤቶች ከቁጥር ያለፈ መገለጫ የሌላቸው መሆናቸው፤ የመምህራን አቅም ከዘመን ዘመን እየተሸረሸረ መታየቱ ፤ የተማሪዎች በራስ የመተማመን ልዕልና ላሽቆ በኩረጃ ላይ የተመሠረተ ከክፍል ክፍል ሽግግር ተለምዷዊ መሆኑ እና ሌሎችም የዘርፉ መገለጫዎች እስከመሆን ደርሰዋል። ለዚህም የትምህርት ዘርፉ ከላይ እስከ ታች ድረስ የተዘፈቀበትን ችግርና የገባበትን ቅርቃር ማሳያዎችን እንመልከት።

በ2015 ዓ.ም አጋማሽ በጅማ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደ አንድ መድረክ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ሦስተኛ ክፍል ደርሰው ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎች ቁጥር 69 በመቶ እንደሆነ ተነግሯል። በተጨማሪም በሚያስተምሩበት ትምህርት የምዘና ፈተና ወስደው 50 በመቶ በማምጣት ያለፉ መምህራን ቁጥር ከ30 በመቶ በታች እንደሆኑ ይፋ ተደርጓል፡፡ ይህ በጣም የሚያስደነግጥና አጠቃላይ የዘርፉን ስብራት የሚያሳይ ነው ፡፡

ከዚህ ከፍ ብለን በቁጥር አሳደግን የምንላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ሳይቀር ብቁ ዜጋ ከማፍራት አኳያ ጥያቄ የሚነሳባቸው ሆነዋል።

መንግሥትም የትምህርት ዘርፉ እነዚህ የጠቀስናቸው ጨምሮ በበርካታ ችግሮች የተተበተበ እንደሆነ አምኗል። ባለፉት የለውጥ የትምህርት ሥርዓቱ የገጠመውን ስብራት ለመጠገን የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ተሞክሯል። በተለይም በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያለውን የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት በሆነው በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል ።

ከነዚህም፣ ውስጥ ለአምስት ዓመታት ጥናት በተደረገበት ፖሊሲ ተደግፎ ተግባራዊ የተደረገው አዲሱ የትምህርት ሥርዓት በዋነኛነት ይጠቀሳል። እንደሚታወቀው ፤ በዓለም ላይ ያሉ ሀገራት ቁሳዊና ሰብዓዊ ዕድገት የሚከተሉት ሥርዓተ ትምህርት ነጸብራቅ ነው። ከዚህ ተጨባጭ እውነታ በመነሳት ከድሀ የዓለም ሀገራት ጥልቅ ድህነት ጀርባ የተበላሸ ሥርዓተ ትምህርት እንዳለ ይታመናል ።

ከ110 ሚሊዮን በላይ ዜጋ ያላት ኢትዮጵያ፣ የድህነቷ ጀርባም ይኸው እውነታ ጎልቶ እንደሚታይ ይታመናል። የትምህርት ሥርዓቱ መስመር ሊይዝ ባለመቻሉና ተቆርቋሪ ባለቤት በማጣቱ ሀገሪቱ የተማረና የሰለጠነ ብቁ የሰው ኃይል እያጣች፣ ያላት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችም በየጊዜው እየተባባሱ መጥተዋል። ከዚህ አንጻር የትምህርት ሥርዓቱን ከገባበት ቅርቃር ለማውጣት የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ መደረጉ ትልቅ ውሳኔ እንደሆነ መረዳት ይቻላል ።

በጥናት ላይ መሠረት ተደርጎ የተቀረጸው ሥርዓተ ትምህርቱ አገር በቀል እውቀትን፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን እንዲሁም ተግባር ተኮር ትምህርትን ከሥነ ምግባር ትምህርት ጋር አቀናጅቶ ለመስጠት እንዲያስችል ተደርጎ የተቀረጸ ነው ፡፡ በዚህ የትምህርት ሥርዓት ትግበራ ላይም ግብረ ገብነት፤ ሀገር በቀል እውቀትና ሙያ፣ የቀለም ትምህርትና ቴክኖሎጂ፤ ምርትና ተግባር እንዲሁም ጥናትና ምርምር ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ።

በትምህርት ሥርዓቱ ብቃት ያላቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ምሩቃንን ለማፍራት በሚደረገው ጉዞም፤ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ከማድረግ ጀምሮ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በአዲስ መልክ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚሰጥበት አሠራር ተግባራዊ ተደርጓል።

ከዚህ በተጓዳኝ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ማወቅ የሚገባቸውን እውቀት የቀሰሙ ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ ይረዳ ዘንድ ባሳለፍነው ዓመት የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ተዘጋጅቶ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። በዩኒቨርሲቲዎች ቆይታቸው ያወቁትን እንዲተገብሩ የሚጠበቀው ምሩቃንን ቦታ በሐሰተኛ ማስረጃ ታግዘው ቀድመው የያዙ እና በሥራ ከባቢው ላይ አሉታዊ ገጽ እየሳሉ ያሉ ግለሰቦችን ለይቶ ከማውጣት አኳያም የትምህርት ማስረጃን የማጥራት ሥራዎች እየተከወነ ነው ።

በዚህ ረገድ ከትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የተቋማት ቁጥጥር ኢንስፔክሽን ክፍል የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ የትምህርት ማስረጃ የቁጥጥርና የማረጋገጥ ሥራ ከተሠራባቸው 22 ሺህ የትምህርት ማስረጃዎች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ሐሰተኛ መሆናቸው ተረጋግጧል። በጥቅሉ እንደ ሀገር በትምህርት ሥርዓቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እና የትምህርት ሥርዓቱን ስብራት ለመጠገን ባለፉት የለውጥ ዓመታት ውጤታማ ሥራዎች ተሠርተዋል። አበረታች ውጤትም ተመዝግቧል ።

ይህም ሆኖ አሁንም በቂ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ፤ ብዙ መሥራት የሚጠይቁ ሥራዎች ስለመኖራቸው ማስታወስ ተገቢ ነው። ለአብነትም ከትምህርት ቤቶች ደረጃ ጋር ተያይዞ ያለው ሁኔታ አንዱ ነው። ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ በኢትዮጵያ ካሉ 47 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉት 4 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው። በ2015 የደረጃ ምደባውን ካገኙት ትምህርት ቤቶች መካከል 99 በመቶ የሚሆኑት ከደረጃ በታች መሆናቸው የተረጋገጡ ናቸው።

ከደረጃ በታች የሆኑት ትምህርት ቤቶች የዳስ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በግብዓት (በመሠረተ ልማትና በሰው ኃይል) ፣ በመማር ማስተማር ሂደትና ውጤት በኩል የሚጠበቅባቸውን ያላሟሉ እንደሆኑ የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል። ይህም በሀገራችን ከተጀመረ ዘመናትን ያስቆጠረው ዘመናዊ ትምህርት በጀርባው ብዙ ችግሮችን አዝሎ ሲጓዝ እንደነበር አመላካች ነው። ችግሩን ለመቅረፍ ጅማሮ ቢኖርም፤ ብዙ መሥራት እንደሚጠብቅ የችግሩ ግዝፈት በራሱ የሚናገረው ነው ።

ሌላው የትምህርትን ነገር ቅርቃር ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት ምክንያቶች የሚጠቀሰው፤ ትምህርት እንደ አንድ በአቋራጭ የመክበሪያ/ የቢዝነስ መንገድ ተደርጎ መታየቱ ነው፡፡ በዚህ ትምህርትን ንግድ አድርገውት ያለ ምንም ሃፍረት ወረቀቶችን የሚቸርችሩ ጥቂት የማይባሉ የግል ኮሌጆች ከቀን ወደ ቀን ቁጥራቸው መበራከቱ ነው። ይህ አይነቱ ችግር በእንጭጩ እንዲቀጭ ማድረግ ካልተቻለ፤ የትምህርት ሥርዓቱ ከገባበት አዘቅት ለማውጣት እየተሠራ ያለውን ሥራ ፍሬ አልባ የሚያደርግ ይሆናል።

በአጠቃላይ ሀገራዊ የትምህርት ሥርዓቱን በሁለት እግሩ ለማቆም በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያለውን የትምህርት ጥራት መሠረታዊ ችግር በጥልቀት በመረዳት ለመፍትሔው ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል፡፡ በዚህም መንግሥት በተለያየ መልኩ የጀመራቸውን አበረታች ተግባራት አጠናክሮ መቀጠልና ከዳር ማድረስ አለበት ።

በተለይ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን ማስተካከል ላይ ትልቅ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል ። ለዚህም የሀገር ውስጥ አቅምን ከውጪ ድጋፍ ጋር አቀናጅቶ፣ አስተባብሮ መሥራት ይገባል። ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነትም መፍጠር ያስፈልጋል።

ትምህርት ሚኒስቴር የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱን ከማሻሻል ጀምሮ ሌሎች አቋራጭ የኩረጃ መንገዶችን ለመዝጋት የጀመራቸውን ሥራዎች በአዲሱ የትምህርት ዘመን አጠናክሮ መቀጠል፤ በዚህም በሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት የገነገነውን የኩረጃ ባሕል ታሪክ ማድረግ ይኖርበታል ፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተደረገ ያለው ሀገራዊ ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ሕዝቡ አሁን ላይ ለትምህርቱ ዘርፍ የፈጠረውን የባለቤ ትነት መንፈስ የበለጠ ማጠናከር ይጠበቅበታል። ለዚህም ሕዝቡ የጀመረውን የፋይናንስና የማቴሪያል ድጋፍ በማሳደግ ትምህርት ቤቶችን፣ ተጨማሪ ክፍሎችን መገንባት፣ ነባሮቹን ማደስ፣ የትምህርት ግብዓቶችን ሟሟላት የሚችልበትን ሕዝባዊ ንቅናቄዎች መፍጠር ይገባዋል፡፡ ለዚህም ከወዲሁ በቂ ዝግጅትና ቁርጠኝነት መፍጠር ወሳኝ ነው።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You